Weyeyet Magazine, Issue No. 10

April 17, 2017 | Author: Zelalem Kibret | Category: N/A
Share Embed Donate


Short Description

Download Weyeyet Magazine, Issue No. 10...

Description

ውይይት 1ኛ ዓመት ቁጥር 10 ነሐሴ 28 /2008 አንድ ሰው

የቋንቋ ፋይዳ በሥራና በትምህርት

ሳሚ-ዳን በሬጌ በዚህ ዓመት ከወጡ አልበሞች መካከል የመጀመሪያ አልበሙን ይዞ ብቅ ያለውን እና ወጣ ባሉ ሥራዎቹ ተወዳጅነትን ማትረፍ የቻለውን የሳሚ-ዳን ‹ከራስ ጋር ንግግር› በመንተራስ የሳሙኤል ብርሃኑን የሙዚቃ ሕይወት መብራቱ በላቸው እንደሚከተለው ያስቃኘናል።

የፌዴራሉ ክልሎች እና በየክልሉ ያሉ ዞኖች… በራሳቸው ቋንቋ የመማር፣ የመሥራት፣ የመዳኘት እና ሌሎችንም መሠረታዊ አገልግሎቶች የማግኘታቸው ጉዳይ አስፈላጊነት ትልቅ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ሲሳይ መንግሥቴ እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች የሚግባቡባቸው የጋራ የሥራ ቋንቋ መኖር ወሳኝነትንም አብረው ተመልክተዋል። የራያን ሕዝብ እና ሌሎችንም እንደማሳያ በማንሳት በቋንቋ ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን በዛሬው መጣጥፋቸው ያስነብቡናል።

ገጽ 23-25

ገጽ 26 - 29

የኢትዮጵያው አገዛዝ እና የሰብኣዊ መብቶች አከባበር ምን እና ምን?

የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ እንዴት ይፈታ?

ደረጀ መላኩ በዚህ ጽሑፉ የዓለምዐቀፉ ሰብኣዊ መብት ድንጋጌ/መግለጫን በመመልከት እና ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማመሳከር በሕገ መንግሥታችን ሳይቀር የተቀመጡት መብቶች አለመከበራቸውን ጽፏል። በተጨማሪም፣ ላለመከበሩ መንስዔ ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አቅርቧል። አምባገነኖች በልማት ሥም ሰብኣዊ መብትን እንደሚጨፈልቁ ገልጾ፣ ልማት ግን ያለሰብኣዊ መብት መከበር እና ያለነጻነት ሊገኝ የማይችል እንደሆነ ይከራከራል። ገጽ 30 - 31

ትኩሳት

አምባሳደር ተስፋዬ ሐቢሶ ከ46 ዓመታት በፊት የወልቃት ሁመራ አካባቢ ይተዳደር የነበረው በቤጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ሥር እንደነበረና የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ከተከዜ መልስ መሆኑን እንደሚያስታውሱ ከግል ገጠመኛቸው ጋር በማስታከክ ያስረዱ ሲሆን፣ ከ1987 በኋላ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት ክልሎች ሲዋቀሩ ወልቃይት ሁመራ ወደ ትግራይ ክልል መካለሉን በመግለጽ፣ እንዲሁም የአካባቢዎች አከላለል በዓለምዐቀፍ ተሞክሮዎች በየጊዜው እንደሚስተካከል አንስተው የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄም በዚያ ስሜት መስተናገድ አለበት ብለዋል። ገጽ 32

ሞላ ዘገየ እና ቤተሰቦቹ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር እየታተመ በየ15 ቀኑ የሚወጣ መጽሔት ሚያዝያ 22፣ 2008 ተጀመረ! አድራሻ፡- ቦሌ ክ/ከተማ፣ ወረዳ 3 የቤት ቁጥር 283 ፖ.ሳ.ቁ. 3845 አዲስ አበባ ስልክ ቁጥር፡- +251118688992 ኢሜይል፡- [email protected] ድረገጽ፡- www.weyeyetmagazine.com ማኔጂንግ ኤዲተር ሞላ ዘገዬ ኢሜይል፡- [email protected] ተባባሪ ማኔጂንግ ኤዲተር አበበ በየነ

ዋና አዘጋጅ በፍቃዱ ኃይሉ አድራሻ፤ አ.አ.፣ የካ ክ/ከተማ፣ ቀበሌ 01፣ የቤት ቁጥር 255 ኢሜይል፡- [email protected] ም/ዋና አዘጋጅ ዘላለም ክብረት ኢሜይል፡- [email protected] አዘጋጅ በሪሁን አዳነ ኢሜይል፡- [email protected] ዲዛይን ካርቱን ሀብ ዲዛይን ኢሜይል፡- [email protected]

አምደኞች አምባሳደር ተስፋዬ ሐቢሶ መስከረም አበራ ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም መብራቱ በላቸው ሔኖክ አክሊሉ ተሾመ ተስፋዬ ቴዎድሮስ አጥላው አታሚ፡ ሶፍ ሚክ ማተሚያ ቤት ኃ.የተ.የግ.ማኅበር አድራሻ፡ ልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 04 የቤት ቁ.064

ያቺ ‘ባነር’ ከሕዝባዊ ተቃውሞዎቹ ባሻገር… 4

ምልክታችን ፈይሳ ሌሊሳ በሮቤል ኪሮስ አሳፋሪ ሽንፈት የተጀመረው የኢትዮጵያ የሪዮ ኦሎምፒክ 2016 ተሳትፎ፣ በፈይሳ ሌሊሳ ድርብ ድል ተጠናቅቋል። እሁድ ነሐሴ 14፣ 2008 ለኢትዮጵያውያን ልዩ ቀን በመሆን ተመዝግባለች። በኢትዮጵያ ያሉትን የመብት ጥሰቶች ለመቃወም ዜጎች እጆቻቸውን በማጣመር የሚያሳዩትን ምልክት አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ ኦሎምፒክ ላይ በማሳየት ልዩ ታሪክ አስመዝግቧል። የዓለም መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ያሉትን ችግሮች ከመቼውም ግዜ በላይ እየተቀባበሉ እንዲዘግቡ እና በዓለምዐቀፉ ማኅበረሰብ ችላ የተባለውን ጉዳይ እንዲያወሱ ፈይሳ ሌሊሳ በድርብ ድሉ አስገድዷቸዋል። መብራቱ በላቸው የዚህን ጀግና አትሌት የጀብድ ታሪክ በጥቂቱ ያስቃኘናል።

8- 10

አራተኛው አብዮት?

የዘንድሮው ሕዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል፣ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. በአገዛዝ ታሪኩ ቀደም ሲል ከተጋፈጠው የ1997ቱ ዐብይ ምዕራፍ፣ ቀጥሎ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ለመሆን የሚችል ነው። በሪሁን አዳነ የአፍሪካ አምባገነን ስርዓቶች አመጣጥና አካሔድ፣ እንዲሁም የ1966ቱን አብዮት መነሻ በማድረግ እና በዚሁ ጉዳይ ባለሙያዎችን በማናገር የዘንድሮውን የተቃውሞ ማዕበል ከአብዮቱ ጊዜ ጀምሮ ከተከሰቱ የለውጥ ምዕራፎች እንደአንዱ አድርጎ ይመለከተዋል።

14-15

የብሔረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ ከየት ወዴት? በተለምዶ ‹ያ ትውልድ› እየተባለ የሚጠራው የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ንቁ ተሳታፊ የነበረው ትውልድ ካነሳቸው ግልጽ ያልሆኑ እና እስካሁንም በትክክል ያልተመለሱ ከሚመስሉ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ‹የብሔረሰብ ጥያቄ› ነው፡፡ ቴዎድሮስ ኃይለማርያም (ዶ/ር) ይህንን ጉዳይ እንዴት ልንሻገረው እንደምንችል ሐሳቡን በዚህ መጣጥፍ አስፍሯል።

19-20

በሕዝብ ብዛት የትልልቆቹ ክልሎች የኦሮሚያ እና አማራ ሕዝቦች በመንግሥታዊ ስርዓቱ ላይ በማመፃቸው የተደናገጠው ሕ.ወ.ሓ.ት. መራሹ መንግሥት እና ደጋፊዎቹ የሁለቱን ሕዝቦች ትብብር ለማክሸፍ ሕዝቦቹን እርስ በርስ የማይስማሙ “እሳትና ጭድ” መሆናቸውን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመግለጽ ለመከፋፈል እና ለማዳከም እየሞከሩ ነው። መስከረም አበራ ይህ ዓይነቱ ፕሮፓጋንዳ እስከዛሬ ባለመሥራቱ ‹ከንቱ ልፋት› ነው በማለት፣ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለው ፍቅር አንዲት ሠላማዊ ሰልፍ ላይ በወጣች ‹ባነር› ሰበብ ከተቀበረበት አቧራውን አራግፎ ተነስቷል ትለናለች።

5-7

ትዕምርታዊው ትዕይንት፤ የተቃውሞዎቹ ሒደትና ተስፋ ‹በኢትዮጵያ የተቀሰቀሱት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በ‹ዓልቦአመፅ ቀኖና› ሲመዘኑ ምን ይመስላሉ?› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ዘላለም ክብረት እጅን አጠላልፎ ወደላይ ከፍ በማድረግ የሚደረገውን የተቃውሞ ትዕምርታዊ ትዕይንት አጀማመር፣ እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ ተቃውሞ መገለጫ የሆኑ ተግባራትን በመዘርዘር እና በዓለማቀፍ ዕውቅና ባገኙ የሠላማዊ ተቃውሞ መንገዶች ሚዛን ላይ በማስቀመጥ በዚህ ጽሑፉ መዝኗቸዋል።

11-13

ፌስቡክ እና የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ

ፌስቡክ የተባለው በዓለም ከፍተኛ ተጠቃሚዎች ያሉት ግንባር ቀደም ማኅበራዊ አውታር በኢትዮጵያ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይነገራል። ቴዎድሮስ አጥላው በአሁኑ ይዞታው ፌስቡክ ባይኖር የማናውቃቸውን ደራሲያን እያወጣልን ቢሆንም፣ ለድርሰት ሥራ ስጋት የሚሆን አዝማሚያም አለው በማለት የመፍትሔ ሐሳቦችን ይጠቁማል።

16-18

የአግላይ የምርጫ ስርዓት ጦስ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የምርጫ ስርዓቱን ለመሻሻል በማይቀል መልኩ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ እንዲካተት አድርጓል። ዕኩል ጡንቻ ያላቸው ፓርቲዎች በሌሉበት ስርዓት ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን አያበረታታም የሚባለው ‹First Past the Post (FPTP)› ስርዓትን በመከተል የፓርላማ መቀመጫዎችን በሙሉ በመቆጣጠር ራሱን ‹አውራ ፓርቲ› ነኝ ብሎ ሠይሟል - ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.። ተሾመ ተስፋዬ ይህንን እውነታ በመገምገም በጊዜ ካልታሰበበት ጦሱ ለአገሪቷ ደኅንነት እንደሚያሰጋ መክሯል።

21-22 2

ውይይት

ነሐሴ 2008

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ርዕስ አንቀፅ

ሕዝባዊ ናዳን መግታት አይቻልም

2008 ተገባድዷል። 100 በመቶ የሚሆኑትን የምክር ቤት ወንበሮች የተቆጣጠረው ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. አዲሱ ምክር ቤት አንደኛ ዓመቱን አጠናቅቋል። ዓመቱ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. በታሪኩ ከገጠመው ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ሁሉ ለየት እና ጠንከር ያለ ተቃውሞ ሳይለየው ያለፈበት ዓመትም ጭምር ነው። ይሁን እንጂ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ብቻ አልነበሩም የዓመቱ ፈተናዎች፤ ድህነት እና የጤና ፖሊሲ ድክመት የሚያመጣቸው ተላላፊ በሽታዎች ወረርሽኝ መነሳት፣ የ“ሕገ ወጥ” ቤቶች መፍረስን ተከትሎ የተከሰተ ግጭት፣ ሌላው ቀርቶ የዋና ከተማዋን ቆሻሻ ማስወገድ አለመቻል ሳይቀሩ መንግሥትን ሲፈታተኑት የቆዩ ከዓመቱ ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው። ችግሮቹ፣ አንዳቸውም ሁነኛ መፍትሔ ሳያገኙ ዓመቱ መገባደዱና አዲሱ ዓመት ተጨማሪ ችግሮችን ይዞ የሚመጣ መሆኑን ማሰብ አገሪቱ እስካሁን የመጣችበትን ብቻ ሳይሆን ወደፊት እየሔደችበት ያለውን አቅጣጫ እንድንፈራው ያደርገናል። ከምርጫ 2002 የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. 99.6 በመቶ ድል በኋላ አቶ በረከት ስምዖን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ብለው በጻፉት መጽሐፋቸው ላይ ከ1997 ምርጫ በፊት የነበሩትን ሁለትና ሦስት ዓመታት ‹በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ላይ ናዳ ይዘው የመጡ ዓመታት› በማለት ነበር የጠሯቸው። አቶ በረከት ‹ናዳውን ለመግታት የተደረገው ሩጫ በስኬት መጠናቀቁን› ለማብሰር የ1997 ምርጫ በፊትና በኋላ የተደረጉ መንግሥታዊ እርምጃዎችን በመጥቀስ ፓርቲያቸውን ያወደሱ ሲሆን፤ የ2002ቱን ምርጫ ውጤት ደግሞ ከናዳው አምልጦ የሚገሰግስ ታላቅ ፓርቲ ድል እንደሆነ ገልጸዋል። እርሳቸው (የፓርቲያቸውን ሐሳብ ይወክላሉ ብለን እንገምታለን) ይሄን ይበሉ እንጂ ናዳ የተባለው ግን እስከዛሬም አልቆመም። ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ቅድመ እና ድኅረ ምርጫ 1997ን የሚያስታውሰው የሕዝብ ጥያቄ እና ስሜት እንደተንፀባረቀበት መልካም አጋጣሚ ሳይሆን፣ ነጻ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለሥልጣን ይዞታው አደጋ ሊሆን እንደሚችል የተረዳበት አስደንጋጭ አጋጣሚ ነው። ለዚህም ይመስላል ከ1997 በኋላ ያለውን ጊዜ ‹ለሠላም እና ልማት ሲባል ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተወሰኑ ሊጨቆኑ እንደሚችሉ› በአደባባይ እስከመነገር የደረሰው። ከ1997 በፊት የነበረውን ዴሞክራሲያዊ ምኅዳር መፈናፈኛ እስከሚታጣ ድረስ ያጠበበውም በዚሁ ሳቢያ እንደሆነ ይታወቃል። ከ1997 ወዲህ መንግሥት በወሰዳቸው የኃይል እርምጃዎች (ከ193 በላይ ዜጎች ነፍስ እንደጠፋ በወቅቱ መንግሥት አምኗል)፣ በመገናኛ ብዙኃን መዘጋት፣ በተቃዋሚዎች መታሰር፤ ከዚያም በኋላ በተከሰቱ

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ምኅዳሩን ባጠበቡ (በአዋጆች ሥም የተደገፉ እና አንዳንዴ ሙሉ ለሙሉ ሕገ ወጥ የሆኑ) አፈናዎች የፖለቲካ ምኅዳሩ ተጣቦ ምርጫዎች ላይ አቅም ያለው ተወዳዳሪም፣ አሸናፊም ራሱ - ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. እና አጋሮቹ ብቻ ሆነው ቀርተዋል። ይሁን እንጂ፣ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የድኅረ 1997ቱን ቀውስ በተቃዋሚዎች “ሁከት ወዳድነት” እና “በአቋራጭ ሥልጣን ለመንጠቅ” እንደተወሰደ እርምጃ በማናናቅ የሕዝቡን ለውጥ ፈላጊነት ዕውቅና ሳይሰጠው አልፏል። ከዚያ በኋላ ያለውን ጊዜም ቢሆን፣ ሕዝቡ ቅሬታውን ለመግለጽ የሚችልበትን ዕድል በማሳጣት በብቸኛ ፈላጭ ቆራጭነት ለመግዛት እየጣረ ቆይቷል። ነገር ግን፣ የተዳፈነ ይመስል የነበረው ሕዝባዊ ቅሬታ እና የለውጥ ፍላጎት መልኩን እና ቅርፁን ቀይሮ፣ ገዢው ፓርቲ መቶ በመቶ ተመርጫለሁ ባለ ማግስት የድጋፍ መሠረቴ ናቸው በሚላቸው የገጠር አካባቢዎች እና ትናንሽ ከተሞች ሳይቀር አመፅ የቀላቀለ ተቃውሞ እየለበለበው ይገኛል። ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ግን አሁንም ከ1997ቱ ስህተት የተማረ አይመስልም። ዛሬም፣ ችግሮቹን በ“ብልሹ አስተዳደር” ብቻ በማሳበብ፣ ሕዝባዊ ተቃውሞዎቹን “ሕዝብ ቅሬታውን እንዴት መግለጽ እንደሚችል ባለማወቁ ነው” በሚል ሕዝብን በሚያንኳስስ ትንታኔ፤ ከማንነትና ነጻነት ጋር የተያያዙትን ጥያቄዎች “በጠባብነት” እና “ትምክህተኝነት” እንዲሁም “አክራሪነት” ጋር በማያያዝ፤ ብሎም፣ የማይጨበጠው ልማት “የሕዝብን ፍላጎት በመጨመሩ ነው” በሚሉ፣ ሕዝብ ላይ ማላገጥ በሚመስሉ መልሶች እና በፓርቲ የውስጥ ተሐድሶ ብቻ የሚፈቱ ችግሮች በማስመሰል፣ የችግሮቹን መሠረታዊነት የሳተ መልስ በመስጠት ላይ ይገኛል። ገዢው ፓርቲ፣ በሕዝባዊ ቅሬታዎች ላይ የሚከተለው አፈታት በትግል አሸንፌያቸዋለሁ ከሚላቸው የቀድሞ የፖለቲካ ስርዓቶች ታሪክ እና ፍፃሜ ትምህርት የወሰደ አይመስልም። ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የሕዝብ ጥያቄዎችን የሚያጠለሹ ሥያሜዎችን ከመስጠት ያለፈ መልስ ለመስጠት መማር አለበት። ይህ አይሆንም ባለ ቁጥር፣ ያመለጣቸው የሚመስለው የሕዝብ ናዳዎች፣ እየበረከቱ ማሳደዳቸውን ይቀጥላሉ። አዲሱ ዓመት፣ አዲስ መፍትሔዎችን የምናገኝበት እና የምንተገብርበት እንዲሆን መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን።

በውይይት መጽሔት ላይ የመጽሔቱ አቋም የሚንፀባረቀው በ‹ርዕሰ አንቀፁ› ላይ ብቻ ነው።

ውይይት ነሐሴ 2008

3

ከሕዝባዊ ተቃውሞዎቹ ባሻገር…



ትዮጵያ በተቃውሞ እየተናጠች ነው። ከዓለምዐቀፍ እስከ አገር ውስጥ ዜናዎች በነዚህ የተቃውሞ ዜናዎች ተጠምደዋል። መንግሥትም ለችግሩ ሁነኛ መፍትሔ ለማበጀት ቁርጠኝነት በማሳየት ፈንታ ተቃውሞዎቹ እንዳይሰሙ የዜና ምንጮች ለማፈን እየተፍጨረጨረ ይገኛል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሕዝባዊ ተቃውሞዎችን እና የፖሊስን በሠላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የሚወሰድ ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ ያክል የሚያሳስባት ነገር የሌለ ይመስላል። ይሁን እንጂ የፖሊሲ እና የአፈፃፀም ችግሮች የፈጠሯቸው፣ በሕዝባዊ አመፆች ዜና የተሸፈኑ ሌሎችም ገመናዎች ያገጠጡባት አገር ሁናለች። ከሕዝባዊ አመፆቹ ውጪ በዚህ ዓመት ተከስተው እስካሁን ሁነኛ ምላሽ ያልተገኘላቸው ጥቂቶቹን ብቻ እንመልከት።

ሥም አይጠሬው ገመና እውነተኛ ሥሙ “ኮሌራ” እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። መንግሥት አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት (አ.ተ.ት.) ተብሎ እንዲጠራ እንደወሰነ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ገልጸዋል። ‹ዋሽንግተን ፖስት› የተባለው የአሜሪካ ዕውቅ ሚዲያ ጤና ላይ የሚሠሩ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች ‹ኮሌራ› የሚለውን ትክክለኛውን የወረርሽኙን ሥያሜ እንዳይጠቀሙ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ባለሥልጣናት እንዳስጠነቀቋቸው ጠቅሶ ዘግቧል። እንደ‹ዋሽንግተን ፖስት› ድርጅቶቹ ያልተፈቀደላቸው የወረርሽኙን ትክክለኛ ሥም እንዳይጠሩ ብቻ ሳይሆን በወረርሽኙ የተጠቁትን ሰዎች ቁጥርም እንዳይናገሩ ጭምር ነው። መንግሥት ወረርሽኙ በሥሙ እንዲጠራ ያልፈለገበትን ምክንያት የጠየቅናቸው ባለሙያዎች የሰጡን መልስ፣ “ኮሌራ በብዙ የዓለም ክፍሎች ታሪክ ሆኗል።… በጣም በቀላሉ መከላከል የሚቻል በሽታ ነው! በሽታው የጤና ፖሊሲ ችግር በመሆኑ እና የአገር ገጽታን በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ ሊጎዳ ይችላል ብለው ስለሚያስቡ” ነው የሚል ነው። በርግጥም፣ ወረርሽኙ የሚቀሰቀስባቸው መንገዶች የፍሳሽ አወጋገድ እና የአካባቢ ንፅንሕና ጉድለት ጋር በተያያዘ ስለሆነ፣ ጉዳዩ ከሕዝብ ብዛት፣ ድህነት ቅነሳ እና አካባቢ ጥበቃ ፖሊሲዎች ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚገናኝ ነው። በአ.ተ.ት. የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እስካሁን ድረስ ስንት እንደሆነ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አልቻልንም፤ በአዲስ አበባ፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ብቻ 18 ሰው መሞቱን በቅርቡ የወጣ ዜና ያመለክታል። ወረርሽኙ በአዲስ አበባ መከሰቱ የታወቀው ከየካቲት ወር ጀምሮ

4

ውይይት

ነሐሴ 2008

ቢሆንም እስካሁን መቆጣጠር አለመቻሉ፣ ወረርሽኝን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ ደርሰንበታል የሚባለውን ደረጃ አጠራጣሪ ያደርገዋል። ወረርሽኙ አፋጣኝ ዘመናዊ ሕክምና ካላገኙለት የመግደል አቅሙ 50 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። በአዲስ አበባ “ሁለት ሆስፒታሎች (ዘውዲቱ እና ራስ ደስታ) እንዲሁም 29 የጤና ጣቢያዎች” በወረርሽኙ የተጠቁትን ሰዎች በማከም ላይ ይገኛሉ። በተለይ ሆስፒታሎቹ በአ.ተ.ት. ከተያዙ ሰዎች በስተቀር ማስተናገድ አቁመዋል። አ.ተ.ት. በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በደቡብ ክልል፣ በኦሮሚያ፣ በባሕርዳር እና መቀሌ ከተሞች አካባቢም ተከስቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከኑሮ ሁኔታ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው የሚነገረው የእከክ በሽታም አዲስ አበባ ውስጥ መከሰቱ ተሰምቷል።

የቆሻሻው ገመና አ.ተ.ት. የሚከሰተው በአካባቢ ንፅሕና ጉድለት እና በውኃ መበከል ነው። የጤና ጥበቃ ሚኒስትርም፣ የአሁኑ ወረርሽኝ መንስዔ የወንዞች መበከል እና የንፅሕና ጉድለት መሆኑን አልሸሸገም። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አዲስ አበባ ፈተና ገጥሟት ነው የከረመችው። በየአካባቢው የተከማቹት ቆሻሻዎቿን ማንሳት እና ማስወገድ ሳትችል በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባት ሰንብቷል። የከተማዋን ቆሻሻ ያስተናግዳል ተብሎ ከአዲስ አበባ 27 ኪ.ሜ. ርቀት፣ ሰንዳፋ ላይ የተገነባው የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃን የአካባቢው ነዋሪዎች በመቃወማቸው አገልግሎት መስጠት አልቻለም። የአካባቢው ነዋሪዎች የቆሻሻ ማስወገጃው አገልግሎት እንዳይሰጥ የተቃወሙት በአካባቢው በሽታ ሊያመጣ የሚችል ሽታ በመፍጠሩ፣ ወንዞቻቸው በመበከላቸው እና አትክልቶቻቸው በመድረቃቸው ወዘተ. እንደሆነ ተናግረዋል። ትክክለኛ እርምጃ ነበር። የሰንዳፋ ነዋሪዎች የአዲስ አበባ ቆሻሻ ማራገፊያ የሚሆኑበት ምንም ምክንያት የለም። ነገር ግን የአዲስ አበባ ቆሻሻ መራገፊያ አጥቶ በየአካባቢው ፈስሶ ከተማዋ ከገጠማት የበሽታ ወረርሽኝ ሌላ እንድትጠራ እያስገደዳት ነው። ‹የዚህ ሁሉ መንስዔ ምንድን ነው?› የሚለው ጥያቄ የተነሳ እንደሆን፣ ኃላፊዎች 40 ሚሊዮን ብር የእርሻ መሬት ካሣ ለአካባቢው ነዋሪዎች ተከፍሎ የተዘጋጀ ነው በሚሉት (በእርግጥ የአካባቢው ነዋሪዎች የተከፈለው ካሣ ከ5 ሚሊዮን ብር እንደማይበልጥ መጥቀሳቸው ተዘግቧል) የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ አገልግሎት መስጠት ያልቻለው የጎንዮሽ ጉዳቱ ላይ በቂ ጥናት ሳይደረግ ወደ አገልግሎት እንዲገባ መደረጉ ነው። አሁን፣ የአዲስ አበባ ቆሻሻ ረጲ ወደተባለ አካባቢ መወገድ መጀመሩ ተሰምቷል፤

ይሁን እንጂ ይህም ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሆን ምንም ማረጋገጫ ሊኖር አይችልም።

የቤት አልባዎቹ ገመና አዲስ አበባ ስትናጥ ከከረመችባቸው ፈተናዎች መካከል “ሕገ ወጥ ቤቶችን በማፍረስ” ሥም የደረሰው ቀውስ ነው። ከ20 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ የሚደርሱ ሰዎች የሚኖሩባቸው መንደሮች፣ ያውም መንግሥት መንገድ የጠረገላቸው፣ የመብራት እና የውኃ አገልግሎት የሠራላቸውን ቤቶች ለማፍረስ በተደረገው “የደንብ አስከባሪዎች” እንቅስቃሴ ለሰው ሕይወት እስከማለፍ መንስዔ ሆኗል። ምንም እንኳን ወራቱ ክረምት ቢሆንም፣ ደንብ አስከባሪዎች የነዋሪዎችን ንብረት ሜዳ ላይ በመበታተን እና ቤቶቹን በማፈራረስ የመንደሮቹን አሳዛኝ ፍፃሜ አፋጥነዋል። ከምርጫ በፊት በሚደረጉ ጦሳቸው ያልታሰሰባቸው “ሕገ ወጥ ቤቶች ሕጋዊ ይሆናሉ” የሚሉ ቀቢፀ ተስፋ ንግግሮች እና ቤቶቹ ሲሠሩ እያዩ እንዳላዩ በማለፍ ቸልተኝነት በተፈጠሩ የመንግሥት ስህተት የተገነቡ “የጨረቃ ቤቶችን” በሌላ ሕገ ወጥ መንገድ በማፍረስ ብዙ የነፍስ እና የንብረት ኪሳራ እንዲደርስ ሆኗል። በሪፖርተር ጋዜጣ (ነሐሴ 18፣ 2008 እትም) “በችግር ላይ የሚገኙ የወረገኑ ተፈናቃዮች የስደተኞችን ያህል ዕርዳታ እንዲፈቀድላቸው ጠየቁ” የሚል ዘገባ ወጥቷል። ዜጎች በገዛ አገራቸው ላይ የስደተኛ ማዕረግ ለማግኘት እስከሚመኙ ድረስ መድረሳቸው በመንግሥታዊ ቅሌትነት የሚወዳደረው የማይገኝለት ዜና ነው። እነዚህ ሦስቱ ከላይ የጠቀስናቸው ገመናዎች በሙሉ ከአስተዳደር ድክመት እና ሕዝብን ያማከለ ፖሊሲ ካለመኖሩ ጋር ተያይዘው የሚወለዱ ችግሮች መሆናቸው አያጠያይቅም። ነገር ግን እነዚህ የሕግ የበላይነት ባለባቸው አገራት በሚኒስትር ማዕረግ ላይ ያሉ አመራሮችን ከሥልጣን እስከማስነሳት የሚያስደርሱ ችግሮች፣ በአገሪቱ የባሱ ችግሮች በመኖራቸው ምክንያት ተዳፍነዋል። ከእነዚህ የባሱት ችግሮችም ቢሆኑ መንግሥትን ለባሰ ተጠያቂነት የሚያስገድዱት ቢሆንም በስርዓቱ ባሕሪ የተነሳ እስካሁን አልተደረገም። ነገር ግን ይህ የትም የማያደርስ ጉዞ መሆኑ መታወቅ አለበት። ምንም እንኳን መንግሥት ሕዝባዊ አመፆቹን ለመቆጣጠር ሙሉ ኃይሉን እና ትኩረቱን እነርሱ ላይ በማድረጉ ሊሳካለት ቢችል፣ እነዚህ ችላ የተባሉት እና ሌሎችም ያልተነገሩ ችግሮች ሌሎች ሕዝባዊ ብሶቶችን እና ተቃውሞዎችን እንዳያስነሱ ማድረግ አይችልም። በመሆኑም፣ መፍትሔው የአስተዳደር እና የፖሊሲ ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግ ብቻ ነው።

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ሐሳብ

ያቺ ‘ባነር’ በሕዝብ ብዛት የትልልቆቹ ክልሎች የኦሮሚያ እና አማራ ሕዝቦች በመንግሥታዊ ስርዓቱ ላይ በማመፃቸው የተደናገጠው ሕ.ወ.ሓ.ት. መራሹ መንግሥት እና ደጋፊዎቹ የሁለቱን ሕዝቦች ትብብር ለማክሸፍ ሕዝቦቹን እርስ በርስ የማይስማሙ “እሳትና ጭድ” መሆናቸውን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመግለጽ ለመከፋፈል እና ለማዳከም እየሞከሩ ነው። መስከረም አበራ ይህ ዓይነቱ ፕሮፓጋንዳ እስከዛሬ ባለመሥራቱ ‹ከንቱ ልፋት› ነው በማለት፣ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለው ፍቅር አንዲት ሠላማዊ ሰልፍ ላይ በወጣች ‹ባነር› ሰበብ ከተቀበረበት አቧራውን አራግፎ ተነስቷል ትለናለች።



ኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ መባቻ ከዘመነ መሳፍንት ማክተም ጋር የሚቆራኝ ነው። የአገራችንን የቀደመ ግርማ አኮስሶ፣ የጦር አለቆች የረብሻ ምድር አድርጓት የኖረው፣ በታሪክ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ የሚታወቀው ወቅት የቆየበት ጊዜ ዘለግ ያለ በመሆኑ ተክሎት ያለፈው ችግር ሥር የሰደደ ነበር። በተለይ ከዘመነ መሳፍንት በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ ነገሥታት በታላቅ አገር ላይ ታላቅ መሪ የመሆን አልፎም ቀይ ባሕርን ተሻግሮ የማስገበር የታላቅነት ምኞት በትንንሽ መንደሮች ትንሽ አለቃ ለመሆን ወደ መቃተት የንዑስነት ምኞት አንሶ ነበር። ይህ የንዑስነት ዘመን መንደርተኛነት በአገራዊነት ላይ የገነነበት፣ መነጣጠል አብሮነትን የረታበት፣ የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሰለለበት ዘመን ነበር። ይህ የድቀት ዘመን ያከተመው ከወደ ጎንደር በተነሳ የቀደመ ታላቅነትን የመናፈቅ ሐሳብ ነበር። ሥር የሰደደው የዘመነ መሳፍንት ዘመን የንዑስነት ምኞት እና የመከፋፈል አባዜ በቋራው ካሣ ታላቅነት የመናፈቅ ከፍ ያለ እሳቦት ፍፃሜውን አገኘ። የካሣን ውድ ሕይወት ቢነጥቅም በዘመነ መሳፍንት የመንደርተኝነት ዝንባሌ እልም-ስልም ሲል የባጀው የኢትዮጵያዊነት ስሜት ወደ ሕዝብ ልቦና ተመለሰ። ሆኖም ከዘመነ መሳፍነት ማክተም ብዙ ዘመን በኋላ ኢትዮጵያዊነት ሌላ ፈተና ገጠመው። በተለይ ከኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ወደ መንበር መምጣት በኋላ ኢትየጵያዊነትን የማቀንቀን ፖለቲካዊ አቋም፣ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ትሩፋቶች መስበክ፣

እውነታው ኢትዮጵያዊነት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልቦና ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ያለው ነው። አከራካሪው ነገር ኢትዮጵያ እንዴት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ዕኩል የሆነች እናት ትሁን በሚለው ታሪክ ከማቃለል ይልቅ እያከማቸው በመጣው የቤት ሥራ ላይ ይመስለኛል

ስለኢትዮጵያዊ ወንድማማች/እህትማማችነት ማውራት እንደ መርገም ጨርቅ ያለ ነገር ሆኖ ኖረ። የመርገም ጨርቁ ሥም ደግሞ “ትምክህተኛ አማራነት” ነው። የኢትዮጵያ አንድነት የሚጠቅመው ለአማራው ብቻ ባለመሆኑ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. አማራ ከሚላቸው ሰዎች ሌላም በሁሉም የአገራችን ጥግ ለኢትዮጵያዊነት የሚቃትቱ ኢትዮጵያዊያን በብዛት አሉ። ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ለእነዚህም ሥም አለው - “የአማራ ተላላኪዎች” ሲል አንድ ሰው ስለ አገሩ ኅልውና እና የአገር ባለቤትነት ጥቅም በራሱ ጭንቅላት አስቦ ይረዳ ዘንድ የማይቻል አስመስሎት ቁጭ ይላል። እውነታው ኢትዮጵያዊነት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልቦና ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ያለው ነው። አከራካሪው ነገር ኢትዮጵያ እንዴት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ዕኩል የሆነች እናት ትሁን በሚለው ታሪክ ከማቃለል ይልቅ እያከማቸው በመጣው የቤት ሥራ ላይ ይመስለኛል። ከእውነት ጋር ብዙ የማይስማማው ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ታዲያ ይህን የታሪክ ክፍተት ለተፈጠረበት ኢትዮጵያዊነትን የማደብዘዝ ዕኩይ ዓላማ በደንብ ተጠቀመበት። አገዛዙ በቆይታው ስኬታማ የሆነበት ዋናው ጉዳይ ይህን እኩይ ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሮጠው ሩጫ ይመስለኛል። ሕ.ወ.ሓ.ት. ዐሥራ ሰባት ዓመት “ጭንጫ ገደሉን ረግጬ፣ ቧጥጬ፣ የታገልኩት ለብሔር ብሔረሰቦች መብት ስል ነው” ባይ ነው። ይህን ያስመሰክር የነበረው ደግሞ የአማራ ሕዝብን ቅስም የሚሰብሩ ንግግሮች፣ ድርጊቶች በማድረግ ነው። ሕ.ወ.ሓ.ት. ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊትም ሆነ ከመጣ በኋላ የፖለቲካ ግንዛቤው ጥግ የአማራን ሕዝብ ማጥላላት፣ ያልሆነ ሥም መለጠፍ፣ ማሰር፣ ማፈናቀል፣ መግደል፣ ሰድቦ ለተሳዳቢ መስጠት ይመስለው ነበር። ለሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች መብት መቆሙን የሚያስመሰክረውም የጠየቁትን፣ ራሱም በሕገ መንግሥቱ የጻፈውን እስከ መገንጠል የዘለቀውን መብት በመተግበር ሳይሆን የአማራን ሕዝብ በአደባባይ በማበሻቀጥ፣ ‘የድሮ በዳያቸውን’ (አማራን መሆኑ ነው) የማጥፋቱን ታዳጊነት ገድል በመተረክ ነው። የድሮው ይቅርና በቅርቡ የአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝን ወደ ሥልጣን መምጣት አስመልክቶ አዛውንትነታቸውን ወደሚቀጥለው ገጽ

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ውይይት ነሐሴ 2008

5

ሐሳብ የሚመጥን የንግግር ጨዋነት የሚያጥራቸው አዛውንቱ ስብሓት ነጋ ‘ሰውየውን መሾማችን አማራን እና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይን ከሥልጣን አጥረግገን የማጥፋታችን ምልክት ነው’ ሲሉ ጫካ የለከፋቸው የጥላቻ ክፉ ደዌ እያደር የሚብስ መሆኑን አመልክተዋል። ይህን ክፉ ጥላቻ ያረገዙት ሕ.ወ.ሓ.ት.ዎች የሕዝብ መገናኛ ብዙኃንን ለብቻቸው አንቀው መያዛቸው፣ በመገናኛ ብዙኃን ይህንኑ የጥላቻ ስብከት ለማጧጧፍ እፍረትም ሆነ ኃላፊነት የማይሞክራቸው መሆኑ ደግሞ የነገሩን ውጤት በተለይ በአማራው ሕዝብ ላይ ክፉ አድርጎት ኖሯል። ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ከኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. በኋላ ያለችውን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ አጨልመው የሚያቀርቡትም ከዚህ እውነታ ጋር በተያያዘ ነው። የሠራውን የሚያውቀው ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ደግሞ በዚህ ኃላፊነት በጎደለው ሥራው ሊያፍር ሲገባው ይኩራራል፣ ‘ከሌለሁ ወዮላት ለኢትዮጵያ’ ሲል ያስፈራራል። በአገሪቱ ሌላ ፍጥረት ያልተፈጠረ ይመስል የእልቂቱ ተዋናዮች፣ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ወሳኞች የአማራ አና የኦሮሞ ሕዝብ እንደሚሆኑ ይተነብያል። የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝብ ለመገዳደል ብቻ የሚፈላለጉ ታሪካዊ ባላንጣዎች አድርጎ ውሸትን እጅግ ደጋግሞ እውነት ሊያስመስል ምንም አልቀረውም ነበር።

ከንቱው ልፋት የስሌት አውዳችን ጎሳን ማዕከል ያደረገ ከሆነ ሕ.ወ.ሓ.ት. ወጣሁበት የሚለው የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያ ንዑስ ቁጥር ካላቸው ጎሳዎች ወገን ነው። እንደ እውነቱ ቢሆን የጎሳ ፖለቲካ መሲህ ነኝ የሚለው ሕ.ወ.ሓ.ት. የሰፈሩን ልጆች ጠርቶ የወረረውን የፖለቲካ ሥልጣን ለታላላቆቹ ኦሮሞ እና አማራ ጎሳዎች መልቀቅ ነበረበት። ይህን እንደማያደርግ ልቦናው የሚያውቀው ንዑሱ ሕ.ወ.ሓ.ት. ታዲያ እንደ አማራጭ ያየው ሥልጣኑ ለሚገባቸው ጎሳዎች እርስበርስ የመናቆር፣ ዓይን እና ናጫ የመሆን የቤት ሥራ መስጠት ነው። ለኦሮሞዎች የተበዳይነት ሙዚቃ ከፍቶ ሲያስቆዝም ለአማራው እንደጉተና የከበደ የበዳይነት ሸክም ጫነበት። አማራው በተነፈሰ ቁጥር በእብሪተኛነት፣ በጭካኔ፣ በትምክህተኛነት እየፈረጀ ሁለተኛ ወደ ሥልጣን ዝር ማለት የሌለበት እኩይ አድርጎ ያቀርበዋል። በትዝታ እንዲቆዝም የተደረገው ኦሮሞ ታዲያ አሁን ሊቀመጥበት የሚችለውን የፖለቲካ ሥልጣን ወንበር ጥያቄ ረስቶ ቀና ብለው “አቤት” የማይሉትን ዐፄ ምኒልክን በመርገም፣ በመውቀስ እንዲጠመድ ተደርጓል። ዐፄ ምኒልክም መላውን አማራ ወክለው የሞቱ ይመስል ለእርሳቸው በተነሳው የጭቃ ጅራፍ አማራ የተባለው ሁሉ ይገረፍ ያዘ፣ ለምኒልክ የተከፈተ የበደል ሙዚቃ ለአማራ ሁሉ የሚበቃ የጥላቻ ስንቅ አስቋጥሮ በጎሪጥ ሲያስተያይ፣ አፍንጫ ሲመታ ዓይን እንዳያለቅስ እንባ አድርቆ ኖሯል። አማራውም በፊናው በዋናነት በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በሌሎች ክልሎችም

6

ውይይት

ነሐሴ 2008

ለፍቶ ያፈራውን ንብረት ለቆ እንዲወጣ ሲደረግ ይህን ያደረገው ማን እንደሆነ ስለሚያውቅ በተዋለደው እና አብሮ በኖረው ሕዝብ ላይ አፉን አላላቀቀም። አማራነቱ ብቻ በደል ሆኖ ተቆጥሮ የሚገረፍበትን በትር ብርታት ስላወቀ አድርጎት የማያውቀውን አንገቱን መድፋት ተማረ፣ ቅዝምዝምን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ ተሽሎት ወገኖቹ ሲታሰሩ፣ ሲገደሉ፣ ከምድር ዳርቻ ሲሳደዱ አዝኖ እንዳላዘነ ሆኖ አለፈው። ሽሽት የማያውቀው ሕዝብ ሽሽት ለመደ። ይሄኔ ነው እነ ስብሓት ነጋ፣ ሳሞራ የኑስ እና መለስ ዜናዊን የመሰሉ የጥላቻ ሰባኪዎች ‘አማራን እንዳይነሳ አድርገን ቀበርነው’ ያሉት። ሰፊውን የአማራ ሕዝብ ብቻቸውን ገድሎ ለመቅበር የንዑስነት አቅማቸው እንደማይፈቅድ የተረዱት ሕ.ወ.ሓ.ት.ዎች ባለግርማውን የኦሮሞ ሕዝብ መጠለያ ማድረግን መረጡ። ‘ከየት አመጣችሁት?’ ተብለው የሚጠየቁበት መድረክ የለምና የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝብ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በኖረ የመረረ፣ የከረረ ጠላትነት እንዳላቸው ብቻቸውን በያዙት መገናኛ ብዙኃን ሲያላዝኑ ኖሩ። በሐሰት የተለወሰ የፈጠራ እና የጥላቻ መርዛቸውን መድኃኒት አስመስለው የሚያቀርቡበትን ስብከት ስለሚያረክስባቸው በሳይንሳዊ መረጃ ላይ የቆሙ የታሪክ ድርሳናትን አጣጣሉ። እውነትን ለመፈለግ በየዋሻው የተሻጡ ‘ኦርጅናል’ የታሪክ መዛግብትን የሚያስሱ ኢትዮጵያ-በቀል የታሪክ ተመራማሪዎችን ፈተናቸውን አብዝተው ከአገር አሰደዱ። ሰሞኑን በፕ/ሮ ፍቅሬ ቶሎሳ አዲስ መጽሐፍ ሽያጭ ላይ የተዘመተው (የመጸሐፍ አዟሪ ነጋዴዎችን የማሰር) ዘመቻ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።

የጎንደሩ ጥሎሽ ሕ.ወ.ሓ.ት. ሁለቱን ሕዝቦች እርቅ ሊጎበኘው በማይችል የጠላትነት አዘቅት ውስጥ ለመክተት የተጠቀመው መንገድ መገናኛ

በትዝታ እንዲቆዝም የተደረገው ኦሮሞ ታዲያ አሁን ሊቀመጥበት የሚችለውን የፖለቲካ ሥልጣን ወንበር ጥያቄ ረስቶ ቀና ብለው “አቤት” የማይሉትን ዐፄ ምኒልክን በመርገም፣ በመውቀስ እንዲጠመድ ተደርጓል

ብዙኃን፣ የራሳቸውን ኃላፊነት አልቦ አንደበት እና ከሁለቱም ብሔር የወጡ ግዙ ባለሥልጣን እና ካድሬዎችን ብቻ አይደለም። የነመለስ ዜናዊ የጥፋት መንገድ እጅግ ረቂቅ ነውና የተስፋየ ገብረአብን ውብ ብዕርም ለዚሁ እንቅልፋቸውን ለሚነሳቸው የሁለቱ ሕዝቦች አብሮነት ማፍረሻ በደንብ አድርገው ተጠቅመውበታል። ተስፋየም ሐፍረት እና ይሉኝታ ባለፈበት ያለፈ ሰው ስላልሆነ ‘ነቅተንብሃል’ እየተባለም በልጅነቱ እንደማተብ የታሰረለትን የጥላቻ ክታብ ሊያወልቅ አልቻለም፤ ከቀድሞ አልባሽ አጉራሾቹ ጋር ከተጣላ በኋላም የጥላቻ ብዕሩ መርዝ መትፋቱን አላቆመም። ሕ.ወ.ሓ.ት. ይህን ሁሉ ከንቱ ድካም ሲደክም የኖረው በአሽዋ ላይ የቆመ ቤት ለመሥራት ነበርና የአንድ ቀን የሕዝብ ድምፅ የሃያ አምስት ዓመት ድካሙን ገደል ከተተው። ከወደ ጎንደር በፍቅር ብዕር፣ በመተሳሰብ ሸማ ላይ የተከተበች አንድ ባነር ታሪክ ለወጠች። “በጎዳና ላይ የሚፈሰው የኦሮሞ ወንድምና እህቶቻችን ደም የእኛም ደም ነው” የምትል የኦሮሞ ፌዴራል ኮንግረስ (ኦ.ፌ.ኮ.) ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንት አቶ በቀለ ገርባን ምስል የያዘችው ባነር ስንቱ ፊደል ጠገብ አጥብቆ የፈተለውን የጥላቻ ገመድ በጣጠሰች፤ በምትኩ ሁለቱን ታላላቅ ሕዝቦች በፍቅር እንባ አራጨች። መብቱን ከማስከበር ጎን ለጎን የጠፋ ወንድማማች/እህትማማችነትን ፍለጋ የወጣው የጎንደር ሕዝብ በፍቅር ፊት መቆም የማይችለውን የሕ.ወ.ሓ.ት.ን በአሸዋ ላይ የተገነባ የጥላቻ ቤት በፍቅር አውሎ ንፋስ ከሥሩ ነቀነቀው። የጥላቻ መንገድ አይቀናም። የሴራ ወንበር አይፀናምና ይህ የሚጠበቅ ነው። የጥላቻ ሰባኪዎች ግን ይህን ይረዱ ዘንድ ብቁ አይደሉም። በወርቅ የማይገዛውን የወንድማማችነት ፍቅር “ያልተቀደሰ ጋብቻ” ሲሉ ያልተቀደሰ ጭንቅላታቸው ያቀበላቸውን ዘባረቁ፤ ፍርሐት ያራደው ከንፈራቸው ላይ የሞላውን ስድብ ሁሉ በሰፊው ሕዝብ ላይ አወረዱ። ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ዎች ጥሩ የተናገሩ እየመሰላቸው ከአንደበታቸው የሚወረውሯቸው ቃላት እና ሐረጋት በመንግሥት መንበር ላይ መሰየማቸውን አይመጥኑም። ሌሎቹ ቀርተው ‹የአንደበታቸው ርቱዕነት ወፍ ያረግፋል› ይባሉ የነበሩት የአቶ መለስ አንደበት እንኳን በግሌ ጨዋነት የጎደለው፣ ማናለብኝነት ያሸነፈው፣ አንዳንዴም ግልብ እንደነበረ ይሰማኝ ነበር። በተከበረው ፓርላማ ፊት ‘ጣትህን እቆርጣለሁ፣ ምላስ እዘለዝላለሁ’ ይሉ ነበር። የሁለት አካላትን ሠላማዊ ግንኙነትም ከዕቁባታዊ ግንኙነት ጋር እየመሰሉ ማስረዳቱ ይቀናቸው ነበር። በ1997 አላሰናዝር ብለው የነበሩትን አና ጎሜዝን በተመለከተ ለ‹አዲስ ዘመን› እና ‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ› ጋዜጦች ኤዲተር በጻፉት ማስታዎሻ “what’s love got to do with this?” የሚለውን የታዋቂዋን ዘፋኝ የቲና ተርነርን ሙዚቃ ግጥም መንግሥትነትን በማይመጥን አላስፈላጊ ሁኔታ አስገብተው ነበር። አሁን የመንግሥት አንደበት ተደርገው

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ሐሳብ የተሰየሙት አቶ ጌታቸው ረዳ መሆናቸው ደግሞ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መንደር ለአንደበት ጨዋነት ብዙ ቦታ እንደሌለ አሳባቂ ነው። ብሶት በጠበንጃ ፊት እንደቆመ እንኳን አስረስቶ የሚያጮኸውን የኦሮሞ ሕዝብ ከጅኒ ጋር እያነፃፀሩ ሲያስረዱ ለአቶ ጌታቸው በአማርኛ መራቀቅ፣ በሐሳብ መምጠቃቸው ሊሆን ይችላል። ለሰሚ ግን ትርጉሙ ሌላ ነው። አንድ ሰው በቤቱ የቀረ በማይመስል ሁኔታ ነቅሎ የወጣውን የአማራ ሕዝብ ጥቂት የሽፍታ ጠበቆች ሲሉ ዘለፉ። ሁለቱ ሕዝቦች ከተገደሉ ልጆቻቸው ዕኩል የተሰደቡት ስድብ አስቆጥቷቸዋል። በዚህ የማያበቁት አቶ ጌታቸው ‘ሁለት ባላንጣዎች ያተቀደሰ ጋብቻ መሥርተዋል’ ሲሉ አከሉ። እውነት ለመናገር ነገሩ በጋብቻ ሁኔታ ባይገለጽ ደግ ነበር:: ሆኖም ሰው በልቡ የሞላውን በአንደበቱ ይናገራልና አቶ ጌታቸው በልባቸው የሞላውን ገለጹ። ነገሩ የሚገባቸው በጋብቻ ሁኔታ መገለጽ ካለበት የኦሮሞ እና የአማራ ታላላቅ ሕዝቦች ቅዱስ ጋብቻ ጎንደር ላይ በቀረበችው የፍቅር ጥሎሽ (ያቺ ባነር) ተጀምሮ ኦሮሚያ ላይ “አማራ የኛ” በሚል ሙዚቃ ታጅቦ ተፈጽሟል። ይህ ቢመርም ሊቀበሉት የሚያስፈልግ ሐቅ ነው! በምድር ላይ የሚያስተዳድረው ሕዝብ መተሳሰብ የሚያናድደው፣ ክፉ የሚያናግረው

መንግሥት ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ብቻ ሳይሆን አይቀርም። “የአማራ እና የኦሮሞ ህዝብ ይህን ዓይነት መፈክር ይዘው መውጣታቸው “የእኛን ሥራ ያለመሥራት ያመላክታል” አሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ለፋና ሬዲዮ። ፋይሉ በድረገጾች ስላለ ዝርዝሩን አንባቢዎቼ ቢያዳምጡ ሙሉ ስዕሉን ለማግኘት ይችላሉ። ይህ ከአእምሮ በላይ ነው!

ቅዱሱ ጋብቻ!

የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን እግር ተከትሎ በአገራችን የተንሰራፋው እትብት እየተማዘዙ የጎሪጥ የመተያየት አባዜ አሁንም የአገራችን ፖለቲካ ዋና ነቀርሳ ነው። ችግሩ የሚመነጨውም ሆነ የሚበረታው ተማርኩ በሚለው የኅብረተሰብ ክፍል ነው። መማሩ ሥነ ልቦናውን ከታሪክ ጋር እያዋቃ ጥላቻን ብቻ እንዲሰብክ ያደረገው የትየለሌ ነው። እንደ ደህና ነገር ስንት ገጽ መጽሐፍ አሳትሞ በየገጹ ጥላቻን ሳይረሳ የሚሰብክ ምሁር በበዛበት አገር፤ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ም ይህን በደንብ ሲያሳልጥ ሃያ አምስት ዓመት ከንቱ ሲደክም ቢኖርም ሰሚው ሰፊ ሕዝብ ጥላቻን የሚሰማበት የጆሮ መስኮቱን ዘግቶ ኖሯል። የጎንደር ሕዝብ የጀመረውን የፍቅር ምልክት የኦሮሚያ ሕዝብ ወዲያው ማስተጋባቱ የሚያረጋግጠው

ድሮም ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. በሚያራግበውን እና ፅንፈኛ የጎሳ ልኂቃን በሚያንፀባርቁት ደረጃ ሕዝቦች በጠላትነት እንደማይፈላለጉ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ሳይውል ሳያድር “እናንተም የእኛ ናችሁ” ሲል መልስ የሰጠው በፍቅር መበለጥን ስላልፈለገ ነው። በፍቅር ላለመበላለጥ መሽቀዳደም ደግሞ የመልካም ልቦና ዝንባሌ ነው። ይህ ብው በሚያደርግ ንዴት ውስጥ የሚከተው ደግሞ ራሱን መመርመር ግድ ይለዋል! ጎንደር እና አዳማ አፋፍ ላይ ሆነው “ደምህ ደሜ፣ አጥንትህ አጥንቴ” ሲባባሉ ሌሎች ከተሞችም ይህን ሲከተሉ የኮምፒውተር “በተን” በነኩ ቁጥር ሕዝብን የመሩ የሚመስላቸው የጥላቻ ሰባኪዎች የወንጀለኝነት ስሜት እንደሚሰማቸው ጥርጥር የለኝም። ወትሮም ገታራነት የማይጫናቸው የኦሮሞ ምሁራን ይህ የሕዝብ መተሳሰብ የኖሩበትን የፖለቲካ አቅጣጫ እንዳስቀየራቸው በአንደበታቸው ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ሁሉም የሚሉት ‘ሕዝብ መራን፤ ሕዝብ በለጠን፤ ሕዝብ ቀደመን’ ነው! የትምህርት ደረጃን ቆጥሮ ብዙኃኑን ሕዝብ ሳይንቁ፣ እኔ አውቅልሃለሁ ሳይሉ፣ ይልቅ መበለጥን አውቆ አካሔድን ማስተካልም የምሁራኑን ትህትና ያመለክታልና በተለይ የኦሮሞ ምሁራን ለዚህ ትህትናቸው ምስጋና ይገባቸዋል።

ያመኑት ፈረስ… ከሕ.ወ.ሓ.ት. የወቅቱ ዘዋሪዎች አንዱ አይተ ኣባይ ፀሓየ የፓርቲያቸውን አርባኛ ዓመት በዓል ድል ባለ ድግስ ሲያከብሩ ‘እነ ኢ.ሕ.አ.ፓ. ሲንኮታኮቱ እኛ ድል የተቀዳጀነው ሕዝብን ለማታገል ቀለል ያለውን የጎሳ ፖለቲካ የሙጥኝ ስላልን ነው’ ዓይነት ንግግር ሲናገሩ ተገርሜ ነበር ያዳመጥኳቸው። ሕዝብን የማታገያ ዘይቤ የሚመረጠው ስለቀለለ ነው ወይስ የሕዝብ እውነተኛ ጥያቄ ስለሆነ? ቀላል የተባለው የጎሳ ፖለቲካ ከምክንያት ይልቅ ስሜትን ስለሚፈልግ ብልጣብልጦቹ የሕ.ወ.ሓ.ት. መኳንንት በጎሳህ ምክንያት የፈረደበት አማራ ቆረጠህ ፈለጠህ እያሉ የብረት ተሸካሚ፣ ወላፈን እሳት ላይ ተማጋጅ ነፍስ ለማግኘት ስለማያስቸግር ነው። ሥልጣን ላይ ከተሳፈረ በኋላም ሕ.ወ.ሓ.ት. መራሹ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ከላይ ለመጥቀስ በተሞከረው መልክ በአገሪቱ የሚገኙ ወንድማማች ሕዝቦችን ከአንድነታቸው ይልቅ ልዩነት ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጉን በቀላሉ ሥልጣን ላይ ተወዝቶ የመኖሪያ ሁነኛ ዘዴ አድርጎት እንደነበር ነገራ ነገሩ ያስታውቃል። በዚሁ በጎሳ እና በጥላቻ ፖለቲካ ተፀንሶ፣ አድጎ ዙፋን ላይ የተሰየመው ሕ.ወ.ሓ.ት./ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የሚወደውን ዙፋኑን እየነቀነቀው ያለው ከጎሳ ፖለቲካ ጋር በተዛመደ የመረረ ጥያቄ መሆኑ ትልቅ የፖለቲካ አያዎ ነው! ከወደ ጎንደር በፍቅር ብዕር፣ በመተሳሰብ ሸማ ላይ የተከተበች አንድ ባነር ታሪክ ለወጠች። “በጎዳና ላይ የሚፈሰው የኦሮሞ ወንድምና እህቶቻችን ደም የእኛም ደም ነው” የምትል የኦሮሞ ፌዴራል ኮንግረስ (ኦ.ፌ.ኮ.) ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንት አቶ በቀለ ገርባን ምስል የያዘችው ባነር ስንቱ ፊደል ጠገብ አጥብቆ የፈተለውን የጥላቻ ገመድ በጣጠሰች፤ በምትኩ ሁለቱን ታላላቅ ሕዝቦች በፍቅር እንባ አራጨች (ፎቶ፤ ማኅበራዊ ሚዲያ)

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

መስከረም አበራ በኢሜይል አድራሻዋ [email protected] ሊያገኟት ይችላሉ፡፡

ውይይት ነሐሴ 2008

7

በሮቤል ኪሮስ አሳፋሪ ሽንፈት የተጀመረው የኢትዮጵያ የሪዮ ኦሎምፒክ 2016 ተሳትፎ፣ በፈይሳ ሌሊሳ ድርብ ድል ተጠናቅቋል። እሁድ ነሐሴ 14፣ 2008 ለኢትዮጵያውያን ልዩ ቀን በመሆን ተመዝግባለች። በኢትዮጵያ ያሉትን የመብት ጥሰቶች ለመቃወም ዜጎች እጆቻቸውን በማጣመር የሚያሳዩትን ምልክት አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ ኦሎምፒክ ላይ በማሳየት ልዩ ታሪክ አስመዝግቧል። የዓለም መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ያሉትን ችግሮች ከመቼውም ግዜ በላይ እየተቀባበሉ እንዲዘግቡ እና በዓለምዐቀፉ ማኅበረሰብ ችላ የተባለውን ጉዳይ እንዲያወሱ ፈይሳ ሌሊሳ በድርብ ድሉ አስገድዷቸዋል። መብራቱ በላቸው የዚህን ጀግና አትሌት የጀብድ ታሪክ በጥቂቱ ያስቃኘናል።

8

ውይይት

ነሐሴ 2008

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

አንድ ሰው

ምልክታችን ፈይሳ ሌሊሳ የማትረሳዋ ምሽት ነሐሴ 14 ቀን 2008 የአዲስ አበባ ፖሊሶች በሥራ ተጠምደው ነበር ሌሊቱን ያነጉት። “እሁድ ይደረጋል” ተብሎ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተናፈሰው የሠላማዊ ተቃውሞ ሰልፍ ጥሪ ነበር የአዲስ አበባን ሕዝብ ምሽቱን በሔደበት ሁሉ በፍተሻ እንዲዋከብ ያደረገው። እሁድ እንደታሰበው መስቀል አደባባይን ሠላማዊ ሰልፈኛ ሕዝብ ሳይሆን የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ነበር የወረረው። ከተማዋም ከፍተኛ ውጥረትን አስተናግዳ የተቃውሞ ሰልፉን አመለጠች። ይሄን የታዘበው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እፎይታ በተሞላበት ሁኔታ፣ ነገር ግን ብዙዎች እንደ ቀልድ በቆጠሩት የማኅበራዊ ድረገጽ መልዕክት “ሠላም ወዳዱን የአዲስ አበባ ሕዝብ እጅ ነሳ”። ሰልፉ ባለመካሔዱ እፎይታ የተሰማው መንግሥት፣ የዛኑ ዕለት፣ እሁድ፣ ነሐሴ 15፣ 2008 እፎይታውን የሚገፍፍ፣ እረፍት የሚነሳ፣ ሊቆጣጠሩት አቅም የሚያሳጣ ክስተት ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩት የሪዮ ኦሎምፒክ አደባባይ ተከሰተ። ዓይኖች ሁሉ በሪዮ ኦሎምፒክ የመዝጊያ ታላቁ የወንዶች የማራቶችን ውድድር ላይ ትኩረት ባደረጉበት በዚያች ሰዐት ነበር ፈይሳ ሌሊሳ በታላቅ ተጋድሎና ጀግንነት ኬኒያዊውን ኢሉድ ኪፕቾግ /Eliud kipchoge/ ተከትሎ የሁለተኝነት ድሉን የተቀዳጀው። ይሄ ድል ግን ዝም ተራ ድል አልነበረም። ታሪክ ቀያሪ፣ ታሪክ ሠሪ፣ የዓለም ሁሉ መነጋገሪያ ልዩ ድል እንጂ! ፈይሳ ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች “ድምፃችን ይሰማ” እያሉ ተቃውሟቸውን በመንግሥት ላይ ሲያሰሙ ይጠቀሙበት የነበረውን ምልክትና በመላው ኦሮሚያና አማራ የተቃውሞ ምልክት ተደርጎ የተወሰደውን እጅን ከፍ አድርጎ መስቀለኛ በማጣመር በአሁኑ ሰዐት በአገሩ እየተደረገ ላለው የተቃውሞ እቅስቃሴ አጋርነቱን አሳየ። ያች ምሽት በኦሎምፒክ ታሪክ ከተመዘገቡ ታላላቅ ክስተቶች እንደ አንዷ ሆና በመላው ዓለም ተመዘገበች። የአዲስ አዲስ አበባ ሕዝብም “በመስቀል አደባባይ የተቀማነውን ሠላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ዕድል በፈይሳ ሌሊሳ በኩል

በሪዮ አደባባይ ገልጸናል፤” ሲል በየማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ለፈይሳ አድናቆቱን እና ክብሩን ገለጾለታል። በመላው ዓለም የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃንም ወሬውን ተቀባበሉት፤ ከአድማስ አድማስም አስተጋቡት። በዓለም ላይ ያሉ የዓለማችን ታዋቂ ሚዲያዎች ዘገቡት፤ ተነተኑት፤ ጉዳዩን ለዓለም አሰሙት።

የሁለት ኦሎምፒኮች ወግ

እንደ ጎርጎሳዊያኑ አቆጣጠር በ1968 ሜክሲኮ ድል ያለ የኦሎምፒክ ድግስ አሰናድታ ነበር። ወቅቱ ጥቁሮች በምድረ አሜሪካ መብታቸው ተረግጦ ለመብታቸው ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ የነበረበት የትግል ወቅት ነበር። በ200 ሜትር ሩጫ አሜሪካንን ወክለው የተሰለፉት ቶሚ ስሚዝና ጆን ካርሎስ በድል አጠናቀቁ። የሜዳሊያ ሽልማት ሲከናወን ግን ሁለቱ ጥቁር አሜሪካዊያን በወቅቱ በወገኖቻቸው ላይ ይደርስ የነበረውን በደልና መድሎ በመቃወም የጥቁር ኃይል ምልክት የሆነውን ጥቁር ጓንት በማድረግ እጃቸውን ከፍ አድርገው ተቃውሟቸውን በዓለም አደባባይ አሳዩ። ይሄ ክስተት በዓለም የኦሎምፒክ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በተጨቆኑና በተበደሉ የሰው ልጆች ታሪክ ሁሉ ሲታወስ ይኖራል። በወቅቱ የደረሰባቸውን ውግዘትና እንዲሸማቀቁ ለማደረግ የተሸረበ ሴራ ተቋቁመው በዓላማቸው በመፅናታቸው ተምሳሌት ሆነው ይታወሳሉ። ዛሬ በሳንሆዜ ዩኒቨርሲቲ የድል ሠላምታ ተብሎ ሐውልት ቆሞላቸዋል። ከ50 ዓመት በኋላ በሪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው ፈይሳ በአገሩ እየደረሰ ያለውን ኢሰብኣዊነት፣ ግድያና ጭቆና በመቃወም ከወገኖቹ ጋር ያለውን አጋርነት ለማሳየት የነጻነት ምልክት እየሆነ የመጣውን እጅን ወደላይ ማጣመርን ከፍ አድርጎ አሳየ። በዚህም ታላቁ የኦሎምፒክ ክስተት መሆን ብቻ ሳይሆን በአገሩ እየደረሰ ያለውን ግፍና መከራ ለዓለም ለማሳየት ቻለ። ፈይሳ አስቦበት ለወገኖቹ አጋርነቱን ለማሳየት ያደረገው እንደሆነና በዚህም ምክንያት የሚመጣበትን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል መቁረጡን ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል። ብዙዎችም በልባቸው የጀግና መታሰቢያ

ሐውልት አቁመውለታል። ቶም ስሚዝና ጆን ካርሎስ “ዛሬ ምን ዓይነት ታላቅ ሥራ እንደሠራን አሜሪካዊያን ሁሉ ያውቃሉ፤” ብለው ሲናገሩ በታላቅ ኩራትና ወኔ ነበር። “ድላችን የሕዝባችንን ድምፅ ለዓለም ሕዝብ ማሰማት መቻላችን ነው” ብለው ነበር። የእኛው ፈይሳ በሪዮ ኦሎምፒክ የአጋርነት ምልክታችንን ካሳየ በኋላ ሲናገር “አስቤበትና አቅጄ ያደረኩት ነው። ለሚገደሉ የአገሬ ልጆች ድምፄን በማሰማቴ ደስ ይለኛል። ሌሎች አትሌቶችም በየመድረኩ ድምፃቸውን ማሰማት አለባቸው” ነበር ያለው። ታሪክ እንደሚነግረን መቼም ይሁን የት የተገፉና ድምፃቸውን ማሰማት ያልቻሉ ሰዎች በታላላቅ አደባባዮች አንዱ እንደ ሁሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ የሚያሰማላቸው ጀግና ያገኛሉ። እውነትም ደግሞ የፈይሳ ግብዣ በከንቱ አለመቅረቱን፣ ገና በሳምንቱ፣ ነሐሴ 23፣ 2008 በኩዩቤክ (ካናዳ) ከተማ የማራቶን ውድድር ላይ በአንደኝነት ያጠናቀቀው ኤቢሳ እጅጉ እጆቹን አጣምሮ የድል ሪባኑን በመበጠስ የፈይሳን ታሪክ ደግሟል።

የፈይሳ የሩጫ ጉዞ ፈይሳ ሌሊሳ ለኦሎምፒክ አደባባይ ለመድረስ ብዙ ልፋትና ድካምን በብዙ የዓለም የአትሌቲክስ መድረኮችን አሳልፏል። የመጀመሪያ ዓለማቀፍ የአትሌቲክስ ተሞክሮው እንደ ጎርጎርሳውያን አቆጣጠር በ2008 የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ላይ በሜጄር ሯጭነት ነበር። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በቡድን ነሐስ ያመጡ ሲሆን የፈይሳ አስተዋፅዖ ትልቅ ነበር። በቀጣዩ ዓመት በተደረገው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ላይ ፈይሳ ‹ሲኔር› በመሆን ሲወዳደር የራሱን ደረጃ ያሻሻለ ሲሆን ኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳሊያ እንድታገኝ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በ2009 መስከረም የ‹ሮክ ኤን ሮል ቨርጂኒያ ቢች› ግማሽ ማራቶን /Rock ‘n’ Roll Virginia Beach Half Marathon/ በመሮጥ 1፡02፡15 ሰዐት በመግባት በተቀናቃኙ ኬኒያዊው ዊሊያም ቺብሮ /William Chebro/ ተቀድሞ ሁለተኛ ወጣ። በቀጣዩ ወር በተካሔደው ደብሊን ወደሚቀጥለው ገጽ

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ውይይት ነሐሴ 2008

9

አንድ ሰው ማራቶን /Dublin Marathon/ ላይ በመሮጥ ከሁለት ጊዜ ባለድሉ አሌክሲ ስኮሎቪ /Alekesey Sokolov/ ላይ በመንጠቅና በ2፡09፡12 ሰዐት በመግባት የወርቅ ሜዳሊያውን አጠለቀ። ፈይሳ ጉዞውን በማጠናከርና በማሻሻል በ2010 ዢማኒ ዓለማቀፍ ማራቶን /Xiamen International Marathon/ ላይ በመሮጥ ለዓመታት በሳሙኤል ሙቱሪ /Samuel Muturi/ ተይዞ የነበረውን ሪኮርድ በማሻሻልና በ2፡08፡47 በመግባት የመጀመሪያውን የሜጄር ማራቶን ድል ተቀዳጀ። ፈይሳ በሮተርዳም ማራቶን / Rotterdam Marathon/ ያስመዘገበው ድል ግን ከሁሉም አስደናቂ ነበር። በ2፡05፡23 በመግባት ኬኒያዊ ያልሆነ ከኃይሌ ገ/ሥላሴና ፀጋዩ ከበደ በመቀጠል በማራቶን ሦስተኛው ፈጣን ኢትዮጵያዊ ሯጭ ለመሆን በቃ። ብዙ ውድድሮችን ያደረገው ፈይሳ በ2012 በሆስተን ግማሽ ማራቶን /Houston Half Marathon/ የርቀቱን ሰዐት በማሻሻል በአንደኝነት አጠናቀቀ። በ‹አር.ኤ.ኬ.› ግማሽ ማራቶን /RAK Half Marathon/ ከሆስተን ግማሽ ማራቶን ሁለት ደቂቃ ዘግይቶ በመግባት አምስተኛ ወጥቷል። በኒዮርክ ግማሽ ማራቶን የአገሩን ልጁ ድሪባ መርጋን ተከትሎ ሦስተኛ ወጥቷል። እነዚህን ለአብነት የጠቀስኳቸውንና ሌሎች እጅግ የበዙ ድሎችና ውድድሮችን በማድረግ በታላቅ ትጋትና ጥረት ውስጥ ያለፈው ፈይሳ ያለው ብቃት አስተማማኝ በመሆኑ ነበር ለሪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ በማራቶን የተሰለፈው።

“X” ለምን ? የሃይማኖት ነጻነት ይከበር በሚል መርሕ “ድምፃችን ይሰማ” በማለት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የጀመሩት ሠላማዊ ትግል ለትግሉ ካበረከቷቸው ብዙ በጎ ነገሮች ውስጥ እጅን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ በማጣመር የ‹X› ምልክት ማሳየት አንዱና ዋነኛው ነው። ታስረናል፤ ነጻነት አጥተናል፤ ታፍነናል እንደ ማለት የሚቆጠረውን ይሄን ምልክት በኦሮሚያ ክልል እየተደረገ ያለው ሕዝባዊ ተቃውሞ እንደ ዋና የተቃውሞ ምልክትነት ከወሰደው ቆየት ብሏል። የዚህ ምልክት አድማስ ወደ ሌሎች ክልሎችም በመዛመት በአማራ ክልል የሚደረገው ሕዝባዊ ተቃውሞ የራሱ አድርጎ በመውሰድ አገራዊ ምልክት እንዲሆን አድማሱን አስፍቶታል። ፈይሳ ሌሊሳ ተወልዶ ባደገበት የኦሮሚያ ክልል እየተደረገ ላለው እንቅስቃሴ ባዳ አይደለም። በየቀኑ የሚሞቱ፣ የሚቆስሉና የሚታሰሩ ወገኖቹን ሲያይ ኅሊናው እረፍት ያጣ ነበር። ባለቤቱ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ስትናገር “የተቃውሞ ምልክቱን ማሳየቱ አልገረመኝም። ምክንያቱም ከፍተኛ ድብደባ የተፈፀመባቸው በርካታ ሰዎች ሲታሰሩና ብዛት ያላቸው ሰዎች ተገድለው አስከሬናቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ሲለቀቅ በሚመለከትበት ወቅት ክፉኛ ያዝንና ይበሳጭ ነበር። በመሆኑም ተቃውሞውን መግለጹ አልገረመኝም” ትላለች ኅሊናው በወገኖቹ ስቃይ እረፍት ያጣ እንደ

10 ውይይት ነሐሴ 2008

ነበር የምትገነዘበው የፈይሳ ባለቤት። የሰው ልጅ በደልና መገፋትን የሚታገስበት ለከት አለው። ቋቱ ሲሞላ ግን መፍሰሱ አይቀሬ ነው። በሕግ የተሰጠ መብት ተነጥቀው ሠላማዊ ወገኖቹ ሲሰቃዩ እያየ እንዳላየ የሚያልፈው ብዙ ነው። ክብሩን፣ ዝናውን፣ ሕይወቱን እና ቤተሰቡን ኅሊናው ለሚያዘው እውነትና ፍትሕ የሚያስገዛ አንድ አንድ ሰዎች ግን አሉ - ፈይሳ ሌሊሳ አንዱ ከእነዚህ አንዱ ነው። እንደዚህ ዓይነት ታላቅ ጀብዱ ለመፈፀም ግን የትልቅ ሞራል ልዕልና ባለቤት መሆንን ይጠይቃል። ፈይሳ ሌሊሳ የዚህ ትልቅ ሞራል ልዕልና ባለቤት በመሆኑ ነው “በሌሎች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ አንድ ቀን እኔ ቤት መምጣቱ አይቀርም” በማለት በዓለም አደባባይ ድምፁን ከፍ አድርጎ ስለ እውነትና ፍትሕ ለዓለም የተናገረው። ዛሬ ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሃይማኖታዊ ነጻነት ጥያቄ ጀምሮ መላ አገሪቱን ያጥለቀለቀው የ‹X› ምልክት በፈይሳ ሌሊሳ አማካኝነት ለፍትሕ፣ ለዕኩልነትና ለነጻነት ለሚደረግ ትግል በመላው ዓለም ምልክት ሆናለች። ፈይሳ በሪዮ ኦሎምፒክ በሩጫው ማገባደጃ ላይ የነጻነት ምልክቱን ካሳየ በኋላ በድጋሚ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅትም በመድገም ምልክቱን ያሳበትን ምክንያት ለዓለም የመገናኛ ብዙኃን አስረድቷል። እንደዚህ ዓይነት ተቃውሞ አድርጎ ወደ አገሩ ቢመለስ ምን ሊገጥመው እንደሚችል ጠንቅቆ የተረዳው ፈይሳ ወደ አገሩ እንደማይመለስ ያሳወቀው ወዲያውኑ ነበር። መንግሥት በበኩሉ ምንም እንኳ ያደረገው ድርጊት ትክክል ባይሆንም ወደ አገሩ ቢመለስ ምንም “የተለየ” ነገር እንደማይደርስበት ገልጾ ነበር። ሮይተርስ የዜና ወኪል የፈይሳን እናት “ይሄን የመንግሥት ቃል ያምኑት እንደሆነ” ሲጠይቃቸው “አይ፣ የሚታመን አይመስለኝም። እኔስ እዛው ቢሆንልኝ ይሻለኛል” ብለዋል። ይሄን ተከትሎ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን

በሕግ የተሰጠ መብት ተነጥቀው ሠላማዊ ወገኖቹ ሲሰቃዩ እያየ እንዳላየ የሚያልፈው ብዙ ነው። ክብሩን፣ ዝናውን፣ ሕይወቱን እና ቤተሰቡን ኅሊናው ለሚያዘው እውነትና ፍትሕ የሚያስገዛ አንድ አንድ ሰዎች ግን አሉ - ፈይሳ ሌሊሳ አንዱ ከእነዚህ አንዱ ነው

ፈይሳን ለመርዳት በተደራጀ መልኩ የተንቀሳቀሱ ሲሆን በአስደናቂ ሁኔታ በአምስት ቀን ውስጥ አንድ መቶ አምሳ አራት ሺሕ አምስት መቶ ሰባ ሶስት /154, 573.00/ የአሜሪካን ዶላር ለማሰባሰብ ችለዋል። ሁለት የሕግ አማካሪዎች ከአሜሪካን አገር በራሳቸው ወጭ ሪዮ፣ ብራዚል ድረስ በመሔድ የሕግ ድጋፍ እያደረጉለት ይገኛል። የዚህ ዓይነቱ ድጋፍና አጋርነት በጣም እንዳስደሰተውና ብርታት እደሆነው የሚናገረው ፈይሳ ይሄን ያህል ድጋፍ አገኛለሁ ብሎ አስቦ እንደማያውቅ ተናግሯል።

እንደ ማጠቃለያ ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ ኦሎምፒክ እጁን ከፍ አድርጎ የነጻነት ምልክትን በማሳየት የከፈለው ትልቅ መስዋዕትነት የሁሉም የተበደሉ ኢትዮጵያዊያን ምልክት ነው። በመላው ዓለም ያሉ መገናኛ ብዙኃን ስለ ሪዮ ኦሎምፒክ ሲያነሱ ከሚጠቅሱት ታላቅ ክስተት አንዱ የሆነው ይሄ ምልክት ፈይሳ በመገናኛ ብዙኃን ያስተላለፈውን መልዕክት ይዞ በመላው ዓለም ይጮሃል። ፈይሳ ሲናገር “ምልክቱን ያሳየሁት በአገሬ እየደረሰ ያለውን በደል በመቃወም አጋርነቴን ለማሳየት ነው” ብሏል በታላቅ ልበ ሙሉነትና ወኔ። ይሄ ድምፅ ደግሞ ፍትሕ፣ ዕኩልነትና ነጻነት የሚፈልገው የዚህ ትውልድ ድምፅ ነው። አሁንም ቢሆን ነገሮችን በሰከነ መንገድ ለመፍታት ካልተቻለና በቀደመው ግደለው፣ እሰረው መንገድ ከተሔደ የፈይሳን ፈለግ ተከትለው በመላው ዓለም በታላላቅ መድረኮች ድምፃቸውን የሚያሰሙ ብዙዎች ይወለዳሉ። ምልክቱን የተመለከተ ሁሉ በደልን፣ ጭቆናንና መታሰርን ያስታውሳል። ከፍትሕ፣ ከዕኩልነትና ከነጻነት ጋር ወዳጅነት ያላቸው ደግሞ አጋርነታቸውን ያሳያሉ። የአፍሪካ ስፖርት ፌዴሬሽን ፈይሳ ላሳየው አጋርነት ያለውን አክብሮት ገልጿል። ፌዴሬሽኑ ፈይሳ ለወገኖቹ ላሳየው አጋርነት ያለውን አድናቆትና ክብር አሳይቷል። ይሄ ድርጊት በሌሎች ነጻነትን በሚሹና በሚደግፉ ዘንድ ሁሉ ይቀጥላል። በሜክሲኮ ኦሎምፒክ ተቃውሟቸውን ያሰሙት ቶሚ ስሚዝና ጆን ካርሎስ ከተቃውሞው በኋላ ከተለያዩ አካላት ብዙ ትችትና ውርጅብኝ ደርሶባቸው ነበር። ከናዚ ሠላምታ ጋር አመሳስለው እንዲሸማቀቁ የሞከሩ ነበሩ። በዚህ ሁሉ ግን ከጎናቸው ቆሞ ሜዳሊያ ሊቀበል የነበረው ነጩ አውስትራሊያዊ ፒተር ኖርማን የብር ሜዳሊያውን ሲያጠልቅ የሁለቱ አትሌቶችን ዓላማ በመጋራት የሰብኣዊ መብት ምልክት የሆነውን ባጅ ደረቱ ላይ አኑሮ አጋርነቱን አሳይቷቸው ነበር። ይሄም ለነሱ ትልቅ ብርታትና ፅናት ሰጥቷቸው ነበር። ዛሬም ፈይሳ የፈፀመውን ጀብዱ በማጣጣል፣ ከአገር ክህደት ጋር በማቆራኝትና ከአይ.ኤስ.አይ. ኤስ. ምልክት ጋር በማያያዝ ለማሸማቀቅና ለማደብዘዝ የሚፍጨረጨሩ አይጠፉም። በፅናት፣ ባንድነትና ባጋርነት በመቆም አርማውን በመላው ዓለም ከፍ በማድረግና አጋርነትን በመግለጽ ሸፍጡን ማምከን ይቻላል።

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ሐተታ

ትዕምርታዊው ትዕይንት፤ የተቃውሞዎቹ ሒደትና ተስፋ ‹በኢትዮጵያ የተቀሰቀሱት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በ‹ዓልቦ-አመፅ ቀኖና› ሲመዘኑ ምን ይመስላሉ?› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ዘላለም ክብረት እጅን አጠላልፎ ወደላይ ከፍ በማድረግ የሚደረገውን የተቃውሞ ትዕምርታዊ ትዕይንት አጀማመር፣ እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ ተቃውሞ መገለጫ የሆኑ ተግባራትን በመዘርዘር እና በዓለማቀፍ ዕውቅና ባገኙ የሠላማዊ ተቃውሞ መንገዶች ሚዛን ላይ በማስቀመጥ በዚህ ጽሑፉ መዝኗቸዋል።

‹የኢትዮጵያ የቱሪዝም አባት ማነው?› ለሚለው ጥያቄ የብዙዎች መልስ ‹ሀብተሥላሴ ታፈሰ› የሚል ነው። አውሮፓና አሜሪካን ዞሮ በ1950ዎቹ አጋማሽ ወደ አገሩ የገባው ሀብተሥላሴ አገሩን ለጎብኝዎች ማስተዋወቅ እንዳለበት በመወሰን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነውን የቱሪዝም ምልክት ‹Thirteen Months of Sunshine› (በአማርኛ ውርስ ትርጉሙ - ‹የ13 ወር ፀጋ›) በሚል ቀምሮ ዓለም አገሪቱን በዚሁ ሥያሜ እንዲያውቃት አድርጓል። በዚህ ምልክት (brand) መጠሪያነት መጽሐፍት ተጽፈዋል፤ የሆሊውድ ፊልም ተሠርቷል፤ የሬጌ ዘፈን ሳይቀር ተቀንቅኗል። የያኔው ጎልማሳ ሀብተሥላሴ ስለ ምልክቱ ሲገልጽ “ጎብኝዎች ‘እንዴት ዐሥራ ሦስት ወራት? እንዴት ሁሌም ፀሐይ?’ ብለው በመገረም ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ” ለማድረግ የታሰበ እንደነበር ያስረዳል። ነገር ግን ይህ ለአምሳ ዓመታት አገሪቱ ራሷን ስታስተዋውቅበት የነበረ ምልክት ከዚህ ረጅም ጊዜ በኋላ ባሳለፍነው መጋቢት 2008 “ካደረግነው ሳይንሳዊ ጥናትና የቱሪስቶች ምክረ ሐሳብ በመነሳት ‹Thirteen Months of Sunshine› የሚለው የቱሪዝም ምልክት ‹Ethiopia: Land of Origins› በሚል አዲስ ገዥ ምልክት ተክተነዋል” በሚል መግለጫ አገሪቱን ለሚጎበኙ ቱሪስቶች አዲስ የቱሪዝም ምልክት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የተዋወቀ ሲሆን፣ ጉዳዩን ለሰሙ ብዙ ሰዎች አዲስ ምልክት ያስፈለገበት ምክንያት ግርታን ከመፍጠሩ በላይ “ኢትዮጵያ የምትታወቅበት ‹Thirteen Months of Sunshine› ከአዲሱ የቱሪዝም ምልክት የተሻለ

የሚስብ ነው” በማለት ትችቶች ቀርበውበታል። ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያ ያስተዋወቀችው አዲስ የቱሪዝም ምልክት ብዙ ሰዎች ያልሰሙት ጉዳይ መሆኑ ነው የአዲስነቱ ምፀት። ከዚህ ይልቅ ለብዙ ኢትዮጵያዊያን በዓመቱ ውስጥ ኢትዮጵያን ሊያስተዋውቅ የሚችለው ምልክት ሁለት የተጣመሩ እጆችን በ‘X’ ምልክት ተቃውሞ የሚያሳየው ምልክት እንደሆነ የሚያስማማ ነው ማለት ግነት አይሆንም። ከሕዳር ወር 2008 ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል የፈነዳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ላይ ከሕፃናት እስከ አዛውንቶች ድረስ ‹ማስተር ፕላኑን አንቀበልም› የሚለውን ተቃውሞ ለማስተጋባት ሁለት እጆቻቸውን አጣምረው የ‘X’ ምልክት በማሳየት በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በመለጠፍ ተቃውሟቸውን ሲያሳዩ የነበሩ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ማናቸውም ተቃውሞዎች በዚሁ ምልክት እየተገለጹ ይገኛሉ። የምልክቱ ወካይነት (Symbolization) ግን አሁን ካሉት ተቃውሞዎችም የሚሻገር ተምሳሌትነት እና ታሪክም ያለው ነው።

የአቡበክር እጆች ጥር 28፣ 2005 ማታ ከሁለት ሰዓት ዜና በኋላ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀረበው ‹ጅሐዳዊ ሃረካት› የተባለ ዘጋቢ ፊልም ለኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ብዙ አስደንጋጭ ነገሮችን ይዞ የመጣ ነበር። በሐምሌ 2004 በአቡበክር አሕመድ የሚመራውን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በከፊል

ከሌሎች ‹የኮሚቴው አባላት ጋር ግንኙነት አላችሁ› ከተባሉ ግለሰቦች ተይዘው በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) የታሰሩ ሲሆን፣ በዘጋቢ ፊልሙ ላይም መንግሥት አቡበክር አሕመድን ጨምሮ አምስት የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው አባላት በድብቅ ካሜራ የተቀረፁ ምስሎቻቸውን በማሳየት “ጥፋተኝነታቸውን ለሕዝብ ያሳይልኛል” ያለውን ጉዳይ በሚፈልገው መንገድ አቅርቧል። ነገር ግን በዚሁ ምሽት በድጋሚ ሊቀርብ የተሞከረው ይሄው ዘጋቢ ፊልም ባልታወቀ ምክንያት ለፊልሙ ግብዓት የሆነው የመፍትሔ አፋላላጊ ኮሚቴው ሊቀመንበር አቡበክር አሕመድ ለፖሊስ ሲሰጠው የነበረው ቃል በድብቅ ካሜራ ተቀርፆ የነበረው ሲሆን፣ ለዐሥራ ስምንት ደቂቃዎች የታየው የአቡበክር ቃል ማስፈራሪያና ማላገጥ እንዳለበት ሆኖ አቡበክር እጆቹን በእጅ ካቴና እንደታሰረ የሚያሳይ ነበር። ከዛን ጊዜ ጀምሮም በተለይም በኢትዮጵያዊያን ሙስሊም የመብት አራማጆች ዘንድ የታሰሩ ሁለት እጆች እንደ ተቃውሞው ማሳያ በስፋት መወሰድ ጀመሩ። ይህ የብዙዎች ትዝታ ቢሆንም ጋዜጠኛና አራማጅ አክመል አሕመድ ከጥር 2005 ቀደም ብሎ ይህ ሁለት እጆችን አጣምሮ በ‘X’ ምልክት የመቃወም ስልት ተጀምሮ እንደነበር ያስታውሳል። “…የሙስሊሙ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት መታሰር እውን ወደመኾን ሲሄድ ሦስት ነገሮች ተፈጠሩ” ይላል አክመል ምልክቱ እንዴት እንደተጀመረ ሲገልጽ “(ሀ). የመንግሥት ተቃውሞዎችን በኃይል የመበተን እርምጃ (ለ). አመራሩ ወደ ሕቡዕ መለወጥ [እና] (ሐ). እንቅስቃሴው ‹ቮካል› መሪውን ወደ መነጠቁ። እነዚህ ሦስት መንስኤዎች የተቃውሞዎቹ ይዘት ለውጥ እየፈጠሩ እንዲሔዱ ምክንያት ሆነዋል። ከዚህም በኋላ ነው የዝምታ ተቃውሞዎች በስፋት መተግበር የጀመሩት። ይሄ ስልት በአንድ በኩል የመንግሥትን የኃይል እርምጃ ለማስቆም ወይም ጉዳትን ለመቀነስ መፍትሔ ተደርጎ ነበር የተወሰደው። በሌላ በኩልም ሌላ የተቃውሞ ስልትን ለማስተዋወቅ አልሞ ነበር። የድምፅ ተቃውሞ ሲኖር ግርግር ስለሚፈጠር ለመንግሥት የኃይል ጥቃት አመቺ ነው፤ ዝምታ ግን የተረጋጋ ሁኔታ ለመፍጠር ጥሩ ወደሚቀጥለው ገጽ

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ውይይት ነሐሴ 2008

11

ሐተታ መፍትሔ ነበር። የዝምታ ተቃውሞ ሲደረግ አንድ አስፈላጊ የነበረው ጉዳይ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን መታሰር በምልክት ተቃውሞ መግለጽ ነበር” ይላል። አያይዞም “በቀዳሚነት ይሄን ለማድረግ የተወሰደው ስልት እጆችን በገመድ ወይም [በ]ሰንሰለት አስሮ ከፍ በማድረግ ማሳየት፣ አፍን ደግሞ ‹በፕላስተር› መለጠፍ ነበር። ይሄ በመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እስር ሙከራ ሰሞንና የመጀመሪያ ጥቂት የእስር ቀናት አካባቢ የተሞከረ ስልት ነበር፤ ኾኖም በመስጂድ በሮች ላይ ጥብቅ ፍተሻ በመጀመሩና ምንም ዓይነት የተቃውሞ ቁሳቁስ ወደ መስጂድ ማስገባት አስቸጋሪ ኾኖ በመገኘቱ፣ ‹አክቲቪስቶች› ምንም ዓይነት ቁሳቁስ የማይጠይቅ አካላዊ የተቃውሞ መንገድ መፍጠር ነበረባቸው” የሚለው አክመል፤ ላጋጠመው ችግር እንደ መፍትሔ ይሆን ዘንድ “[…] እጅን አጠላልፎና ከፍ አድርጎ ማሳየት አማራጭ የተቃውሞ መግለጫ መንገድ ተደርጎ መተግበር ጀመረ። ይሄ ስልት መጀመሪያ የተተገበረው[ም] ሐምሌ 20፣ 2004 በታላቁ አንዋር መስጂድ ከጁሙዓ ሶላት በኋላ ነበር” ይላል። እንግዲህ በሐምሌ 2004 የተጀመረው እጆችን አጣምሮ መታሰርን ለመግለጽ ይካሔድ የነበረው የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ተቃውሞ ከጥር 2005 ጀምሮ ከላይ ባየነው አግባብ ተጠናክሮ በመቀጠል በአለፉት ዐሥር ወራት ደግሞ የመንግሥትን ዕቅድ ከመቃወም ጀምሮ፣ አፈናንና አፋኝን እስከማውገዝ እንዲሁም ሐዘንን እስከ መግለጫነት ውሎ እናገኘዋለን። ነገር ግን ሁለት እጆችን አጣምሮ የ‘X’ ምልክት ማሳየት ተምሳሌትነቱ ከምልክትነቱ አልፎ ሥር የሰደደውን የአገሪቱን ችግሮች እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሲባልለት የኖረውን ‹ሕዝባዊ እምቢተኝነት› (Civil Disobedience) መጀመር አብሳሪ ሆኖ ተገኝቷልን? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ክስተት ሁኗል።

የአንዳርጋቸው 30 ወራት፤ የእስክንድር 106 ገጾች በመጀመሪያ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. አመራር ሆኑ። ይህን ግን ብዙም አልገፉበትም። ቀጥሎ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን ከሥልጣን ለማውረድ በሠላማዊ መንገድ የታገለው የቅንጅት ለአንድነትና ዴሞክራሲ አመራር ሆኑ። ይሄኛውም መንገድ ብዙ አላስኬዳቸውም። የትግል አጋሮቻቸው መታሰራቸውን ተከትሎ የውስጥ ለውስጥ የሕዝባዊ እምቢተኝነት የትግል ቡድን አቋቁመው ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን ለመታገል ‹ሕቡዕ› ገቡ። ‹ይሄም አያዋጣም› አሉና በመጨረሻ እርሳቸው “ከአመፅ ውጭ ወያኔ ለሠላማዊ ትግል በሩን እንዲከፍት ሊገፋው የሚችል ሌላ ምንም ዓይነት ሁኔታ በአሁኑ ወቅት [የካቲት 2000] የማይታይ በመሆኑ” ባሉት ምክንያት የትጥቅ ትግል ጀመሩ። ይሄኛውን የትግል ስልት በጀመሩ በስድስተኛው ዓመት ግን ዕድል ከእርሳቸው ጋር አልነበረችምና በሚታገሉት

12 ውይይት ነሐሴ 2008

አካል ታስረው ወኅኒ ወረዱ፤ አንዳርጋቸው ፅጌ። የአንዳርጋቸውን የሕይወት ታሪክ መጻፍ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም። ይልቁንም የመጡበት የትግል ስልት ስለአሁኗ ኢትዮጵያ ጠቋሚ በመሆኑ ነው ያነሳነው። በተለይም ከመስከረም 1998 እስከ የካቲት 2000 ድረስ ባሉት 30 ወራት አንዳርጋቸው ሕዝባዊ እምቢተኝትን እንደትግል ስልት ለመተግበር ወስነው የተንቀሳቀሱባቸው ጊዜያት አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሔዱ ካሉት ተቃውሞዎች አንፃር መመልከቱ የተቃውሞዎቹን ስልት የበለጠ እንድንረዳው ያደርገናል። የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር የነበረው አንዳርጋቸው ፅጌ ከምርጫ 97 አራት ወራት በኋላ በመስከረም 1998 “የተዘረፈውን የሕዝብ ድምፅ ለማስከበር” በሚል መነሻ ሕዝባዊ እምቢተኝነትን እንደ የትግል ስልት ለመተግበር ያስችላል ያለውን 19 ገጽ የግምገማና ‹የወዴት እንሒድ› ሰነድ ለቅንጅቱ ከፍተኛ አመራር አባላት ያቀረቡ ሲሆን፣ አቶ አንዳርጋቸው ባቀረቡት ሰነድ “የኢትዮጵያ ሕዝብ የተቀማውን ድምፅ ለማስመለስ የተለያዩ ዓይነት የሕዝባዊ እምቢተኝነት የተቃውሞ ስልቶች በመጠቀም ሕዝቡን ማደራጀትና ስርዓቱን በግድ የሕዝብ ድምፅን እንዲያከብር ማድረግ አለብን” በሚል መነሻ ቀጣዩን ጉዞ ለመጠቆም ሞክረው ነበር። አቶ አንዳርጋቸው በግላቸው ይሄን ዓላማቸውን እውን ለማድረግ የተለያዩ አደረጃጀቶች በማቋቋም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በተለይም እርሳቸው ከታሰሩ በኋላ የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል። በሌላ በኩል አንዳርጋቸው የሕዝባዊ እምቢተኝነት አስፈላጊነትን ባቀረቡበት መስከረም 1998 ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ‹ሠላማዊ ትግል› የምትል 106 ገጽ መታሰቢያነቷን “ሰኔ 1/1997 በግፍ ለተጨፈጨፉት ንፁኃን የዴሞክራሲ ሰማዕታት” ያደረገች ትንሽ መጽሐፍ የጻፈ ሲሆን፣ እስክንድር በመጽሐፉ “የሕዝባዊ እምቢተኝነት ፅንሰ ሐሳብ በሰፊው እያነጋገረ ባለበት በአሁኑ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ይሠራል ወይ? ብለው የሚጠራጠሩ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ። በእኔ በኩል፣ ለጊዜው፣ ይሠራል ወይም አይሠራም ለማለት አልፈልግም” በማለት እንዲሁ ደፋር ድምዳሜ ላይ መድረስን እንዳልመረጠ ይገልጻል። ነገር ግን እስክንድር መጽሐፏን የጻፈበት ዓላማ ሕዝባዊ እምቢተኝነት በሌሎች አገራት እንዴት እንደሠራና እንደተተገበረ በማሳየት ለኢትዮጵያም ይበጃል በሚል ሐሳብ ያቀረበው እንደሆነ ለማየት ይቻላል። አንዳርጋቸው የሕዝባዊ እምቢተኝነት ‹ስትራቴጅ› አቅርቦ ለመተግበር 30 ወራትን ደፋ ቀና ካለ በኋላ በየካቲት 2000 በጻፈው ሌላ 23 ገጽ ሰነድ “ሠላማዊ እና ሕጋዊ ትግል ሊጓዙ የሚችሉበት ድረስ ሒደው የተወሰኑ ድሎችን አስመዝግበው አብቅተዋል” በማለት ቀጣዩ መንገድ “የአመፅ መንገድ ብቻ ነው” በማለት ሕዝባዊ እምቢተኝነትም ቢሆን ትንሽ ‹ፈሪሀ-

ሕግ› ያለው መንግሥት ያስፈልገዋል በሚል ምክንያት መሣሪያ ማንሳትን መምረጡን ጠቅሶ የትግል ስልት መቀየሩን አሳውቋል። እስክንድር በበኩሉ “የዐረቡ ዓለም ዓይነት ሕዝባዊ እምቢተኝነት (‹የቀለም አብዮት› ይለዋል ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.) ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስነሳት አሲረሃል” ተብሎ የዐሥራ ስምንት ዓመታት እስር ተፈርዶበት እስሩን እየገፋ ይገኛል። አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ቢመለከቱ አንዳርጋቸውም ወደ ትጥቅ ትግል ከመግባት ይልቅ የሕዝባዊ እምቢተኝነት ሐሳቡን ይቀጥልበት ነበር፣ እስክንድርም “በእኔ በኩል [ሕዝባዊ እምቢተኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ]፣ ለጊዜው፣ ይሠራል ወይም አይሠራም ለማለት አልፈልግም” ብሎ ከመጻፍ ይልቅ ወደ መጀመሪያው አማራጭ ያደላ ነበር ብለን ብንደመደም ‹ደፋር› አያስብለንም። ነገር ግን እዚሁ ላይ አሁንም ጥያቄው እየተካሔዱ ያሉት ተቃውሞዎች ሕዝባዊ እምቢተኝነት በሚባሉበት አግባብ እስከ መቼ ይቀጥላሉ? ዘላቂነታቸውስ እስከመቼ ነው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አግባብ ነው።

ተቃውሞዎቹ ‘በዓልቦ-አመፁ ማኬቬሊ’ መነፅር የአራት ጊዜ የኖቤል ሽልማት እጩው እና የ88 ዓመቱ ጅን ሻርፕ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1968 ታላቁን ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ የጥናት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪውን ለመሥራት ሲቀላቀል ዛሬ ዓለም ላይ በክፉም ሆነ በበጎ የሚነሳበት ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብሎ አላሰበም ነበር። አሁን ጅን ሻርፕ በዓልቦ-አመፅ የትግል ስልት (Non-violent Struggle) ዋነኛው ተጠቃሽ ሊቅ ነው፡ ፡ በጃንዋሪ 2013 የወጣው የእንግሊዙ ‹ኒው ስቴስትማን› መጽሔት ጅን ሻርፕን ‹The Machiavelli of Non-Violence› በማለት ነበር የገለጸው። ሻርፕ የዶክትሬት ማሟያ ጽሑፉን የሠራው በዓልቦ-አመፅ የትግል ስልት ሲሆን ከዚህም ተነስቶ እስከ አሁን ድረስ ለሕዝባዊ እምቢተኝነት እንደ መሪ ጽሑፍነት የሚቆጠረውን ‘The Politics of Non-Violent Action’ በ1973 በሦስት ክፍል በ902 ገጽ አቅርቧል። ይህ የጅን ሻርፕ ሥራ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በተነሱ ቁጥር ትግበራቸውንና ስኬታቸውን ለመተንበይና ለመመዘን በብዙ ምሁራን ዘንድ ጥቅም ላይ እየዋለም ይገኛል። በዚህ ዳጎስ ያለ ብሉይ ሥራቸው ጅን ሻርፕ እጅግ ዝነኛ የሆኑትን 198 የዓልቦ-አመፅ የትግል ዘዴዎችን በሦስት መሠረታዊ ክፍሎች በመክፈል ያቀረቡ ሲሆን። የመጀመሪያው ተቃውሞን ማሰማት (Protest and Persuasion)፣ ሁለተኛው ትብብርን መንፈግ (Non-Cooperation) እንዲሁም ሦስተኛው መብትን ለመጠየቅ ጣልቃ መግባት (Intervention) እንደሆኑ ያትታሉ። ጅን ሻርፕ ተቃውሞን ማሰማት የሚሉት በዋናነት አንድን ድርጊት በመቃወም ከቃላት

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ሐተታ ባለፈ ተምሳሌትነት ባላቸው ነገሮች ተቃውሞን ማሰማትን ሲሆን ይሄም የዓልቦ-አመፅ ተቃውሞ ጅማሬ እንደሆነ ይገልጻሉ። በመግቢያችን ላይ ያየነው አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት እጆችን አጠላልፎ በ‘X’ በማሳየት እየተደረገ ያለው ተቃውሞ በዚህ ደረጃ የሚመደብ ሲሆን ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ውስጥ ያሉ የተቃውሞ ሰልፎች ምልክቱን የተለያዩ ነገሮችን ለመቃወም እየተጠቀሙበት እንደሆነ ለማየት ይቻላል። ይህም ምልክቱን የሚያሳዩት ኢትዮጵያዊን አንድን ነገር ብቻ እየተቃወሙ እንዳልሆነ የሚያሳይ ቢሆንም የሚቃወሙት ጉዳይ የተገለጸና አንድ ዓይነት ቢሆን ተቃውሞውንም ሆነ ተምሳሌትነቱን የበለጠ በማጉላት የሚፈልጉትን ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል የዓልቦ-አመፅ ‹ኤክስፐርቶች› የሚገልጹት ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ግን ሁለት እጆችን አጣምሮ በ‘X’ ምልክት ማሳየት ‹እጅግ ሠላማዊ ናቸው› ከሚባሉት ተምሳሌታዊ (symbolic) የተቃውሞ ስልቶች መካከል የሚመደብ መሆኑ፣ መንግሥት “እየተካሔዱ ያሉት ተቃውሞዎች ኃይል የቀላቀሉ ናቸው” የሚለውን ክስ ባዶ የሚያስቀሩ ናቸው። ተምሳሌትነታቸውም ይሄው ነው። ጅን ሻርፕ በሁለተኛ ጎራ የመደቧቸው የተቃውሞ ስልቶች ትብብርን መንፈግ (Non-Cooperation) የሚወክሉ ሲሆን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ በዋናነት የሚገለጹ ናቸው። ይህ የተቃውሞ ደረጃ የመጀመሪያው የተቃውሞ (Protest and Persuasion) ደረጃ ዕድገት እንደሆነ የሚገልጹት ጅን ሻርፕ፣ በዚህ የተቃውሞ ስልት ውስጥ ያሉ የተቃውሞ ዓይነቶች መንግሥት ላይ ከተምሳሌታዊ ተቃውሞ ባለፈ ጉዳት የሚያደርሱና በሚገባ ካልተተገበሩ ተቃዋሚውንም የሚጎዱ እንደሆነ ያስረዳሉ። በአሜሪካ ካሊፎርኒያ የሚገኘውን የኑክሊየር ኃይል ማመንጫ ለማዘጋት ረጅም ጊዜ የፈጀ ዓልቦ-አመፅ ትግል በተደረገበት ወቅት የተቃውሞው ተሳታፊዎች በጎርጎርሳዊያኑ አቆጣጠር 1978 ባዘጋጁት ‹Diablo Canyon Blockade Handbook› ትብብርን የመንፈግ ተቃውሞን አስፈላጊነት ሲገልጹ “መንግሥት የምንለው አካል ሁሌም የግለሰቦችና የተለያዩ ቡድኖች ጥገኛ ነው። ትብብርን በተነፈገ ቁጥር ያ መንግሥት ፈራሽ ነው” በማለት ነበር፡፡ በዚህ ረገድ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሔዱ ካሉት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች መካከል በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች እየተካሔዱ የሚገኙት ከቤት ያለመውጣት (Stay-at-home) ተቃውሞዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የተቃዱት ያለመገበያየት የኢኮኖሚ የተቃውሞ ስልት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። የመንግሥት አካላት “ሕዝቡ ቤት የማይወጣው ፀረ-ሠላም ኃይሎች እንዳይወጣ ስለሚያስፈራሩት ነው” ከማለት ውጭ “ዜጎች ለምን እንዲህ ያሉ የተቃውሞ ጥሪዎችን ሰምተው ቤት ይውላሉ?” የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ለመመለስ ብዙም እየጣሩ አይደለም። በሌላ በኩል በሦስተኝነት ጅን ሻርፕ

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ላጋጠመው ችግር እንደ መፍትሔ ይሆን ዘንድ “[…] እጅን አጠላልፎና ከፍ አድርጎ ማሳየት አማራጭ የተቃውሞ መግለጫ መንገድ ተደርጎ መተግበር ጀመረ። ይሄ ስልት መጀመሪያ የተተገበረው[ም] ሐምሌ 20፣ 2004 በታላቁ አንዋር መስጂድ ከጁሙዓ ሶላት በኋላ ነበር” (ፎቶ፤ የ‹ድምፃችን ይሰማ› ፌስቡክ ገጽ)

የመደባቸው ተቃውሞዎች ጣልቃ በመግባት መብትን ለማስከበር የሚሞከርባቸው (Intervention) የተቃውሞ ዓይነቶች ሲሆኑ፣ እኒህ የዓልቦ-አመፅ ዓይነቶች ቀጥተኛ ተግዳሮት ለመንግሥታት የሚጋርጡም ናቸው። በዚህ ጎራ የተካተቱት የተቃውሞ ዓይነቶች ለረጅም ጊዜ ለማስቀጠል ከባድ ሲሆኑ ለጫናም የተጋለጡ መሆናቸውን ሻርፕ ይገልጻሉ። በዚህም ምክንያት ይህ ዓይነቱ ተቃውሞ አንድን ነገር በተምሳሌታዊ የተቃውሞ ስልቶች መቃወም እና ትብብርን መንፈግን አልፈን በመጨረሻ ልንደርስባቸው የሚገቡ የተቃውሞ ዓይነቶች ሊሆኑ እንደሚገቡም አክለው ያሳስባሉ። አሁን በኢትዮጵያ እየተካሔዱ ካሉት ተቃውሞዎች መካከል በጣልቃ መግባት ጎራ ልንመድበው የምንችለውና በተለያዩ ቦታዎች የምናየው የመንግሥት ተቋማትን በሠላማዊ መንገድ መቆጣጠር (Non-Violent Invasion - NVI) እና ‹ይወክሉኛል› የሚሏቸውን ሰንደቅ ዓላማዎችን መስቀል ነው። እንግዲህ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሔዱ ያሉት ሰልፎች በአብዛኛው ዓመፅአልባ ተቃውሞዎች ሲሆኑ ነገር ግን የዘርፉ ምሁራን እንደሚጠቅሱት ከትንሹ መቃወም ጀምሮ እስከ ትልቁ ጣልቃ መግባት በሒደት የሔዱ ሳይሆኑ ሦስቱንም የዓልቦ-አመፅ የትግል ስልቶች በአንድ ጊዜ እየተሞከሩባቸው ያሉ ናቸው። ምንአልባትም ይህ ሁኔታ ተቃውሞዎችን የሚያስተባብር አንድ የሚታወቅ አካል ካለመኖሩ (ቢኖር መንግሥት በቀላሉ እሱን ለማጥፋት ጠዋት ማታ መድከሙ አይቀርም ነበር) እና ተቃውሞዎቹ ይዘዋቸው የተነሱት ጥያቄዎች ከቦታ ቦታ የሚለያዩ በመሆናቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ነገር ግን ተቃውሞዎቹ ሁሉንም የትግል ስልቶች በተመሳሳይ ጊዜ

እየሞከሩ የሚቀጥሉ ከሆነ ስኬታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል የብዙ አገራት ተሞክሮ የሚነግረን እውነት ነው፡፡ በሌላ በኩል ተቃውሞዎቹ እየቀረቡበት የሚገኘው ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ዓመፅ-አልቦ ተቃውሞን ለአለፉት ዐሥር ዓመታት “የውጭ ኃይሎች ሴራ (በተለይም የምዕራብ መንግሥታትና ድርጅቶች ሴራ) ነው” በማለት በማጣጣል የሚታወቅ ሲሆን፣ አሁን የተከሰቱትን አመፅ አልባ ተቃውሞዎች ግን ተቃውሞዎቹ በተነሳባቸው አካባቢዎችና በጥያቄዎቹ ማንነት ላይ ተመሥርቶ ወቀሳውን በዚሁ አግባብ በማቅረብ የጥንቱን ጠባብነትና ትምክህተኝነት እንደገና ለማነቃቃት እየሞከረ ይገኛል። ኢትዮጵያዊያንም ከትንንሽ መንደሮች ጀምሮ እስከ ዓለማቀፍ መድረኮች ድረስ ሁለት እጆቻቸውን አጣምረው የ‘X’ ምልክት በማሳየት ተቃውሟቸውን ቀጥለዋል። አሁን የበዙት ዓለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት ኢትዮጵያን የሚያውቋትም በዚህ የተቃውሞ ምልክት እየሆነም ነው። አዲሱ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ምልክትም የውጭ ዜጎቹን ወደኢትዮጵያ ይጠራ ዘንድ ኢትዮጵያዊያን በተቃውሞ እያቀረቧቸው ያሏቸው ጥያቄዎች መጀመሪያ ምላሽ ማግኝት ይኖርባቸዋል። ወሳኙ ጉዳይም ይሄ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በመንግሥት ግትር አቋሞች ምክንያት በቅርቡ የሚቆሙ የማይመስሉት ተቃውሞዎችም ለስኬት ይበቁ ዘንድ አካሔዳቸውንና ስልታቸውን ከትናንት ዛሬ እያሻሻሉ አገሪቱን ዜጎቿ እንደሚፈልጓት ያደርጓታል ብለን ተስፋ ማድረጋችን መልካም ነው። ‹የዓልቦ-አመፅ ትግል አባት› እየተባለ የሚታወቀው ማሕተማ ጋንዲ እንዳለውም ‘If one takes care of the means, the end will take care of itself’ (‹አካሔዱ ከታወቀበት፣ ውጤቱ ለራሱ ያውቅበታል› እንደማለት)።

ውይይት ነሐሴ 2008

13

ሐተታ

አራተኛው አብዮት? የዘንድሮው ሕዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል፣ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. በአገዛዝ ታሪኩ ቀደም ሲል ከተጋፈጠው የ1997ቱ ዐብይ ምዕራፍ፣ ቀጥሎ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ለመሆን የሚችል ነው። በሪሁን አዳነ የአፍሪካ አምባገነን ስርዓቶች አመጣጥና አካሔድ፣ እንዲሁም የ1966ቱን አብዮት መነሻ በማድረግ እና በዚሁ ጉዳይ ባለሙያዎችን በማናገር የዘንድሮውን የተቃውሞ ማዕበል ከአብዮቱ ጊዜ ጀምሮ ከተከሰቱ የለውጥ ምዕራፎች እንደአንዱ አድርጎ ይመለከተዋል። እ.ኤ.አ. ኅዳር 7 ቀን 1987 “የሕይወት ዘመን ፕሬዚዳንት” ሲባሉ የነበሩት ሀቢብ ቡርጊባ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤን አሊ የተገለበጡበት ቀን ነው። ቤን አሊ “ሕገ መንግሥታዊ መፈንቅለ መንግሥት” የሚል ሥያሜ ባተረፈው ደም ያላፋሰሰ ሒደት የርዕሰ መንግሥትነቱን ሥልጣን በጨበጡ ማግስት በርካታ የፖለቲካ እስረኞችን ከመፍታታቸውም በላይ፣ ቱኒዚያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ኃይሎች በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ከባቢ እንደሚፈጠርና አገራቸው አዲስ የፖለቲካ ጎዳና እንደምትጀምር አብስረው ነበር። ይህን የፕሬዚዳንት ቤን አሊን እርምጃ ተከትሎ ከእስር የተፈቱት ዝነኛው ምሁርና ፖለቲከኛ ረሽድ ጋኑሺም እሳቸውና የትግል ጓዶቻቸው ቤን አሊ የጀመሩትን የፖለቲካ ሒደት እንደሚደግፉ፣ ይልቁንም ቀደም ሲል እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ተከልክሎ የነበረው ‘አል ናህዳ’ የተሰኘው ፓርቲያቸው የተፈጠረውን የፖለቲካ ሁኔታ ተጠቅሞ እንደሚንቀሳቀስና የሒደቱ አካል እንደሚሆን ገለጸው ነበር። ወቅቱ ሁሉም በወደቁት ፕሬዚዳንት ላይ የሚረባረብበት፣ በአገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ስለመከፈቱ የሚገልጽበት፣ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ባልተለመደ ሁኔታ የሚከባበሩበት፣ የሚደናነቁበትና ሁሉም በተስፋ የተሞላበት ወቅት ነበር። ችግሩ፣ ይህ ሁሉ የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ ብሩኅ ተስፋ ብዙም አልቆየም። የ‹አል ናህዳ› የፖለቲካ እንቅስቃሴና ድርጅቱ በሕዝቡ ዘንድ ማግኘት የጀመረው ድጋፍ ያሰጋቸው ቤን አሊ፣ ብዙም ሳይቆዩ በንቅናቄው ላይ የተለያዩ የእመቃ እርምጃዎችን መውሰድ፣ የድርጅቱን አባሎች ማሰርና ማሳደድ ጀመሩ። ከዚህም በላይ እ.ኤ.አ. ሚያዚያ 1989 በተካሔደው ብሔራዊ ምርጫ የደርጅቱ አባላት በግላቸው ካልሆነ በስተቀር፣ ድርጅታቸውን ወክለው መወዳደር እንደማይችሉ፣ ድርጅቱም በምርጫው እንደማይሳተፍ ዕቀባ ተደረገባቸው። ሆኖም

14 ውይይት ነሐሴ 2008

የንቅናቄው አባላት ተስፋ ሳይቆርጡ በግለሰብ ደረጃ ተወዳደረው ራሱ የቤን አሊ መንግሥት ባመነው መሠረት 14 በመቶ ድምፅ ማግኘት ቻሉ። ውጤቱና የንቅናቄው አካሔድ ለቤን አሊ መንግሥት የሚዋጥ አልሆነም። ስለሆነም ይህ የ‹አል ናህዳ› ግስጋሴና የሕዝብ ደጋፍ ያሰጋው መንግሥት፣ ንቅናቄውንና የንቅናቄውን አባላት አንዴ እስላማዊ መንግሥት ሊመሠርቱ ይንቀሳቀሳሉ እያለ እየወነጀለ፣ ሌላ ጊዜ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየከሰሰ ብዙዎችን ወደእስር ቤት ወረወራቸው። በክስ ላይ ክስ እየተደራረበባቸው በፅናት ሲታገሉ የቆዩት ጋኑሺም የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው ከሰኔ 1989 በኋላ ወደ ለንደን ለመሰደድ ተገደዱ። በሌሉበት የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው ረሽድ ጋኑሺ፣ በስደት ሆነው የንቅናቄው መሪና አገር ውስጥ የሚደረገው ትግል ዋና አንቀሳቃሽ (የመንፈስ መሪ) ነበሩ። አገር ቤት ካለው ሕዝብና ከድርጅታቸው አባላት ጋር ያላቸው ግንኙነትም ጠንካራ ነበር። እ.ኤ.አ ከ1990 ጀምሮ በየጊዜው እየተቀሰቀሰና በመንግሥት እየተመታ የቀጠለው የቱኒዚያ ወጣቶች ተቃውሞ ለሁለት ዐሥርት ዓመታት ውጤት ማምጣት ባይችልም፣ እንደአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2010 መገባደጃ ላይ ዓለምን ባስደመመና ለሌሎች የዐረብ አብዮቶች በር ከፋች በሆነ ሠላማዊ ተቃውሞ የቤን አሊን አገዛዝ ለማስወገድ በቅቷል። የቤን አሊን አገዛዝ መወገድ ተከትሎ ወደ አገራቸው የተመለሱት ጋኑሺ፣ በቱኒዚያ የፖለቲካ ሽግግር ላይ ትልቅ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል። ስደተኛው ጋኑሺ ወደ አገራቸው ሲመለሱ፣ አሳዳጁ ቤን አሊ ከአገር ተባረሩ። አሳዳጁ ተሳዳጅ የሚሆንበት እና ተሳዳጁ መልሶ አሳዳጅ የሚሆንበት የጥፋት አዙሪት አስቀያሚው የአፈና አገዛዝ ትሩፋት! ቤን አሊ መፈንቅለ መንግሥት ባደረጉ

ማግስት አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ እንዳሉት ሁሉ፣ በአገራችንም የደርግ አገዛዝ ወድቆ የሽግግር መንግሥት በተመሠረተበት ወቅት ብዙ ብዙ ተብሎ ነበር። ስለ አዲሲቱ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ምሥረታ፣ ስለመድበለ ፓርቲና መድበለ ሐሳብ ስርዓት ግንባታ፣ ስለሕግ የበላይነት፣ ስለሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ወዘተ. ያልተባለ በጎ ነገር አልነበረም። በወቅቱ ልክ እንደቱኒዚያ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች የተፈቱ ሲሆን፣ በውጭ አገራት የሚኖሩ ብዙ ወገኖችም በታላቅ ተስፋ ወደአገራቸው ተመልሰው ከመንግሥት ጋር መሥራት ጀምረው ነበር። ሆኖም በእኛም አገር ተስፋው ለብዙ ጊዜ አልቆየም። ሁኔታዎች በሒደት እየተፈተሹ ሲመጡና አሸናፊው ኃይል እንደሚለው ልዩነትን እንደማያከብርና ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ያለው ቁርጠኝነት በጣም ደካማ መሆኑ ግልጽ ሲሆን፣ በሽግግር መንግሥቱ ተሳታፊ የነበሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ራሳቸውን ከሒደቱ ማግለል ጀመሩ። አንዳንዶችም ከሒደቱ በግፊት እንዲወጡ ተደረገ። በ1992 የመጀመሪያው ብሔራዊ ምርጫ ተቃዋሚዎች ያልተጠበቀ የምክር ቤት ወንበር ማግኘታቸው፣ በተለይ ደግሞ በምርጫ 97 አገዛዙን ያስደነገጠ የሕዝብ ድጋፍ ማግኘታቸው ያልተዋጠለት መንግሥት፣ የዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚፈጠርበትን ዕድል ዘጋው። በሒደቱ ተሳታፊ የነበሩ ፖለቲከኞችን ማሰርና ማሳደደ የተለመደ ሆነ። በዚህ ምክንያት በሠላማዊ ትግሉ ተሳታፊ የነበሩት ወገኖች፣ ሌላ መንገድ መቀየስ ጀመሩ። ከእነዚህ ውስጥ ልክ እንደጋኑሺ በሌሉበት የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው አሉ። አገዛዙ ሁሉንም ነገር ካፀዳ በኋላ፣ በልማታዊ መንግሥትና በአውራ ፓርቲ ስርዓት ሥም በፍፁም የበላይነት አሸነፍኩ እያለ የፖለቲካ ከባቢውን አፈነው። ይህ የመንግሥት አካሔድ ትመሠረታለች የተባለችውን አዲሲቷን ኢትዮጵያም ይገነባል የተባለውን የመድበለ ፓርቲ ስርዓትም ገደል የከተተ ሆኗል። በየአካባቢው እየተቀሰቀሰና የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ የቀጠለው ሕዝባዊ አመፅ አገዛዙ የገባውን ቃል ካለማክበሩ የመጣነው ነው። “እንቅስቃሴው ለሕዝቦች ዕኩልነት፣ ለሐቀኛ ፌደራሊዝምና ለሕግ የበላይነት የሚደረግ ትግል ነው” ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ደረጀ ጥላሁን (ሥማቸው የተቀየረ)። “ኢ-ዴሞክራሲያዊ አገዛዞች ራሳቸውን ማረም

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ሐተታ ስለሚሳናቸው እስከመጨረሻው ድረስ አይበገሬ መስለው መታየት ይፈልጋሉ። ይህ አካሔድ ደግሞ ይበልጥ እንዲጠሉ፣ ይበልጥ ከሕዝብ እንዲነጠሉና የለውጡ አካል እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል” የሚሉት ዶ/ር ደረጀ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ የተለመደ አውዳሚ አካሔድ ታርሞ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩት ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን በበጎ ሊመለከታቸውና ሐቀኛ ለሆነ ብሔራዊ መግባባት ሊዘጋጅ እንደሚገባው ይመክራሉ።

ምዕራፍ አራት? በየካቲት 66ቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት ላይ የጻፉ ምሁራን እንደሚነግሩን የዐፄ ኃይለሥላሴ አገዛዝ በሐሳብ የተበለጠውና ውድቀቱ የተፋጠነው የኢትዮጵያ ተማሪዎች “መሬት ላራሹ!” የሚለውን ዝነኛ መፈክር ካነገቡ በኋላ ነው። መሬት ላራሹና ሌሎች ጥያቄዎች፣ በተለይም የሕዝቦች ዕኩልነትና የሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄዎች ከተነሱ እነሆ ግማሽ ክፈለ ዘመን ተቆጠረ። ሆኖም ከእነዚህ ግንባር ቀደም ጥያቄዎች ውስጥ ብዙዎቹ አሁንም በቂ ምላሽ አላገኙም። ይልቁንም ሌሎች ተጨማሪ ጥያቄዎችን እየወለዱ በመቀጠላቸው ምክንያት አገራችን አሁንም ወደሌላ ግጭት ልትገባ ብቻ ሳይሆን ኅልውናዋም ፈተና ላይ ሊወድቅ የሚችልበት ዕድል እየታየ ነው። አብዮት ለምን፣ መቼና እንዴት ይከሰታል? የአብዮት መሠረታዊ ባሕርያትስ ምንድን ናቸው? ወዘተ. የሚሉት ጥያቄዎች በአብዮት ጉዳይ ላይ የሚጽፉ ምሁራንን በሰፊው ሲያከራክሩ የቆዩ ትላልቅ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው። በምሁራኑ መካከል የሚደረጉት ክርክሮች አሁንም መቋጫ አላገኙም፤ ወይም የሚያገኙ አይመስሉም። ክሬን ብሪተን (Crane Briton) የተባለው በዚህ ዘርፍ ጥልቅ ምርምር ያደረገ ምሁር፣ ‹The Anatomy Of Revolution› በሚለው መጽሐፉ፣ የሩሲያውን የጥቅምት አብዮት ጨምሮ ሌሎች ትላልቅ (ክላሲካል) አብዮቶች በሰባት ጉዳዮች ላይ ተመሳስሎሽ እንዳላቸው ገልጿል። እነኝህ አብዮቶች በተከሰቱባቸው አገራት (ሀ) ኅብረተሰቦች ከቀደመው ጊዜ ይልቅ መሻሻሎች (ለውጦች) በማሳየት ላይ ነበሩ፣ (ለ) በኅብረተሰቡ መካከል ግልጽ የሆነ የመደብ መቃቃር ነበር፣ (ሐ) ገዥ ኃይሎች ወይም መንግሥታት ደካማ (አቅመ ቢስ) ሆነው ነበር፣ (መ) ገዥ ‘ኤሊቶች’ በራስ መተማመን የጎደላቸው ሆነው ነበር፣ (ሠ) መንግሥታቱ የፋይናንስ ችግሮች ነበሩባቸው፣ (ረ) የተማረው ኃይል (ኤሊት) ስርዓቱን ከድቷል ወይም መደገፉን አቁሟል፣ (ሰ) የተከሰቱትን አመፆች ለመቀልበስ የተወሰዱት የኃይል እርምጃዎች ደካማ (አነስተኛ) ነበሩ። በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ የነበራቸውና በኢትዮጵያ አብዮት ላይ የጻፉት ዶ/ር ጳውሎስ ሚልኪያስ ከላይ ብሪተን የጠቀሳቸው ሁኔታዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተከሰቱና አገሪቱም በወቅቱ ለአብዮት

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ዝግጁ እንደነበረች ይነግሩናል። የየካቲት 66ቱ ኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት ከሌሎች ሶሻል አብዮቶች ጋር የሚጋራቸው ነጥቦች ግን እነኝህ ብቻ አይደሉም። ብዙዎች እንደሚስማሙበት የየካቲቱ አብዮት እንደ ታላቁ የፈረንሳይ አብዮትና እንደ ሩሲያው አብዮት በተስፋ ጀምሮ በሰቆቃና ፀፀት የተደመደመ አብዮትም ነበር። ከዚህም በላይ፣ ፅንፈኝነት የክላሲካል አብዮቶች አካል ነውና የየካቲት 66ቱ አብዮት በፅንፈኝነት የታጀበና ሽብር የነገሠበት፤ እንደሌሎች አብዮቶች ሁሉ አገሪቱን ወደ መልካም ነገር ያሸጋግራታል ሲባል ጨቋኝ ኃይል በመትከል የተጠናቀቀ አብዮትም ነበር። “የየካቲት 66ቱ አብዮት ፍፃሜ አሳዛኝ ከመሆን አልፎ ያልመለሳቸው ብዙ የሕዝብ ጥያቄዎች ቢኖሩም፣ አብዮቱን ተከትሎ የወጣው የመሬት አዋጁ የባለመሬት-ጭሰኛ ግንኙነትን በማጥፋቱ ፍትሐዊ ነበር። በሌላ በኩል፣ እንደሚታወቀው ከአብዮት በፊት ብዙኃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭሰኛ እንጂ ዜጋ አልነበረም። ከአብዮት በኋላ ነው እውነተኛ ዜጋ ለመሆን የበቃው። ስለሆነም በዚህም ረገድ ቢሆን ያ አብዮትና አብዮቱን የመራው አገዛዝ ሊመሰገኑ ይገባል” ይላሉ ዶ/ር ደረጀ። ሆኖም ምሁሩ እንደሚገልጹት “በአብዮቱ ወቅት የተነሱና ምላሽ ያልተሰጣቸው ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ስለነበሩ፣ በተለይ በወቅቱ የብሔረሰቦች ጥያቄ ምላሽ ያላገኘ ስለነበረ፣ ይህን ጥያቄ ያነገቡ ድርጅቶች ከየአቅጣጫው ተፈልፍለው ለወታደራዊው አገዛዝ መውደቅ ምክንያት ሆነዋል። ስለሆነም አብዮት ልክ እንደ መሬት መንቀጥቀጥ በአንድ ፍንዳታ የሚቆም ክስተት ባለመሆኑ የ1983 ለውጥ ከየካቲቱ አብዮት ቀጥሎ የተከሰተ የመጀመሪያው ንዝረት (aftershock) ወይም ሁለተኛው ምዕራፍ ነው ሊባል ይችላል። በሌላ በኩል ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ቃል ገብቶ ሲያበቃ፣ ያልመለሳቸው በርካታ መሠረታዊ ጥያቄዎች ስላሉ፣ በእነዚህ የሕዝብ ጥያቄዎች ላይ ተመሥርቶ የተደረገው ምርጫ 1997 እንደ ሦስተኛ፣ እንዲሁም በዚህ ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች መጠኑንና አድማሱን እያሰፋ የመጣው ሕዝባዊ ንቅናቄ እንደ አራተኛ ምዕራፎች ሊቆጠሩ የሚችሉ ናቸው።” ዶ/ር ደረጀ በበቂ ሁኔታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ከሚሏቸው መካከል የሚጠቀሰው የብሔረሰቦች ጥያቄ ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ሲያወዛግብ የቆየ አጀንዳ እንደሆነ ይታወቃል። ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ሥልጣን ከያዘና ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ በኋላ የብሔረሰቦች መብት ያለገደብ ስለመከበሩና በአገሪቱ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እየተጠናከረ ስለመምጣቱ በስፋት ቢነገርም፣ ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸውን እያስተዳደሩ አለመሆኑና በፌደራል መንግሥት ደረጃ የሕ.ወ.ሓ.ት. የበላይነት መንገሡ በራሱ በገዥው ፓርቲ ስብሰባዎች ውስጥ ሳይቀር የሚነሳ የዘወትር ጥያቄ ነው። በአሁኑ ወቅት በተለይ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የሚታየው ሕዝባዊ ተቃውሞ መነሻም ይኸው ጥያቄ ነው ማለት ይቻላል። የክልላችን ወሰን ይታወቅ፣

ክልላችን ያለሕ.ወ.ሓ.ት. ጣልቃ ገብነት ራሳችን እናስተዳደር፣ በፌደራል መንግሥት ደረጃ የሕዝብ ቁጥራችን መሠረት ያደረገ ውክልና ይኑረን ወዘተ. ነው ሲባል የሚሰማው። “የሕዝቦች ዕኩልነት ጥያቄ በአብዮቱ ወቅት ከተነሱት ዓበይት ጥያቄዎች አንዱ ነበር። ጥያቄው አብዛኛውን ሕዝብ የሚያስማማ አጀንዳ ሳይሆን አይቀርም። ልዩነት የሚመጣው፣ የብሔረሰቦች መብት በምን መልኩ ይከበር? በሚለው አጀንዳ ላይ ነው። አሁን የተያዘው መንገድ ምግቡን ሰጥቶ እጅን የማሰር ያህል ነው። ከመነሻው ተቀባይነት ለማግኘት በሚል መነሻ የተፈጠሩት ክልሎች ካርታው ከተሰጣቸው በኋላ የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ጉዳይ ላይ እንደፈለገ ለመወሰን የሚያደርገው ጥረት የራስ አስተዳደር ከሚለው አሠራር ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ነው። መፍትሔው ሐቁን መጋፈጥ ነው። ያ ካልሆነ ግን ስርዓቱ ሥልጣኑን ለማቆየት ሲል ራሱ በፈጠረው ስትራቴጂ ሊወገድ ይችላል። መቀበሪያውን የሚቆፍር ስርዓት እንበለው?” ሲሉ ይጠይቃሉ ዶ/ር ደረጀ።

ጥያቄውን ወይስ ጠያቂውን? የዕኩልነት ጥያቄው የፍትሐዊ ልማት ጥያቄንም ያጣመረ ነው። እንደሚታወቀው ጥቂቶች እጅግ በተጋነነ ሕይወት በመምራት ላይ ሲሆኑ፣ ብዙኃኑ ሕዝብ አሁንም እንደድሮው በከፍተኛ ድህነት ላይ የሚገኝ ነው። በየካቲት 66ቱ የአብዮት ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ሲነገርለት የነበረውና መቀስቀሻ የነበረው የጥቂቶች ምቾትና የሰፊው ሕዝብ አስከፊ ድህነት በዘመናችን በኢንዱስትሪ ደረጃ አድጎ፣ በሀብታሙና በድሃው መካከል ያለው ልዩነት ለመናገርም የሚከብድ ሆኗል። ሌላው በየካቲት 66ትም ሆነ በዘመነ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ምላሽ ያላገኘው ጥያቄ፣ የሕግ የበላይነት ጥያቄ ነው። በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበሩት ሕገ መንግሥታትና ሌሎች ሕጎች ንጉሠ ነገሥቱን የሚያገለግሉ የመግዣ መሣሪያዎች እንደነበሩ በስፋት ተጽፏል፤ ተዘግቧል። ይህን አስተሳሰብ በመቃወም የተጀመረው “ሕዝባዊ መንግሥት ይመሥረት!” የሚለው የአብዮት ዘመን መፈክር ሕዝቡ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት መሆን እንደሚገባውና ማንም ኃይል ከሕግ በላይ ሆኖ የሕዝቡን መብት እንዳይደፈጥጥ የሚያስገነዝብ ነበር። ሁሉም በሕግ ፊት ዕኩል የሚሆንበትን ስርዓት ለመፍጠር እንቅስቃሴ ከተጀመረ ከ40 ዓመታት በኋላም ግን የሕግ የበላይነት ጥያቄ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። በአጠቃላይ፣ “ያለሞግዚት ራሳችን በራሳችን እናስተዳድር”፣ “ፍትሐዊ ልማት ይኑር”፣ “የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ” ወዘተ. እየተባለ ነው። የሕዝቡን ሐሳብ አክብሮ፣ እነዚህን መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ጥያቄውንና ጠያቂውን ለማጥፋት መሞከሩ ግን ለነ መንግሥቱ ኃይለማርያምም፣ ለነቤን አሊም፣ ለሌሎች በርካታ አፋኝ አገዛዞችና መሪዎችም አልሠራም። አይሠራም።

ውይይት ነሐሴ 2008

15

ውይይት

ፌስቡክ እና የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ፌስቡክ የተባለው በዓለም ከፍተኛ ተጠቃሚዎች ያሉት ግንባር ቀደም ማኅበራዊ አውታር በኢትዮጵያ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይነገራል። ቴዎድሮስ አጥላው በአሁኑ ይዞታው ፌስቡክ ባይኖር የማናውቃቸውን ደራሲያን እያወጣልን ቢሆንም፣ ለድርሰት ሥራ ስጋት የሚሆን አዝማሚያም አለው በማለት የመፍትሔ ሐሳቦችን ይጠቁማል።

ፌስቡክ "ቨርቹዋል" የሆነ ማኅበራዊ ግንኙነትን መፍጠሪያ እንደመሆኑ መጠን፣ በዚህ መድረክ የሚገናኙ ሰዎች የተለያዩ መረጃዎችንና ዕውቀቶችን እንዲለዋወጡ፣ በአንድ ወይም በሌላ የጋራ ዓላማ እንዲተባበሩ፣ አንዳቸው የሌላቸውን ስሜቶች እንዲካፈሉ የራሳቸውንም አውጥተው እንዲናገሩ፣... ዕድል ይሰጣል። ከእነዚህ ሰዎች በፌስቡክ አማካይነት ከሚጋሯቸው ጉዳዮች አንዱ ደግሞ ሥነ ጽሑፍ ነው።

ሥነ ጽሑፍ በፌስቡክ ደራሲዎች የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸውን ያስነብቡበታል፤ የፌስቡክ መታወቂያ ያላቸው ደራሲዎች ግጥሞቻቸውን፣ አጫጭር ልቦለዶቻቸውን፣ ወጎቻቸውን ፌስቡክ ለየግላቸው በሰጣቸው ሰሌዳ (Wall) ላይ ይለጥፋሉ፤ እዚያው ወዲያውም ከጓደኞቻቸውና ከተከታዮቻቸው ስለለጠፉት ጽሑፍ የሚሰጧቸውን አስተያየቶች እና ስሜቶች፣ ማበረታቻዎች እና ማጣጣያዎች፣ ከንቱ ውዳሴዎች እና ስድቦች፣... ይቀበላሉ። ሰዎች ስለ ሠነ ጽሑፍ እና ስለ ሥነ ጽሑፍ ሥራዎች (መጻሕፍትን ጨምሮ) የተሰማቸውን እና ያሰቡበትን ያካፍሉበታል፤ የሥነ ጽሑፍ ወይም የመጻሕፍት ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ግለሰቦች የዳበረ ሒስ፣ የመጻሕፍት ዳሰሳ፣ ያነበቧቸው መጻሕፍት የቀሰቀሱባቸውን የአድናቆት፣ የብስጭት፣ የተስፋ፣ እና ሌሎችም ስሜቶች በፌስቡክ ሰሌዳዎቻቸው አማካይነት ለጓደኞቻቸው እና ለተከታዮቻቸው ያጋራሉ። ደራሲዎች፣ አሳታሚዎች፣ መጽሐፍ ሻጮች፣ የደራሲ ወዳጅ ዘመዶች ወዘተ. ደግሞ መጻሕፍትን ያስተዋውቁበታል።

16 ውይይት ነሐሴ 2008

እንግዲህ ይሄ ሥነ ጽሑፍ የሚባለው ቋንቋን መሠረቱ ያደረገ ኪነት፣ በዚህ የዓለምን ሕዝብ ያቀራረበ ማኅበራዊ ግንኙነት መፍጠሪያ መድረክ ውስጥ አንድ ሰብኣዊ ገደድ በመሆኑ የራሱን ሥፍራ ይዞ እናገኘዋለን። የየአገሩ ሥነ ጽሑፍ እና የሥነ ጽሑፍ እንቅስቃሴ በፌስቡክ መድረክ ያቅሙን ያህል ቦታ ወስዶ የመጎልበትም የመቀጨጭም ለውጡን እያሳየ ነው። ለምሳሌ እነ ሩትሊጅ፣ ፔንጊውንን እና ራንደም ሀውስን የመሳሰሉት ታላላቅ አሳታሚዎች፣ በተለይ ራሳቸው ያሳተሟቸውን መጻሕፍት እና ደራሲዎቻቸውን በፌስቡክ ገጾቻቸው ያስተዋውቃሉ፤ ስለመጻሕፍቱ የተጻፉላቸውን ሒሶች/ ዳሰሳዎች በመቶ እና በዐሥር ሺሕዎች ለሚቆጠሩ ተከታዮቻቸው ሥራችን ብለው ያስነብባሉ። ከማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን መምጣትም በፊት የመጻሕፍት ሒሶችን በማሐዘብ የሚታወቁት እነ ዘ ፓሪስ ሪቪው፣ ዘ ኒው ዮርክ ሪቪው ኦፍ ቡክስ፣ ዘ ጋርዲያን ካልቸርን የመሳሰሉት መገናኛ ብዙኃንም በአማካይ እስከ አራት መቶ ሺሕ ከሚደርሱ አንባቢዎቻቸው ጋር በመደበኛነት ይገናኛሉ። በምርምር ጆርናልነት ከፍ ያለ ሥፍራ የሚሰጣቸው እንደ JSTOR ያሉ ጆርናሎችም ወደ ፌስቡክ መጥተዋል። በዓለም ከፍተኛ ተነባቢነት ያላቸው እንደነፓውሎ ኮኤልሆ (28 ሚሊየን ተከታዮች አሉት) ያሉ ደራሲያን ሳይቀሩ ሥራዎቻቸውን በትጋት ያስተዋውቃሉ።

ሥነ ጽሑፋችን በፌስቡክ ምን ዓይነት ቦታ አለው? የአገራችንን

ሥነ

ጽሑፍ

ጉዳያቸው

ያደረጉ በርካታ የፌስቡክ ቡድኖች እና ገጾች አሉ። አንዳንዶቹ ስለ መጻሕፍት የመወያየት፣ ስለ መጻሕፍት መረጃ የመለዋወጥ፣ እንዲሁም መጻሕፍትን በሶፍት ኮፒ ጭኖ የመካፈል ዓላማ እና ተግባር ያላቸው ናቸው፤ ሌሎቹ ወይም ብዙዎቹ ደግሞ የቡድኑ አባላት በተለይ የግጥም ሙከራዎቻቸውን እንዲያስነብቡ የሚጋብዙ፣ ለጀማሪዎቹም ለበቁትም ዕኩል ቦታ የሚሰጡ መድረኮች ናቸው፤ ያሳተሟቸውን መጻሕፍት የሚያስተዋውቁ አልፎ አልፎም ስለመጻሕፍት አንዳንድ አባባሎችን እና መረጃዎችን የሚለጥፉ የመጻሕፍት አሳታሚዎች እና የመጻሕፍት መደብሮች አሉ፤ አንዳንዶቹ ገጾች እና ቡድኖች ደግሞ በግለሰብ ደራሲዎች ወይም በአድናቂዎቻቸው ተከፍተው፣ እነዚህ የገጾቹ ባለቤቶች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን እና አንዳንዴም ያሰኟቸውን ዓይነት ጽሑፎች፣ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች የሚለጥፉባቸው ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የፌስቡክ የግል ሰሌዳቸውን የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸውን ለማስነበብ፣ ስለመጻሕፍት ለማውራት፣... የሚጠቀሙ ደራሲዎችም በተቋም ደረጃ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበርን ጨምሮ ሌሎች የሥነ ጽሑፍ መርሐ ግብሮችን በሬዲዮ/ቲቪ ወይም በመድረክ በማካሔድ ላይ የሚገኙ ድርጅቶችም፣ በተለይ ከሥነ ጽሑፍ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የሚሰጡባቸው ገጾች እና ሰሌዳዎች አሏቸው።

ሥነ ጽሑፋችን ከፌስቡክ ምን አተረፈ? በእኔ አተያይ ፌስቡክ የሚባል ሉላዊ መድረክ ላይ እነዚህ የጠቀስኳቸው ገጾች እና ቡድኖች መኖር በየዘመኑ መፋዘዝ ለማያጣው ሥነ ጽሑፋችን አዲስ መነቃቃትን ፈጥሮለታል። እንዲህ የሚያስብሉኝን ነጥቦች በዝርዝር ላንሳ፡አንደኛ፦ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ፌስቡክ እና ሥነ ጽሑፍ ባለበት ሁሉ፣ ሐሳቦቻቸውን፣ የአጻጻፍ ክኂላቸውን፣ ስሜቶቻቸውን፣ ግንዛቤዎቻቸውን እና አመለካከቶቻቸውን በሥነ ጽሑፋዊ ቅርፆች አማካይነት ለአንባቢ ማቅረብ እየፈለጉ በአሳታሚ ተቀባይነት በማጣት፣ መድረክ በማጣት፣ መድረክም በመፍራት፣ ወይም ድርሰቶቻቸውን ወደ አንባቢ ማድረሻውን መላ በማጣት ተቸግረው ለቆዩ ያልታተሙ

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ውይይት ደራሲዎች ፌስቡክ ትልቅ እና ሆደሰፊ መድረክ ሆኖ ተገኝቷል። ቁጥሩን ካሰብን ከመቼውም ጊዜ በላይ ድርሰትን ለሚሞካክሩ ሰዎች ወደ አደባባይ መምጣት ፌስቡክ ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል። በዚህ ሒደት ውስጥ አብዛኞቻችን ቅድመ ፌስቡክ በደራሲነት የማናውቃቸው፣ ምናልባትም ፌስቡክ ባይኖር ሳናውቃቸው እና የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በረከቶችም ሳንቋደስ ልንቀር የምንችልባቸው የአጫጭር ልቦለድ ደራሲዎች፣ ገጣሚዎች እና ወግ ጣፊዎች ሥነ ጽሑፋችን ውስጥ ተከስተዋል። ለምሳሌ እነ ዮናስ አንገሶም፣ በላይ በቀለ፣ አሌክስ አብረሃም፣ ዮሐንስ ሞላ፣ ሕይወት እምሻው፣ ረድኤት ተረፈ፣ እነ አሳዬ ደርቤ እነሱለይ አደም፣ ሌሎችም ጸሐፊዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ። እነዚህ በፌስቡክ የተዋወቅኋቸው ደራሲዎች በፌስቡክ ብቻ ሳይገደቡ በታተሙ መጻሕፍት ድርሰቶቻችንን በእጅ በእጃችን ሰጥተውናል። በተለይ ‹መስቀል አደባባይ› የተባለው እና በፌስቡክ ታዳሚዎች የተመረጡ፣ በገጣሚነታቸውም በፌስቡክ የታወቁ አምስት ወጣቶች በኅብረት ያሳተሙት የግጥም መድበል የፌስቡክ ፍሬ ነው። ቅድመ ፌስቡክ በመጻሕፍት እና በተለያዩ መድረኮች የምናውቃቸው እንደ ሰሎሞን ሳህሌ፣ ዮሐንስ ሀብተ ማርያም፣ በዕውቀቱ ሥዩም፣ አዳም ረታ፣ በኃይሉ ገብረእግዚአብሔር፣ ቸርነት ወልደገብርኤል፣ አለማየሁ ገላጋይ፣… እና ሌሎችም ጸሐፊዎች ፌስቡክን ከአንባቢዎቻቸው ጋር በመገናኘት እየተነበቡ ለመዝለቅ የሚያስችል መድረክ አድርገው ሲጠቀሙበት እናያለን። ለዚህም በየሰሌዳዎቻቸው ላይ ወጎቻቸውን፣ የሥነ ጽሑፍ አተያዮቻቸውን፣ ግጥሞቻቸውን፣ ከትላልቅ ሥራዎቻቸው የተወሰዱ ቅንጭብ ሥራዎቻቸውን ያካፍሉናል። ሁለተኛ፦ ፌስቡክ በኢትዮጵያ ባልተለመደ መልኩ ደራሲያን ከአንባቢዎቻቸው ጋር በመገናኘት አንባቢዎቻቸው ስለድርሰቶቻቸው የሚሰጡትን አስተያየት (የእውነትም የውሸትም ቢሆን፣ የይሉኝታም የምቀኝነትም ቢሆን፣ የቡድናዊነትም ጭምር ቢሆን) ማግኘት የሚችሉበትን መድረክ ፈጥሮላቸዋል። በርግጥ ፌስቡክ በአብዛኛው እንደ ሥሙ የፊት እንጂ የልብ ሐሳብ ስለማይከፈልበት የሚሰጡት አስተያየቶች ሙሉ በሙሉ ጠቃሚዎች ናቸው ብሎ ለመናገር ይከብዳል። ሆኖም በጥበብ የአንባቢዎቻቸውን ስሜቶች እና ሐሳቦች መበዝበዝ የሚችሉት ደራሲያን ራሳቸውን ለማሻሻል እንደሚጠቀሙበት መገመት ይቻላል። ወይም ደግሞ የአንባቢያቸውን ፍላጎት፣ አቋም፣ ምንትነት ለማጥናትም ይጠቀሙበታል ብሎ ተስፋ ማድረግም ይቻላል። ያም ሆነ ይህ ግን ፌስቡክ የመገናኛውን መድረክ ፈጥሯል። ከዚሁ ጋር አያይዤ ማንሳት የምፈልገው የአዳም ረታን ምሳሌነት ነው። ብዙዎቹ ነባርም አዲስም ደራሲዎቻችን የፌስቡክ ሰሌዳ ላይ የምናየው ደራሲዎቹ ግጥሞቻቸውን ወይም ተረኮቻቸውን ወይም ወጎቻቸውን ያቀርባሉ፤

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ከዚያ ምን ያህል ተከታይ "እንደወደደላቸው" ይቆጥራሉ፤ የተሰጧቸውን አስተያየቶችም ውጠው ዝም ይላሉ፣ ወይም ጠቅልለው “ወዳጆቼ ሆይ ስለሰጣችሁኝ አስተያየቶች አመሰግናለሁ” ይሉና ከምልልስ ይገላገላሉ። በርግጥ ከ“ያምራል” እና ከ“ወረድክብኝ” የዘለለ እና ለውይይት የሚጋብዝ አስተያየት ብዙ ጊዜ ላያጋጥማቸው ይችላል። ስለታተሙ መጽሐፎቻቸው የሚሰጡባቸውን አስተያየቶችም እንዳዩዋቸው ማወቅ እንኳን አይቻልም። የአዳም ረታ ገጽ ግን በዚህ ረገድ ዳይናሚክ ነው ማለት ይቻላል፤ ለሚጽፍበት ስልት ወይም ቅርፅ ከሚጽፈው ሐሳብ/ታሪክ ዕኩል ቦታ የሚሰጠው ደራሲ አዳም ለሚነሱለት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ዝግጁ ሆኖ ከመጠበቁም በላይ፣ ከአንባቢዎቹ አስተያየቶች በመነሳት ብዙዎቹ አንባቢዎቹ ሊወዛገቡበት ይችላሉ ብሎ በሚጠረጥረው ጉዳይ ላይ ከብዙዎቹ የሥነ ጽሑፍ አጥኚዎች እና አስጠኚዎች በላይ የላቁ የረቀቁ ማብራሪያዎችን የመጻፍ ትጋቱን ገጹ ላይ እናያለን። ፌስቡክ ይህን መድረክ ለሁሉም የፌስቡክ ገጽ ላላቸው ደራሲዎቻችን እና አንባቢዎቻችን በመክፈቱ፣ አጠቃቀማችን በተሻሻለ መጠን ሥነ ጽሑፋችንም እንደሚያድግ መገመት ይቻላል። ሦስተኛ፦ አንዳንድ አጥኚዎች እንደሚሉት ፌስቡክ አንባቢያንን እያበራከተ መጥቷል። እኛ ሦስት እና አምስት ሺሕ ቅጂ አሳትመው ሸጠው የጨረሱ ሰዎችን እንደ ቤስት ሴለርስ ለምንቆጥረው ሰዎች፣ በፌስቡክ መቶ ምናምን ሺሕ ተከታይ ያለው ቡድን፣ ሰማኒያ ሺሕ ገደማ ተከታዮች ያሉት የአንድ ደራሲ ገጽ ማየት ምናልባትም አንባቢ የለንም የሚለውን ድምዳሜያችንን ከቀድሞው የበለጠ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ጉዳይ ነው። የፌስቡክ ገጽ ተከታይ ሁሉ አንባቢ ነው ወይም አይደለም የሚል ሙግት ማንሳት ይቻላል። አራተኛ፦ የአንባቢያን እና የደራሲያን መተዋወቅ፣ እንዲሁም የፌስቡክ አንባቢያንም መበራከት ለተወዳጅ ደራሲዎች መጻሕፍት ሰፊ

“ማኅበራዊ ድረ ገጾች የተሻሉ ደራሲዎች እያደረጉን አይደሉም፤ ይልቁንም አያሌ ሰዎች ደራሲዎች የሆኑ እንዲመስላቸው እያደረጉ ነው።”

ገበያ በመፍጠርም ረገድ አስተዋፅዖ አበርክቷል። በዚህ ረገድ የአሌክስ አብረሃምን መጻሕፍት ሽያጭ በራሱ ምስክርነት ማየት ይቻላል፤ በተለይ ሁለት የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጻሕፍቱ በተደጋጋሚ ታትመው በደንብ እየተሸጡ መሆናቸውን ነግሮኛል። የበዕውቀቱ ሥዩም "ከአሜን ባሻገር" በአጭር ጊዜ በብዙ ሺሕ ቅጂዎች መሸጥ በዕውቀቱ በሌሎች ሥራዎቹ ከገነባው ሥሙ በተጨማሪ፣ የፌስቡክ ውጤት መሆኑን አይቻለሁ። የዮሐንስ ሞላን "የብርሐን ሰበዞች" የማስታወቂያ ዘመቻ እና ውጤቱንም መመርመር ይቻላል። አምስተኛ፦ በየዕለቱ ከማደርገው የፌስቡክ ንባብ የተነሳ፣ ፌስቡክ ላይ የሚወጡ ግጥሞችን እና ዝርው የፈጠራ ጽሑፎችን ሥራዬ ብሎ የሚመረምር አጥኚ የሚደርስባቸው አዳዲስ የሥነ ጽሑፍ ዘውጎች፣ የአደራረስ ዘይቤዎች እንደሚኖሩ እገምታለሁ። ወይም ቢያንስ ፌስቡካዊ ሥነ ጽሑፍ የምንለው ይኖረናል። የፌስቡክ ተወዳጅ ጽሑፎች በመጽሐፍ ላይ ከሚታተሙ ጽሑፎች የሚለዩዋቸው ባሕርያት ላይ ተመሥርቶ አዲሶቹን ዘውጎች መልክ ማስያዝ ይቻላል። ለምሳሌ የፌስቡክ ጽሑፎች አጫጭሮች፣ አንባቢውን የማጫወት ዓይነት አተራረክ ያላቸው፣ ብዙ ጊዜ በምስል የሚደገፉ፣ የጸሐፊውን እና የአንባቢዎቹን ሐሳቦች አንድ መድረክ ላይ የሚያገናኙ ናቸው።

ስጋቶች

ፌስቡክ እነዚህ እና እነዚህን የመሳሰሉ ጥቅሞች ለሥነ ጽሑፍ ይሰጣል እንበል እንጂ ሥነ ጽሑፋችን ላይ ስጋት የሚሆንበት ጠባይ የለውም ማለት አይደለም። ፌስቡክ እና መሰሎቹ በተለይ የሥነ ጽሑፍን ዕድገት በተመለከተ ሲወራ ተወድሰው፣ በርቱ ተብለው ብቻ የሚተዉ ጉዳዮች አይደሉም። ፌስቡክ እና ሌሎቹ ጽሑፍ ተኮር ማኅበራዊ ድረ ገጾች ለዓለም ሥነ ጽሑፍ የመነበቢያ ዐውድ ሆነው ብቻ ሳይሆን የመቃብር ጉድጓዱ ሆነው ጭምር መምጣታቸውን የተለያዩ አጥኚዎች ይናገራሉ። ሩቅ ሳንሔድ አንድ የጎረቤታችን የኬንያ ጸሐፊ የእነዚህን ድረገጾች አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲህ ሲል ያስቀምጠዋል፦ “ማኅበራዊ ድረ ገጾች የተሻሉ ደራሲዎች እያደረጉን አይደሉም፤ ይልቁንም አያሌ ሰዎች ደራሲዎች የሆኑ እንዲመስላቸው እያደረጉ ነው።” የዳበረ የሒስ ባሕል ያላቸው ሥነ ጽሑፎች ሳይቀር ሒስ በ"ላይክ" እና በ"ኮመንት" መተካቱ፣ ይህም የዓለም ሥነ ጽሑፍ ማስተር ፒሶች በቁርጥራጭ ፖስቶች፣ ባላለቁ ሥራዎች እና የአርትኦትን ደረጃ ዘለው ለሕዝብ በደረሱ ድፍድፍ ድርሰቶች ይተካሉ የሚል ስጋት አድሮባቸዋል። ለዚህም ነው በተለያዩ የንባብ አጋጣሚዎች ‹DEATH› እና ‹APPOCALYPS› የሚሉ ቃላትን ከሥነ ጽሑፍ ዕጣፈንታ ጋር ተቆራኝተው የምናገኛቸው። በዚህ ረገድ ማኅበራዊ ድረገጾች ላይ ወደሚቀጥለው ገጽ

ውይይት ነሐሴ 2008

17

ውይይት የሚቀርቡት ትችቶች ብዙ ናቸው፤ በእኔ ንባብ ካገኘኋቸው አንዱ የሆነው ፊል ጀምስ የተባለ ጸሐፊ ማኅበራዊ ድረገጾች በሥነ ጥበብ እና በኪነጥበብ ላይ ውድቀትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ተፅዕኖዎች ስላሏቸው፣ እነዚህ የኪነጥበብ ዘርፎች ከማኅበራዊ ድረገጾች መነጠል አለባቸው ወደማለት ደርሷል። እሱ ከዘረዘራቸው ስምንት ምክንያቶቹ አንድ ሦስቱን በምሳሌነት ማየት እንችላለን፦ የመጀመሪያው፣ ነጥቡ ማኅበራዊ ድረገጾች ሁሉም ነገር በፍሬው ሳይሆን በቆዳው የሚለካባቸው መድረኮች ናቸው ይላል። በእነዚህ መድረኮች ፍሬው ከገለባው ያነሰ ሥፍራ ስለሚያገኝ የኪነ ጥበብም ሆነ የሥነ ጥበብ ሥራዎች እንዳያድጉ የሚያንቅ ፈተና መጥቶባቸዋል። ሁለተኛው፣ ማኅበራዊ ድረገጾች በቀረቡባቸው የኪነጥበብ ወይም የሥነ ጥበብ ሥራዎች ላይ ተጠቃሚዎቹ እንዲያስቡባቸው፣ እንዲያሰላስሉባቸው፣ ከዚያም እንዲመዝኗቸው ከማበረታታት ይልቅ ቴክኖሎጂን እንዲጠቀሙ ይገፋፋሉ። ተጠቃሚውን ለፍርድ ያጣድፋሉ፣ "ቶሎ ውደዱ - ቶሎ ጥሉ" ይላሉ። ሦስተኛው፣ የማኅበራዊ ድረገጾቹ ተከታዮች ከገጾቹ በሚደርስባቸው የእጃዙር ግፊቶች እና በሌሎችም ግላዊ ሰበቦቻቸው ምክንያት ያሸበረቁ ርዕሶችን፣ ስሜቶቻቸውን የሚነኩ ደካማ ሽራዎችን በማድነቅ፣ ኪናዊ ደረጃቸው ከፍ ያሉ ሥራዎችን ያገልላሉ። የእኛ ሥነ ጽሑፍ እስካሁን ባለው አካሔዱ የመሞት ወይም የመጥፋት ዋዜማ ላይ ነው ከሚያስብለው ስጋት ይልቅ፣ የታፈነው ተሰጥዖ ወጥቶ አወንታዊ ለውጥ ሊያመጣ ነው የሚለው ተስፋ ጎልቶ ቢታይበትም፣ የተወሰኑ ስጋቶችን ማንሳቱ ግን አይከፋም።

‹ላይክ›፣ ‹ኮመንት›፣ ‹ሼር› አሰጣጥና አቀባበል፣ ሳናነብ ‹ላይክ› እናደርጋለን፣ ሳያምረን ያምራል እንላለን፣ ሳናምንበት ‹ሼር› እናደርጋለን፤ አንዳንዶቻችን ደግሞ ወደነውም ላይካችንን እንነፍገዋለን፣ እንከን እንፈልግበታለን፣ እያደነቅነው እናጣጥለዋለን፤ ወይም በዝምታ ልንቀጣው እንሞክራለን። የአንባቢያን ምላሽ ደራሲያን ራሳቸውን ከሚያሻሽሉበት የፌስቡክ ዕድል አንዱ ሆኖ ሳለ፣ ብዙ ጊዜ ሐቀኛ አስተያየት የመስጠት ልማድ የለንም፤ ድሮ በጭብጨባ ዛሬ ደግሞ በ‹ላይክ› ደራሲዎቻችንን በማታለል ልባቸውን እናሳብጠዋለን። ይሄ ሆነ ብለን የምናደርገው ጥፋት እንዳለ ሆኖ፣ በንባብ ልምድ ማነስ ምኑንም ምኑንም በማዳነቅ የሥነ ጽሑፋችን ሰማይ ዕድሜ ልካቸውን ከጅምርነት በማይዘሉ አርቲ ቡርቲዎች እንዲሞላ እናደርጋለን። ከዚህ ባሻገር ከጥሩ ደራሲ ግጥም ይበልጥ፣ የአንዲት ቆንጆ ኮረዳ የተሟዘዘ ኣረፍተ ነገር ወይም መንግሥትን የሚቃወም መፈክር፣ ወይም ሃይማኖታዊ ጥቅሶች የመቶዎችን ልብ

18 ውይይት ነሐሴ 2008

ለ‹ላይክ› እና ለ‹ኮመንት› ያነሳሳሉ።

የ‹ላይክ› እጦት ምላሾች በአመዛዛኝ አእምሮ ስናስበው የ‹ላይክ› ብዛት የአንድን ደራሲ የመጻፍ ብቃት ሙሉ በሙሉ አይመሰክርም ብንልም፤ ይሄ ‹ላይክ› የበዛለትን ደካማ ደራሲ ወደ ግብዝነት የመምራቱን ያህል፤ ያነሰበትን ወይም ተመልካች ያጣውን ምርጥ ጀማሪ ደራሲ ቅስሙን እንደሚሰብረው ስለፌስቡክ ሥነ ልቡናዊ ተፅዕኖዎች ከተሠሩ ጥናቶች መገመት ይቻላል። በዚህ ረገድ ከደረሰባቸው ሥነ ልቡናዊ ጉዳት የተነሳ በሥራዎቻቸው ልቀት በፌስቡክ ተከታዮቻቸው የሚመሰገኑ ደራሲዎችን ሳይቀሩ በግልጽ በመሳደብ ተመልካች ለመሳብ የሚሞክሩ የተዘነጉ ወጣት ደራሲያን እንዳሉ አይቻለሁ። የግል ሰሌዳዎቻቸውንም ሆነ፣ ተመልካች ቢኖረን ብለው የከፈቷቸውን ገጾቻቸውን በጥላቻ ሞልተውት ደህና ነገር ለመጻፍ ሲቸገሩ አይቻለሁ።

ለ‹ላይክ› መጣደፍ ፌስቡክ አብዛኛው ነገሩ የጥድፊያ ነው። አብዛኛው ነገሩ ከጥድፊያ ዕይታ ጋር የተያያዘ ነው። ግጥም እንኳን በፎቶ ተደግፎ ካልቀረበ አብዛኛውን ጊዜ ተነባቢነት ያለው አይመስልም። ደራሲዎቹ፣ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደራሲዎች ይህንን የአንባቢውን ችኮላ ስለሚገነዘቡ ያላለቁ ድርሰቶቻቸውን ለጥፈው ላይክ በመቁጠር ሊደክሙ ይችላሉ። አንዳንድ፣ ጊዜ እና የረጋ መንፈስ ቢያገኙ በስለው ማስተር ፒስ የሚሆኑ የድርሰት ሐሳቦች/ታሪኮች ለቸኳዩ አንባቢ፣ ለ‹ላይክ› ቀላቢያችን፣ ለመጽሐፍ ሽያጭ ተስፋችን ሲባል ተቆራርጠው ይለጠፉና ይባክናሉ። ከዚህ ደግሞ ሥነ ጽሑፋችን ቁጭትን ብቻ ነው የምታተርፈው።

የረዥም ልቦለድ እጦት አሁን ፌስቡክ የአጫጭር ሥራዎች መድረክ ብቻ ነው የሚመስለው። ኖቭሉን በየምዕራፉ እየለጠፈ የሚያስነብበን ትጉህ ካልተነሳ፣ ከፌስቡክ አንጻር ስናየው ወትሮም ያልሆነልን የኖቭል ነገር ያበቃለት እንዳይሆንብን እሰጋለሁ። ይሄ ጉዳይ ሥነ ጽሑፋቸው በዳበረላቸው ዓለማትም በስጋትነት እየተነሳ ያለ ነው፤ የተራቀቁ ኖቭሎች እና ቅኔዎች አንባቢ እያጡ ነው፤ ከዚህም በኋላ እነሱን መጻፍ ሊቀር ይችላል የሚሉ የሥነ ጽሑፍ ተቆርቋሪዎች አሉ። በተቃራኒው በተለያዩ የሆሊዉድ ፊልሞች ላይ በተዋናይነት እንደሚታወቀው እንደ ቢ.ጄ. ኖቫክ ዓይነቶቹ ደግሞ ይሄ የማኅበራዊ ድረገጾች ጠባይ የተሻሉ ደራሲዎች አደረገን እንጂ ምን አጎደለብን ብለው በአደባባይ ይሟገታሉ። ለምሳሌ ኖቫክ የተቆራረጡ፣ ከመቶ በማይበልጡ ቃላት የተዋቀሩ ተረኮች የሚበዙበትን የአጫጭር ተረኮች መድብል አሳትሟል።

ጉዳዩን ወደኛ መልሰን ስናየው ስጋት የሚሆንብን፣ ቀድሞውንም የኖቭል ድርሰት ድርቀት ያለብን በመሆናችን እና አንባቢ የለንም ብለን አንባቢነትን ለማበረታታት የምንተጋ በመሆናችን ነው። እንግዲህ ፌስቡክ አስተዋፅዖዎችና አሉታዊ ተፅዕኖዎች አሉት ካልን፣ ሥነ ጽሑፋችን የዚህ ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነቱ እንዲጎላ ምን ቢደረግ ይሻላል?

ታዲያ ምን ይደረግ? ሥራዬ ብሎ ፌስቡክን በቁምነገር እንደሚከታተል ተጠቃሚ ሥነ ጽሑፋችን እና ደራሲዎቻችን፣ እንዲሁም እኛ አንባቢዎቻቸው ከዚህ መድረክ የተሻለ ጥቅም እንድናገኝ ያስችሉናል ብዬ የምጠቁማቸው ጥቂት ሐሳቦች አሉኝ፦ ደራሲያን አንባቢያቸውን አክብረው ፌስቡክ ላይ ከመለጠፋቸው በፊት የተቻላውን ያህል ያርሙ፤ ምክንያቱም በፌስቡክ መለጠፍ ማሳተም ማለት ነው። ከማሳተም የምትገኘው ጥሬ ገንዘብ ካለመኖሯ በቀር፣ ስንለጥፍ ያለድካም ከአንባቢ ጋር እንገናኛለን። ስለዚህ የምንለጥፈውን ድርሰታችንን በተቻለን መጠን መልሶ የማንበብ ልማዱ ቢኖረን ደግ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ደራሲያን ፌስቡክ ላይ እስካለን ድረስ በሥራዎቻችን ላይ ውይይት እንጋብዝ፣ እንወያይ። አንባቢያን የተሰማንን በሐቅ እንመስክር፣ የእኛ ምስክርነት ነገ ለምናነበው ሥራ ጥራት አስተዋፅዖ አለውና፤ ላይካችንን አናባክን። ረጅም ጽሑፍ ለማንበብ ትዕግስት ይኑረን። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ማኅበራዊ ድረገጾችን ብቸኛ የንባብ መድረካችን አድርገን ከመጻሕፍት አንቆራረጥ። ብዙ ተከታይ ያለውን ጸሐፊ ግር ብሎ ከመከተል ይልቅ ኪነትም፣ ቁምነገርም ያላቸውን ጸሐፊዎች መርጦ ማንበብም መልካም ነው። ደራሲያን ይሄንን ታላቅ የሻጭ እና የገዢ መገናኛ ገበያ ሥራዎቻችንን ለማስነበብ፣ በደራሲነታችንም የሚገባንን ዋጋ ለማግኘት እንጠቀምበት። ዓይናፋርነት ገበያ ላይ አይጠቅምም። በርግጥ ከአንባቢያችሁ ምን ዓይነት ክብር/ንቀት፣ ውዳሴ/ነቀፋ እንደሚደርስባችሁ መገመት ስለማይቻል፣ ቆዳችሁን አወፍራችሁ ቅረቡ። ፌስቡክ የተመረጡ ሰዎች ብቻ መድረክ ባለመሆኑ እና ከሁሉም ዓይነት አንባቢ ጋር ስለሚያገናኛችሁ፣ ከምትጽፉለት እና ከምትጽፉበት ማኅበረሰብ ጋር በደንብ እንድትተዋወቁ ይረዳችኋል። ሐያሲያን ደግሞ ለሥነ ጽሑፉ አቅጣጫ መሪዎች በመሆን የተሻሉ ድርሰቶች እንዲበረቱ ግሩም ግሩም ድርሰቶቻችንን በማድነቅ፣ ደካሞቹም የሚሻሻሉበትን መንገድ በመጠቆም የበኩላችሁን ብታደርጉ ፌስቡክ የፈጠረውን ዕድል በአግባቡ የመጠቀም ምሳሌዎች ትሆኑናላችሁ። ቴዎድሮስ አጥላው የቋንቋ እና የሥነ ጽሑፍ ተመራማሪ ናቸው፡፡ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ይገኛሉ።

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ውይይት

የብሔረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ ከየት ወዴት? በተለምዶ ‹ያ ትውልድ› እየተባለ የሚጠራው የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ንቁ ተሳታፊ የነበረው ትውልድ ካነሳቸው ግልጽ ያልሆኑ እና እስካሁንም በትክክል ያልተመለሱ ከሚመስሉ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ‹የብሔረሰብ ጥያቄ› ነው፡፡ ቴዎድሮስ ኃይለማርያም (ዶ/ር) ይህንን ጉዳይ እንዴት ልንሻገረው እንደምንችል ሐሳቡን በዚህ መጣጥፍ አስፍሯል።

ሀ. ብሔርተኝነት ምንድነው ? ይህ ከሁሉ አስቸጋሪው ጥያቄ ቢሆንም በአገራችን ከሁሉ የቀለለ ተደርጎ የተወሰደ ነው። የአጨቃጫቂነቱ አንደኛው ምክንያት ከራሱ ተፈጥሮ ይመነጫል። ብሔርተኝነት ወደኋላ እያስታወሰና ወደፊት እያለመ፣ እግሮቹን በጥንታዊነትና በዘመናዊነት አድማሶች አንፈራጦ የቆመ እሳቤ ነው። በአንድ ወገን ብሔርተኝነት የጥንታዊውን ማኅበረሰብ አፈጣጠር፣ እምነት፣ ማንነትና የሕይወት ውጣ ውረድ የሚያቅፍ ታሪካዊ ፍልስፍና ነው። በሌላ በኩል በዘመናዊነት ሒደት ውስጥ የሚነሱ ትግሎችና ሙግቶች አካል በመሆኑ የተለያዩ ባለድርሻ ማኅበረሰቦችን፣ ተቋማትን ፣ መደባትንና ማኅበራትን ፍላጎቶችና ርዕዮቶች ያንፀባርቃል። ባለንበት ዓለም ብሔርተኝነት በተለይ ከዴሞክራሲና ፍትሕ ጥያቄዎች ጋር የተቆራኘ አስተሳሰብ ነው። ለብሔርተኝነት ሁሉን አስማሚና የተሟላ ትርጉም መስጠት አይቻልም። እስካሁንም ለብሔሮችና ብሔርተኝነት መስፈርትነት የዋሉት እንደ ቋንቋ፣ ዘውግ፣ ባሕል፣ ወዘተ. ያሉት በራሳቸው ያልነጠሩና ሙልጭልጭ ጉዳዮች ናቸው። በአጠቃላይ ግን ብሔርተኝነት መልከ ብዙ ነው። የፖለቲካ አስተምህሮ ነው፤ አገራዊ ስሜት ነው፤ ማኅበራዊ ንቅናቄ ነው፤ ዘውጋዊ ተቆርቋሪነት ነው። ለ. ብሔር ምንድነው፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብስ? የብሔረሰቦች ጥያቄ እስስታዊ ባሕሪ ምሥጢር በከፊል ብሔር በሚለው መሥራች ቃል ላይ ጥገኛ በመሆኑና ይህ ደግሞ በተራው ከትውልድ ሥፍራ ጀምሮ መንግሥት፣ ሕዝብ፣ አገር የሚሉትን ሰፋፊ ሐሳቦች ከማጠቃለሉ ጋር ይያያዛል። ብሔራዊ መዝሙር ማለት አገራዊ ነው። ብሔረ አማራ ሲል ዘውጋዊ ነው። ዘብሔረ ቡልጋ ማለቱ ደግሞ አውራጃዊ ይሆናል። የኢትዮጵያ አብዮተኞች የብሔር ትርጉም አንድ ወጥና የስታሊንን ትንታኔ ቃል በቃል የሚደግም ነበር። አሁንም ጥቂት የይስሙላ ለውጥ ካልሆነ ለብሔር በአገራችን ታሪክና ተጨባጭ እውነታ ላይ የተመሠረተ ትንታኔ የለም። ስለዚህ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የሚሉት የተምታቱ አስተሳሳቦች ተኮርጀው በሕገ

መንግሥታችን ውስጥ ስፍራ ይዘው ቀርተዋል። አንዳንድ ጊዜ የማኅበረሰብን ዕድገት ደረጃን የሚያመለክቱ ቢመስሉም በዘፈቀደ ጥቅም ላይ ይውላሉ። ብሔርነት የክብር ጉዳይም ስለሆነ እነዚህን ማዕረጎች ከራስ ፍላጎት ውጭ ማን እንደሚመድብ መወሰን አይቻልም።

ሐ. ኢትዮጵያዊነት ምንድነው? ይህም እስከዛሬ አጥጋቢ መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ ነው። በኢትዮጵያ ተማሪዎች የትግል ታሪክ ውስጥ፣ ኢትዮጵያዊነት በጠላትነት ካልሆነ የረባ ቦታ አልነበረውም። በጥር 1961 የኦጋዴኑ ኢትዮጵያዊ አብዱል መጅድ ሑሴን ‹ኢትዮጵያዊነት ማለት ከግላዊ፣ ነገዳዊና አውራጃዊ ስሜቶች የላቀ ፅንሰ ሐሳብ ነው። በአጠቃላይ ከሕዝብ አንፃር የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ያለው እምነት ነው› ብሎ ከገለጸው በኋላ የረባ ሙከራ አልተደረገበትም። አብዮቱ ሊፈነዳ ጥቂት ዓመታት እስኪቀሩት ድረስ፣ የአብዛኛው ተማሪ ጠንካራው የጋራ ማንነት ከፍ ሲል ኢትዮጵያዊነት ዝቅ ሲል ደግሞ ተማሪነት ነበር። በተጓዳኝም ራስን በኢትዮጵያዊነት ውስጥ መፈለግ፣ ‹ማነው ኢትዮጵያዊ?› የሚል ጥያቄ በከተሜው ምሁር ዘንድ እያቆጠቆጠ ነበር። ይህ ጥያቄ በውል ሳይጠራ ማርክሳዊ ሌኒናዊ አብዮተኝነት ‹የብሔር ጥያቄን› ይዞ መጣ። አዲሱ የተማሪ ርዕዮተ ዓለም በብሔር ግንዛቤ ዙሪያ ያለው ውዥንብር ጉዳዩን በተፃራሪ ትርጓሜዎች የታገተ አደረገው።

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መንታ ገጽታዎች አብዮተኝነትና ጎሰኝነት

አብዮተኝነትና ጎሰኝነት ከአንድ ዓለማቀፍ ርዕዮተዓለምና ከአንድ ማኅበራዊ መደብ የመነጩ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኅልውና ተፃራሪ ገጽታዎች ናቸው። በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ቀድሞ የተፈጠረው አገራዊ አድማስ ያለው፣ አዲሱ ትውልድ በአባቶቹ ላይ የሚያምፅበት ትውልዳዊ ብሔርተኝነት ነው። ይህ ለዘብተኛው አገራዊ ብሔርተኝነት ሚዛናዊ፣

አካታች፣ ተደራዳሪ ነው። በጋራ ገድልና ዕጣፈንታ የሚወሰን ነው። ተማሪው ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን ከተቀበለና፣ ‹ለቀለም ብቻ ሳይሆን ለተጋድሎ› እንሰለፍ ማለት ከጀመረበት ከ1960 መባቻ በኋላ ፅንፋዊው አብዮታዊ ብሔርተኝነት ዋጠው። ዘውጌ ብሔርተኝነት ወይም ጎሰኝነት፣ ከአገራዊ ብሔርተኝነት በተቃርኖ የሚቆምና፣ በተወሰነ ደመነፍሳዊ ማኅበረሰብ ጥቅም ላይ የሚያተኩር ርዕዮት ነው። በተማሪው መንፈስ ውስጥ ውስጡን የከረመና በ1950ዎቹ በተለይ በትግይ ተወላጅ ተማሪዎች መካከል እየጎላ የመጣ ተካራሪ የዘረኝነት፣ ጎሰኝነት ወይም አውራጃዊነት መንፈስ ነበር። በወቅቱ የአብዛኞች ስጋት የተማሪዎችን ኅብረት ይጎዳል የሚል ነበር እንጂ፣ እንዲህ ጎሰኝነት እዚህ ደረጃ ይደርሳል ብሎ የጠረጠረ አልነበረም። ከቀዳሚው አብዮታዊ ብሔርተኝነት ተገንጥሎ ገሃድ የወጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት በፈነዳበት በ1966 ገደማ ነው። ሁለቱም አብዮታዊና ዘውጌ ብሔርተኝነቶች ነባሩን ብሔራዊ ታሪክ ለመከለስና የሕዳጣንና ጭቁን አመለካከቶችን ለማሳየት ቢሞክሩም፣ በክፉ ጎናቸው ደግሞ ታሪክን ለርዕዮትዓለም ደንገጡር በማድረግና ግጭትና ውጥረት በማራገብ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። በተለይ ጎሰኝነት በተፈጥሮው ቀናተኛ፣ ስግብግብና ጠበኛ ነው። ለራስ ማኅበረሰብ ጥብቅና በመቆም አይመለስም። ማኅበረሰቡን አለቅጥ ማቆላመጥንና ሌሎችን በተፃራሪነት መመልከት ድረስ ይሔዳል። የኢትዮጵያ ተማሪዎች አንዱ መለያ ባሕሪ ልኂቃዊነት ነው። ለልኂቅ አንድ የተቆረጠ ትርጉም ባይኖረውም፣ በአገራችን የብሔረሰቦች ጥያቄ ታሪክ ውስጥ ከ1960ዎቹ በኋላ ተፅዕኖው እያደገ የመጣውን ዘመናዊ ምሁር ይመለከታል። በተለይ በጋራ ርዕዮተ ዓለምም ሆነ በጋራ ዘውግ ተቧድኖ በኢትዮጵያ ዕጣፈንታ ላይ አድራጊ ፈጣሪ ነኝ የሚል አጉል እምነቱና ከዚህ የመነጨው የፖለቲካ አስተሳሰብና ባሕል ልኂቃዊነት ይባላል። ይብዛም ይነስ በድኅረ አብዮት የተፈራረቁ አገዛዞች ብሔርተኝነትን ለሥልጣን ማደላደያነትና ማስጠበቂያነት አውለውታል። የፖለቲካ ባሕላችን በከማናንሼና ማናለብኝነት ተመርዟል። የብሔረሰቦች ጥያቄ የመርሕ ጉዳይ ብቻ አልነበረም። ሥር መሠረት የሚያናውጥ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ተግባራዊ አንድምታ ያለው ነበር። በተለይ የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚለው ፅንሰ ሐሳብ አደገኛ ውጤቶች ነበሩት። ይህም ምንጩ ለዘብተኝነት የሆነና፣ በተለይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በምሥራቅ አውሮፓ ዘውጌ ብሔርተኝነት ሲዛመት ዕውቅና ያገኘ አስተሳሰብ ነው። ቀላሉ መገለጫው ራስን በራስ ማስተዳደር ሲሆን፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ ላይ በዊልሰን 14 ነጥቦች ወደሚቀጥለው ገጽ

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ውይይት ነሐሴ 2008

19

ውይይት ውስጥ ተካትቶ ዓለማቀፍ ሰውነት አግኝቷል። ሆኖም ለነገሩ ትልቅ ትኩረት የሰጡት ሌኒኒስቶች ናቸው። እኛም አገር ሐሳቡ በኤርትራ የመገንጠል ንቅናቄ በግርድፉ ሲወሰድ ውሎ አድሮ ያን ያህል ችግር ያስከተለ አልመሰለም። ከእናት አገር ለመገንጠል ውጊያ ማለት እኮ በራሱ ተቃርኗዊ ነው። በተለይ ደግሞ አባቶቹ ወደ እናት አገራችን እንመለስ ብለው ያፈሰሱት ደማቸው ሳይደርቅ። ተገንጥሎስ ምን? ከዘውዳዊ አሀዳዊ መንግሥት የተለየ ምንም አማራጭ ማሰብ ይከብድ ነበር። በቅኝ ያልተገዛ ሕዝብስ እንዴት ልገንጠል ይላል። ለሰሚው ግራ በመሆኑ ከሹክሹክታ በላይ አይወራም ነበር። ጥላሁን ግዛው በ1960 ለተማሪ ፕሬዚዳንትነት ውድድሩን በመኮንን ቢሻው የተሸነፈው በ‹ተገንጣይነት› አሉባልታ ነው ይላሉ ደጋፊዎቹ። ጥላሁን ግዛውን የብሔረሰብ ጥያቄ የመጀመሪያው ሰማዕት ልንለው እንችላለን። በሱ ግድያ ጦስ የተፋፋመው የተማሪ አመፅ፣ በቀጣዩ ዓመት ዋለልኝ መኮንን ሀዱሽ ምንነቱ በቅጡ ያልታወቀ፣ አይነኬዎቹን አገርን፣ ባሕልን፣ ማንነትን የመካድ አስፈሪ ርዕስ ይዞ የሚቀርብበት ድፍረት ሰጠው። በተማሪነቱ ጥቃት ያቆሰለውን ወጣት በውል ላልታወቀ ተልዕኮ የሚያሰልፍ መፅናኛ አቀረበለት። እስከዚህ ድረስ የተማሪው ገድል ከማኅበረሰቡ ያልተለየ ዝገምተኛና ብዙም ሊወራለት የሚችል ነገር አልነበረውም። ‹ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እስር ቤት ናት› የሚለው በቀጥታ የተቀዳ ሌኒናዊ ሽሙጥ ነው። የኢትዮጵያ ተማሪዎች ታሪካቸውንና ማንነታቸውን ለመመርመር ፋታ አላገኙም። አዲሱን ራዕይ ከነባራዊው ሁኔታ አላገናዘቡም። በጭፍንና በጥራዝ ነጠቅነት አመለኩት። ዓለምን ያስደነቀ የአክራሪነት ባሕሪ አሳዩ። ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጋር የተያያዘ ማናቸውንም ነገር ካዱ። ወይም ማንነታቸውን ጠሉ። ክፉ ነገር ሁሉ የተፈጠረው በኢትዮጵያ፣ ደግ ነገር ሁሉ ሌላ አገር ሆነ። ጭቆና የትውልድ አገሩ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ‹የብሔረሰቦች እስር ቤት›፣ እንዲያውም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ብቸኛዋ ቅኝ ገዥ አገር ናት ብለው ራሳቸውን አዋረዱ። ከዚህ በኋላ እረፍትና መደማመጥ የሌለበት፣ በጥድፊያ፣ በግርግር፣ በሴራና በጀብደኝነት የተሞላ፣ የአፍለኛን ልብ የሚያቀልጥ ዘመን ነበር። ያ ትውልድ ማተቡን በጥሶ በጅምላ ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን አምላኪ የሆነበት ምትሐታዊ ዘመን ነው። በዚህ ውስጥ የተማሪው አገራዊ አብዮተኝነት ተዳቀለና፣ የብሔረሰቦች ጥያቄ የአብዮተኝነት መለኪያ ቱንቢ ሆነ። ተማሪው ‹በመርሕ ደረጃ› ከፀሐይ በታች ማናቸውንም ነገር ለመቀበል ተሰለፈ። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ምን ዓይነት ጭቆና ነው ሲል ጠየቀ። የመደብና የብሔር ጥምር ጭቆና የሚለው፣ ማርክሲዝምንና ስታሊኒዝምን ለማስታረቅ የሚሞክር ድምዳሜ ነው። ትንታኔውን ከመደብ በተጨማሪ በባሕልና ብሔር ጭቆና ላይ ያደረጋል። ይህ ክፍል ጥምር ጭቆና ያለበት ስለሆነ ተቃውሞው ይበረታል ተብሎ ነበር። ነገር ግን የብሔር ፍልሚያ የተነሳውና፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን እስከመካድ የተደረሰው በተገላቢጦሹ በሰሜናዊው

20 ውይይት ነሐሴ 2008

የአገሪቱ ክፍል ነው። ‹ማነው ኢትዮጵያዊ?› የሚለው አጭር ጥያቄ ሲሆን፣ ይበልጥ ታሪካዊ ይዘት ካለው ‹መቼ ተፈጠረች ኢትዮጵያ?› ከሚለው ጥያቄ ጋር ይቆራኛል። የታላቂቱ ኢትዮጵያ አስተምህሮ፣ ሁሉን አካታችና ወግአጥባቂ፣ ዜግነታዊ - ግዛታዊና በአገሪቱ ረዥምና ቀጣይ መንግሥትነት የሚያምን ነው። ጎሰኞች በቀጥታ ለማጥቃት በደፍጣጭነት ወይም ጠቅላይነት በመወንጀል፣ በተለይ ከአንድ ከአማራ ብሔረሰብ ጋር ሊያቆራኙት ይሞክራሉ። ከዚህ በተቃራኒና በአፀፋ ዲስኩር መልክ የቆመው ታናሺቱ ኢትዮጵያ አስተምህሮ፣ ደመነፍሳዊ አስተሳሰብ ሲሆን ሐበሻና ኢትዮጵያን በመነጣጠል ይጀምራል። ‹አስኳል ሐበሻ› ወይም ‹ቅኝ ገዥ ኢትዮጵያ› የሚለው ከፍፍል በኢትዮጵያ/አቢሲኒያና በደቡባዊ ሕዝቦች መካከል ልዩነት አለ በሚል የተመሠረተ ነው። በተለይ የደቡቡን የአገሪቱን ክፍል ከሰሜናዊው ወይም ሐበሻዊው ወይም ታሪካዊ አስኳል ከሚባለው ለይቶ በማየት የመጣ ስህተት ነው። ከናካቴው ይህ ክፍል በታሪክም፣ በባሕልም፣ በዘርም ከኢትዮጵያ አይመደብም፣ ስለዚህም ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚል ክህደትን ይጨምራል። በዚህ ላይ ኢትዮጵያ የደቡባዊው ክፍል ቅኝ ገዥ ናት ይላል። ሰሜናዊ ወይም ሐበሻ የሚለውንም እንደ አንድ ወጥ ሕዝብ ያያል። ደቡባዊውንም በውስጡ ልዩነት የሌለው አሀድ አድርጎ ይቆጥራል። ከተማሪው ንቅናቄ በቀጥታም በተዘዋዋሪም የወጡ ቡድኖች፣ የጀብደኝነት ድርጊቶቻቸው ወደፊት ምን ያስከትሉ ይሆን ብለው ለመጭው ትውልድ ለማሰብ አይፈልጉም። ማፍረሳቸውን እንጂ ምን እንደሚያፈርሱና በምትኩ ምን እንደሚገነቡም አያወቁም። እስከዛሬም አምሳ ዓመት ሙሉ እነዚህን አጥፊ ሐሳቦች በጭፍንነት ማራመዳቸው ከምን የመነጨ እንደሆን ለመረዳት ያስቸግራል። በተለይ ጎሰኝነትና የአገር ክዳት በዘመነ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መከበሪያ ሆኖ አሁን ለምንገኝበት መስቀለኛ መንገድ አደረሰን። በዚህ ዘመን የናጠጠውን የከፋፋይነት ፖለቲካ በሁለት ዓይነት መልኩ ማየት እንችላለን። አንዱ መልክ ብድር መላሽ የሆነና የጎሳ ባላንጣዎችን ዒላማ የሚያደርግ ነው። ‹የነፍጠኞች ሴራ ትናንትና ዛሬ› በሚለው መርዘኛ አባባል ይገለጻል። ሁለተኛው የዳግም ውልደት መልክ ሲሆን፣ በራስ ደመነፍሳዊ ማኅበረሰብ ላይ ያተኮረ ነው። የጎሳ ማንነትን፣ ባሕልን፣ ታሪክን በመፍጠር የተሠማራ ቢሆንም፣ በተፈጥሮው በዚህ አይቆምም። በአንድ በኩል ስለጎሳዬ ከኔ ውጭ ማንም ሊያገባው አይችልም የሚል ጤናማ ያልሆነ አስተሳሰብ ነው። የአጎራባች ማኅበረሰቦችን መስተጋብር ቆርጦ የሚጥል፣ ነጥሎ የሚያይና ብሔራዊ ራዕይ የሌለው ከሆነ አደጋ ይደቅናል።

አሮጌውን ትውልድና አሮጌ ሐሳቡን ማለፍ ይቻላል የብሔራዊ ጥያቄ መነሻ፣ ሒደትና ውጤት በተመለከተ የዘውጌ-ብሔርተኛው ትግል አንጋፋ መሪዎች እንኳን የነበራቸውን የተምታታ

አመለካከት በፀፀት እየከለሱ ናቸው። እንደ ተስፋፅዮን መድኅኔ፣ አረጋዊ በርሔና ዲማ ነገዎ የመሳሰሉ ምሁራን ትውልዳቸው የብሔር ጥያቄን መሰሪ ማወናበጃ መሣሪያ በማድረግ፣ ታሪክን በማዛባትና የማጭበርበሪያ ዲስኩር ስለማድረጉ ይስማማሉ። በተለይ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.አዊው የዘውግ ፖለቲካ በአገሪቱ አብዛኛ ክፍል ውስጠማኅበረሰባዊ ግጭቶችን ከመጫር በተረፈ፣ ለብሔረሰቦች ፍትሕና ዴሞክራሲን አላመጣም። ለጥቂቶች የእንጀራ ዘይቤ ሆኖ ቀረ ብለው ያማርራሉ። ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ታሪክና እሴቶቸ ያለው ግንዛቤ እጅግ የተዛባና፣ በአመዛኙ በፖለቲካ መድልዎ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ያሳስባል። በኢትዮጵያ ታሪክና አንድነት ላይ በቅድመና ድኅረ-አብዮት በግልጽና በስውር የተከፈቱ ጥቃቶችና በሕዝብ ላይ የተጫኑ መርዘኛ አመለካከቶች፣ በተለይም ዛሬ በሕዝባችን መካከል እንደዋዛ እየሰረጉ የመጡ ውዥንብሮች አደጋቸው ግልጽ እየሆነ ነው። መቋጫ የሌላቸው የሚመስሉትን የዚያን ትውልድ ከፋፋይ አመለካከቶች አንጥሮ የድኅረአብዮቱ ተተኪ የሚኖረውን አማራጭ አመለካከት ለማቅረብ፣ በአገርና በብሔረሰብ፣ አልፎም በተለያዩ አሰባሳቢ ማኅበረሰቦች መካከል ያለው ልዪነትና አንድነት መመርመርና መጥራት አለበት። ኢትዮጵያ፣ ብሔረሰቦቿና ታሪኳ በተቃርኖ የቆሙ ሳይሆኑ፣ አንድነትም ልዩነትም ያላቸው፤ አንዱ ያለአንዱ የማይታለሙና የተሟላ ትርጉም የማይሰጡ ናቸው። አገራዊና ነገዳዊ ማንነቶች የግድ አይቃረኑም። ብዝኃ ማንነት ብዝኃ ታሪኮችን የግድ ይላል። የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የባሕል ልዩነት እንደ ኢትዮጵያ ባለች ብዝኃነት ተፈጥሮዋ በሆነ አገር የተለመደና፣ በዘመናት ያደረጀውም የተቻችሎ ስርዓት ያለው ነው። በዚህ ላይ ማንነት በርካታ ተጠላላፊ ዘርፎች ያሉት በመሆኑ፣ በአንዱ ያጣውን በአንዱ እየካሰ እንደ ሁኔታው የሚታይ ኅብረት ፈጥሯል። በአውራጃ ቢለያይ በቋንቋ፣ በቋንቋ ቢለያይ በእምነት፣ በእምነት ቢለያይ በመደብ ይዛመድ ነበር። ስለዚህም አገራዊነት ወይም ዜግነታዊ ማንነት በጋራ ተሞክሮዎችና እሴቶች ዙሪያ ሊገነባ ይችላል። ኢትዮጵያዊነት የሞተና የተዘጋ አጀንዳ አድርጎ ማሰብ ራስን ማሞኘት ነው። ብሔራዊ ግብ የሌለው የመንደር ፖለቲካ ጥቂቶችን በሥልጣን ለማክረም ሊጠቅም ይችላል። ነገር ግን አብሮ በሠላም የመኖርን እውነታ ስለሚዘነጋ አገር አጥፊ ነው። ትውልድ ገዳይ ነው። በተለይ ወጣቱ በታሪኩና በማንነቱ የሚኮራና በጋራ ለለውጥ የሚነሳ ኃይል እንዲሆን መታገዝ አለበት። ወጣቱ አገሩን የሚያስባትና የሚወዳት እንጂ ግድየለሽ የሚሆንባት፣ የሚሸሻት፣ የሚያፍርባት አልፎም የሚጠላት እንዲሆን መገፋቱን መቃወም ያስፈልጋል። ልጆቻችን የወደፊቷን ኢትዮጵያ በብሩህ መንፈስ የሚጠብቋት፣ ተስፋ የሚሰንቁባት አገር ለማድረግ መጣር፣ ያ ትውልድ ያቆየልንን የቂምና ጥላቻ ባሕል መሻር የአያቶቻችን ሳይሆን ዛሬ የኛ ኃላፊነት ነው። ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃይለማርያም የታሪክ መምህርና ተንታኝ ናቸው፡፡ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ይገኛሉ፡፡

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ሕግ ፍትሕ አስተዳደር

የአግላይ የምርጫ ስርዓት ጦስ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የምርጫ ስርዓቱን ለመሻሻል በማይቀል መልኩ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ እንዲካተት አድርጓል። ዕኩል ጡንቻ ያላቸው ፓርቲዎች በሌሉበት ስርዓት ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን አያበረታታም የሚባለው ‹First Past the Post (FPTP)› ስርዓትን በመከተል የፓርላማ መቀመጫዎችን በሙሉ በመቆጣጠር ራሱን ‹አውራ ፓርቲ› ነኝ ብሎ ሠይሟል - ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.። ተሾመ ተስፋዬ ይህንን እውነታ በመገምገም በጊዜ ካልታሰበበት ጦሱ ለአገሪቷ ደኅንነት እንደሚያሰጋ መክሯል።

በአገራችን በ2007 በተደረገው ምርጫ በርካቶችን ባስገረመ ሁኔታ ገዢው ፓርቲ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. 100% ማሸነፉን ማወጁ ይታወቃል። ሆኖም ድርጅቱ ድሉን ባበሰረ ማግስት ሰፊ ሕዝባዊ ተቃውሞና አመፅ የገጠመው መሆኑንም ሁላችንም እናውቃለን። ይህ በተለይም በኦሮሚያና አማራ ክልል ተስፋፍቶ የሚገኘው ተቃውሞውና አመፅ ምክንያቱ ከመሬትና ከማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ ቢመስልም የተቃውሞው ስፋትና ተራዛሚነቱን መነሻ በማድረገ ብዙዎች ከድርጅቱ አጠቃላይ ቅቡልነት ማጣት ጋር ያያይዙታል። በዚህ አጭር ጽሑፍ የምርጫ ሕጉ አርቲፊሻል አብላጫ ድምፅን በማዋለድ ገዢውን ፓርቲ ተገቢነት ለሌለው መታበይ መዳረጉ፣ ገዢውን ፓርቲ የማይደግፉ ዜጎችን ድምፅ ደግሞ ባዶ በማስቀረት በመንግሥት ውስጥ ውክልና እንዳይኖራቸውና በምርጫ ብሎም በፖለቲካ ስርዓቱ ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ ማድረጉ ከተቃውሞው ጋር ሊተሳሰር የሚችልበትን ሁኔታ ለማሳየት ይሞክራል። የምርጫ ስርዓት በርካታ ጉዳዮችን የሚያካትት ቢሆንም ለዚህ ጽሑፍ ዓላማ ድምፅ ወደ ፓርላማ ወንበር የሚቀየርበትን ሒደት የሚያመለክት ነው። በዓለም የተለያዩ የምርጫ ስርዓቶች ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙ ሲሆን ለመንደርደሪያ እንዲያገለግለን ሁለት ዋና ዋና ስርዓቶችን በአጭሩ እንመልከት። የመጀመሪያው የአብላጫ ድምፅ ስርዓት ሲሆን ‹first past the post› እና ‹absolute majority vote (50% + 1)› የሚባሉትን ያካትታል። በ‹first past the post› የምርጫ ስርዓት መሠረት አገሪቱ በምርጫ ክልሎች ትከፋፈልና በያንዳንዱ የምርጫ ክልል ከተሳተፉ ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫውን ድምፅ ያገኘው ተወዳዳሪ አሸናፊ ይሆናል። በ‹absolute

majority› ስርዓት ደግሞ አሸናፊው ተወዳዳሪ ከያንዳንዱ ተፎካካሪው የተሻለ ድምፅ ከማግኘት ባለፈ የአብዛኛውን መራጭ ሕዝብ (50% + 1) ማግኘት ይጠበቅበታል። ነገር ግን በሁለቱም አማራጮች ተሸናፊዎቹ ተወዳዳሪዎች ያገኙት ድምፅ ዋጋ አልባ ሆኖ ይቀራል። ሁለተኛው ደግሞ ተመጣጣኝ ውክልና (‹proportional representation›) በመባል ይታወቃል። በዚህ የምርጫ ስርዓት ተወዳዳሪዎቹ በአገሪቱ አጠቃላይ ያገኙት ድምፅ መጠን መሠረት ተመጣጣኝ ወንበር ያገኛሉ። እያንዳንዱ ተወዳዳሪ የሚያገኘው ወንበር በአገሪቱ የሚገኙ መራጮች ከሰጡት ድምፅ የተመጣጠነ ነው። የሁሉም መራጭ ድምፅ ከሞላ ጎደል የፓርላማ ውክልና ያገኛል።

አግላይ የምርጫ ስርዓት የአገራችንን ሁኔታ የተመለከትን እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 እና በምርጫ ሕጉ አዋጅ ቁጥር 532/99 አንቀጽ 25 እና 49 (1) ድንጋጌዎች ለመረዳት እንደሚቻለው የምንከተለው ‹first past the post› የሚባለውን የምርጫ ስርዓት ነው። በዚሁ መሠረት አገሪቱ ከ550 ባልበለጠ የምርጫ ክልል ተከፋፍላ በያንዳንዱ የምርጫ ክልል ሊወዳደሩ ከሚችሉት ከ12 ያልበለጡ ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምፅ ያገኘው ተወዳዳሪ አሸናፊ ይሆናል። አሸናፊው ከሌሎቹ የበለጠ ድምፅ ከማግኘት ባለፈ የአብዛኛውን መራጭ ድምጽ (50% + 1) ማግኘት አይጠበቅበትም። በሌላ በኩል ለተሸነፉ ተወዳዳሪዎች የተሰጠው ድምፅ በሙሉ ዋጋ አልባ ሆኖ ይቀራል። በመሠረቱ በዓለም ላይ እየተተገበሩ ከሚገኙ የምርጫ ስርዓቶች መካከል ምርጡ የትኛው ነው? በሚለው ላይ መግባባት የለም። ሁሉም የምርጫ ስርዓቶች የየራሳቸው ጠቃሚና

ጎጂ ገጽታ ሊኖራቸው ይችላል። ሆኖም የየአገራቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት አንዱ ከሌላው በተሻለ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይስማማሉ። በዚህም መሠረት በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራንና ፖለቲከኞች ለኢትዮጵያ ተመራጩ የምርጫ ስርዓት ሕገ መንግሥቱ ላይ የተካተተው ሳይሆን ተመጣጣኝ ውክልና የሚባለው እንደሆነ ይገልጻሉ። እንደ ባለሙያዎች ገለጻ ይህ የምርጫ ስርዓት ሁሉም ፓርቲዎች ባገኙት ድምፅ መጠን ወንበር የሚያገኙበትና የሚመሠረተው ፓርላማ የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ምርጫ የሚያንፀባርቅ ስለሆነ ቢያንስ በሦስት ዐበይት ምክንያቶች ለኢትዮጵያ ተመራጭ እንደሆነ ያስረዳሉ። 1ኛ፣ አገሪቱ ከእርስ በርስ ጦርነት የተላቀቀችና የተለያየ ፍላጎት ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚኖሩባት ከመሆኑ አንፃር ሁሉም ተመጣጣኝ ውክልና እንዲያገኙ በማድረግ አካታች የፖለቲካ ስርዓት ለመፍጠር ስለሚያስችል። 2ኛ፣ ለአገሪቱ ከተመረጠው የፌደራል አወቃቀር አንፃር ተጣጥሞ የሚሔድ በመሆኑ። 3ኛ፣ በአንፃሩ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ የተመለከተው የ‹first past the post› የምርጫ ስርዓት ጠንካራ መዋቅራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ከነበረው ገዢው ፓርቲ አንፃር ደካማ የሆኑት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወዳድረው የሚያሸንፉበትን ዕድል በእጅጉ ስለሚያጠብና በሒደትም ከፖለቲካ ተሳትፎ የሚያገላቸው መሆኑ ነው። ሕገ መንግሥቱን በማርቀቅና በማፅደቅ ሒደት አወዛጋቢ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱም ይህ የምርጫ ስርዓት ጉዳይ ነበር። በወቅቱ በገዢው ፓርቲ በኩል የቀረበው ምክንያት የተመረጠው የምርጫ ስርዓት መንግሥት ለማደራጀትም ሆነ የመንግሥትን ሥራ ለማከናወን ቀላል ስለሆነና ኋላቀር የሆነው የፖለቲካ ባሕላችንና የኢኮኖሚ ሁኔታችን ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ስርዓትን ለመከተል አያስችለንም የሚል ነበር። ሆኖም ይህን የድርጅቱን መከራከርያ ከመነሻው ብዙዎች በጥርጣሬ የተመለከቱት ነው። 1ኛ፣ ድርጅቱ ያነሳቸው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ባሕል ኋላ ቀርነት በሒደት የሚፈቱ ሆነው ሳለ ወደ ፊት በቀላሉ ለማሻሻል በማይቻልበት ሁኔታ በመቃብሬ ላይ ካልሆነ አይሻሻልም የሚለው ሕገ መንግሥት ላይ ማስፈሩ። 2ኛ፣ ከዓመታት በኋላ እንኳን ድርጅቱ አገሪቱ በኢኮኖሚ አደገች፣ ዴሞክራሲም አበበ እያለ በሚለፍፍበት ሁኔታ እንኳን የምርጫ ስርዓቱን ለማሻሻል አንዳችም ጥረት አለማድረጉን ለተመለከተ በእርግጥም ወደሚቀጥለው ገጽ

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ውይይት ነሐሴ 2008

21

ሕግ ፍትሕ አስተዳደር

መከራከርያው ከልብ እንዳልቀረበ ለመረዳት ይቻላል። ይልቁንም ድርጅቱ የምርጫ ስርዓቱን የመረጠውና ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያካተተው ከመነሻው የነበረውን ድርጅታዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት በመጠቀም የተከፋፈሉና አቅማቸው የተዳከመ ተቃዋሚዎች በመታጀብ ምርጫ እያደረገ በቀላሉ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ስለሚያስችለው ነው። የእስካሁኑ የምርጫ ታሪካችንም ከሞላ ጎደል ያረጋገጠው ይህንኑ ነው። የምርጫ ስርዓቱ ለአገራችን ተመራጭ ባይሆንም ባለበት ሁኔታ በአገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓትን እንዲያሰፍን ከተፈለገ የተወሰኑ ሁኔታዎች ሊሟሉ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ። በዚሁ መሠረት 1ኛ፣ ከሁለትና ሦስት የማይበልጡ ጠንካራና ልዩነታቸውም ጠባብ የሆነ ፓርቲዎች ሊኖሩ ይገባል። 2ኛ፣ ጠንካራና ከፓርቲ ታማኝነት ባለፈ ለሕዝብ ጥቅም የቆመ ፓርላማ ሊኖር ይገባል። 3ኛ፣ ጠንካራና ነጻ ፍርድ ቤት፣ የሲቪክ ማኅበራትና ሚዲያ ሊኖሩ ይገባል። እነዚህን መመዘኛዎች መነሻ አድርገን አገራችንን የተመለከትን እንደሆነ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ እንገኛለን ለማለት ያስደፍራል። ከ97 ምርጫ በስተቀር ጠንካራና የተባበረ ተቃዋሚ ፓርቲ ለማየት አልታደልንም። ከገዢው ፓርቲ በሚደርስባቸው ግልጽና ስውር ጫና የተነሳ፣ እንዲሁም በብሔርና በመሪዎቹ የሥልጣን ጥም የተነሳ የተከፋፈሉና የተዳከሙ ሆነው ይገኛሉ። የሲቪክ ማኅበራትና ነጻ የሚዲያ ተቋማትም ቢሆን በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ገዢው ፓርቲ በደረሰበት ድንጋጤ የተነሳ በተከታታይ አፋኝ ሕጎችን በማውጣትና የአፈና ተግባሮችን በመፈፀሙ እንዲከስሙ አድርጓል። እንግዲህ እነዚህ ሁኔታዎች ከምርጫ ስርዓቱ አግላይነት ጋር ተዳምረው ገዢው ፓርቲ 100% ቢያሸንፍ ላይገርም ይችላል። ነገር ግን ይህ ሁኔታ በሒደት የፖለቲካ ስርዓቱን አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ለመገመት አይከብድም።

መልኩ ለሕዝብ ሲቆሙ አይታይም። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልል ሰፊ ሕዝባዊ ተቃውሞ ደርሶ በርካቶች ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለእስራት ተዳርገው ይገኛሉ። ፓርላማውም ስለሁኔታው፣ በተለይም የመንግሥት ታጣቂ ኃይሎች በሕዝቡ ላይ የሚያደርሱት እስራትና ግድያ የዜጎችን መብት ስለመጣስ፣ አለመጣሱ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ የሚመለከተውን አስፈፃሚ አካል መጠየቅና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይጠበቅበታል። ይሁን እንጂ ያን ያክል አንገብጋቢ ያልሆኑ አዋጆችን ለማፅደቅ በቅርቡ አሰቸኳይ ስብሰባ የጠራ ፓርላማ ስለ ተቃውሞው ሁኔታ ዝም ማለቱ የሚያሳዝን ነው።

ያልተወከሉ ድምፆች የምርጫ ስርዓታችን አንዱ ችግር አርተፊሻል አብላጫ ድምፅ መፍጠር መቻሉ ነው። ከላይ እደተገለጸው ገዢው ፓርቲ ወንበሮቹን ለማግኘት በየምርጫ ክልሉ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች የበለጠ ድምፅ ማግኘት እንጂ የመራጮችን አብላጫ ድምፅ ማግኘት አይጠበቅበትም። በአንድ የምርጫ ክልል ደግሞ እስከ 12 ተወዳዳሪ ሊወዳደር የሚችል በመሆኑ ለእያንዳንዱ ተወዳዳሪ የሚሰጠው ድምፅ ከገዢው ፓርቲ ያነሰ ቢሆን የሌሎች ተወዳዳሪዎች ድምፅ ተደምሮ በርካታ ሊሆን የሚችልበት አገጣሚ ሰፊ ነው። ይህም ማለት ገዢው ፓርቲ መንግሥት ቢመሠርት እንኳን የግድ አብዛኛው ሰው ይደግፈዋል ማለት አይደለም። ማለትም ገዢው ፓርቲ ከ50% በታች ድምፅ አግኝቶ እንኳን ሊያሸንፍና መንግሥት ሊመሠርት

ገዢው ፓርቲ ከ50% በታች

የሕዝብ ወይስ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ተወካይ?

ድምፅ አግኝቶ እንኳን

በመሠረቱ የፓርላማ አባላት የሕዝብ ተወካይ እንደመሆናቸው ለአገሪቱና ለሕዝቡ አጠቃላይ ጥቅም መሥራት እንዳለባቸው ይታመናል። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54/4/5 ላይ በግልጽ እንደተመለከተው የምክር ቤቱ አባላት ተገዢነታቸው ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝብና ለኅሊናቸው ሲሆን በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰጡት ድምፅም ሆነ አስተያየት ምክንያት ተጠያቂነት እንደሌለባቸው ተደንግጓል። ሆኖም የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የፓርላማ አባላት ድርጅቱ በሚከተለው የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የፖለቲካ ዲሲፕሊን የተጠረነፉ በመሆኑ የሕዝቡን ፍላጎት ለማስተጋባትና የአስፈፅሚውን አካል ለመቆጣጠር አቅም የላቸውም። በፓርቲው አሠራር መሠረት አብዛኛው ነገር አስቀድሞ በፓርቲው የሚወሰን በመሆኑና አባላቱም ይህን የማስፈፀም ግዴታ ስላለባቸው ከዚህ ባፈነገጠ

ሊያሸንፍና መንግሥት

22 ውይይት ነሐሴ 2008

ሊመሠርት ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ በየምርጫ ክልል ተቃዋሚዎችን የመረጡ መራጮች ድምፅ ዋጋ አልባ ሆኖ ይቀራል

ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ በየምርጫ ክልል ተቃዋሚዎችን የመረጡ መራጮች ድምፅ ዋጋ አልባ ሆኖ ይቀራል። ምክንያቱም የምርጫ ስርዓቱ አሸናፊ ሁሉን የሚያገኝበት ተሸናፊው ደግሞ ምንም የማያገኝበት ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ በአብዛኛው በከተሞች አከባቢ የተወሰነ ስለሆነ የሚያገኙት ድምፅ በየምርጫ ክልሉ የተበታተነ ነው ለማለት ይቻላል። በዚህ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተበታተኑና ያልተባበሩ መሆን ሲታከልበት ገዢውን ፓርቲ ከማጀብ ባለፈ የማሸነፍ ዕድላቸው ጠባብ እንዲሆን ያደርጋል። ለምሳሌ የ2007ቱን ምርጫ እንመልከት። በምርጫው ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. 100% አሸንፏል ተብሏል። ይህን እንዳለ ብንቀበል እንኳን ዝርዝር ሁኔታው ጥናት የሚጠይቅ ሆኖ ገዢው ፓርቲ የሚያደርስባቸውን ግልጽና ስውር ተፅዕኖ ተቋቁመው በርካታ ዜጎች ተቃዋሚዎችን መምረጣቸው ይታወቃል። የተመጣጣኝ ውክልና ስርዓትን ብንከተል የእነዚህ ዜጎች ድምፅ በዚያው ልክ የፓርላማ ውክልና ያገኝ እንደነበር ይታወቃል። ነገር ግን በምርጫ ስርዓታችን አግላይነት የተነሳ አንድም ወንበር ሊያስገኙ አልቻሉም። ገዢውን ፓርቲ የመረጡት ድምፆች ወደ ፓርላማ ወንበርነት ሲቀየሩ የተቃዋሚዎች ድምፅ የተበታተነ በመሆኑ ብቻ የቆሻሻ መጣያ ውስጥ ከመጣል ያለፈ ሚና አልነበረውም። የምርጫ ስርዓቱ ጥንቃቄ ካልተደረገበት በስተቀር የእርስ በርስ ጦርነት እስከማስነሳት የዘለቀ አደጋ ሊያስከትል አገራችን የምትከተለው የምርጫ እንደሚችል ፖለቲካውን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ገዢው ፓርቲ የምርጫ ስርዓቱ በፈጠረለት አመቺ ሁኔታ በየወቅቱ በሚያገኘው አርተፊሻል አብላጫ ድምፅ በመታበይ “አውራ ፓርቲ” መሆኑን በማወጅ ሰፊ የሕዝብ ተቀባይነት አለኝ ወደሚል ቅዠት ውስጥ ከገባ ቆይቷል። በዚህም የተነሳ ለተቃውሞ ድምፆች ተገቢውን ትኩረትና ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ወደማፈን ተግባሩ አዘንብሏል። በሌላ በኩል አስፈፃሚዉን አካል የሚገራና የሚቆጣጠር ጠንካራ ፓርላማ ባለመኖሩ ስርዓቱ ይበልጡኑ በሙስናና በብልሹ አሠራሮች እየበሰበሰ ሄዷል። መራጩ በተለይም ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን የሚቃወመውና የማይደግፈው የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ በፓርላማ ውስጥ አንዳችም ውክልና እንዳይኖረው ስለተደረገ በምርጫ ተስፋ እንዲቆርጥ ሆኗል። እነዚህንና ተዛማጅ ሁኔታዎችን የታዘቡ ፖለቲከኞች በሒደት ስርዓቱ ቅቡልነትን እንደሚያጣ፣ ሕዝባዊ ቁጣና ተቃውሞ ሊገጥመው እንደሚችል ከተነበዩ ቆይተዋል። በእርግጥም በዚህ ዓመት በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልል እንደ ሰደድ እሳት የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞና አመፅ የትንቢቱን እውን መሆን የሚያሳይ ነው።

ጸሐፊው ተሾመ ተስፋዬ በኢሜይል አድራሻው [email protected] ይገኛል።

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

አንድ ሰው

ሳሚ-ዳን በሬጌ በዚህ ዓመት ከወጡ አልበሞች መካከል የመጀመሪያ አልበሙን ይዞ ብቅ ያለውን እና ወጣ ባሉ ሥራዎቹ ተወዳጅነትን ማትረፍ የቻለውን የሳሚ-ዳን ‹ከራስ ጋር ንግግር› በመንተራስ የሳሙኤል ብርሃኑን የሙዚቃ ሕይወት መብራቱ በላቸው እንደሚከተለው ያስቃኘናል።

እንደ መነሻ

የሬጌ የመዚቃ ዘውግ በጃማይካውያን የበደል፣ የመገፋትና የመጨቆን ዘመን የተወለደ፣ ጭቆናን እና በደልን ለመታገል እንደ መሣሪያ ያገለገለ፣ ድምፃቸውን ለዓለም ያሰሙበት የሙዚቃ ዘውግ ነው። ለዘመኑ የሰብኣዊነት ጥያቄ ትልቅ ድምፅ መሆን የቻለ ስልት ነው። የሬጌ ንጉሥ በመባል የሚታወቀው ቦብ ማርሌም ሆነ ጃማይካውያን በጥቁር የሰው ልጆች መበደልና መገፋት ውስጥ ትልቅ ተስፋንና ብርታት የሰጠቻቸውን ኢ ት ዮ ጵ ያ ን ና ን ጉ ሥ ዋ ን እስከ ማምለክ በሚደርስ ፍቅሯ ወድቀዋል። ብ ዙ ም አዚመዋል።

ሬጌ ሙዚቃ በጣም የበለፀገና የሚያነሳቸው ሐሳቦችም ጥልቅ፣ ዓለማቀፋዊ ይዘት ያላቸው እንደ ሠላም፣ ነጻነት፣ ዕኩልነት፣ ፍቅር የመሳሰሉትን የሚያቀነቅን ነው። ከተገፉትና ከተበደሉት ጋር በመቆም ለመላው የሰው ልጆች አጋርነቱን ያሳያል። ለዚህም ነው ባለሙያዎች ሲናገሩ ሬጌ ‹ሊሸከማቸው የማይችላቸውና የማይፈቅዳቸው ሐሳቦች አሉ› የሚሉት። የሳሚ-ዳን “ከራስ ጋር ንግግር” አልበም በሬጌ ስልት የተቀነቀኑ በዛ ያሉ ሙዚቃዎችን ያካተተ በ2008 በአገራችን ከወጡ ድንቅ የሙዚቃ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ነው። በዚህ ሥራ ውስጥ መንፈሳዊነት፣ እውነት፣ ፍትሕ፣ ፍቅር፣ ሠላም እና መሰል የሰው ልጆችን የሚመለከቱ ሐሳቦች በድንቅ ዜማና የድምፅ ቅላፄ ቀርበውበታል።

የሙዚቃ ሕይወት የመድረክ ሥሙ ሳሚ-ዳን፤ የመታወቂያ ሥሙ ሳሙኤል ብርሀኑ ይባላል - ‹ከራስ ጋር ንግግር› አልበም አቀንቃኝ። ሙዚቃን በልጅነቱ እንደጀመረ ይናገራል። ገና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እያለ ኤልዳና ባንድ የቀበሌ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ባወጡት ማስታወቂያ መሠረት እምነት በምትባል ወዳጃቸው አማካኝነት እሱና ዲጀሪ እንደሔዱ ያስታውሳል። በወቅቱ ወጥተው የነበሩትን የጎሳዬን እና አሌክስን ዘፈን የሚጫወት ሰው ነበር የተፈለገው። በዚህም እሱ የቴዲ አፍሮን በመጫወት ከኤልዳና ባንድ ጋር የመሥራት ዕድል አገኘ። ከኤልዳና ባንድ ጋር ያለው ቁርኝት በጣም አድጎ ለአምስት ዓመት እንደቆየና እሱ ለትምህርት ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ እንደተቋረጠ ይናገራል። “ከኤልዳና ጋር በነበረኝ ቆይታ በልጅነት ብዙ የሙዚቃ ትምህርት ቀስሜያለሁ” ይላል ሳሚ-ዳን። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ማኔጅሜንት በምሕንድስና ሙያ ተመርቆ ከወጣ በኋላ ሐሴት አኮስቲክስ ባንድን በመቀላቀል ለሦስት ዓመት አብሮ ሠርቷል። በመኃል ኢምፔሪያል ማጀስቲ ሲድኒ ሶሎሞን ጋር ለአንድ ዓመት በመሥራት የሬጌንና ሌሎች የሙዚቃ ልምዶችን እንደገበየ ይናገራል። ከዚህ በኋላ ነበር ከኤንዲ ጋር በመሆን ዘውድ አኮስቲክስ የተባለ ባንድ ያቋቋሙት። የባንዱ አባላትም ኤንዲ፣ ኪያ (ቤዚስት)፣ ከቤ ወደሚቀጥለው ገጽ

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ውይይት ነሐሴ 2008

23

አንድ ሰው (ድራመር) እና ድምፃዊ ሳሚ-ዳን ናቸው። አሁን ዘውድ አኮስቲክስ ብዙ አባላትን አካትቶ ‹ዘውድ ባንድ› በመሆን በመሥራት ላይ ይገኛል።

ሬጌ ለምን? “በዕለት

ተለት

ኑሮዬ

የታዘብኳቸውና

በውስጤ የሚመላለሱ የራሴ የሆኑ ብዙ ሐሳቦች አሉ። እነዚህን ሐሳቦች በሙዚቃ ማስተላለፍ እፈልግ ነበር” የሚለው ሳሚ-ዳን ሐሳቦቹን በተገቢው መልኩ ለመግለጽ ግን ቀላል እንዳልሆነ ይናገራል። “እያንዳንዱ የሙዚቃ ዘውግ የተፈጠረበት የራሱ ምክንያት አለው ። የትኛው ምን መልዕክት ቢተላለፍበት ጠንካራ ይሆናል የሚለውን ማወቅ በጣም ጠቃሚ ነው” የሚለው ሳሚ-ዳን እሱም ሬጌን እንደ ስልት ሲመርጥ ከዚህ አንፃር እንደሆነ ይናገራል። ሳሚ-ዳን ሬጌን በዋናነት እንደ ስልት የመረጠበትን ምክንያት ሲያስረዳ የጥቁሮች የዕኩልነት፣ የሠላምና የፍቅር ሐሳብ ሊገለጽበት የተፈጠረ መሆኑ፣ ጃማይካዊያን በሬጌ ስልታቸው የኢትዮጵያን የነጻነት ፈር ቀዳጅነት የሚሰጡት ዕውቅናና ከነሱ ጋር ያለን ትስስር፣ እንዲሁም ስልተ-ምቱ ከብዙ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ምቶች ጋር ስለሚሔድ ነው” ይላል። “ሬጌ ለእኔ ሠላም፤ ፍቅርና አንድነት የምገልጽበትና ለተገፉት የምናገርበት የሙዚቃ ስልት ነው” ይላል ሳሜ ዳን። ከሲድኒ ሶሎሞን ጋር በሠራባቸው ጊዚያት

ብዙ የሬጌ ሙዚቃ አስተሳሰብ እንደተማረ የሚናገረው ሳሚ-ዳን ለጃማይካዊያንና ለሬጌ ሙዚቃ ያለው አድናቆትና ክብር ከፍ ያለ ነው። ሬጌ እንዲሁ በቀላሉ የሚጫወቱት የሙዚቃ ስልት አይደለም። በብዙ ጥልቀትና ጥረት የሚጫወቱት ስልት ነው። የሚተላለፍባቸውም መልዕክቶች ላቅ ያሉና ዓለማቀፋዊ የሆኑ ናቸው። ባለሙያዎች ሲናገሩ ሳሚ-ዳን በአልበሙ ይሄን በብቃት ተወጥቷል።

ከራስ ጋር ንግግር

ፍሬስብሓት “ከ1999 በኋላ

“በ2008 ከወጡ ሙዚቃዎች አዳምጫቸው በስሜትም በልኬትም ልክ የመጣልኝ ሙዚቃ የሳሚ-ዳን ‹ከራስ ጋር ንግግር› የሚለው አልበም ነው” የሚለው የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሓት “ከ1999 በኋላ በሬጌ ቅርፅ አዲስ ስልት ይዞ የመጣ ነው” ይለዋል። ኢዮብ መኮንን በ1999 የቆየውን ‹ሩት ራውንድ› የሚባለውን የሬጌ ስልት ራሱን ሬጌን ከሚመጥን አስተሳሰብ ጋር ይዞ እንደመጣ የሚያስታውሰው ሰርፀ ከዚያ በኋላ እነ ጃሉድ፣ ኃይሌ ሩትስ፣ የመሳሰሉት ሬጌን እንደተጫወቱ ይገልጻል። የሳሚ-ዳን ‹ከራስ ጋር ንግግር› አልበም ‹አር ኤንድ ቢ›ንና የሬጌን ስልት በመቀላቀል አሁን በዓለም ላይ እየታየ ያለ አዲስ የሬጌ ስልት የያዘ አልበም ነው። የሐሳቡን ጥልቀትና ትልቅነት ሰርፀ ሲገልጽ “ከለመድናቸው ሮማንቲክ የዘፈን ግጥም ስልቶች ወጣ ያለ ዓለማቀፋዊ ይዘት ያላቸው የእውነት፣ የፍትሕ፣ የሞራል፣ የሥነ ምግባርና ፍልስፍናዊ ጥያቄዎችን የያዘ ነው” ይለዋል። “ዘፈን ማለት የሴት ልጅ ገላ፣ ሴት ልጅ ማለት ደግሞ ገላዋ አድርገው ለሚሰብኩን ሸቀጣም ዘፈኖቻችን ትልቅ መሸጋገሪያ ድልድይ መሆን የሚችልና ዘፈንን ከሚነሱበት የሞራል ትችት የሚያወጣ ነው” በማለት የሳሚዳንን ሥራ ትልቅነት ይገልጻል - ሰርፀ። ብዙ አድማጮች እንደሚስማሙበት ከተራ የ‹ሮማንስ› ግጥሞች በዘለለ ለሬጌ በሚመጥን መልኩ ሳሚ-ዳን በሥራዎቹ ተገልጧል። ‹ከራስ ጋር ንግግር› ሳሚ-ዳን ለረጅም ጊዜ በሕይወቱ ሲያወጣና ሲያወርዳቸው የነበሩ ሐሳቦችና የሙዚቃ ልምዶች ድምር ውጤት እንደሆነ ይናገራል። አልበሙ በወጣ ሦስትና አራት ወር ውስጥ በጣም ጥሩ የሚባል አቀባበል እንደተደረገለት የሚናገረው ሳሚ “የራስን መንገድና ፍልስፍና ጥራት ባለው መልኩ ይዞ ከተመጣ ተቀባይነት ማግኝት እንደሚቻል ተረድቻለሁ” ይላል። ‹ከራስ ጋር ንግግር› የሚለው የአልበሙ መጠሪያ ለየት የሚያደርገው አጠቃላይ የአልበሙን መንፈስና ሐሳብ የያዘ እንጂ ከአልበሙ ውስጥ ተነጥሎ የወጣ የአንድ ሙዚቃ ርዕስ አለመሆኑ ነው።

በሬጌ ቅርፅ አዲስ ስልት ይዞ

ከሙዚቃዎቹን በጨረፍታ

“በ2008 ከወጡ ሙዚቃዎች አዳምጫቸው በስሜትም በልኬትም ልክ የመጣልኝ ሙዚቃ የሳሚ-ዳን ‹ከራስ ጋር ንግግር› የሚለው አልበም ነው” የሚለው የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ

የመጣ ነው” ይለዋል 24 ውይይት ነሐሴ 2008

ከራስ ጋር ንግግር ዐሥራ ሦስት ሙዚቃዎችን የያዘ ግጥምና ዜማው በራሱ በሳሚ-ዳን የተዘጋጀ ሲሆን ቅንብር/ሚክሲንግ እና ማስተሪንግ ‹ኤንዲ ቤተ ዜማ› በግሩም ሁኔታ

የሠራው ነው። ‹ብሉ ሚዲያ› አሳታሚውና አከፋፋዩ ነው። ሳሚ-ዳን በያንዳንዱ ሙዚቃ መግቢያ በሚያምር ቃና ለ‹ኤንዲ ቤተ ዜማ› ዕውቅናና ምስጋናውን ያቀርባል። የአልበሙ መጠሪያ ብቻ ሳይሆን ፖስተሩም ማራኪና ብዙ እንደተለፋበት ያሳያል። ለፖስተሩ ማማር ፎቶግራፈር አሮን ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ይላል ሳሚ-ዳን። ‹የአንድ ጥሩ የጥበብ ሥራ መነሻና የአንድ ፈላስፋ መነሻ ጥያቄ ሁለቱ አንድ ናቸው› ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች። የአንድ ፈላስፋ የመጨረሻ ግቡ ጥሩ ወይም ሰናይ፣ እውነት እና መልካም የተባሉትን እሴቶች መፈለግ ነው። የአንድ የጥበብ ሥራ መጨረሻም እነዚህን እሴቶች በሥራዎቹ መዳሰስ፣ ከሰው ልጆች ነባራዊ ሕይወት ጋር እያዛመዱ ማቅረብ ነው። በዚህ አንፃር ከሳሚ-ዳን ሥራዎች የተወሰኑትን ለማቃኘት እሞክራለሁ። ሳሚ-ዳን “ወደ ላይ” በሚለው ዘፈኑ ከሰው አዕምሮ በላይ የሆነ ከእኛ አቅም በላይ ለሆነ ነገር መፍትሔ ያለበት አለ ይለናል። ለሁሉም ነገር መነሻና መድረሻ አለው። ከአዕምሮአችን በላይ ለሆነም ማንኛውም ነገር ከላይ መፍቻ አለ ይለናል። በግርግርና መደናቆር በተሞላች ዓለም ውስጥ ስንኖር አንዳንዴ የፅሞና እና ወደላይ መመልከቻ ጊዜም ያስፈልገናል የሚለው ሳሚ እንዲህ ይላል በዘፈኑ፦ “…የሁሉምመነሻ - እሱ መነሻ የለው መጨረሻ - መጨረሻ የምሥጢራት መፍቻ - እሱ ብቻ የምንመካበት - የለው አቻ…” በዚህ ዘፈኑ ስለፈጣሪ ሁሉን ቻይነትና የሰውልጆች ከአቅማቸው በላይ ለሆነ ነገር ወደ ላይ እንዲያዩ ይመክራል። ሳሚ-ዳን “ድምፅ አልባው ሰው” ብሎ በሰየመው ዘፈኑ የተገፋውን ባለመርዳቱ፣ ለድምፅ አልባው ድምፅ ባለመሆኑ ስለሚደርስ የኅሊና ወቀሳ በግሩም ሁኔታ ይገልጻል። የሞራል ልዕልናችንን፣ ውስጣችንን፣ አካባቢያችንን እንድናይ ይገፋፋናል። ቸልተኝነታችን ምን ያህል ጥፋት እንደሚያመጣ እየነገረ ይሸነቁጠናል። እንዲህም ይለናል፦ “…ዝምታዬ መልሶ እኔው ላይ ይጮሀል - ይጠይቀኛል ዝምታዬ መልሶ እኔው ላይ ይጮሀል ያሳድደኛል ዝምታዬ መልሶ እኔው ላይ ይጮሀል ለምን ዝም አልክ ይለኛል ዝምታዬ መልሶ እኔው ላይ ይጮሀል… የተራበውን አይቼ ሳልፈው የተጨነቀውን ሳልሰማው ለቸገረው ምንም ሳላካፍለው ለራሴ ብቻ ነው ለካ የምኖረው ጉልበተኛው ደካማውን ሲረግጠው ድምፁ እንዳይሰማ ሲያደርገው አንድ ቀንም ሳልዋጋለት ለካ ትቼው ነው ጥዬው ያለፍኩት…” ለደካማው ድምፅ አለመሆንን፣ ለድምፅ አልባው ድምፅ አለመሆን ከኅሊና ወቀሳ

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

አንድ ሰው የማያድን የኅሊና ዕዳ እንደሆነ ሲነግረን እውነትም ሳሚ-ዳን ሬጌ የሚጠይቀውን ሐሳብ ይዞ መጥቷል ያሰኘናል። ቸልተኝነት ሲበዛ ምናገባኝነት ሲያይል ለውጥም እንደናፈቀችን እንደምትቀር ያስረዳናል። የዘመናችንን ቸልተኝነት የተረዳ የሚመስለው ሳሚ-ዳን በመቀጠል እንዲህ ይለናል፦ “…ቸልተኝነቴ ለካ በዝቶ ነው - ለውጥ የሌለው ቸልተኝነቴ ለካ አድርጎኛል - ድምፅ አልባ ሰው ቸልተኝነቴ ለካ በዝቶ ነው - መኖር ያስጠላው ቸልተኝነቴ ለካ አድርጎኛል የዳርተመልካች…” “እውነት” በተሰኝው ዘፈኑ ደግሞ የእውነትን ዓለማቀፋዊነት፣ እውነት ከፍትሕ ጋር ያላትን ቁርኝት፣ እውነት የያዘ ከጉልበተኛውና ከግፈኛው እውነት እንደምታድነው አበክሮ ይናገራል። መሣሪያ ባይኖረን፣ አቅማችን ከጉልበተኛው ቢያንስ እውነትን ከያዝን እንደምናሸንፍና ተስፋ መቁረጥ እንደሌለብን እንዲህ ሲል ይነግረናል፦ “…እውነት የለውም አንድ አገር የለውም አንድ አገር ተቀብሮ የማይቀር ፍፁም ማነው ጉልበተኛ እውነትን ማጥፋት የሚች ልከኛ ኧረ ማነው የሰው ደካማ እውነትን ይዞ የማይሰማ ፍትሕ እያለ የተጠማ እስኪ ድምፁን የተቀማ ግንእውነትመቼያርፋል እንደተዳፈነ እሳት ይነሳል ስፍራ ጊዜ ሳይገድበው በሁሉም የሚፈርደው… ትልቅ ጦር መዞ ጋሻ ይዞ በሐሰት ቃል ተመርዞ ደካማ ናቸው ብሎ አስቦ ግን እኛ ደግሞ እውነት አለን ከምንም ነገር የሚያድነን ትንሽ ብንሆንም እንዳንፈራ የሚያደርገን…” እውነትንና ፍትሕን ለተነፈጉ ሁሉ እውነት አርነት እንደምታወጣቸው በግሩም ጣዕመ ዜማው ሳሚ-ዳን ሲያቀነቅን የዘመናችን የፍትሕና የእውነት አራማጅ የጥበብ ሰው ያደርገዋል። ፍትሕ በጠፋበት በዚህ ዘመን፣ ለእውነት መቆምንና ከጨቋኞች መዳኛ አለኝታችን መሆኑን የሚነግርልንና የሚያነቃ አቀንቃኝ በዚህ ዘመንና በዚህ አገር ማግኝት አስደሳች ነው። ለመጨረሻ ዕይታ “ፍቅር ሠላም” የተባለውን የሳሚ-ዳን ሥራ እንይ። በዚህ ሥራው ሳሚ በሰው ልጆች መካከል፣ በዘመናት መካከል፣ በታሪክ የሚከሰት ቁርሾ ስለሚፈወስበትና ለሠላምና ለፍቅር ፀር ሰለሆነው ‹ከእኔ ሐሳብ በላይ ሌላው ላሳር ነው› ስለሚለው አምባገነናዊ አስተሳሰብ ያዜማል። እንዲህ በማለት፦ “በዘመን መንገድ ታሪክ ላይ ስንት ጊዜ ተፈትነናል ክፉና ደጉን ዓመታት አብረን ሆነን

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

አሳልፈናል ክፉ ሐሳብ በሰዎች እየገባ መሆን የሌለበትም ሆነ እኛ ግን ላመንንበት ቆመናል ልባችን እንደደነደነ… የኔ ሐሳብ ብቻ ይበልጣል ከሚለው እኔን ብቻ ስሙኝ ብሎ ከሚጮኸው ሀብትና ገንዘብ ብቻ ከሚመኘው የጋራ ታሪካችንን ከሚያጠፋው ሀሳባችንአይገጥምምየእኛከቶ ይሂድልን ይራቀን ይጥፋ ከቶ ለሁሉም የሆነች ምድር ከሌለን እኛ ታዲያ ምን እንሠራለን?” ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ ነው ሲሉ ባለሙያዎች መግባቢያነቱ ለሁሉም የሰው ዘሮች ስሜት ሰጭ ስለሆነ፣ የሚያነሳቸው ሐሳቦች በሁሉም የሰው ልጆች ያሉ ስለሆኑ ነው። ሠላምን፣ ፍቅርን፣ ፍትሕን፣ እውነትንና ውበትን በሁሉም የሰው ዘሮች የምናገኛቸው እሴቶች ናቸው። እንደ ሬጌ ያሉ የሙዚቃ ስልቶች ደግሞ በጎነትን፣ ሠላምን፣ እውነትንና ፍትሕን በተለይ ከተገፉ ሰዎች አንፃር በማቀንቀን ይታወቃል። ሳሚ-ዳን በዚህ አልበሙ እነዚህን እሴቶች ከፍ አድርጎ በማጉላት የሬጌ ስልትን በላቀ ደረጃ ከተጫወቱ የአገራችን ባለሙያዎች እንዲመደብ ሆኗል።

መደምደሚያ ሳሚ-ዳን የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከተለመደው የዜማና የግጥም ስልት እልፍ እንዲል ካስቻሉ የሙዚቃ ሰዎች የሚመደብ የዘመናችን አቀንቃኝ ነው። ሬጌን እንደ አንድ ስልት በአልበም ደረጃ ይዞ ሲመጣና ሸቀጥ ከሆነው የዘመናችን የግጥም ይዘት ተላቆ ከፍ ያሉና ስለ ሰው ልጆች ዕኩልነት፣ ሠላም፣ ፍትሕና ፍቅር የሚተርኩ ግጥሞችን በውብ ዜማና ድምፀ ሲያቀነቅን ትልቅ አድናቆት ሊቸረው ይገባል። የአገራችን የሙዚቃ አድማጭ የ‹ሮማንስ› ዘፈኖችን ብቻ የሚያፈቅር ለሚመስላቸውና ትልቅ ሐሳብ ያለበት ሙዚቃ ለመሥራት ለሚጨንቃቸው ሙዚቀኞች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ይመስለኛል። የሙዚቃ ቪዲዮ የተሠራላቸው ሥራዎቹን ለተመለከተ ሳሚ-ዳን ለጥራት ምን ያህል እንደሚጨነቅ በቀላሉ መረዳት ይችላል። መድረክ ላይ ሲጫወት የመታደም ዕድሉ ለገጠመው ደግሞ የድምፃዊውን ልዩ ችሎታ ሳያደንቅ አያልፍም። የ2008 የለዛ የአድማጮች ሽልማት ላይ በአራት ዘርፍ ማለትም የዓመቱ ምርጥ አልበም፣ የዓመቱ ምርጥ አርቲስት፣ የዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ (‹ወደ ላይ› እና ‹ጠፋ የሚለየን›) እንዲሁም የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ ላይ ዕጩ የሆነው ሳሚ-ዳን አልበሙ በወጣ ባጭር ጊዜ ውስጥ ሽልማቶችን ሊወስድ እንደሚችል ይጠበቃል። ሳሚ-ዳን ሽልማቶቹን ቢወስድ ቢያንስበት እንጅ አይበዛበትም። መብራቱ በላቸውን በኢሜይል አድራሻው [email protected] ሊያገኙት ይችላሉ።

ውይይት ነሐሴ 2008

25

ትኩሳት

የቋንቋ ፋይዳ በሥራና በትምህርት የፌዴራሉ ክልሎች እና በየክልሉ ያሉ ዞኖች… በራሳቸው ቋንቋ የመማር፣ የመሥራት፣ የመዳኘት እና ሌሎችንም መሠረታዊ አገልግሎቶች የማግኘታቸው ጉዳይ አስፈላጊነት ትልቅ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ሲሳይ መንግሥቴ እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች የሚግባቡባቸው የጋራ የሥራ ቋንቋ መኖር ወሳኝነትንም አብረው ተመልክተዋል። የራያን ሕዝብ እና ሌሎችንም እንደማሳያ በማንሳት በቋንቋ ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን በዛሬው መጣጥፋቸው ያስነብቡናል።

አሁን ላይ በአገራችን ያለው የቋንቋ አጠቃቀም በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑ ይታወቃል፤ በአንድ በኩል በርካቶች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መተዳደር፣ መዳኘትና መማር ባለመቻላቸው በየዕለቱ አስከፊ ችግር ሲገጥማቸው በሌላ በኩል በተወሰኑ ክልሎች የፌዴራሉን ቋንቋ እንኳ መስማትና መናገር የማይችሉ ዜጎች ሆነው እየተፈጠሩ በመሆናቸው በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በብቃት እንዳይሳተፉ እያደረጋቸው ይገኛል። በዚህ ዙሪያ ያለውን ሁኔታ በዝርዝር ከመዳሰሴ በፊት በአገራችን ሥነ ጽሑፍም ሆነ ሥነ ልሳን ትልቅ ቦታ የነበራቸው ልኂቃን ስለቋንቋ ጠቀሜታ ምን ብለው እንደ ነበር አንድ ሁለት ጥቅሶችን በማስቀመጥ መሠረታዊ መልዕክታቸውን በአግባብ እንድንገነዘብ ካደረግሁ በኋላ ወደ ዝርዝር ሐሳቤ እገባለሁ። “ትሰሙኝ እንደኾን ልንገራችሁ እኔ፣ አለቋንቋ ትምህርት ሥልጣኔ፣ ስይጣኔ።” (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ) “ቋንቋን ቢናገሩት ለማይሰማ ጆሮ፣ እንዳልተናገረ ይመስላል ተናግሮ።” (ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ) በአጠቃላይም ውብሸት ሙላት ‹በአንቀጽ 39› መጽሐፉ ላይ ከላይ በሁለት ስንኞች የተቀመጠውን የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን አባባል በተን በማድረግ በማይረዱት ቋንቋ ማውራት እንዲሁ ከሚሰማ ድምፅ በስተቀር መልዕክቱን ሊረዱት እንደማይችሉት ዓይነት ጩኸት ማውጣት ብቻ መሆን እንደሚችል መሣሪያ ከመሆን አያልፍም በማለት በማያውቁት ቋንቋ የመናገርም ሆነ የመማር ውጤቱ የገደል ማሚቶ ድምፅ ሲያስተጋባ የመስማት ያህል ትርጉም የለሽ ከመሆን አይዘልም ሲል ይደመድማል። በአሁኑ ወቅት በተወሰኑ የአገራችን አካባቢዎች ከቋንቋ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ እየተፈፀመ ያለው ሁኔታም ከላይ በጥቅሉ የተቀመጠውን አባባል ይበልጥ ያረጋግጣል። ስለሆነም ቀጥሎ በሚኖሩት ሁለት ንዑስ ክፍሎች ከቋንቋ አጠቃቀም ጋር ተያይዘው መታየት ያለባቸውን ሐሳቦች በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ። በመጀመሪያ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርና መጠቀም አለመቻል ሊያስከትል የሚችለውን ችግር በምሳሌ አስደግፌ የማሳይ ሲሆን በሁለተኛው ንዑስ ክፍል ደግሞ እንደ አገር ሲታይ በአንድ ቋንቋ ላይ የመወሰናችን አንድምታ በራሱ ችግር ያለበት

26 ውይይት ነሐሴ 2008

መሆኑን ከመጠቀም አልፌ መፍትሔ ይሆናል ያልሁትን አማራጭ ሐሳብም ሰንዝሬበታለሁ።

ማኅበራዊ ቀውስ ስለ ቋንቋ መሠረታዊ ጥቅምና በአፍ መፍቻ ቋንቋ አለመጠቀም ደግሞ ሊያስከትለው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በተመለከተ የቋንቋ ምሁራን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ሊተነትኑት የሚችሉትን ያህል የጠለቀ ዕውቀትና ክኅሎት ባይኖረኝም ከሕግና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ጋር ባለኝ ቅርበት እና ከራሴ የሕይወት ልምድና ተሞክሮ እንዲሁም በተግባር እያየሁት ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ስመዝነው ግን ማንኛውም ሰው እንደሚገምተው ቋንቋ ለመግባቢያነት ብቻ ሳይሆን የሚያገለግለው የማንነት መለያ፣ የባሕል ማበልፀጊያ፣ የፍትሕና የአሰተዳደር ሥራዎች ቀጥተኛ መተግበሪያ፣ የማኅበረሰቡ ባሕላዊ እሴቶችና ሃይማኖታዊ ትውፊቶች ማስተላለፊያ፣ የአንድ ዓይነት ሥነ ልቦና ማሳደጊያ፣ የታሪካዊ ሁነቶችና ክስተቶች ዘግቦ ማቆያ፣ የዕውቀት መግቢያ፣ የክኅሎት መቅሰሚያ እና የቴክኖሎጂ ማሸጋገሪያ፣ ማፍለቂያ ብሎም መተግበሪያ ወዘተ. የሆነ ወሳኝ መሣሪያም ጭምር መሆኑን የቋንቋ ምሁራን እንደሚያረጋግጡ እገነዘባለሁ። በመሆኑም ለአንድ ማኅበረሰብ በአጠቃላይና ለሕፃናት ልጆቹ በተለይ በራሱ ቋንቋ መዳኘት፣ መተዳደር፣ መግባባትና መማር አለመቻል ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱትንም ሆኑ ሌሎች እዚህ ላይ ያልተጠቀሱትን በርካታ ቁሳዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቅሞችን ያጣ እና የበይ ተመልካች የሚሆንበት አጋጣሚ ይፈጠራል። የራያ ሕዝብን ጨምሮ በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች እየታየ ያለው ወቅታዊ ክስተትም ይህን እውነታ ይበልጥ የሚያረጋግጥ እንደሆነ ይታመናል። ምክንያቱም ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ አግኝቶ ሥራ ላይ የዋለው የፌዴራል ስርዓት በዋናነት በቋንቋ ላይ ተመሥርቶ የተደራጀ እንደሆነ ቢነገርም በሽግግር ወቅት በተሠራ የአከላል ስህተት ሳቢያ በርካታ ብሔርብሔረሰብ ሕዝቦች በቋንቋም ይሁን በባሕል ያን ያህል ወደ ማይመሳሰላቸው ክልል ተካተው በመገኘታቸው ሳቢያ ቋንቋቸው ሊያስገኝላቸው ይችል የነበረውን ቁሳዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቅም ሁሉ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። ከዛም አልፎ

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ትኩሳት በውሰት መልክ እንዲጠቀሙበት በቀረበላቸው ቋንቋና ባሕል እንዲተዳደሩ፣ እንዲዳኙ፣ እንዲግባቡና እንዲማሩ ስለሚገደዱም አሉታዊ ተፅዕኖው እጅግ የከፋ እየሆነ ይመጣል። አንድ ሕዝብ የኔ ነው በሚለው ቋንቋ መዳኘትና መጠቀም ካልቻለና ባሕልና ወጉንም በአግባቡ መግለጽ እንዲሁም ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ የማይችል ከሆነ ደግሞ ማንም ሰው በቀላሉ ሊገነዘበው እንደሚችለው ሁሉ የሞራል ውድቀት ሊያጋጥመው የሚችል ከመሆኑም በላይ የዕለት ከዕለት ማኅበራዊ ግንኙነቱ በሚፈጥረው አለመግባባት ላይ ተመሥርቶ ቢከስ ወይም ቢከሰስ በበቂ ሁኔታ ክሱን ለፍርድ ቤት ማስረዳትም ሆነ በብቃት መከላከል ይሳነውና ለተዛባ ዳኝነት ስለሚዳረግ አላስፈላጊ ጉዳት ይደርስበታል። ከዛም አልፎ በራሱ ቋንቋ ባለመማሩና ባለመጠቀሙ ምክንያት ስለ አካባቢው፣ ስለክልሉ፣ ለአገሩም ሆነ ስለዓለም የሚኖረው መረዳት ያንኑ ያህል የተወሰነ ይሆናል። እንዲሁም በቂ ሊባል የሚችል ዕውቀትና ክኅሎት ሳይጨብጥ ይቀርና በሕይወቱ ውስጥ የሆነ ጉድለት አስከትሎ ኑሮውን ለመምራት እስኪሳነው ድረስ ቀውስ ውስጥ ሊገባ ይችላል። በዚህም የተነሳ ትምህርት የሁሉም ዜጋ መብት መሆኑ ቀርቶ የጥቂት ምርጥ የስርዓቱ ተጠቃሚዎች ብቻ ሆኖ ይቀራል። ዳኝነትና አስተዳደራዊ ፍትሕ ብቸኛ የሥራ ቋንቋ በሆነው ብሔር ልክ ተስፍቶ የሚሰጥበት አጋጣሚ ስለሚኖርም ማኅበራዊ ፍትሕ በእጅጉ ይዛባል፤ አስተዳደራዊ በደልም ያንኑ ያህል ይነግሣል። በመሆኑም የክልሉን የሥራ ቋንቋ መናገር የማይችለው የአካባቢው ነዋሪ ሕዝብ ሐኪም ቤት ሄዶ ለመታከም አንኳ አንድም በሸታውን ለሐኪሙ በብቃት ለማሳወቅ የራሱን ቋንቋ ተጠቅሞ የማስረዳት ዕድል ስለሚነፈገው ሁለትም በበቂ ሁኔታ የሚያስተረጉም ሰው ስለማያገኝ ተገቢውን ሕክምና ሳያገኝ የሚቀርበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ከዚህም በተጨማሪ ባሕልና ወጉን በአግባቡ ማክበር ባለመቻሉም ትክክለኛ ማንነቱንና የወጣበትን ማኅበረሰብ መሠረታዊ እሴትና ትውፊት እየረሳ የማንነት ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል። ከዛም አልፎ በራስ የመተማመን ስሜቱን አሳድጎ እምቅ ችሎታውንም ሆነ ክኅሎቱን በአግባቡ እንዳይጠቀም ምክንያት ይሆናል። የዚህ ዓይነት ሁኔታ በቀጣይነት ተጠናክሮ ሲተገበር ደግሞ ክልላዊና አገራዊ ተሳትፎውን በብቃት የሚያሳድግበት አቅም እያነሰው ስለሚመጣ ለአካባቢው ብሎም ለአገሩ ሊያበረክት የሚችለውን ሁለንተናዊ አሰተዋፅዖ በዛው ልክ ያቀጭጨዋል። የሚስተዋለው ችግር ግን ይህ ብቻ አይደለም፤ በተውሶ ቋንቋ፣ ባሕልና አሠራር እየኖረ መሆኑን ሲገነዘብና አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ጫናው እየበዛበት ሲመጣ ራሱን የመሆን ፍላጎቱ ይበልጥ ጎልቶ ስለሚወጣ አብሮት ከሚኖረው የገዥው ብሔር አባላት ጋር ተስማምቶና ተባብሮ የመኖር ፍላጎቱ በሒደት እየቀነሰና እየደበዘዘ ይሔዳል ብቻ ሳይሆን

በተቃራኒው መጥፎ ስሜት እያሳደገ ይመጣል። የችግሩ መጠን ሰፋ እያለ ሲሔድ ደግሞ በራስ የመተማመን ስሜቱ በእጅጉ ይሸረሽራል። በራሱ ባሕልና ወግ መልካም ተደርጎ ይወሰድ የነበረው ነገር ሁሉ በሌላኛው ዓይን ኋላቀር ተደርጎ ስለሚታይበት ከሌላኛው ብሔር አባላት ጋር በቀላሉ ተግባብቶ ከመኖር ይልቅ የጎሪጥ የሚተያይበት ዕድል እየሰፋ ይሔዳል። በዚህም ምክንያት በትውልድ አካባቢው እየኖረና በአገሩ ላይ እየተንቀሳቀሰ ራሱን እንደ ባዕድ የሚቆጥርበትና በክልሉ በሚካሄድ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባሕላዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ዕኩል መብት ኖሮት ከውጤቱም በዕኩልነት ተጠቃሚ እሆናለሁ ለማለት የሚቸገርበት አጋጣሚ ይፈጠራል። አንዳንድ ጊዜም በሒደት የሚያሳድገው የበታችነት ስሜት እየተጠናከረ ይመጣና የእነሱን ቋንቋና ባሕል በእኔ ላይ በግዳጅ እየጫኑብኝ ነው በሚላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ አላስፈላጊ የሆነ የጥላቻ ስሜት አርግዞ ከእነሱ ጋር በሒደት

የክልሉ የሥራ ቋንቋ ትግርኛ ብቻ በመሆኑ በክልሉ ውስጥ የሚገኙት የቴክኒክና ሞያ ኮሌጆችም ሆኑ የጤና፣ የትምህርትና የግብርና ኮሌጆች ተማሪዎችን ለመቀበል በብሔራዊ ፈተና በትግርኛ ቋንቋ ቢያንስ እንደ ሁኔታው ‹C› ወይም ‹B› ያመጣ ይባልና አብዛኛዎቹ የራያ ልጆች ‹F› እና ‹D› ያቸውን ስለሚታቀፉ ከጫወታ ውጭ ይሆናሉ

እየተግባባና እየተዋኸደ ከመሔድ ይልቅ ሰበብ አስባብ እየፈጠረ በመካከላቸው አለመግባባት እንዲኖር ምክንያት ሊሆን ይችላል። የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ ለዘላቂ ሠላም መታጣት፣ ለአላስፈላጊ ውጥረት መንገሥና ከዛም አልፎ ለግጭት መከሰት በር ይከፍታል። በአሁኑ ወቅት በአገራችን በአጠቃላይ እና በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አማካኝነት በራያና በወልቃይት ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው አስተዳደራዊ ሁኔታም ከላይ በጥቅሉ የተገለጸውን ሳይንሳዊ ሐቅ ፍንትው አድርጎ ሊያሳይ እንደሚችል ይታመናል። ለምሳሌ አብዛኛው የራያ ሕዝብ ለትግራይ ክልል የሥራ ቋንቋና ለትግራይ ብሔር ባሕል እንግዳ ነው። ከዛም አልፎ የራሱ የሆነ ባሕልና ቋንቋ አለው። ሆኖም ያለ ውዴታውና ፍላጎቱ ወደ ትግራይ ክልል እንዲካተት በመደረጉ ሳቢያ በትግርኛ ቋንቋ እንዲዳኝ፣ እንዲተዳደርና የትግራይን ባሕል እንዲላመድ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ጫና (acculturation and forced assimilation) እየተደረገበት ይገኛል። በዚህም ምክንያት ልጆቹ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዳይማሩና ከዛ ይገኝ የነበረውን መሠረታዊ ጥቅም እንዳያገኙ በመደረግ ላይ ይገኛል። ስለሆነም የራያ ልጆች ምንም ያህል በትምህርታቸው ጎበዝ ቢሆኑ በትግራይ ልማት ማኅበር በተገነባውና ቃልአሚኖ እየተባለ በሚጠራው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቶ የመማር ዕድላቸው ጠባብ ነው። እንዲሁም የብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ወስደው ዩኒቨርስቲ የሚያስገባ ውጤት ካላመጡ በስተቀር ቀጣይ የትምህርትም ሆነ ሥራ የማግኘት ዕድላቸው በእጅጉ የጨለመ ይሆንባቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው፤ ከላይ እንተገለጸው የክልሉ የሥራ ቋንቋ ትግርኛ ብቻ በመሆኑ በክልሉ ውስጥ የሚገኙት የቴክኒክና ሞያ ኮሌጆችም ሆኑ የጤና፣ የትምህርትና የግብርና ኮሌጆች ተማሪዎችን ለመቀበል በብሔራዊ ፈተና በትግርኛ ቋንቋ ቢያንስ እንደ ሁኔታው ‹C› ወይም ‹B› ያመጣ ይባልና አብዛኛዎቹ የራያ ልጆች ‹F› እና ‹D› ያቸውን ስለሚታቀፉ ከጫወታ ውጭ ይሆናሉ። በዚህም ሳቢያ የራያ ልጆች በክልሉ ውስጥ ሥራ የማግኘት ዕድላቸው የጠበበ ብቻ ሳይሆን ጭራሹኑም ዝግ የሚሆንበት አጋጣሚ ይፈጠራል። በዛ ላይ የሥራ ኃላፊዎቹ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አያያዝ ሲጨመርበት አብዛኛዎቹ የአካባቢው ታዳጊ ወጣቶች በሁኔታው ተስፋ ይቆርጡና በእግራቸው ጭምር ወደ ዐረብ አገር ይሰደዳሉ። የተወሰኑት ደግሞ እንደ ቅርበታቸውና ቤተሰባዊ ትስስራቸው ወደ አማራ ክልል ሰሜን ወሎ አስተዳደር ዞንና ዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሔደው የሥራ ዕድል ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። ከፊሎቹ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሥራ ፍለጋ ሲንከራተቱ ይታያሉ። ለዚህም ይመስላል በአንድ ወቅት የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የኮረም ከተማና በዙሪያው የሚገኘውን ሕዝብ ሰብስበው ‹ያለባችሁ ችግር ምን እንደሆነ እስኪ ሐሳባችሁን በግልጽ ወደሚቀጥለው ገጽ

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ውይይት ነሐሴ 2008

27

ትኩሳት አካፍሉንና እንነጋገርበት› በማለት ሲጠይቋቸው በሳልና ነገር አዋቂ የሆኑት የዕድሜ ባለፀጎች ተነስተው ‹አይ ክቡርነትዎ ምንም ችግር የለብንም፤ ልጆቻችንም ቢሆኑ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ጎረቤታችን ወደሆነው አማራ ክልል በተለይ ደግሞ ዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እየሔዱ ሥራ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ› በማለት እየገጠማቸው ያለውን ወቅታዊ ችግር በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋሪ መንገድ በመግለጽ ጭምር እንደ መለሱላቸው የሚነገረው። ስለሆነም በአፍ መፍቻ ቋንቋ አለመማርና አለመጠቀም የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለምና በአግባቡ ለታሰብበት ይገባል።

የፌዴራል የሥራ ቋንቋ በአንድ ብቻ የመወሰኑ አንድምታ ከፍ ብሎ በተቀመጠው ንዑስ ክፍል በሥራም ሆነ በትምህርት ሒደት ውስጥ በአፍ መፍቻ ቋንቋ አለመጠቀም ሊያስከትል የሚችለውን ቁሳዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ችግር ለማስገንዘብ በሞከርሁበት ጽሑፍ ላይ በራያ ሕዝብ በአጠቃላይና በበርካታ የራያ ተወላጅ ወጣቶች ላይ በተለይ እየደረሰ ያለውን አስከፊ ሁኔታ በምሳሌ አስደግፌ ለማቅረብ ከመሞከሬም በላይ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያካሔዱ ምሁራን በማስረጃ አስደግፈው እንዳቀረቡት በ2002 ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱት ከ1200 በላይ ተማሪዎች ውስጥ 41% የሚሆኑት ‹F› ሲያገኙ ሌሎቹን የትምህርት ዓይነቶች በሙሉ ‹A› ያስመዘገበው እጅግ በጣም ጎበዝ የሆነው ተማሪ እንኳ የትግርኛ ቋንቋን ‹C› ብቻ ማምጣት እንደቻለ ተረጋግጧል። በዚህ ንዑስ ክፍል ደግሞ ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ባሻገር መመልከትስ የለብንም ወይ የሚል አንድምታ ያለው ሐሳብ ላንሳና በሰከነና በሠለጠነ አኳኋን እንድንወያይበት ልጋብዝ። በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀፅ አንድ መሠረት በአገሪቱ የሚገኙት ሁሉም ቋንቋዎች ዕኩል ዕውቅና እንዲያገኙ ቢደረግም የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን የሕገ መንግሥት አርቃቂዎችና አፅዳቂዎች (Framers (Fathers) of the Constitution) በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ላይ መወሰናቸው ይታወቃል። ከዛም አለፍ ብለው ክልሎች የራሳቸውን የሥራ ቋንቋ እንዲወስኑ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ይህም በዛን ወቅት ለነበረው ማኅበረ-ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ አስፈላጊም ጠቃሚም እንደነበረ መገመት ይቻል ይሆናል። ነገር ግን የማኅበረሰቡ ንቃተ-ኅሊና ከፍ እያለ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ መስተጋብሩ እየጠነከረና የመሠረተ ልማት አውታሮች አቅርቦት እየተሻሻለ በተለይም የመገናኛ ቴክኖሎጂ ይበልጥ እየዘመነ ከመሔዱ ጋር ተያይዞ ከመደበኛዎቹ የመገናኛ ብዙኃን (ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣና መጽሔት) በተጨማሪ የማኅበራዊ ሚዲያው በእጅጉ

28 ውይይት ነሐሴ 2008

እንደዛም ሆኖ ወላጆችና ሕፃናቱ ብቻ ሳይሆኑ የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎቹ ሳይቀሩ ‹አማርኛ በኃይል የተጫነብን የነፍጠኞች/የገዥዎች ቋንቋ ነው› በማለት ባልተገባ መልኩ በማጥላላት ስለሚቀሰቅሱ የጥላቻ ስሜት እንዲያሳድሩ የሚደረግበት አጋጣሚ ሰፊ ስለሆነና ትምህርቱም በአብዛኛው ብቃት ባላቸውና በአግባቡ በሠለጠኑ መምህራን አማካኝነት እንዲሰጥ ስለማይደረግ ተገቢ ትኩረት ሲሰጠው አይስተዋልም እየተስፋፋ በሔደ ቁጥር ሕዝቦች በአንድ አካባቢ ተወስነው የመኖራቸው ሁኔታ እየቀነሰ በተቃራኒው ደግሞ የግንኙነት አድማሳቸውም በእጅጉ እየሰፋ መሄዱ አይቀርምና ተጨማሪ የመግባቢያ ቋንቋ እንዲኖራቸው መሻታቸው እንደ የውዴታ ግዴታ እየሆነ ይመጣል። በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዓለምዐቀፍ ደረጀም የሚኖራቸውን ተሳትፎና ማኅበራዊ መስተጋብር ይበልጥ በማሳደግ ምጣኔ-ሀብታዊ ተጠቃሚነታቸውንም ማስፋት ይፈልጋሉ። ለዚህም ነው የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ሲወሰን፣ የቋንቋ አጠቃቀምን አስመልክቶ የትምህርት ፖሊሲ ሲረቀቅም ሆነ ስርዓተ ትምህርት ሲዘጋጅ የሚመለከታቸው አካላት ከላይ በጥቅሉ የተቀቀመጡትን ሁኔታዎች ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል የሚባለው። ለመሆኑ ‹የእኛ አገር የሥራና የትምህርት ቋንቋ አወሳሰን ምን ይመስላል?› የሚለውን መሠረተ ሐሳብ የወቅቱን ፖለቲከኞች ጨምሮ ለቋንቋና ሥነ ልሳን ምሁራን ልተወውና እዚህ ላይ የተወሰኑ ነጥቦችን ብቻ በማንሳት የውይይት አጀንዳ ለመክፈት ወደድሁ። ለምሳሌ ከላይ እንተገለጸው የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን በሕገ መንግሥት ቢወሰንም የብሔራዊ ቋንቋነትን ደረጃ ስላላገኘ የራሳቸውን ቋንቋ ለመጠቀም በወሰኑ ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ አማርኛን እንደ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ አድርገው እንዲገለገሉበትም ሆነ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ቆጥረው ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንዲያስተምሩበት አይገደዱም። ሌላው ቀርቶ የባዕድ ቋንቋ የሆነው እንግሊዘኛ በሁሉም ክልሎች ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ (ምናልባትም ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ) እንዲሰጥ ሲደረግ የእኛው አገር በቀሉና የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ በመሆን የሚያገለግለው አማርኛ

ግን እንደየክልሎቹ ለጋስነት ከ4ኛ ወይም ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲሰጥ ይደረጋል። እንደዛም ሆኖ ወላጆችና ሕፃናቱ ብቻ ሳይሆኑ የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎቹ ሳይቀሩ ‹አማርኛ በኃይል የተጫነብን የነፍጠኞች/የገዥዎች ቋንቋ ነው› በማለት ባልተገባ መልኩ በማጥላላት ስለሚቀሰቅሱ የጥላቻ ስሜት እንዲያሳድሩ የሚደረግበት አጋጣሚ ሰፊ ስለሆነና ትምህርቱም በአብዛኛው ብቃት ባላቸውና በአግባቡ በሠለጠኑ መምህራን አማካኝነት እንዲሰጥ ስለማይደረግ ተገቢ ትኩረት ሲሰጠው አይስተዋልም። በዚህም ምክንያት ተማሪዎቹ የብሔራዊ ፈተናዎችን እንደምንም አልፈው ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ወይ የእንግሊዘኛውን ቋንቋ በአግባቡ አይረዱ አሊያም የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ በሆነው በአማርኛ መግባባት አይሆንላቸው እንዲሁ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ግራ ሲያጋቡ ይታያሉ። ይህንን ክፍተት በአሉታዊ መልኩ አስፋፍተው ለመጠቀም የሚሹ አንዳንድ የቀድሞ ስርዓተ ትምህርት ናፋቂዎች ደግሞ ይህ ችግር የአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ውጤት እንደሆነ አድርገው በመመልከት በጅምላ ሲያንቋሽሹና የተማሪዎቹንም ችሎታ ሲያናንቁ ይስተዋላሉ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የሁለቱም ስርዓተ ትምህርት ውጤት የሆኑትን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በ1997 እና በ1998 አስተምሬያቸው ስለነበር፣ ክፍተቱ የት ላይ እንደሆነ በሚገባ ለመገንዘብ ችዬ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ በቀድሞው ስርዓተ ትምህርት የተማሩት ልጆች ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድል የሚገጥማቸው 3.20 እና ከዛ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት በጣም ጎበዝ ተማሪዎች ሲሆኑ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ያለፉት ግን 2.00 እና ከዛ በላይ ያገኙት በሙሉ

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ትኩሳት ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድል በማግኘታቸው የትምህርት አቀባበል ደረጃቸው በዛው ልክ የተለያየ መሆኑ አይቀርም። ልብ በሉ ልዩነቱ የመጣው ቀደም ሲል በነበረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስንነት ሳቢያ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት እጅግ በጣም ጎበዝ የሆኑት ብቻ ሲሆኑ በአሁኑ ስርዓተ ትምህርት ግን ዩኒቨርሲቲዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ መካከለኛ ተማሪዎችን ጨምሮ ዝቅተኛውን ውጤት ያስመዘገቡት ደካማዎቹ ተማሪዎች ሳይቀሩ ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድሉ ደርሷቸዋል። ከዛ ውጭ አስተማሪዎቹም ሆኑ ትምህርት ቤቶቹ በመሠረቱ እስካልተቀየሩ ድረስ ያን ያህል ልዩነት ባልመጣም ነበር። በእርግጥ የተማሪዎቹ ጥረትና የመምህራን በቀናነት መንፈስ ትምህርቱን በአግባቡ መስጠት/ አለመስጠት የራሱን አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ እገነዘባለሁ። ይህም ሆኖ የቋንቋ ለውጥን ጨምሮ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ በተደረገበት ወቅት ተገቢ ዝግጅት ተደርጎ ተገብቶበታል የሚል እምነት የለኝም። ከዛም ባሻገር የመምህራንን አመለካከት በሥልጠናና ተጨማሪ ትምህርት ከማስተካከል ጀምሮ አስፈላጊውን የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን በተሟላ አኳኋን በማቅረብ ረገድ ውስንነት እንደነበረበት የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ስለሆነም ባልተሟላ ሁኔታ በዋነኛነት እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ በራሳቸው ቋንቋ ብቻ ተምረው የሚመጡት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ በኋላ እንኳ ሥራ

ፍለጋ የሚሔዱት ወደ መጡበት ክልል መሆኑ ሲታይ ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ እንዲሆን ያደርገዋል። በመሆኑም ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ እስካሁን እየታዩ ያሉትን መሠረታዊ ችግሮች በተለይም ከቋንቋ አጠቃቀም ጋር የሚያያዙትን መሠረታዊ ክፍተቶች በዘላቂነት ለመቅረፍ ከተፈለገ ቀጥሎ የቀረቡትን አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን ግምት ውስጥ አስገብተን ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት ብናደርግ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ። ሀ). አማርኛ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንደመሆኑ መጠን የራሳቸውን ቋንቋ በሥራና በትምህርት ቋንቋነት ለመጠቀም የወሰኑ ክልሎችና ዞኖች የአማርኛ ቋንቋን እንደሁለተኛ የሥራም ሆነ የትምህርት ቋንቋ አድርገው እንዲጠቀሙበት የሚያደርግ በስምምነት ላይ የተመሠረተ አስገዳጅ አሠራር ተግባራዊ ቢደረግ እነሱንም በፌዴራል መንግሥት ደረጃ የሚኖራቸውን ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተሳትፎ በእጅጉ ያሳድገዋል። የባሕልና የዕውቀት ሽሽግሩንም ይበልጥ አፋጥኖ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ያደርገዋል። ለ). አማርኛን በሥራ ቋንቋነት ለመጠቀም የወሰኑት ክልሎች ደግሞ አንድ ተጨማሪ ቋንቋ በመምረጥ በሥራም ሆነ በትምህርት ማስተማሪያ ቋንቋነት እንዲገለገሉበት ቢደረግ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ይመስለኛል። ለምሳሌ የአማራ ብሔራዊ ክልል የኦሮምኛ

የፌዴራሉ መንግሥት ከአማርኛ በተጨማሪ የኦሮምኛ ቋንቋን እንደሁለተኛ የሥራ ቋንቋ አድርጎ ቢጠቀምበትና አማርኛና የኦሮምኛ ቋንቋዎች ከሥራ ቋንቋነትም በላይ የብሔራዊ ቋንቋነት ደረጃ እንዲኖራቸው በማድረግ ሥራ ላይ ቢያውል አንድም የአብዛኛውን የኦሮሞ ሕዝብ ወቅታዊ ጥያቄ በመመለስ ሥነ ልቦናዊ ቅቡልነትን ያስገኛል፣ ከሁሉም በላይ ግን፣ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ይበልጥ ያጠናክራል

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ቋንቋን ቢያንስ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት አድርጎ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጥ ቢያደርግ አንድም በተሻለ ሁኔታ የኦሮሞን ሕዝብ ማንነት፣ ቱባ ባሕል፣ ትክክለኛ እምነትና እውነተኛ ታሪክ ይበልጥ ለማወቅና በአግባቡም ለመገንዘብ ይረዳል። ወዲህም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ በቅርቡ የኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች የዘር ምንጭ አንድ ነው በሚል ርዕስ አሳትመው ገበያ ላይ ባዋሉት መጽሐፋቸው አበክረው ለማስገንዘብ ጥረት እንደሚያደርጉት ሁሉ በሁለቱ ታላላቅ ሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትንና አብሮነትን ከማጠናከሩም በላይ የአማራ ክልል ተወላጅ ምሩቃን ወደ ኦሮሚያ አካባቢ በመሔድ ለመሥራት የሚያስችል ዕድል እንዲፈጠርላቸው ያደርጋል። በዛ ላይ በክልሉ ውስጥ በሚገኘው የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚጠቀምበትን የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት ወደ ሌሎች ዞኖችና ወረዳዎች በማስፋት መስጠት የሚችል በመሆኑ እንደ ተጨማሪ ሸክም ተደርጎ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ አይመስለኝም። የአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲም ቢሆን የዚህ አይነቱን መልካም ሐሳብና አማራጭ የትምህርት አሰጣጥ በእጅጉ የሚደግፍና የሚያበረታታ እንጂ የሚከለክል አለመሆኑ ግምት ውስጥ ገብቶ በአፋጣኝ ሥራ ላይ ቢውል ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል። ሐ). በመጨረሻም የፌዴራሉ መንግሥት ከአማርኛ በተጨማሪ የኦሮምኛ ቋንቋን እንደሁለተኛ የሥራ ቋንቋ አድርጎ ቢጠቀምበትና አማርኛና የኦሮምኛ ቋንቋዎች ከሥራ ቋንቋነትም በላይ የብሔራዊ ቋንቋነት ደረጃ እንዲኖራቸው በማድረግ ሥራ ላይ ቢያውል አንድም የአብዛኛውን የኦሮሞ ሕዝብ ወቅታዊ ጥያቄ በመመለስ ሥነ ልቦናዊ ቅቡልነትን ያስገኛል፣ ከሁሉም በላይ ግን፣ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ይበልጥ ያጠናክራል። በአጠቃላይም ከፍተኛ የሆነ ቁጥር ያለውን ማለትም ከአንድ ሦስተተኛ በላይ የአገሪቱን ሕዝብ ቁጥር የሚሸፍነውን የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ በአገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ዕኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ስለሚያደርግ ፍትሓዊነቱንም ይበልጥ ያረጋግጣልና በየደረጃው የሚገኙት ፖሊሲ አውጭዎችና ውሳኔ ሰጭዎች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ቢመክሩበትና በአዎንታዊ መልኩ ተመልክተው ሥራ ላይ እንዲውል ቢያደርጉት በአሁኑ ወቅት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን አብዛኛውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ ዕድል የሚያስገኝ ከመሆኑም ባሻገር በየጊዜው ከማንነትና ከቋንቋ አጠቃቀም ጋር ተያይዘው እዚህም እዚያም ለሚነሱ መሠረታዊ ጥያቄዎች በተወሰነ መልኩም ቢሆን ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይታመናል። አቶ ሲሳይ መንግሥቴ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ሌክቸረር እና የሰብኣዊ መብቶች ፒ.ኤች.ዲ. ካንዲዴት እንዲሁም የሕግ አማካሪ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ይገኛሉ።

ውይይት ነሐሴ 2008

29

ትኩሳት

የኢትዮጵያው አገዛዝ እና የሰብኣዊ መብቶች አከባበር ምን እና ምን?

ደረጀ መላኩ በዚህ ጽሑፉ የዓለምዐቀፉ ሰብኣዊ መብት ድንጋጌ/ መግለጫን በመመልከት እና ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማመሳከር በሕገ መንግሥታችን ሳይቀር የተቀመጡት መብቶች አለመከበራቸውን ጽፏል። በተጨማሪም፣ ላለመከበሩ መንስዔ ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አቅርቧል። አምባገነኖች በልማት ሥም ሰብኣዊ መብትን እንደሚጨፈልቁ ገልጾ፣ ልማት ግን ያለሰብኣዊ መብት መከበር እና ያለነጻነት ሊገኝ የማይችል እንደሆነ ይከራከራል።

መግቢያ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዓ የሰብኣዊ መብቶች ዓለምዐቀፍ መግለጫ (universal declaration of human rights) ለሁሉም ሕዝቦችና አገሮች የጋራ መመሪያ እንዲሆን አውጇል ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉም የዓለም አገራት (ከጥቂት በፍፁም አምባገነን ከሚገዙ አገራት በስተቀር) በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ አካተውታል። ገቢራዊነቱ ግን ‹ላም አለኝ በሰማይ› እየሆነ ይገኛል፤ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉት አገራት ውስጥ። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ሁሉ ቀዳማይ በመሆን (ምናልባት ግብጽ ትቀድመን ይሆናል) የሰብኣዊ መብቶች ዓለምዐቀፍ መግለጫ ሰነድ ላይ ብተፈርምም፤ አሁን ባለው አገዛዝ ሕገ መንግሥት ሰነድ ውስጥ ሁሉም በሚባል መልኩ የሰብኣዊ መብቶችን የሚያወሱ አንቀፆች ቢካተቱም በእውነቱ በኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብቶች አጠባባቅ ሁኔታ አሳፋሪ ነው። ሰብኣዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ከማክበር አኳያ ያልተሳካላቸው የፊውዳሉም ሆነ የወታደራዊው የኢትዮጵያ ቀደምት አገዛዞች ወደ ታሪክ ማሕደር ውስጥ ከተዶሉ በኋላ ኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብቶች የሚከበሩባት ምድር ልትሆን ትችላለች የሚል ተስፋ በብዙዎች ዘንድ ተጥሎ ነበር። ሆኖም ግን ተስፋው መና ሆኖ ቀርቷል።

የሰብኣዊ መብቶች ምንድን ናቸው? በመሠረቱ ሰብኣዊ መብቶች ነጻነቶች ናቸው። እነዚህን ነጻነቶች በአጠቃላይ በሁለት መመደብ ይቻላል። አንደኛ ማንኛውም ሰው ከባሕርዩ ጋር የሚስማማውንና ሌላውንም ሳይጎዳ ለማድረግ የሚፈልገውን ሁሉ እንዲያደርግ ሊኖሩት የሚገባው ነጻነቶች ናቸው። ማናቸውም ሰው የራሱንና የቤተሰቡን ሕይወትና የአካል

30 ውይይት ነሐሴ 2008

ደኅንነት ለመጠበቅ ነጻነት አለው፤ ራሱንና ቤተሰቡን ለመመገብና የተደላደለ ኑሮ እንዲያገኙ ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት ነጻነት አለው። ሁለተኛ ማንኛውም ሰው ከኅሊናው፣ ከእምነቱና ከሃይማኖቱ ውጭ በተለያዩ መንገዶች በማስፈራራትና በማስገደድ የሚሞከርበትን ጥቃት ሁሉ ለመከላከል ነጻነቶች አሉት። የሰው ልጅ ከፍርሓት ነጻ ካልሆነ ሰውነቱ ሙሉ አይሆንም። በአንዳንደ የኢትዮጵያ ትውፊታዊ ፍልስፍና የሰው ልጅ ሁለት ባሕርያት አሉት፤ አንደኛው ባሕርያተ ሥጋ ሲሆን፣ ሁለተኛው ባሕርያተ ነፍስ ነው። ባሕርያተ ስጋ የሰው ልጅ ከሌሎች እንስሳት ጋር የሚጋራቸውን ባሕርዮች የሚያመለክት ነው። እንደ ሌሎቹ እንሰሳት ሁሉ የመብላትና የመጠጣት፣ እራሱን ከአዳኞች የመጠበቅና ራሱንም የማራባት ፍላጎት አለው። ከእነዚህ ፍላጎቶችም የሚመነጩ ነጻነቶች አሉ። ሰርቶ ለማግኘት፣ ሀብት ለማከማቸት፣ ኑሮውን በፈለገው መንገድ ለመምራትና ልጆቹን ለማሳደግ የሚያስችሉት የተፈጥሮ መብቶች አሉት። እነዚህን መብቶች ሲያጣ ከእንሰሳም ደረጃ ይወርድና በዱላ እየተነረተች እንደምትገራ አህያ ወይም በእንሰሳት መካነ ጥናት ውስጥ ተዘግቶባቸው እንደሚኖሩ እንሰሶች ይሆናል። በባሕርያተ ነብሱ የሰው ልጅ ከሌሎች እንሰሳት ይለያል። ባሕርያተ ነብስ የሚባሉት ማሰብ፣ መናገር እና ኅያውነት ናቸው። ለሰው ልጅ ማሰብ የተፈጥሮ የሆነውን ያህል ሐሳብን መግለጽም የተፈጥሮ ነው። ይህንን የተፈጥሮ ችሎታ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በውራጅ ኸሳባቸው የሌሎችን ሐሳብ በማፈን ሕዝብን የሚያደነቁሩ ኋላቀር፣ ደሃና በችጋር የተጎዳ የሚያደርጉ ሁሉ፣ ከሰው ልጅ ባሕርያተ ነፍስ የሚመነጩትን መሠረታዊ መብቶች የሚረግጡ ናቸው። አንድ ሐሳብን በሰው ልጆች ላይ በግዴታ መጫን ከኋላቀርነትና ከደሃነት እንደማያወጣ ኢትዮጵያ ታላቅ ዩኒቨርስቲ

ናት። ታላቋ አሜሪካ፣ አውሮፓውያን ሌሎች የሠለጠኑ አገራት በምድር ሳይወሰኑ የኅዋ ምርምር እያካሔዱ የሚገኙት የዜጎቻቸውን የሐሳብ ነጻነት ስላከበሩ ነው። የሐሳብ ነጻነት ባለበት አገር ሁሉ የሐሳብ ገበያ አለ፤ የሐሳብ ገበያ ካለ ደግሞ ምርጥ-ምርጥ የሰው ልጅ የአእምሮ ጭማቂ የሆኑ ይገኛል። ምሥጢሩ ይሄው ነው። በሳንቲሙ ግልባጭ የኢትዮጵያ ገዢዎች በበኩላቸው ከእነርሱ የተለየ ሐሳብ ያላቸውን ኢትዮጵያውን ያስራሉ፤ ደብዛ ያጠፋሉ፤ ወይም አገር ጥለው እንዲሰደዱ ያስገድዳሉ። ሲያሻቸውም ያስገድላሉ። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ የምርጥ ልጆቿን አእምሮ ጭማቂ መጠቀም ያልቻለች አሳዛኝ አገር ሆናለች (ወይም) ናት ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም። ላለፉት አምሳ ዓመታት የነበረው የሰብኣዊ መብቶች አጠባበቅ ሪኮርዳችን መሻሻል የታየበት ቢመስልም ዛሬም በዓለም ላይ ከሚገኙት አገራት ሁሉ በመጨረሻዎቹ ረድፍ ላይ እንገኛለን። ሁላችንም እንደምንገነዘበው አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ መንግሥት በዓለምዐቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ሰነዶች ላይ የሚገኙትን አንቀፆች አካቶ የያዘ ነው (መሻሻል ታይቷል ያልኩት በሕገ መንግሥቱ የሰብኣዊ መብቶች ዕውቅና ስላላቸው ነው) ዛዲያ ለምን ይሆን ገቢራዊ ማድረግ የተሳነን በእኔ በኩል የሚከተሉትን ሦስት ምክንያቶች ለመተንተን እሞክራለሁ።

ሀ. ከአገዛዝ ስርዓት መውጣት ባለመቻላችን የአገዛዝን ስርዓት የሚመሩ ሰዎች አእምሮአቸውን ከስህተት ልባቸውን ከፍርሐት፣ ኅሊናቸውን ከክፋት ያፀዱ አይደሉም። ለዚህም ነው ስህተታቸው ስህተትን፣ ፍርሐታቸው ፍርሐትን፣ ክፋታቸውም ክፋትን እየወለደ ሰብኣዊ መብቶች ሊከበሩበት የማይችሉበት ሁኔታ የሚፈጠረው በስህተት ፋንታ የዕውቀት የበላይነት፣ በጥርጣሬና ፍርሐት ፋንታ ልበ ሙሉነት፣ በክፋት ፋንታ ቅንነት በሰፈነበት ሁኔታ ሰብኣዊ መብቶችን ለማስከበር አመቺ ይሆናል። በካናዳ የኩቤክ ሕዝብ እና በታላቋ ብሪታኒያ የስኮትላንድ ሕዝብ ሪፈረንደም ጥያቄ፣ በቅርቡ የታላቋ ብሪታኒያ ሕዝብ ፍላጎት በሠለጠነ መንገድ ተፈቷል። እኛ ግን ለዚህ ቁም ነገር አልበቃንምና ለምናቀርበው ጥያቄ ሁሉ ምላሹ እስር፣ ስደት አሊያም ጥይት ነው።

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ትኩሳት ለ. ሰብኣዊ መብቶችና ጎሰኛነት በመሠረቱ ጎሰኛነት ከዘረኛነት ጋር የተዛመደ ነው፤ ዘረኛነት ማለት የእኔ ዘር ከሁሉም ሌሎች ዘሮች የበላይና የተሻለ በሚል ከንቱና ምንም መሠረት በሌለው ትምክህት ላይ የተገነባ ስሜት ነው። ገና ከመነሻው ሰብኣዊ መብቶችነ በሙሉ ይጥሳል። ኢትዮጵያን ላለፉት 25 ዓመታት እየገዛ ያለው የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መንግሥት ሰብኣዊ መብቶችን ከማስከበር አኳያ አልተሳካለትም፤ ምክንያቱም ደግሞ በጎሰኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው።

ሐ. ሰብኣዊ መብቶችና ልማት የምዕራባውያን ታሪክ ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳየን ማናቸውም ዕይነት ዕድገት የሰብኣዊ መብቶች መከበር ውጤት ነው። በሰው ልጅ ውስጥ የታመቀው የአካል፣ የአእምሮና የመንፈስ ኃይል ከፍተኛ ነው። ይህ ኃይል የሚወጣው፣ የሚያብበውና የሚያፈራው በነጻነት ነው። ፍርሓትና ስጋት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ነው። በልበሙሉነት መስራት ሲቻል ነው። ለአንድ አገር ሰብኣዊ መብቶች መከበር ትልቅ ኃይል እንደሚሆን ምንም አያጠራጥርም። ሕዝቡ የአእምሮ እና የመንፈስ ኃይሉ ከተገደበ ዕድገት በምንም ሌላ መንገድ ሊመጣ አይችልም። በየጊዜውና በተለያዩ አገሮች አምባገነኖች (የእኛዎቹንም ይጨምራል) የሚያቀርቡት ክርክር አለ። ‹ዲሞክራሲ ወይም መንግሥተ ሕዝብ ሊመሠረት የሚቻለው ልማት ወይም ዕድገት ከተረጋገጠ በኋላ ነው› ይላሉ። ይህ አባባል እሳት የሚነድደው አለማገዶ ነው፤ እንደ ማለት ነው። የቱ ነው የሚቀድመው መንግሥተ ሕዝብ ወይስ ዕድገት። የሕዝቡ ኃይል ተገድቦና ታፍኖ ጥቃትና ግፍ የሰው ልጅን አካል፣ አእምሮና መንፈስ አደንዝዞና አሰናክሎ በሥልጣን መባለግን፣ ዝርፊያንና ውንብድናን መረን ለቅቆ፣ ለፍቶ ማግኘት የማያዋጣ እንደሆነ አረጋግጦ ዕድገት እንዴት ብሎ ሊገኝ ይቻላል? መንግሥተ ሕዝብ ከልማት በኋላ የሚለው አስተሳሰብ አምባገነኖች በሥልጣን ኮርቻ ላይ እስከ ዕድሜ ልካቸው እንዲቆዩ ከሚያደርጉት ጥረት አንዱ ነው። ከዓለምዐቀፋዊ የሰብኣዊ መብቶች መግለጫ ውስጥ አምባገነኖች በተለይ የማይወዱት አንቀጽ 21 ነው፣ እንዲህ ይላል፦ 1. ማንም ሰው በአገሩ መንግሥት ውስጥ በቀጥታ ወይም በነጻ በተመረጡ ወኪሎች አማካይነት የመሳተፍ መብት አለው፤ 2. ማንም ሰው በአገሩ መንግሥታዊ አገልግሎት (እንደ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ጭምር ማለት ነው) ከሌሎች ዕኩል የመጠቀም መብት አለው፤ 3. የመንግሥት ሥልጣን መሠረቱ የሕዝብ ፈቃድ ነው፤ የሕዝብ ፈቃድ የሚገለጠው በተወሰኑ ጊዜያት በሚካሔዱ ትክክለኛ ምርጫዎች ሲሆን እነዚህ ምርጫዎች ለሁሉም ሰው ዕኩል ዕድልን የሚሰጡና በምሥጢር ወይም በተመሳሳይ ነጻ የምርጫ ስነ ስርዓት የሚካሔዱ መሆን አለባቸው።

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

ልማት ወይም ዕድገት የሥልጣን ባለቤት ከሆነ ሕዝብ ከራሱ ጥረት የሚመነጭ ውጤት ነው። ታስሮና የተያዘ ሕዝብ በየትኛው ኃይሉ ነው ልማትን ለማምጣት የሚቻለው? ትላንትም፣ ሆነ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብኣዊ መብቱን የሚያከብርለት ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ለማቆም ባለመቻሉ የሠለጠነው ዓለም ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ላይ ሊደርስ ቀርቶ ማለም ተስኖታል። እስቲ የሰብኣዊ መብቶች መግለጫ አንቀጽ 25 (1) የሚለውን እንመልከት፦ “ማንም ሰው ለራሱና ለቤተሰቡ ጤንነትና ደኅንነት በቂ በሚሆን የኑሮ ደረጃ የመኖር መብት፤ ይህም ምግብን፣ ልብስን፣ መጠለያን፣ የሕክምና አገልግሎትን፣ አስፈላጊ የሆኑ ማኅበራዊ አገልግሎትን ማግኘትንና ለሥራ አጥነት፣ ለሕመም፣ ለአካል መጉደል፣ ለአባወራ ሞት፣ ለእርጅና ወይም ለሌሎች ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ የሕይወት መሠረትን ለሚያሳጡ ችግሮች ዋስትና የማግኘት መብትን ይጨምራል።” ከሕዝቡ ጥረት ውጭ እነዚህን መብቶች ለማስተናገድ የሚቻለው እንዴት ነው? ማናቸውንም ማኅበራዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚቻለው እንዴት ነው? ሁለት መንገዶች አሉ፤ አንደኛው ሕዝቡን ለራሱ ምንም ኃላፊነት እንደማይሰማው እንደ ሕጻን ልጅ በመመልከት ሕዝቡ ለራሱ የሚበጀውን አያውቅምና እኔ ግን የሚበጀውን ስለማውቅለት ሞግዚት ሆኜ ልግዛው ከሚል የአምባገነንነት ምኞት የሚመጣ ነው። ይህ መንገድ ሕዝብን ወደ ልማት አድርሶ አያውቅም። በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ምድር የበቀሉት አምባገነኖች ሁሉ ‹ሕዝቡ የሥልጣን ባለቤት ከመሆኑ በፊት በልማት ላይ ማተኮር አለበት› እያሉ ሲሰብኩ በርካታ ዐሥርተ ዓመታት ቢቆጠሩም አብዛኛው የአፍሪካ ሕዝቦች ቁልቁል ወረዱ እንጂ አላደጉም። በተለይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዕድገት ደረጃ ብዙ አገራት ቀድመዋት እየገሰገሱ ይገኛሉ። ሰዎች ሁሉ ዕኩል ክብርና መብቶች ይዘውና ነጻ ሆነው ተፈጥረዋል፤ የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ በተፈጥሮ ስለታደሉ፣ እርስ በርሳቸው በወንድማማችነት መንፈስ ሊተያዩ ይገባል። እንግዲህ ማንም ለማንም ሞግዚት ወይም ገዢ ሊሆን አይችልም ማለት ነው። ምን እንደምትሠራና የት እንደምትሠራ፣ ምን እንደምትበላና ስንት ጊዜ እንደምትበላ፣ ምን እንደምትለብስና እንዴት እንደምትኖር እኔ አውቅልሃለሁና እኔን ስማ የሚል አስተሳሰብ ሁሉ የሰው ልጆችን ዕኩልነት ከማይቀበል አምባገነንነት የሚመነጭ ነው። ተራራዎችን መቅደድ፣ ወንዞችን መገደብ፣ መሬትን መቆፈር፣ ብቻውን ልማት አይደለም። የሰውን ልጅ የውስጥ አእምሮ የመንፈስ ኃይል የሚያወጣና በፈጠራና በተግባር ላይ የሚያውል እንቅስቃሴ ነው ልማት የሚባለው እንዲህ ባይሆን ኖሮ እና የልማት መግለጫው የፎቅና ኢንዱስትሪ ብዛት የእርሻ ምርት መትረፍረፍ ቢሆን ጥቁር አሜሪካኖችና የደቡብ አፍሪካ ጥቁር አፍሪካውያን የልማቱ ተካፋይ ይሆኑ

ነበር። እንደሚታወቀው የሥልጣን ተካፋይ ስላልነበሩ የልማቱም ተካፋይ አልነበሩም ። ነገር ግን በሁለቱም አገሮች ጥቁሮች ከሥልጣን ውጭ ነበሩ። በዚህም ምክንያት ከልማት ውጭ የነበሩት በዘረኝነት አመራር የተነሳ ነበር። ሌሎች አምባገነኖችም ልማትን ሥልጣነ-ሕዝብ ከሰፈነበትና ሰብኣዊ መብቶች ከሚከበሩበት ስርዓት መቅደም አለበት የሚሉበት ምክንያት ሕዝባቸውን ዝቅ አድርገውና አዋርደው በመገመታቸው በመሆኑ ከዘረኞች እምብዛም የተለየ አስተያየት አይደለም። ልማት የነጻነት ልጅ ነው። የአምባገነኖች የአገዛዝ ስርዓት ፀረ ነጻነት ነውና ልማትን አይወልድም። ሰው ሰው መሆኑ ማረጋገጥ ካልቻለ ልማት ትርጉም የለውም፤እንደሚቀለብ የእሽቅድድም ፈረስ ወይም እንደ ጭነት አህያ ነው። ለዚህም ነው ማኅበረሰባችን ከምግብ በላይ ሰውነት እንደሚያስከብር ለመጠቆም እንዲህ ሲል የገጠመው፣ “ሰው ባገሩ ቢበላ ሳር፣ ቢበላ መቅመቆ፤ ይከበር የለም ወይ ሰውነቱ ታውቆ።”

መደምደሚያ

እንደ ትሮይ ፈረስ የሚጋልበን ይህ አገዛዝ የሰብኣዊ መብቶችን ከማስከበር አኳያ የተሳካለት አይመስለኝም። ታሪክ የሰጠውን ዕድል እያበላሸው ይገኛል ። ለወደፊቱ ትውልድ ተስፋ የነበሩ ለም መሬቶችን በዓለም ታይቶ በማይታወቅ እጅግ ርካሽ በሆነ ዋጋ ለዓለም ቱጃሮች መቸብቸብ፣ ነባር የከተማ ባለጥሪቶችን ከአፅመ ርስታቸው ያለ በቂ የካሣ ክፍያ ማፈናቀል፣ ከድህነት ወለል በታች የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የአዲስ አበባ በርካታ ነዋሪዎችን ሽልጦ እና ቆሎ ነግደው ከሚኖሩበት አካባቢዎች ያለ በቂ መልሶ ማቋቋም ወደ ሌላ አዲስ አካባቢዎች ማስፈር (ለኮንዶኖሚኒየም ሕንፃ መኖሪያ የቅድመ ክፍያ ማጠናቀቅ የቻሉትን ማለቴ ነው)… ፍፁም ሠላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚያካሔዱ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን እና ተቺ ጋዜጠኞችን በየጊዜው እንደ ጥጃ እያሠሩ መፍታት ሲያሻውም ለዓመታት በእስር እንዲማቅቁ ማድረጉ አገዛዙ የሰብኣዊ መብቶችን ለማስከበር አለመቻሉን ማሳያዎች ይመስሉኛል። ውድ ወገኖቼ አስተውለን የምንራመድ፣ ቆም ብለን የምናስብ ከሆነ መጠለያ የማግኘት መብት አተገባበር ብቻውን በችግር የተሞላ እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን። ለመሆኑ እነማን ናቸው በጋራ የመኖሪያ ቤት ውስጥ ተከራይተው የሚኖሩት? የዕጣ አወጣጡ እንዴት ነው? እውን ድህነት ቤቱን የሠራበት የአዲስ አበባ ነባር ነዋሪ ቅድመ ክፍያውን አጠናቆ የቤት ባለቤት መሆን ይችላልን? ኅሊና ያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። ኢትዮጵያ የሞት፣ የግፍና የስቃይ፣ የፍርሓትና የመሸማቀቅ አገር ሳትሆን ማንም ሰው አንገቱ ቀና አድርጎ በክብርና በኩራት የሚኖርባት አገር እናድርጋት። የሁላችንም ኃላፊነት ይህ ነው። ደረጄ መላኩን በኢሜይል አድራሻው [email protected] ሊያገኙት ይችላሉ፡፡

ውይይት ነሐሴ 2008

31

የአገር ነገር

የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ እንዴት ይፈታ? አምባሳደር ተስፋዬ ሐቢሶ ከ46 ዓመታት በፊት የወልቃት ሁመራ አካባቢ ይተዳደር የነበረው በቤጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ሥር እንደነበረና የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ከተከዜ መልስ መሆኑን እንደሚያስታውሱ ከግል ገጠመኛቸው ጋር በማስታከክ ያስረዱ ሲሆን፣ ከ1987 በኋላ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት ክልሎች ሲዋቀሩ ወልቃይት ሁመራ ወደ ትግራይ ክልል መካለሉን በመግለጽ፣ እንዲሁም የአካባቢዎች አከላለል በዓለምዐቀፍ ተሞክሮዎች በየጊዜው እንደሚስተካከል አንስተው የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄም በዚያ ስሜት መስተናገድ አለበት ብለዋል። በ1962 አም ከቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቅሁ በኋላ በመንግሥት ሠራተኛነት የተቀጠርኩት በትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ሥር ይተዳደር በነበረው የመንገድ ማመላለሻ አስተዳደር መሥሪያ ቤት ነበር። በ1963/64 የተለያዩ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶችን በመላ አገሪቱ ስናቋቋም ለሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚያገለግል ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት የተቋቋመው በጎንደር ከተማ፣ ለትግራይ በመቀሌ፣ ለኤርትራ ደግሞ በአስመራ ከተማ ነበር። ያን ጊዜ የጠቅላይ ግዛቱ ሥያሜ የቤጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ተብሎ ሲጠራ ጠቅላይ ገዥ የነበሩት ኮሎኔል ታምራት ይገዙ ነበሩ፡፡ የትግራይ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ የኤርትራ ደግሞ ልዑል ራስ አሥራተ ካሳ ነበሩ። በ1963 በወልቃይት ጠገዴ በሚገኘው የሁመራ መሬት ጥጥ፣ ሰሊጥና ማሽላ በሰፊው የሚያመርት የወልቃይት ጠገዴ ሁለገብ የገበሬዎች ማኅበር ነበር፤ በማኅበሩ ውስጥ አባል ሆነው ለመሠማራት የሚሹ ሁሉ ከኮሎኔል ታምራት ይገዙ፣ ከጎንደር የድጋፍ ደብዳቤ እየተጻፈላቸው ነበር የሚመዘገቡት። ማኅበሩ ከዓለም ባንክ እርዳታ የሚያገኝ ነበር፣

ምርታቸውን በተመለከተ ማሽላውን ወደ ከረንና አሥመራ የሚያስጭኑ ሲሆን ጥጡንና ሰሊጡን በምፅዋ ወደብ በኩል ወደውጭ አገሮች ነበር ኤክስፖርት የሚያደርጉት። እነዚህን ምርቶች ወደ ምፅዋ የሚጭኑት የቀይ ባሕር ኤርትራ የጭነት ማመላለሻ ማኅበር ነበር። እኛም የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ቡድን በ1963 ወደ ሁመራ የሔድነው ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ማኅበራት በጭነት ታሪፍ የተነሳ ስላልተስማሙ ለማስታረቅ ነበር፡ ፡ የሁለቱን ማኅበራት መሪዎች በማወያየት በኩንታል 3 ብር የነበረው ወደ 4 ብር ከፍ እንዲል በማስማማት ወደ ጎንደር ተመለስን። ያን ጊዜ ማለትም የዛሬ 46 ዓመት ሁመራ (ወልቃይት ጠገዴ) የቤጌምድርና ስሜን አካል ነበር፡፡ የቤጌምድርና ስሜን እና የትግራይ ጠቅላይ ግዛቶች የድንበር ወሰን የተከዜ ወንዝ ነበር። ከሁመራ የሚጫነውም ምርት ተከዜ ሰቲትን ተሻግሮ ከኦምሀጀር (ኤርትራ) ወደምፅዋ ወደብ ድረስ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስከደርግ ውድቀት ድረስ ወልቃይት ጠገዴ የጎንደር ጠቅላይ ግዛት ክልል ነበር፡፡ በነዚያ ዓመታት አማራ የሚባል ክልል አልነበረም። አማራ የሚባል ክልል የተዋቀረው ከ25 ዓመታት በኋላ በ1987 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዴ.ሪ.) ሕገ መንግሥት ከፀደቀ በኋላ ከሌሎች 8 ስምንት ክልሎች ጋር ነበር። ክልሎቹም የተዋቀሩት በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 46 መሠረት "በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመሥረት" ስለ ነበር ከ46 ዓመታት በኋላ በመሬት ላይ የተከሰቱትን ማኅበራዊ ለውጦች አላውቅም፡፡ ሆኖም የክልሎች አከላለል በሠላማዊ መንገድ የተዋቀረ

ከናይጄሪያ እስከ ሕንድ፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ካናዳ፣ ከስዊዘርላንድ እስከ አውስትራልያ ያሉት የፌዴራል አገሮች በየጊዜው የአባል ክልሎቻቸውን ወሰኖች ይከልሳሉ፤ ያሻሽላሉ፤ ይለውጣሉ። የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄም በተመሳሳይ ሁኔታ ሊፈፀም ይገባል 32 ውይይት ነሐሴ 2008

ሳይሆን በተለያዩ ክልሎች ደም አፋሳሽ ሁኔታዎች ተከስተዋል፡፡ የሰዎች ሕይወት ሳይቀጠፍ የተከናወነ የክልል አወቃቀር ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም። ይህ በዚህ እንዳለ፣ የወልቃይቶችንም ሆነ የማንኛውንም ዘውግ ማንነት የሚወስኑት ራሱ ማኅበረሰቡ እንጂ ማንም ሌላ አካል ማንነትን (identity) እንደ ቦሎ አይለጥፍላቸውም። በሌላ አንፃር፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 መሠረት፣ "የአከላከል ለውጥ ወይም የክልል ወሰን የሚመለከት ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት፣ እነዚህ ለመስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሕዝብ አሰፋፈርንና ፍላጎት መሠረት በማድረግ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ"፣ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል ። ይህ ጉዳይ ዛሬ የዚህን ያህል ውዝግብ ካስተለ በታዛቢዎች ዘንድ ጭምር ጉዳዩ ቀድሞም ተድበስብሶና ተሸፋፍኖ የተዘጋ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ ስለሚያሳድር ከላይ የተጠቀሱት የመንግሥት አካላት ኃላፊነታቸውን አሁንም በአግባቡ ለመወጣት በአስቸኳይ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ ተኣማኒነት ያለው የድንበር ኮሚሽን በማቋቋምና የትግራይና የአማራ ክልሎች ሽማግሌዎች በሚገኙበት ኮሚሽን እንደገና ተጠንቶ የመጨረሻ ውሳኔ ሊሰጠው ይቻላል። የፌዴራል አባላት ክልሎችን ወሰን በተመለከተ በየጊዜው መከለስና ለሕዝቦች መስተጋብር በሚያመች ሁኔታ ጂኦግራፊን፣ የማኅበረሰብ አሰፋፈር፣ የሚመለከታቸው ወገኖች ፍላጎት፣ የክልሎችን ዕኩልነት ወይም ተመጣጣኝነት፣ ወዘተ. መሥፈርቶች በመጠቀም ማካለል አዲስ ክስተት አይደለም፡ ፡ ከናይጄሪያ እስከ ሕንድ፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ካናዳ፣ ከስዊዘርላንድ እስከ አውስትራልያ ያሉት የፌዴራል አገሮች በየጊዜው የአባል ክልሎቻቸውን ወሰኖች ይከልሳሉ፤ ያሻሽላሉ፤ ይለውጣሉ። የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄም በተመሳሳይ ሁኔታ ሊፈፀም ይገባል። ከዚህ ውጭ የሁለቱን ክልሎች ወንድማማች ሕዝቦች ለማጋጨት የሚደረገው እንቅስቃሴ ወይም ሴራ ሁሉ በፅኑ መወገዝ አለበት። አምባሳደር ተስፋዬ ሐቢሶ የሽግግር መንግሥቱ የተወካዮች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ በመሆን እንዲሁም በደቡብ አፍሪካና እና በኡጋንዳ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. አምባሳደርነት አገልግለዋል፡፡ በሦስቱም መንግሥታዊ ስርዓቶች በኃላፊነት የሠሩ ሲሆን አሁን በጡረታ ላይ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ሊያገኟቸው ይችላሉ።

1ኛ ዓመት ቁጥር 10

View more...

Comments

Copyright ©2017 KUPDF Inc.
SUPPORT KUPDF