ጀብሃ እና ሻዕቢያ (2)

October 18, 2017 | Author: Samson Wolde | Category: N/A
Share Embed Donate


Short Description

Download ጀብሃ እና ሻዕቢያ (2)...

Description

F -X C h a n ge

F -X C h a n ge

N y bu ac

.c

tr

om

to k lic C

k lic C

.c

re

.

.

k e r- s o ft w a

w

w

ac

ww

ww

tr

om

to

bu

y

N

O W !

PD

O W !

PD

k e r- s o ft w a

(1961-1991 G.C)

re

ጀብሃ እና ሻዕቢያ (1961-1991 G.C) -----ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ -------

ብዙ አንባቢዎች በፌስቡክ እና በኢ-ሜይል ከሚያቀርቡልኝ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የኤርትራ የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚመለከተው ነው፡፡ ጥያቄው ንባብ የሚያሻው በመሆኑ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ጎን ስገፋው ኖሬአለሁ፡፡ በዚህ ሰሞን የአምባሳደር ዘውዴ ረታን “የኤርትራ ጉዳይ”፣ የፖል ሄንዝን Eritrea’s War እና የጌታቸው ሀይሉን “ቀያይ ተራሮች” በድጋሚ ካነበብኳቸው በኋላ ግን የጓደኞቼን ጥያቄ ለመመለስ ተነሳሳሁ፡፡ እናም “ጀብሃ” እና “ሻዕቢያ”ን በመጠኑ የሚያስቃኘውን ይህንን ጽሑፍ እንዲህ አሰናድቼዋለሁ (በጽሑፉ ውስጥ ያለው የዘመን አቆጣጠር በሙሉ በአውሮፓዊያን ካሌንደር ነው የተጠቀሰው)፡፡

ቅድመ-ታሪክ እ.ኤ.አ በ1952 ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ተሳሰረች፡፡ ይህ የፌዴሬሽን አሰራር ከመነሻው ላይ የብዙሃኑ ኤርትራዊ ድጋፍ አግኝቶ ነበር፡፡ ወደ ተግባር ሲተረጎም ግን ብዙዎች ግራ መጋባት ጀመሩ፡፡ ኤርትራዊያኑ አስተዳደራቸው ሙሉ በሙሉ ነጻ ሆኖ በስም ብቻ ከሃይለ ስላሴዋ ኢትዮጵያ ጋር የተሳሰረ ነበር የመሰላቸው፡፡ በትክክለኛው አገላለጽ ግን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘችው እንደ ነጻ ሀገር ሳይሆን እንደ አንድ ራስ ገዝ ክፍለ ሀገር በመሆን ነበር፡፡ የኤርትራ መንግሥት ተብሎ የተሰየመው አካል በውስጥ ጉዳዮች ላይ በነጻነት የመወሰን መብት ቢሰጠውም በውጪ ጉዳይ፣ በመከላከያ፣ በፋይናንስ፣ በወደቦችና በመገናኛ ዘርፎች የመወሰን ስልጣን አልነበረውም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የሚከናወኑት በፌዴሬሽኑ ህገ-መንግሥት መሰረት የፌዴራሉ መንግስት ሆኖ እንዲሰራ ስልጣን በተሰጠው የአጼ ሀይለ ስላሴ ንጉሣዊ አስተዳደር ነው፡፡ ኤርትራዊያኑም እንደ ኢትዮጵያ ዜጋ ነበር የሚቆጠሩት፡፡ በዚህም የተነሳ አንዳንድ ኤርትራዊያን ከፌዴሽኑ ምስረታ በኋላ “እንግሊዝና አሜሪካ ለሀይለስላሴ መንግሥት ሸጡን” የሚል ተቃውሞ ማሰማት ጀምረው ነበር፡፡ በዚያ ዘመን የተቃውሞው መሪ ሆነው የወጡት አቶ ወልደአብ ወልደማሪያም የሚባሉት የቀድሞው “ሊበራል ፕሮግሲቭ ፓርቲ” መሪ እና “የራቢጣ አል-ኢስላሚያ ፓርቲ” መሪ የነበሩት ሱልጣን ኢብራሂም ናቸው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ፌዴሬሽኑ ለሶስት ዓመታት ያህል በነጻነት ቆየ፡፡ ከኤርትራ ህዝብ የሚበዛው ክፍል በፌዴሬሽኑ መንግስት ደጋፊነት ኖረ፡፡ የመጀመሪያው የኤርትራ ስራ አስፈጻሚ (Chief Executive) የነበሩት ደጃዝማች ተድላ ባይሩ በ1955 ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው ሲለቁ ግን ኤርትራ የተቃውሞ መድረክ መሆን ጀመረች፡፡ በተለይ የአጼ ኃይለ ስላሤ የቅርብ ሰው የሆኑት የቢትወደድ አስፍሐ ወልደሚካኤል የኤርትራ ስራ አስፈጻሚ ሆኖ መመረጥ ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ አስነሳ፡፡ በ1956 የፖለቲካ ፓርቲዎችና ነጻ ፕሬስ ሲታገዱ አብዛኛው ኤርትራዊ የፌዴሬሽኑ መጥፊያ የተቃረበ መሆኑን መተንበይ ጀመረ፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሃድ የደከሙ ሰዎች እየተገፉ ሌሎች መሾማቸው ደግሞ ነገሩን አባባሰው፡፡ እነዚህ የአንድነት ወገን የሚባሉ መሪዎች “ባይተዋር ሆነናል” በማለት ለአጼ ሀይለ ስላሴ አቤቱታ አቀረቡ፡፡ ፌዴሬሽኑን የመጠበቅ ግዴታ የተሰጠው የአጼ ኃይለ ስላሴ መንግሥት ግን የፌዴሬሽኑን ህልውና የሚያናጉ

እርምጃዎች ሲወሰዱ አይቶ እንዳላየ ሆኖ አለፈ፡፡ በተለይ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ለማዋሃድ በእጅጉ የደከሙት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ ፌዴሬሽኑ እንዳይፈርስ የሚቻለውን ሁሉ ቢያደርጉም አጼ ኃይለስላሴ በተቃራኒው የቢትወደድ አስፋሐ “አይዞህ ባይ” ሆኑ፡፡ የቢትወደድ አስፋሐ መንግሥት የሚወስደው እርምጃ እለት ተዕለት እየጠነከረ ሄደ፡፡ በ1958 የኤርትራ ሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን የጠራው የስራ ማቆም አድማ በሀይል ተደመሰሰ፡፡ ብዙ ሰዎች ተገደሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ ኤርትራዊያን “ሓርነት” የሚል ድምጽ ማሰማት ጀመሩ፡፡ ሆኖም የቢትወደድ አስፋሐ መንግሥት የህዝቡን ተቃውሞ ከምንም አልቆጠረውም፡፡ በ1958 የፌዴሬሽኑ የስራ ቋንቋዎች የሆኑት ትግርኛና ዐረብኛ ታግደው በአማርኛ ተተኩ፡፡ በ1959. የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ ታገደ፡፡ በ1962 ዓ.ል. ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር መሆኗ ታወጀ፡፡ የኤርትራ ፌዴሬሽን የፈረሰበት ታሪካዊ ሂደት በአጭሩ ይህንን ይመስላል፡፡ ለሰላሳ ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝቦችን ደም ሲያስገብር የነበረው ጦርነት የተለኮሰው ይህንን እርምጃ ተከትሎ ነው፡፡ ያኔ የተፈጸመው ብዙዎችን ያሳዝናል፤ ያስቆጫልም፡፡ በተለይ የሚያስቆጨው ግን የአጼ ሃይለ ስላሴ መንግሥት የመካሪዎቹን ጥቆማ አልቀበልም በማለት ሲፈጽማቸው በነበሩት ስህተቶች የተነሳ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ ለማድረግ መብቃቱ ነው፡፡ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ለማዋሃድ የደከሙት ጸሓፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ለንጉሳቸው ሲሰጡት የነበረው ምክር በስራ ላይ ቢውል ኖሮ የዛሬው ሁኔታ ሌላ መልክ በያዘ ነበር (ምናልባትም እኔ ራሴ ይህንን ጽሑፍ ባልጻፍኩ ነበር)፡፡ የቢትወደድ አስፋሐ እርምጃ በተጠናከረበት በ1956 ገደማ አንዳንድ ኤርትራዊያን “ፌዴሬሽኑ የፈረሰ እንደሆን ምን እናድርግ” እያሉ በድብቅ የሚወያዩበትን “ማህበር ሸውአተ” የተሰኘ እድር መሳይ ማህበር መስርተው ነበር፡፡ ይህ ማህበር በጅምሩ ላይ ዝግ ብሎ ይጓዝ ነበር፡፡ በ1959 የኤርትራ ባንዲራ ሲሰረዝ ግን “የፌዴሬሽኑ መፍረስ እውን ነው” በማለት ደመደመ፡፡ በዚህም የተነሳ የማህበሩ መስራቾች እንቅስቃሴአቸው ድርጅታዊ መልክ እንዲይዝ አደረጉት፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላም ከዚሁ ማህበር አስኳል “ምንቕስቓስ ሓርነት ኤርትራ”/Eritrean Liberation Movement ወይንም በአጭሩ “ሀረካ” በሚል ስያሜ የሚጠራ የፖለቲካ ድርጅት ተወለደ (“ሀረካ” በዐረብኛ “እንቅስቃሴ” ወይም “ንቅናቄ” ማለት ነው፤ ድርጅቱ በሙሉ የዐረብኛ ስሙ “ሀረካት ታህሪረል ኤሪትሪያ” ይባላል፤ “የኤርትራ ነጻነት ንቅናቄ” ማለት ነው)፡፡ “ሀረካ” ሁለት አማራጮችን ይዞ ነው ወደ ትግሉ የገባው፡፡ ቀዳሚ ምርጫው “የኤርትራ ፌዴሬሽን መፍረስ የለበትም” የሚል ሲሆን ዓላማውም የቢትወደድ አስፋሐ እና የአጼ ኃይለ ስላሴ መንግሥት ሹማምንት የፌዴሬሽኑን አሰራር በትክክል በስራ ላይ እንዲያውሉ መጠየቅ ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ “ኤርትራ ራሷን የቻለች ሉዓላዊት ሀገር ሆና ነጻ ትውጣ” የሚል ነው፡፡ ሆኖም የ“ሀረካ” ቀዳሚ ምርጫ ፌዴሬሽን እንጂ “ነጻነት” አልነበረም፡፡ የሀረካ መሪዎች ጥያቄአቸውን ለኤርትራ አስተዳደር አቀረቡ፡፡ ይሁንና የቢትወደድ አስፋሐ መንግሥት በጎ ምላሽ ነፈጋቸው፡፡ እንዲያውም “የዐረብ ምንደኛ” እና “ሽብር ፈጣሪ” በማለት ከሰሳቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ሀረካዎች ለትጥቅ አመጽ ተነሳሱ፡፡ በፌዴሬሽኑ ማክተሚያ ዋዜማ ላይ

ንቅናቄው 50 ያህል ተዋጊዎችን አደራጅቶ ወደ ሳህል በረሃ ወረደ፡፡ ሆኖም ለሶስት ዓመታት ያህል የሚረባ እንቅስቃሴ ሳያደርግ ከርሱ በኋላ በተቋቋመ አዲስ ድርጅት ተበለጠ፡፡ በ1964 ገደማም አዲሱ ድርጅት በከፈተበት ጥቃት ክፉኛ ተመታ፡፡ የሀረካ ህልውናም በዚያው አከተመ፡፡

ጀብሃ በኤርትራ ሜዳ አዲሱ ድርጅት “ተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ/Eritrean Liberations Front ይባላል፡፡ የታሪክ ሰነዶችና መላው ኤርትራዊያን ድርጅቱን የሚጠሩት ግን “ጀብሃ” በሚል አጭር ስም ነው፡፡ “ጀብሃ” የሚለው ቃል “ጀብሃት ታሕሪረል ኤሪቲሪያ” ከሚለው የድርጅቱ የዐረብኛ መጠሪያ ተቀንጭቦ የወጣ ነው፡፡ ይህም ድርጅቱን ከ“ሀረካ” ለይቶ ለመጥራት በሚደረግ ጥረት የተፈጠረ ልማድ ነው (የሁለቱ ድርጅቶች የዐረብኛ መጠሪያ አንድ ዓይነት ሆኖ በስሞቹ መጀመሪያ ላይ ባሉት “ጀብሃ” እና “ሀረካ” በሚሉት ቅጽሎች ብቻ ነው የሚለዩት)፡፡ “ተሓኤ”/ጀብሃ የተመሰረተው በ1961 በካይሮ ከተማ ነው፡፡ የድርጅቱ መስራቾች በስደት ላይ የነበሩ ኤርትራዊያን ተማሪዎች፣ የቀድሞ “ራቢጣ” እና “ፕሮግሬሲቭ ፓርቲ” አባላት፣ ከኤርትራ ፓርላማ የኮበለሉ ጥቂት ግለሰቦችና በዐረቡ ዓለም የሚኖሩ ነጋዴዎች ነበሩ፡፡ ድርጅቱ በምስረታ ጉባኤው ከኤርትራ ነጻነት በስተቀር ሌሎች አማራጮችን እንደማይቀበል አስታወቀ፡፡ ፌዴሬሽን የሚባለው አስተሳሰር ለኤርትራዊያን በጭራሽ የማያስፈልግ የባርነት እስር ቤት ነው በማለት ደመደመ፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ጋር በነጻነት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በሌሎች አጀንዳዎች እንደማይደራደር ገለጸ፡፡ የኤርትራ ፓርላማ ፕሬዚዳንት የነበረውን ኢድሪስ መሐመድን በሊቀመንበርነት መረጠ፡፡ ጀብሃ በምስረታው ማግስት ለትጥቅ አመጽ መዘጋጀት ጀመረ፡፡ በሀገር ቤት ካሉ ባላባቶች ጋር ግንኙነት ከተፈጠረ በኋላ ምዕራባዊው የኤርትራ ቆላ ለትግል ምቹ መሆኑን አመነበት፡፡ የአካባቢው ታዋቂ ባላባት የሆኑት “ሃሚድ ኢድሪስ አዋቴ” የሚባሉት የቤኒ አምር ጎሳ ተወላጅ የግንባሩን የትጥቅ ትግል እንዲመሩ ውክልና ተሰጣቸው፡፡ በኝህ ሰው አስተባባሪነትም አስራ አንድ ሰዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን መስከረም 1/1961 በኤርትራ ምድር ለ30 ዓመታት የሚቆየውን የትጥቅ ትግል በምዕራባዊው የባርካ አውራጃ ጀመረ (ሆኖም ሃሚድ አዋቴ ከአንድ ዓመት በኋላ በተደረገ ውጊያ ላይ ተገድለዋል)፡፡ ጀብሃ ወደ ትግሉ ሜዳ የገባው በከረረ ስሜት ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ከኤርትራ ነጻነት በስተቀር በየትኛውም አማራጭ ላይ ለመደራደር ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ የትግል ዓላማው ኤርትራን ነጻ ሀገር ማድረግ ከመሆኑ በመለስ ድርጅቱ በምስረታው ዋዜማ የየትኛው የርዕዮተ-ዓለም አቅጣጫ ተከታይ እንደነበረ በትክክል ለመረዳት ይቸግራል፡፡ በርካታ ጸሓፊያን “ተሓኤ” (ጀብሃ) ብሄርተኛ ከመሆኑ ውጪ የተለየ ጎራ ተከታይ እንዳልነበረ ያስረዳሉ፡፡ አንዳንዶች ግን ድርጅቱ ከኢራቅና ከሶሪያ “በዕሥ” (“Ba’th” ) ፓርቲዎች ጋር የነበረውን ጠንካራ ግንኙነት በመመልከት “ጀብሃ የዐረብ ሶሻሊዝም ፍልስፍና ተከታይ ነበር” ይላሉ፡፡ በርግጥም “ጀብሃ” በዐረቦች ዘንድ ከፍተኛ እውቅናና ድጋፍ አግኝቶ ነበር፡፡ ራሱንም እንደ ዐረብ ብሔርተኛ ድርጅት የማየት አዝማሚያዎች ነበሩት፡፡ ሆኖም ይህንን ሁሉ ለታክቲክ ሲባል የሚያደርገው ነው የሚመስለው፡፡ ድርጅቱ ዐረባዊ እየመሰለ እና ዐረብኛን የስራ ቋንቋነት በማድረግ

እየተገለገበት እንኳ ዐረብ ካልሆኑ የኮሚኒስት ሀገራትም ጋር ግንኙነት ነበረው፡፡ ለምሳሌ ጀብሃ ከኩባ፣ ቻይና እና ሶቪየት ህብረት ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቶ ነበር፡፡ እንዲሁም የሶሻሊዝም ጠላት ናቸው ከሚባሉት ሳዑዲ ዐረቢያን ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር የነበረው ግንኙነት በጣም የጠነከረ ነው፡፡ ጣሊያንን የመሳሰሉ የምዕራብ ሀገራትም የድርጅቱ ደጋፊዎች ነበሩ፡፡ ከዚህ ሁሉ እንደምንረዳው ድርጅቱ የታክቲክ ወዳጅ እንጂ የርዕዮተ ዓለም ወዳጅ ነበረው ለማለት ይከብዳል፡፡ የጀብሃ መስራቾች በአብዛኛው የትግረ ቋንቋ ከሚናገሩት የቤኒአምር፣ አሳውርታ እና ቢለን ጎሳዎች የተውጣጡ ነበሩ፡፡ በዚህም የተነሳ በምስረታው ዘመን ከድርጅቱ አባላት ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ሙስሊሞች ነበሩ፡፡ የድርጅቱ እንቅስቃሴም በቆላማዎቹ የሳህል፣ ከረን እና ባርካ አውራጃዎች የተገደበ ነበር፡፡ በምስረታው ዘመን ከሀምሳ የማይበልጡ ተዋጊዎች የነበረው ይህ እንቅስቃሴ ከሁለት ዓመታት በኋላ ሰራዊቱን በብዙ እጥፍ በማሳደግ ወደ ሶስት ሺህ አድርሶታል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የአጼ ሀይለስላሴ መንግስት ጀብሃን እንደ ተራ የሽፍታ ስብስብ ስለቆጠረው በፖሊስ ሀይል አሳድዶ ሊያጠፋው ሞክሮ ነበር፡፡ በ1963 ከከረን ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ ስፍራ ላይ በተደረገ ከባድ ውጊያ በርካታ ፖሊሶች ከሞቱ በኋላ ግን የንጉሡ መንግሥት መደበኛ ሰራዊቱን ወደ ኤርትራ ማንቀሳቀስ ግድ ሆኖበታል፡፡ ጀብሃ በምስረታው ማግስት ጥርት ያለ የድርጅት መዋቅር አልነበረውም፡፡ በ1964 ግን የድርጅቱን አመራር ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መዋቅሩን በልዩ ልዩ እርከኖች በመከፋፈል በስራ ላይ አውሎታል፡፡ በዚህም መሰረት አምስት አባላት ያሉት “ቃኢዳ አል-አማ” (በዐረብኛ “ጠቅላይ መምሪያ” እንደማለት ነው ) የሚባለው አካል የድርጅቱ ከፍተኛ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሆኖ ተሰየመ፡፡ የግንባሩን አጠቃላይ የፖሊሲ ውሳኔዎች የሚያስፈጽመው ይህ አካል ነው፡፡ ድርጅቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወክለውም ይኸው “ቂያዳ አል-አማ” ነው፡፡ ኢድሪስ መሀመድ፣ ኡሥማን ሳልህ ሳቤ፣ ጣሃ መሐመድ ኑር፣ ኢድሪስ ገላውዴዎስ እና አብደላ ኢድሪስ የጀብሃ ስራ አስፈጻሚዎች ነበሩ፡፡ የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴው የሚቀመጠው የድርጅቱ ዋና ጽ/ቤት ባለበት የካይሮ ከተማ ነው፡፡ ኢድሪስ መሐመድ እና ኢድሪስ ገላውዴዎስ የግንባሩ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ዑስማን ሳልህ ሳቤ የድርጅቱ የውጪ ጉዳይ ሃላፊ ነበሩ፡፡ ከስራ አስፈጻሚው ኮሚቴው ዝቅ ብሎ ደግሞ “አብዮታዊ እዝ” የሚባል ምክር ቤት አለ፡፡ የዚህ እዝ ተቀማጭነቱ በሱዳኗ ከሰላ ከተማ ሲሆን መደበኛ ተግባሩም በአምስቱ ዞኖች የሚከናወኑትን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ተግባራት ማቀናበርና ማቀላጠፍ ነው (ስለዞን አወቃቀር ከታች እንመጣበታለን)፡፡ የመጀመሪያው የጀብሃ ወታደራዊ አዛዥ ዑመር ኢዛዝ ይባላል፡፡ ይህ ሰው የብሌን ብሄረሰብ ተወላጅ ሲሆን ጀብሃ እስከዛሬ ካፈራቸው አዋጊዎች በጀግንነቱ የሚወደሰው እርሱ ነው፡፡ ዑመር ኢዛዝ የተወለደው በከረን ከተማ ነው፡፡ በወጣትነቱ ወደ ሱዳን ተሰዶ በሱዳን ጦር ሀይል ውስጥ በመቀጠር እስከ ሻምበል ማዕረግ ለመያዝ ችሏል፡፡ ከርሱ ጋር የተዋጉና አሁንም በህይወት ያሉ የጀብሃ አባላትና መሪዎች በጣም ያደንቁታል፡፡ ሆኖም በጭካኔው ወደር እንዳልነበረው ታሪኩን የጻፉ ወገኖች ይመሰክራሉ (ዑመር ኢዛዝ በ1972 በውጊያ ላይ ሞቷል)፡፡ ጀብሃ እስከ 1965 ሲያካሄደው የነበረው ወታደራዊ ኦፕሬሽን በአንድ የዘመቻ ማዕከል ነበር የሚመራው፡፡ በነዚያ ዓመታት ግንባሩ ነጻ ያወጣው ትልቅ ከተማ ባይኖርም ሳህል እና ባርካ በሚባሉት ቆላማ የኤርትራ አውራጃዎች ውስጥ ያለው የገጠሩ ክፍል በቁጥጥሩ ስር ገብቶ ነበር፡፡ ከ1965 ጀምሮ የአጼ ኃይለ ስላሤ መንግሥት የግንባሩን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በሚል የወሰዳቸው የጅምላ ቅጣቶች ተቃራኒ ውጤቶች ነው የነበራቸው፡፡ በተለይ የኤርትራ ሀገረ ገዥ

የነበሩት ልዑል ራስ አስራተ ካሳ በ1967 “ይህቺን ቆላ ሀገር እንደ ራስ ጸጉሬ ምድረ በዳ አደርጋታለሁ” በማለት በባርካ አውራጃ ከፍተኛ ህዝብ ያለቀበትን ዘመቻ ማካሄዳቸው በታሪክ ምሁራን ተጽፏል፡፡ በወቅቱ በኤርትራ ክፍለሀገር ወታደራዊ ኦፊሰር የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ በጻፉት መጽሐፍ እንደገለጹት ከአምስት ሺህ የማያንሱ ሰላማዊ ኤርትራዊያን ራስ አስራተ ካሳ ባዘመቱት ሰራዊት ተፈጅተዋል (አጼ ኃይለ ሥላሴ በራስ አስራተ ካሳ የተወሰደውን ጭካኔ የተመላበት እርምጃ ከሰሙ በኋላ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ እንደሰጧቸው ይነገራል፤ በዚህም የተነሳ ራስ አስራተ በንጉሡ ላይ ቂም ይዘው ከስልጣን ሊያወርዷቸው ሲያደቡ ነበር)፡፡ ሆኖም የራስ አስራተ እርምጃ የትጥቅ አመጹን አባባሰው እንጂ አላቆመውም፡፡ በተለይ ከመንግስት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የነበራቸው ክርስቲያኖቹ የደጋው ኤርትራ ክፍል ነዋሪዎች በብዛት ወደ በረሃ እየወረዱ ከጀብሃ ጋር መቀላቀል የጀመሩት የራስ አስራተ ጦር በኤርትራዊያን ላይ ያደረሰው ፍጅት ከተሰማ በኋላ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነበሩት እነ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ወልዳይ ግደይ፣ ሰለሞን ወልደማሪያም፣ ሙሴ ተስፋዮሐንስ ወዘተ… የመሳሰሉ ፋኖዎች ጀብሃን የተቀላቀሉት በዚያ ዓመት ነው፡፡ ከምጽዋ አካባቢም እንደ ኢብራሂም አፋ እና ረመዳን መሐመድ ኑርን የመሳሰሉ ተዋጊዎች ጀብሃን ተቀላቅለዋል፡፡

ጀብሃ “ትግሌን እንደ አልጄሪያ ነጻ አውጪዎች አጠናክርበታለሁ” ያለውን የዞን አከፋፈል በስራ ላይ አውሏል፡፡ ሆኖም በግንባሩ ውስጥ የተከሰተው ቀውስ ከቀን ወደ ቀን እየጠነከረ ነው የሄደው፡፡ ግንባሩ ኤርትራዊያንን በጎሳ እና በሀይማኖት ይከፋፍላል በማለት የተቆጡ ታጋዮችን ለማለዘብ አንዳንድ ለውጦች ቢካሄዱም ቅሬታዎቹ ሌላ መልክ እየያዙ ቀጥለዋል፡፡ ለምሳሌ በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ከዩኒቨርሲቲና ከከፍተኛ ሁለተኛ ትምህርት ቤቶች ወደ ድርጅቱ የተቀላቀሉ ወጣቶች “ኤርትራን ነጻ የሚያወጣው በላብ አደር መደብ የሚመራ ሀቀኛ አብዮት ነው” የሚል መፈክር በማንሳት ግንባሩ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም እንዲያውጅ ይወተውቱ ነበር፡፡ ይህም “ግንባሩ የማርክሲዝም ርዕዮተ ዓለም ተከታይ መሆኑን በይፋ ያሳውቅ” እንደማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል “የድርጅቱ አመራር በጉባኤ ያልተመረጠ ስለሆነ ጉባኤ ተደርጎ አዳዲስ መሪዎች ወደ አመራሩ መምጣት አለባቸው” የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ክፍሎች ነበሩ፡፡ በ1969 መጀመሪያ ላይ የጀብሃ አመራር ለመጀመሪያ ጊዜ ለጥያቄዎቹ አዎንታዊ ምላሽ ሰጠ፡፡ ቅሬታዎችም ሆኑ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚመለሱ ቃል ገባ፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ የሀይለ ሥላሤ መንግሥት በግንባሩ ላይ ሁለተኛ ዙር የማጥቃት ዘመቻ እያካሄደ ስለነበር ጉባኤው ከሁለት ዓመት በኋላ (1971) ሊደረግ እንደተወሰነ ለጠያቂዎቹ ተገለጸላቸው፡፡ ነገር ግን ጠያቂዎቹ በዚህ አልረኩም፡፡ “ቢያንስ አስቸኳይ ኮንፈረንስ መደረግ አለበት” በማለት ወተወቱ፡፡ የጀብሃ አመራር በዚሁ በመስማማቱ ኮንፈረንሱ በሳህል አውራጃ ውስጥ በሚገኘው “አርዳይብ”

በተባለ ቦታ ተካሄደ፡፡ በዚህ ኮንፈረንስ ላይ በውጊያ ላይ የነበሩት አንደኛና ሁለተኛ ዞኖች አልተሳተፉም፡፡ ሶስተኛ፣ አራተኛና አምስተኛ ዞኖች ብቻ ናቸው ከቦታው የተገኙት፡፡ በዚህም የተነሳ ከሶስቱ ዞኖች ወደ ጉባኤው የመጡ ታጋዮች የልባቸውን አውጥተው የሚናገሩበት ዕድል ተፈጠረ (እነዚህ ዞኖች በምስራቅና ደቡብ ኤርትራ በሚገኙ ቦታዎች የሚቀንሳቀሱ መሆናቸውን አስታውሱ፤ በጀብሃ ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ የነበሩትም በነዚህ ዞኖች ስር የተደራጁት ናቸው)፡፡ በኮንፈረንሱ ላይ ከደጋው የኤርትራ ክፍል ወደ ድርጅቱ የተቀላቀሉ ወጣቶች የዘመናት ብሶታቸውን ይፋ አውጥተው ተናገሩ፡፡ ለኤርትራ ነጻነት እፋለማሁ የሚለው ድርጅት የፋሺስት አዝማሚያ እየተከተለ ነው በማለት ኮነኑት፡፡ አሟሟታቸው የተደበቀ የበርካታ ታጋዮችን ስም እየጠሩ ጀብሃን አወገዙት፡፡ “ግንባሩ በአንድ ዓመት ጊዜ ራሱን ካላስተካከለ ከድርጅቱ እንወጣለን” የሚሉ መግለጫዎች ተሰሙ፡፡ የጀብሃ አመራሮች ጫናውን ለመቋቋም ከበዳቸው፡፡ “ሁሉንም እንጣራለን” በማለት ቃል ቢገቡም የተሰብሳቢዎቹን ልብ ለማግኘት አልቻሉም፡፡ በመጨረሻ ግን ሁሉም ከአመት በኋላ በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በመስማማት ተለያዩ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ የሁሉም ዞኖች ወታደራዊ መሪዎች የተገኙበት አስቸኳይ ኮንፈረንስ “አዶብሃ” በተባለ ስፍራ ተካሄደ፡፡ በኮንፈረንሱ ላይ ዱላ-ቀረሽ ክርክር ከተደረገ በኋላ ተቀማጭነቱ በሱዳኗ ከሰላ ከተማ የሆነው “ቃኢዳ ሰውራ” (አብዮታዊ እዝ) እንዲፈርስ ተወሰነ፡፡ ከያንዳንዱ ዞን ስምንት ወጣት ሰዎች የተመረጡበትና 40 አባላት ያሉት “ቃኢዳ አል-አማ” (ጠቅላይ መምሪያ) ተመሰረተ፡፡ ሆኖም የካይሮው ላዕላይ ምክር ቤት በነበረበት ይቀጥል ተባለ፡፡ የድርጅቱ መሪዎች እርምጃውን ህገ ወጥ ቢሉትም የ“አል-አማ” አባላት ግን ህጋዊ ነን በማለት በእርምጃቸው ቀጠሉበት፡፡

ከአዶብሃ ኮንፈረንስ በኋላ በአዶብሃ ኮንፈረንስ ከተሳተፉት መካከል የሶስቱ ዞኖች (ሶስተኛ፣ አራተኛ እና አምስተኛ ዞን) ታጋዮች ልብ ለልብ ተግባቡ፡፡ ውለው ሳያድሩም “ወታደራዊ ዞን” የሚባለውን አከፋፈል ለማፍረስ ተስማሙ፡፡ “የአንዱ ዞን ታጋዮች በሌላኛው ዞን እንዳሻቸው ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ ይችላሉ” በማለትም አሰመሩበት፡፡ ሊያጠቃቸው የሚመጣውን የመንግሥት ጦር ሀይል በህብረት ለመመከትም ተስማሙ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም በነዚህ ዞኖች ውስጥ ያሉ ታጋዮች “ሰልፊ ነጻነት” እና “ህዝባዊ ኃይሊ” በሚባሉ ቡድኖች ስር ራሳቸውን አደራጁ፡፡ “ህዝባዊ ኃይሊ” በአብዛኛው የምጽዋና የሰምሃር አካባቢ ተወላጆችን ያቀፈ ነው፡፡ ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም በፖለቲካም ሆነ በወታደራዊ ችሎታ አንቱ የተሰኙ ናቸው፡፡ ረመዳን መሐመድ ኑር፣ ኢብራሂም አፋ እና መስፍን ሐጎስ የቡድኑ መሪዎች ነበሩ፡፡ የዚህ ቡድን መንቀሳቀሻ ከምጽዋ በስተሰሜን የነበረው የባህር ጠረፍ ነበር፡፡ “ሰልፊ ነጻነት” ደግሞ በአብዛኛው የሐማሴን እና የአከለ ጉዛይ ተወላጆችን ነው ያቀፈ ነው፡፡ አብርሃም ተወልደ፣ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ሀብተሥላሤ ገብረ

መድህን፣ ሰሎሞን ወልደማሪያም፣ ወልደ ሚካኤል ኃይለ እና ባራኺ ንጉሡ የቡድኑ መስራቾች ናቸው፡፡ ኢሳያስ አፍወርቂ የዚህ ቡድን ጊዜያዊ መሪ ሆኖ ተሰይሟል፡፡ የቡድኑ ዋነኛ መንቀሳቀሻ በደቀምሐረ ወረዳ የሚገኘው “የዓላ በረሃ” ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ቡድኖች በይፋ ከጀብሃ መገንጠላቸውን ሳያሳውቁ ትግሉን በየፊናቸው ማካሄድ ጀመሩ፡፡ ጀብሀም ስሙን በድጋሚ ላለማስጠቆር እስከ ቀጣዩ ጉባኤ ድረስ የቡድኖቹን ሁኔታ በዝምታ መከታተሉን ቀጠለ፡፡ በሌላ በኩል ጀብሃ እስከ ዛሬ ድረስ የሚጸጸትበትን ታሪካዊ ስህተት የፈጸመው በዚሁ ወቅት ነበር፡፡ ይኸውም የዑሥማን ሳልሕ ሳቤ ከስልጣን መባረር ነው፡፡ የጀብሃ መሪዎች ሳልህ ሳቤ በደገኞች ላይ የሚፈጸመውን ኢ-ፍትሐዊ ቅጣት በመቃወሙ ቂም ይዘውበታል፡፡ በተጨማሪም ከዐረቦች የሚሰጣቸው እርዳታ ወደ ኤርትራ ምድር የሚገባው በርሱ በኩል በመሆኑ በቅናት ዐይን ይመለከቱት ነበር፡፡ ስለዚህ እርሱን አባርረው ሳሊህ አህመድ ኢያይ በሚባል ሰው ለመተካት ወሰኑ፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ በልባቸው ሳልህ ሳቤ “ሽርሽር እንጂ የበረሃ ትግል የማይችል ሰው በመሆኑ በሶሪያና ካይሮ ጎዳናዎች ተወስኖ ይቀራል” የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው፡፡ ውጤቱ ግን እነርሱ ከጠበቁት ውጪ ነው የሆነው፡፡ ሳልህ ሳቤ በኤርትራዊያን ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ ያገኘበትን ገድል ለመፈጸም የተነሳሳው የጀብሀ መሪዎች ይህንን እርምጃ ከወሰዱ በኋላ ነው፡፡ ሰውዬው ጀብሃዎች እንደገመቱት በዐረብ መዲናዎች አልቀረም፡፡ በቀጥታ ወደ ሳህል በረሃ መጥቶ “ህዝባዊ ሀይሊ” ከሚባለው ቡድን ጋር ነው የተቀላቀለው፡፡ የቡድኑ ታጋዮችም ወዲያውኑ በመሪነት ቦታ ላይ አስቀመጡት፡፡ ዑስማን ሳልህ ሳቤ በተለመደው የዲፕሎማሲ ጥበቡ ከዐረብ መዲናዎች የሚያሰባስበውን የጦር መሳሪያ ወደ ኤርትራ በረሃ እያመጣ “ህዝባዊ ሀይሊ” የተባለውን ቡድን እስከ አፍንጫው ድረስ አስታጠቀው፡፡ ሆኖም ቡድኑ ከፍተኛ የሰው ሀይል እጥረት ስላነበረበት ኢሳያስ አፍወርቂ በጊዜያዊነት ከሚመራው “ሰልፊ ነጻነት” ጋር በጋራ ግንባር ለመስራት መነጋገር ጀመረ፡፡ በውይይታቸው ወደ ስምምነት ተቃረቡ፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ከጀብሃ ታጋዮች መካከል የማሪያ ጎሳ ተወላጆች (የአቆርዳት አካባቢ ልጆች) የሆኑት ጥቂት ሰዎች “ጀብሃ ለቤኒ አምር ልጆች ያደላል” በሚል ቂም ቋጥረው ኖሮ ከጀብሃ ተገንጥለው ወደ ሳሕል ወረዱና ከሰልፊ ነጻነት እና “ህዝባዊ ኃይሊ” ጋር የጋራ ግንባር ፈጠሩ (ይህ የማሪያ ልጆች ቡድን “ዑበል” ይሰኛል)፡፡ ጀብሃ በ1971 ድርጅታዊ ጉባኤ ጠራ፡፡ የሁለቱ ዞኖች (ዞን አንድ እና ዞን ሁለት) ተወካዮች በጉባኤው ተገኙ፡፡ ከግንባሩ የወጡት ሶስቱ ቡድኖች ግን በጉባኤው ላይ እንደማይገኙ አስታወቁ፡፡ ጀብሃ ለጊዜው እነርሱን ችላ በማለት ጉባኤውን በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት አካሄደ፡፡ በጉባኤው ፍጻሜ ላይ በርካታ ስር-ነቀል እርምጃዎች ተወሰዱ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የጀብሃ መለያ ሆኖ የሚታወቀው “ሰውራዊ ባይቶ” (“አብዮታዊ ምክር ቤት” ማለት ነው- በትግረ ቋንቋ) የሚባለው የግንባሩ ላዕላይ ምክር ቤት በዚያ ጉባኤ ውሳኔ መሰረት ተፈጠረ፡፡ እነ ህሩይ ተድላ ባይሩን የመሳሰሉ ታዋቂ ደገኛ ግለሰቦች ወደ አመራሩ መጡ (ህሩይ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የጀብሃ ምክትል ፕሬዚዳንት ነው)፡፡ ተቀማጭነቱ ከሰላ ላይ የሆነው “አብዮታዊ እዝ” (ቃኢዳ ሰውራ) ህጋዊ ስለሆነ በዚያው ይቀጥል ተባለ፡፡ ሆኖም አላግባብ ሰው ገድለዋል የተባሉ የጦር መሪዎች ከስልጣን ተባረው በአዳዲስ ሰዎች ተተኩ፡፡ የጀብሃ መሪዎች ራሳቸውን እንዲህ ከቀያየሩ በኋላ “በድርጅቱ ውስጥ የነበረው ችግር ሙሉ በሙሉ ተፈቷል፤ ከዚህ በኋላ የሚያንገራግር ወይንም ቅሬታ አለኝ የሚል አካል ለኤርትራ ነጻነት እንቅፋት

ነው” የሚል አዋጅ አወጁ፡፡ በተጨማሪም በብዙዎች አንደበት ተደጋግሞ የሚጠቀሰውን “የኤርትራ መሬት ከአንድ ድርጅት በላይ አይችልም” የሚለውን የድርጅታቸውን መርህ በይፋ አሰሙ፡፡ በዚህም መሰረት በጉባኤው ላይ ካልተሳተፉት ሶስት ቡድኖች መካከል “ዑበል” እና “ህዝባዊ ኃይሊ” በሚባሉት ላይ ጥቃት ለመክፈት ወሰኑ፡፡ በ“ሰልፊ ነጻነት” ላይ የሚወሰደው እርምጃ ግን ለጊዜው እንዲዘገይ ተወሰነ (እንዲህ የተደረገው፣ በሁለት ምክንያት ነው ይባላል፤ አንደኛው ምክንያት “አብርሃም ተወልደ” የሚባለው የቡድኑ ዋነኛ ሰው ከጀብሃ ጋር ለመደራደር ፍላጎት እንዳለው በድብቅ መልዕክት ልኳል የሚል ነው፤ ሁለተኛውና ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ቡድኑ በአብዛኛው ክርስትያን የሆኑ ታጋዮችን ያቀፈ በመሆኑ ከባድ እርምጃ ከተወሰደበት “ጀብሃ ጸረ-ክርስቲያን ነው” የሚለው ፕሮፓጋንዳ ይጠናከራል በማለት ስለተፈራ ነው ይባላል)፡፡

ሻዕቢያ ተወለደ ጀብሃ በአንደኛው ድርጅታዊ ጉባኤ በተወሰነው መሰረት አፈንጋጮቹን ለማጥፋት ሰራዊቱን ወደ ሳሕል በረሃ አዘመተ፡፡ የዑበል እና “ህዝባዊ ኃይሊ” አባላት በሰፈሩበት ጎራ ላይ ጥቃት ተከፈተባቸው፡፡ ሆኖም ቡድኖቹ ነቅተው ይጠብቁ ስለነበር አጥቂው ሀይል ሲመጣባቸው በሰሜን አቅጣጫ ወደ ሱዳን ሸሹ፡፡ ይህንን ያየው የጀብሃ ሰራዊት “ሰልፊ ነጻነት” የሚባለውን ቡድን ሳይነካው ወደ ባርካ ተመለሰ፡፡ “ሰልፊ ነጻነት” በበኩሉ የጀብሃን እርምጃ “እኛን ለማታለል የተደረገ ነው” በሚል ስለወሰደው ሰራዊቱን በመያዝ በፊት ወደ ነበረበት የ“ዓላ በረሃ” (አከለ ጉዛይ አውራጃ/ደቀምሐረ ወረዳ) ተመለሰ፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከሳሕል የተባረሩት የዑበል እና “ህዝባዊ ኃይሊ” አባላት በዑስማን ሳልሕ ሳቤ መሪነት በቀይ ባህር አቋርጠው በደቡብ ኤርትራ “እምባሶይራ” በሚባለው ተራራ እንደመሸጉ ተሰማ፡፡ “የሰልፊ ነጻነት” ቡድን አባላት ከቦታው ድረስ ሄደው ከተቀበሏቸው በኋላ በፊት የተጀመረው በጋራ ግንባር የመስራት ጥያቄ በአጭር ጊዜ መልስ እንዲያገኝ ጠየቋቸው፡፡ የተቀሩት ቡድኖችም ጥያቄውን በደስታ በመቀበላቸው ቤይሩት ላይ ህብረቱ እንዲታወጅ ተወሰነ፡፡ በዚህም መሰረት በ1972 በቤይሩት ከተማ የጋራ አወጁ፡፡ ለአሰራር ያመቻል ስለተባለም “ተጋድሎ ሓርነት ኤርትራ” የሚለው የቀድሞው የድርጅታቸው ስም በነበረበት እንዲቀጥልና በስሙ ላይ “ህዝባዊ ሓርነት ኃይልታት” የሚል ቅጥያ እንዲጨመርበት ተወሰነ (በእንግሊዝኛ Eritrean Liberation Front-Popular Liberation Forces ተብሎ ነበር የሚጠራው)፡፡ ቡድኖቹ የግንባሩ አመራር ወደፊት እንዲመረጥም ነው የተስማሙት፡፡ “ኦሥማን ሳልሕ ሳቤ” ግን የግንባሩ የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ እንዲቀጥል በአንድ ድምጽ ወስነው ነበር፡፡ ይህ ግንባር በታሪክ ምዕራፎች በአጭሩ “ህዝባዊ ኃይልታት” ተብሎ ነው የታወቀው፡፡ ብዙዎች እርሱን የሚያውቁት ግን “ሻዕቢያ” በሚል የዐረብኛ ስሙ ነው (“ሻዕቢያ” ህዝባዊ ማለት ነው-በዐረብኛ፤ ነገር ግን ይህ የመጀመሪያው “ሻዕቢያ” አሁን ካለው “ሻዕቢያ” ይለያል)፡፡ “ህዝባዊ ኃይልታት” በሳሕልና በዓላ በረሃዎች እንቅስቃሴውን ሲጀምር “ጀብሃ” በከፍተኛ ሽብር ውስጥ ወደቀ፡፡ ይህ አዲስ የበቀለው ግንባር በእንጭጩ ካልተቀጨ ለስልጣኔ ያሰጋኛል በሚል ደመደመ፡፡ በተለይም የጀብሃ መሪዎች ዑስማን ሳልህ ሳቤ የግንባሩ የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ መሰየሙን በዝምታ ሊያልፉት አልፈለጉም፡፡ ስለዚህ የልባቸውን ለማድረስ ሰራዊታቸውን ወደ ሳሕል በረሃ አዘመቱት፡፡ ሆኖም ጀብሃዎች በአዲሱ ግንባር ተሸነፉ፡፡ እንደገና ጥቃት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡ ዓመቱን በሙሉ ከህዝባዊ ሀይልታት ጋር ቢዋጉም ውጤቱ ሊቀየር አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎም በስተመጨረሻ በአዲሱ ግንባር ሙሉ በሙሉ በመሸነፋቸው ከሳሕል በረሃ ተጠራርገው ወደ ባርካ አውራጃ ገቡ፡፡ አዲሱ “ህዝባዊ ኃይልታት” ጀብሃን እንዲህ ከመከተ በኋላ ግን አንድነቱን ማስጠበቅ አልቻለም፡፡ “ዑበል” የተሰኘው ቡድን አባላት “በግንባሩ ውስጥ ተሰሚነት የለንም፤ በሌሎቹ ተውጠናል” የሚል ቅሬታ ስለተፈጠረባቸው ከአንድነት ግንባሩ በመውጣት በባርካ አውራጃ የራሳቸውን የውጊያ ግንባር

ለመክፈት ወደ ትውልድ መንደራቸው ሄዱ፡፡ ሆኖም በመንገድ ላይ ባልተጠበቀ ሁኔታ በጀብሃ ሰራዊት ቀለበት ውስጥ ገቡ፡፡ ጀብሃዎችም አንዳቸውንም ሳያስተርፉ ፈጁአቸው፡፡ በዚህም የ“ዑበል” እንቅስቃሴ ታሪክ አከተመ፡፡ በ“ህዝባዊ ኃይልታት” ውስጥ የቀሩት “ህዝባዊ ኃይሊ” እና “ሰልፊ ነጻነት” ወደ ውህደት ለመሸጋገር ከጫፍ ላይ ደረሱ፡፡ ሆኖም ሁለት ያልታሰቡ እንግዳ ክስተቶች ገፍተው ስለወጡ የውህደቱን እርምጃ ገቱት፡፡ ታዲያ እነዚህ እንግዳ ነገሮች መሰረታቸውን የጣሉት ሶስቱ ቡድኖች ከጀብሃ በይፋ ተነጥለው ከመውጣታቸው በፊት ነው፡፡ ከነዚህ ክስተቶች መካከል አንደኛው የኤርትራ ገዥ የነበሩት ልዑል ራስ አስራተ ካሳ ጀብሃን ለማጥፋት ከሰልፊ ነጻነት ጋር በስውር በተዋዋሉት መሰረት ኢሳያስ አፈወርቂን የመሳሰሉ የቡድኑ መሪዎች “ጀብሃን እስከ መጨረሻው መደምሰስ አንጂ መታረቅ አይታሰብም” የሚል አቋም ይዘው መገኘታቸው ነው፡፡ ሁለተኛው እንግዳ ክስተት ደግሞ ሲ.አይ.ኤ. በ1970 ከኢሳያስ አፍወርቂ ጋር በሚስጢር ተገናኝቶ የቀበረው ፈንጂ እየፈነዳ ማስቸገሩ ነው፡፡ የዚህ የሲ.አይ.ኤ ፈንጂ የአጭር ጊዜ ዓላማ በፍልስጥኤም ነጻ-አውጪ ድርጅት ደጋፊነት የተጠረጠረውን ጀብሃን ማዳከም ነው፡፡ የረጅም ጊዜ ዓላማው ኤርትራን አስገንጥሎ በአንድም ወቅት ከሌሎች ሀገራት ጋር በስምምነት መኖር የማትችል ሀገር ማድረግ ነው (ስለራስ አስራተ ካሳ ሴራ እና በሲ.አይ.ኤ ስለተቀበረው ፈንጂ የሴራው ተባባሪ በነበሩት አቶ ተስፋሚካኤል ጆርጆ የተጻፈውን ጽሑፍ ከዚህ በፈት አቅርቤው ነበር፡፡ ኦሪጂናሉን ዶክመንት ለማግኘት ይህንን ሊንክ ይክፈቱት http://www.ehrea.org/TesfaMikegiorgioAmarina.pdf) እነዚህ ሁለት ጎታች ድርጊቶች ሚስጢራዊ በሆነ መንገድ የተጫወቱት ሚና “ህዝባዊ ኃይልታት” ወደ አንድ ግንባር ለመለወጥ የተደረገውን ጥረት ገድለውታል፡፡ በሌላ በኩል ግን በ“ህዝባዊ ኃይልታት ኤርትራ” ውስጥ የሚገኙት አንዳንድ ስም ያላቸው መሪዎች ከጀብሃ ጋር የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም ጥረታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ የአስመራ ከተማ ህዝብም “እስከ መቼ በካራ ትተራረዳላችሁ?” በማለት ሽማግሌዎችን ወደ ሁለቱም ግንባሮች መላካቸው በታሪክ ገጾች ይታወቃል፡፡ የሽማግሌዎቹ ጥረት ስለሰመረ ጀብሃ እና “ሻዕቢያ” (ህዝባዊ ኃይልታት) በ1975 የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገዋል፡፡ ሁለት መሪዎች ደግሞ ከዚህም ይበልጥ ገፍተው ሄደው ከጀብሃ ጋር ውህደት ለመፈጸም ጥረት አድርገው ነበር፡፡ እነርሱም አብርሃም ተወልደ እና ዑስማን ሳልህ ሳቤ ነበሩ፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ከጀብሃ ጋር ያለው ችግር በሰላም ተፈትቶ የኤርትራ ታጋዮች ሁሉ ወደ አንድ ግንባር መምጣት አለባቸው በማለት ጥረት ያደረገው አብርሃም ተወልደ ነው፡፡ ሆኖም አብርሃም በ1971 እስከ ዛሬ ድረስ እንቆቅልሽ በሆነ መንገድ ሲሞት ጥረቱ በአጭሩ ተቀጨ (እንደሚባለው ከሆነ አብረሃም በነ ኢሳያስ አፍወርቂ ተመርዞ ነው የተገደለው)፡፡ በ1975 ግን ዑስማን ሳልሕ ሳቤ በከፍተኛ ድፍረትና ልበ ሙሉነት ከጀብሃ ጋር ወደ አንድ ግንባር የመጠቃለሉን ጉዳይ አንቀሳቀሰ፡፡ ጥረቱ ስለሰመረ ከዓመት በኋላ በካርቱም ከተማ ከጀብሃ ጋር የትብብርና የጋራ ግንባር የመፍጠር ስምምነት ተፈራረመ፡፡ ሆኖም ስምምነቱ ዘላቂ ሊሆን አልቻለም፡፡ በሀገር ቤት ያሉት እነ ኢሳያስ አፍወርቂ “ሳልህ ሳቤ የውጪ ጉዳይ ኃላፊ እንጂ የግንባሩ መሪ አይደለም” በማለት ስምምነቱን ውድቅ አድርገውበታል፡፡ በዚህም የቁርጥ ቀን ወዳጃቸው ከሆነው ሳልህ ሳቤ ጋር እስከወዲያኛው ለመቆራረጥ በቅተዋል፡፡

በነዚህ እርምጃዎች የተነሳ በጅምሩ ላይ የሶስት ቡድኖች ጥምረት የነበረው “ህዝባዊ ኃይልታት” በስተመጨረሻ “ሰልፊ ነጻነት” በተሰኘው ቡድን ቁጥጥር ስር ገባ፡፡ ይህ ቡድን በዚሁ ስም (ህዝባዊ ኃይልታት) ራሱን ሲጠራ ከከረመ በኋላ በ1977 የመጀመሪያ ጉባኤውን አካሄደ፡፡ በጉባኤው በተወሰነ ውሳኔ መሰረት ስሙን ትንሽ ለወጥ ለማድረግ “ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ”/Eritrean People’s Liberation Front በሚል ተጠራ፡፡ ረመዳን መሐመድ-ኑር ዋና ጸሐፊ ሆኖ ተመረጠ፡፡ ግንባሩን በሙሉ ሀይል የመምራት ስልጣን ግን “ምክትል ዋና ጸሓፊ” ተብሎ በተሰየመው ኢሳያስ አፍወርቂ ተጠቀለለ፡፡

የ“ብጽኣይ” እንቅስቃሴ በሻዕቢያ ውስጥ የፈነዳው የመንካዕ ንቅናቄ ከተዳፈነ በኋላ የድርጅቱ ታጋዮች ማጉረምረማቸውን አላቆሙም፡፡ በተለይ የመንካዕ መሪዎችን የገጠማቸው ሰቆቃ የተመላበት እስርና የሞት ቅጣት ብዙዎቹን አስከፍቷል፡፡ ሆኖም ታጋዩ እርስ በራሱ ይጠራጠር ስለነበር ድምጹን ከፍ አድርጎ አላሰማም፡፡ በዕድሜው ጠና ያለ አንድ ታጋይ ግን “ድርጅቱ ውስጣዊ ዲሞክራሲ እንዲኖረው አደርጋለሁ” በማለት የበኩሉን ጥረት ለማድረግ ተነሳ፡፡ ያ ታጋይ ጎይቶም በርሄ ይባላል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሩቅ ነው፡፡ ሻዕቢያን የተቀላቀለው በ1972 ነው፡፡ ይህ ሰው ከፍተኛ የሆነ የስነ-ጽሑፍና የርዕዮተ ዓለም ትንታኔ ችሎታ ነበረው፡፡ በዘመኑ እጅግ በጣም ይፈለጉ የነበሩትን ማርክሳዊና የዲያሌክቲክ ፍልስፍና መጻሕፍትን ከውጪ ቋንቋዎች ወደ ትግርኛ ተርጉሟል፡፡ እርሱ ራሱ ከጻፋቸው ኦሪጂናል ጽሑፎች መካከል ደግሞ “መን እዩ ብፅአዊ? መን እዩ ሰውራዊ?” (“ጓድ” ማለት ማን ነው? አብዮታዊውስ ማን ነው?) የሚል ርዕስ ያለው ባለ 30 ገጽ መጣጥፍ ከፍተኛ ተቀባይነት እንደነበረው የታሪክ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ሻዕቢያ የርሱን ጽሑፎች ታጋዩን ለማስተማር ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ይህ ሰው በዕድሜውም ሆነ በተሰጥኦው አንቱታን ያገኘ ስለሆነ ሁሉም ታጋዮች “ብጽአይ” (ጓድ) በማለት ነበር የሚጠሩት፡፡ “ብጽአይ” ጎይቶም በመንካዕ ንቅናቄ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ አላደረገም፡፡ ሆኖም ውጥረቱን እንዲሸመግሉ ከተመረጡ ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ እነ ኢሳያስ የመንካዕ መሪዎችን በከባድ ቅጣት ዝም ሲያሰኟቸው ግን “የተሰጠው ፍርድ ኢ-ፍትሓዊ ነው” በሚል ተቃውሞ አሰምቷል፡፡ በዚህም ከሃላፊነት እንዲወርድ ተደርጓል፡፡ ታዲያ ብፅአይ ጎይቶም ስልጣኔን ተቀማሁ ብሎ ወደ

ኩርፊያ አልሄደም፡፡ ድምጹን አጥፍቶ በድርጅቱ ውስጥ ዲሞክራሲ የሚሰፍነበትን መንገድ ያውጠነጥን ነበር፡፡ በ1975 መጨረሻ ላይም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነበሩ ጥቂት ጓዶች ግንባሩን ሲቀላቀሉ ከነርሱ ጋር መቀራረብ ጀመረ፡፡ ከተማሪዎቹ ጋር ባደረገው ውይይትም “ድርጅቱን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ አለብን” የሚል አጀንዳ አስታጠቃቸው፡፡ እነዚያ ወጣቶችም የርሱን ሀሳብ ማቀንቀን ጀመሩ፡፡ በዚህ ነጥብ ዙሪያ ታጋዩን ማወያየትና ድጋፍ ማሰባሰብ ሞከሩ፡፡ አንዳንዶች ወደነርሱ ተጠጉ፡፡ ብዙዎቹ ግን የመንካዕ ትውስታ ከአዕምሮአቸው ያልጠፋ በመሆኑ ወደ ብጽአይ ጎይቶምና ጓዶቹ ለመጠጋት አልፈቀዱም፡፡ እነ ብጽአይ ግን ጥረታቸውን ቀጠሉ፡፡ በርካታ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ድጋፍ ሰጡአቸው፡፡ ሆኖም ዓላማቸውን በሚያስፈጽሙበት መንገድ ላይ በመምከር ላይ ሳለ ግን በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ የስለላ መረቡን በሁሉም የሻዕቢያ ታጋዮች ላይ እንደ ሸረሪት ድር ያደራው የ“ሀላዋ ሰውራ” አዳኞች በቀላሉ “ቀጨም” አደረጓቸው፡፡ የንቅናቄው መሪዎችና ተባባሪዎች የተባሉት በሙሉ እየተፈለጉ ታሰሩ፡፡ የ“ሀለዋ ሰውራ” ኃላፊዎች ብጽአይ ጎይቶምንና ጓዶቹን ለአራት ዓመታት በእስር ካቆዩአቸው በኋላ በ1980 በሞት ቀጡአቸው፡፡ ብጽአይ ጎይቶም የተረጎማቸው መጻሕፍትና በራሪ ወረቀቶችም ከያሉበት እየተሰበሰቡ ተቃጠሉ፡፡ በጎይቶም ጽሑፎች የተበላሸውን የታጋይ አዕምሮ ለማደስ በሚልም ስታሊናዊ የሶሻሊዝም ፍልስፍና ድርሰቶች በብዛት እንዲተረጎሙ ተደረጉ (የትርጉም ስራውን በዋናነት ያከናወነው በ1985 ገደማ በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር የነበረውና አሁን በሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕክተኛ ሆኖ የሚያገለግለው ሀይሌ መንቆርዮስ እንደሆነ ይነገራል)፡፡ ይህ ብዙ ሳይራመድ በእንጭጩ የተቀጨው ንቅናቄ “ብፅአይ ምንቕስቓስ” ይባላል፡፡ “የጓዱ እንቅስቃሴ” ማለት ነው፡፡ “ጓድ” ወይንም “ብፅአይ” ተብሎ የሚጠራው ጎይቶም በርሄ ነው፡፡ ከርሱ ጋር በቅርበት ሆኖ እንቅስቃሴውን መርቷል የሚባለው ደግሞ ዓለም አብርሃ የተባለ ታጋይ ነው፡፡ እነዚህ ጓዶች እንደ “መንካዕ” ንቅናቄ መሪዎች “የድርጅቱ አመራር ከስልጣን ይውረድልን” አላሉም፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ለመጠየቅ ብቻ ነበር የተነሱት፡፡ ሆኖም የሰልፊ ነጻነት መሪዎች በእንቅስቃሴው አልተደሰቱም፡፡ እንዲያውም የድርጅቱን ህልውና የሚያናጋ መናፍቃዊ ንቅናቄ አድርገው ነው የወሰዱት፡፡ ሻዕቢያዎች “የብፅአይ ምንቕስቃስ” መሪዎች “የኤርትራ አብዮታዊ ፓርቲ (ERP) የተባለ ህገ-ወጥ ፓርቲ በግንባሩ ውስጥ አቋቁመዋል፤ የታወቀውን የግንባሩን ሶቪየት ቀመስ የርዕዮተ ዓለም አቅጣጫ በመቀልበስ የሊቀመንበር ማኦ ዜዱንግን መስመር ለማስፈን ሞክረዋል፤ በመሆኑም የሞት ቅጣት መፈጸሙ በግንባሩ ህግ መሰረት ተገቢ ነው” ይላሉ፡፡ ሆኖም ይህ “የኤርትራ አብዮታዊ ፓርቲ” የተሰኘ ፓርቲ በግንባሩ ውስጥ ስለመፈጠሩ ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ በዚህ ንቅናቄ ጦስ ታስረው ህይወታቸው ካለፈው ታጋዮች መካከል ጎይቶም በርሄ (“ብፅአይ”)፣ ዓለም አብረሃ፣ መሲህ ርዕሶም፣ ተክላይ ገብረ ክርስቶስ፣ ሚካኤል በረከተአብ፣ ሀይሌ ዮሐንሶም፣ ሳሙኤል ገብረ ድንግል፣ በረከት ሀይሌ፣ ሀይሌ ሀብተጽዮን እና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡ ተወልደ እዮብ የሚባለው የቀድሞው የድርጅቱ ቁልፍ ሰውም ከነዚህ ሴረኞች ጋር አብረሃል በሚል በጥይት ተደብድቦ ተረሽኗል (እነዚህ ታጋዮች የተረሸኑት በ1980 ሳሕል በረሃ ውስጥ በሚገኘው አራግ በተሰኘ ቀበሌ ነው)፡፡ === የ“የማናዊ” (ቀኝ መንገደኞች) እንቅስቃሴ====

ይህኛው እንቅስቃሴ የብጽዓይ ንቅናቄ ተከታይ ሆኖ ነው የፈነዳው፡፡ ንቅናቄው የተካሄደው “ሰልፊ ነጻነት” እና “ህዝባዊ” ሀይሊ በይፋ ተዋህደው “ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ” የተሰኘውን ግንባር መፍጠራቸው ከተነገረበት ጊዜ ትንሽ ቀደም ብሎ ነው (በተጨማሪም በዚያ በወቅት (1977-78) ብዙዎቹ የኤርትራ ከተሞች ከመንግሥት እጅ በመውጣት በሻዕቢያ እና ጀብሃ ቁጥጥር ስር ገብተው ነበር)፡፡ በዚህ ንቅናቄ ገፍቶ የወጣው ዋነኛ ጥያቄ “በግንባሩ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣው ሙስናና ብልሹ አሰራር ይወገድ” የሚል ነው፡፡ ይሁንና የዚህ ንቅናቄ ጀማሪ ማን እንደሆነ በትክክል አይታወቅም፡፡ በንቅናቄው ውስጥ ከተሳተፉት ግንባር ቀደም መሪዎች መካከል ዶ/ር እዮብ ገብረ-ልዑል፣ መሓሪ ግርማ-ጽዮን፣ ገብረ-ሚካኤል መሐሪ-እዝጊ፣ ህብረት ተስፋ-ጋብር፣ ኪዳኔ አቤቶ፣ ፍሥሐዬ ኪዳኔ፣ አርአያ ሰመረ፣ አማኑኤል ፊላንሳ የተባሉት ይጠቀሳሉ (ብዙዎቹ በአውሮጳ ሀገራት የተማሩ ናቸው)፡፡ የሻዕቢያ መሪዎች በንቅናቄው የተሳተፉ ታጋዮችን “የቀይ መንገደኛነት ፈለግ ተከታዮች” በማለት ይጠሯቸዋል፡፡ እነዚያ የንቅናቄ መሪዎች ጥያቄዎቻቸውን ለሻዕቢያ አመራር ባቀረቡ ማግስት ነው የታሰሩት፡፡ ታዲያ ንቅናቄው ከተዳፈነና ሻዕቢያ አንደኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ካካሄደ በኋላ የቀድሞ የግንባሩ ቀንደኛ መሪ እና የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሓፊ የነበረው ሰለሞን ወልደማሪያምም ከንቅናቄው ጋር ንክኪ አለው ተብሎ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ የግንባሩ ዋነኛ መርማሪ የነበረው ሀይሌ ጀብሃም በዚያው ወቅት እንዲታሰር ተደርጓል፡፡ ሀይሌ ጀብሃ የታሰረው “በእስረኞች ላይ ከመጠኑ ያለፈ ኢ-ሰብአዊ ሰቆቃ ይፈጽማል” በሚል ምክንያት ነው፡፡ በርግጥም በርካታ ኤርትራዊያን ስለርሱ ጭካኔና ገዳይነት በሰፊው ጽፈዋል፡፡ ለምሳሌ እውቁ ኤርትራዊ ምሁር ዶ/ር በረከት ሀብተስላሴ በቅርቡ ከአንድ ድረ-ገጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሀይሌ ጀብሃ አንዱን እስረኛ በብትር ጭንቅላቱን እየቀጠቀጠ ሲመረምረው ማየታቸውን መስክረዋል፡፡ ሰለሞን ወልደማሪያም የታሰረበት ምክንያት ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ሰለሞን ወልደማሪያም በግንባሩ ውስጥ የነበረው ተፈላጊነት እየቀነሰ መምጣቱን የሚያሳዩ ምልክቶች የታዩት ቀደም ብለው ነው፡፡ ለምሳሌ በ1975 መጨረሻ ላይ ለህክምና ፖርት ሱዳን ደርሶ ከተመለሰ በኋላ ቁልፍ ከሆኑ የድርጅቱ የስልጣን ቦታዎች ተገፍቶ የካድሬ ትምህርት ቤት አሰልጣኝ እንዲሆን ተመድቧል፡፡ የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሓፊነቱንም ከህዝባዊ ሀይሊ ለመጣው ዓሊ ሰዒድ አብደላ አስረክቧል፡፡ እርሱ ግን የድርጅቱ ጉባኤ እስኪካሄድ ድረስ የግንባሩ መሪዎች ይከዱኛል የሚል ጥርጣሬ አልነበረውም፡፡ ለሰለሞን ሁሉም ነገር ፍንትው ብሎ የታየው 37 አባላት ያሉት የማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡ በዚያ ምርጫ ላይ ሰለሞን በእጩነት ሲጠቆም ካድሬው በከፍተኛ ጩኸት ተቃውሞውን እንደገለጸ ይወሳል፡፡ አንዳንድ ካድሬዎች ከመቀመጫቸው እየተነሱ “ይህ ሰው የቀኝ መንገደኞቹ አንጃ መሪ ነው፤ ለርሱ እስር ቤት እንጂ ስልጣን አይገባውም” የሚል ሐሳብ መስጠታቸው ተመዝግቧል፡፡ በዚህም ሳቢያ ከኢሳያስ አፈወርቂ በፊት ወደ ዓላ በረሃ ሄዶ ከጥቂት ወጣቶች ጋር “ሰልፊ ነጻነት” የተባለውን ቡድን የመሰረተው ሰለሞን ወልደማሪያም “አዛዥ ናዛዥ” ሆኖ ብዙዎችን ካንቀጠቀጠበት መንበረ ስልጣን ላይ ተገፍትሮ ወደታች ተወርውሯል፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ ሰለሞንን ከስልጣኑ ያስነሳው “ይህ ወጣት በድርጅቱ ውስጥ ቁልፍ የሆኑ ቦታዎችን በመዳፉ ጠቅልሎ በመያዙ ወደፊት ከሊቀመንበርነቴ ያባረኛል” የሚል ስጋት ስለገባው መሆኑን ታሪኩን የሚያውቁ ምስክሮች ያስረዳሉ፡፡ በርግጥም ሰለሞን በሰልፊ ነጻነት ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ

ሰው ነበር፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ የቡድኑ መሪ ሆኖ ቢቀመጥም ድርጅቱን በቀጥታ የሚመራው ሰለሞን ወልደማሪያም ነበር፡፡ በወቅቱ የድርጅቱ አባል የነበሩት አቶ አድሓኖም ፍትዊ የተባሉ ኤርትራዊ በጊዜው የነበረውን የስልጣን ክፍፍል ሲያስረዱ “ሰለሞን ሁሉንም ነገር ነበር፤ የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሐፊ ነው፡፡ ወታደራዊ አዛዥም ነው፤ የስልጠና ማዕከል ሀላፊም ነው፤ የጠቅላይ እዙ የበላይ አዛዥም ነበር፤ በግንባር ያለውን ጦር የሚያንቀሳቅሰው እርሱ ነው፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ ለስም ብቻ ነው ሊቀመንበር ሆኖ የተቀመጠው” በማለት አስረድተዋል፡፡ ታዲያ ኢሳያስ ሰለሞንን ከስልጣን ያስነሳው ብልጠት በተመላበት ዘዴ ነው፡፡ ሰለሞን ለረጅም ጊዜ የጉበት በሽተኛ እንደሆነ ስለሚታወቅ “እስከዛሬ ድረስ ለኛ ስትል ደክመሃል፤ አሁን ግን መታከም አለብህ፤ ህክምና እያለ መሞት የለብህም፤ ሱዳን ሄደህ ከፍተኛ ሐኪም መጎብኘት አለብህ” አለው፡፡ በተጨማሪም “ኡሥማን ሳልህ ሳቤ የድርጅታችንን የእርዳታ መስመር ስለዘጋብን ወደ ውጪ ሄደህ እርሱንም ማስከፈት አለብህ፤ ይህንን ማድረግ የምትችለው አንተ ብቻ ነህ” በማለት አከለበት፡፡ ሰለሞን የኢሳያስን ምክር ሲሰማ በልቡ ኩራት ተሰማው፡፡ “ለካስ እንዲህ ዓይነት ትልቅና ተፈላጊ ሰው ኑሬአለሁ?” በማለት ተንጠራራ፡፡ ወዲያኑ ስልጣኑን በሙሉ ለኢሳያስና ለተከታዮቹ አስረክቦ ወደ ፖርት ሱዳን ሄደ፡፡ እነ ኢሳያስም የርሱን እግር ተከትለው በድርጅቱ ቁልፍ ቦታዎች ላይ ሰዎቻቸውን አስቀመጡ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የሰለሞንን ግለኝነትና የስልጣን ጥመኛነት የሚያስረዳ ፕሮፓጋንዳ በሰፊው ተናፈሰ፡፡ ታዲያ ታጋዩም ሰለሞንን በፊቱኑ ይጠላው ነበርና ፕሮፓጋንዳውን ሲሰማ “ይህ አምባገነን! እርሱ ነው ለካስ ሁሉንም ሲቆላልፍ የነበረው” በማለት ተራገመ፡፡ ሰለሞን ህክምናውን ጨርሶ ከሱዳን መጣ፡፡ እነ ኢሳያስ ስልጣኔን ያስረክቡኛል ብሎ ሲጠብቅ “ላንተ እረፍት ስለሚያስፈልግህ የድርጅቱ ጉባኤ እስኪካሄድ ድረስ ቀለል ባለው የካድሬ ስልጠና ስራ ላይ መድበንሃል” አሉት፡፡ ሰለሞንም ምንም ሳይጠራጠር በስልጠና ስራ ላይ ተሰማራ፡፡ የድርጅቱ ጉባኤ ተካሂዶ በድርጅታዊ መንገድ በተካሄደው ምርጫ ከአመራሩ ሲወገድ ግን ከእንቅልፉ ባነነ፡፡ “የገዛ ወዳጆቼ ተጫወቱብኝ እያለ” ተቆጨ፡፡ ከዚያ በኋላ ነገረ-ስራው ሁሉ የግንባሩን መሪዎች በአደባባይ መሄስና ማብጠልጠል ሆነ፡፡ እርሱ ራሱ ያጠፋቸውንም ጥፋቶች በግልጽ ማውገዝ ጀመረ፡፡ በተለይ በከረን ከተማ በተደረገ ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ስለ መንካዕ ንቅናቄ መሪዎች ሲጠየቅ “የተሰጠው ፍርድ ትክክል አይደለም፤ የህዝብ ልጆችን ገድለን ቀብረናል” የሚል ምላሽ ሰጠ፡፡ ታዲያ እርሱ በየወረዳው እየሄደ የሚናገረው ንግግር ወደነ ኢሳያስ ይደርስ ሰለነበር መላ እንዲበጅለት ተወሰነ፡፡ ካድሬዎች በድርጅቱ ጉባኤ ላይ ያነሱትን ክስ እንደ አዲስ በማንቀሳቀስ “የየማናዊ ምንቓስቓስ ደጋፊ ነህ” ተብሎ ታሰረ፡፡ ለአራት ዓመታት በሀለዋ ሰውራ ከቆየ በኋላ በ1983 ሳህል ውስጥ ሀክሺብ በተባለ ስፍራ ተረሸነ፡፡

በሰለሞን ወልደማሪያም ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ አይበዛበትም፡፡ ይህ ፍርድ እርሱ ራሱ በ“ሀለዋ ሰውራ” ሲፈጽመው ከነበረው ምህረት የለሽ ሰቆቃ እና ርሸና ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ችግሩ ግን ፍርዱ በስነ-አመክኖአዊ መንገድ ያልመጣ መሆኑ ነው፡፡ የሻዕቢያ ሰዎች ሰለሞንን የረሸኑት በኢሳያስ አፈወርቂ ስልጣን ላይ አደጋ የደቀነ ሆኖ በመገኘቱ ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪም ሰለሞን ከስልጣን ከተወገደ በኋላ በሄደባቸው ቦታዎች ባይለፈልፍ እና ታማኝ መስሎ ስራውን ቢቀጥል ኖሮ ሻዕቢያዎች “ከስልጣን ተወግዶ እንኳ ሞራሉ ያልተነካ፤ ለስልጣን

የማይስገበገብ ትክክለኛው የህዝብ ልጅ” በማለት በአንድ ቦታ ላይ ይሸጉጡት እንደነበር አያጠራጥርም፡፡ ይሁንና ሰለሞን እንደ ጓዶቹ ብልህ ሆኖ አልተገኘም፡፡ እዚያው “ሀለዋ ሰውራ” ውስጥ ተደራራቢ ስቃይ አይቶ፣ በቅማልና በትኋን ከተበላ በኋላ የመቀበሪያ ጉድጓዱን ራሱ ቆፍሮ በጥይት ተሰናብቷል (በየማናዊ ንቅናቄ ሰበብ የተያዙ ታጋዮች ከርሱ ቀደም ብለው በ1980 ነው የተረሸኑት፡፡ ሀይሌ ጀብሃም ከነርሱ ጋር ነበር የተገደለው)፡፡ በእስከ አሁኑ ትረካዬ እንዳያችሁት “ሀለዋ ሰውራ” የሚል ስም ደጋግሜአለሁ፡፡ በዚህ ስም የሚጠራው በሻዕቢያ ውስጥ እጅግ የሚፈራ ተቋም ነው፡፡ ለመሆኑ ይህ ብዙ ያልተጻፈለት ተቋም ምን ይመስላል? ወደፊት እናየዋለን፡፡

በዚህ ክፍል አስቀድሜ ቃል በገባሁት መሰረት ስለ አንድ የሻዕቢያ ተቋም በመጠኑ እናወጋለን፡፡

ሀለዋ ሰውራ “ሀለዋ ሰውራ” የተሰኘ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት በበዓሉ ግርማ “ኦሮማይ” ውስጥ ነው፡፡ የኦሮማዩ “ስዕላይ በራኺ” የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሓፊ ነው በሚል በድርሰቱ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ ነገሩ ግን ልብ ወለድ ነው፡፡ ስዕላይ በተሰኘ ስም የተጠቀሰው ገጸ-ባህሪ የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሃፊ ሆኖ አያውቅም፡፡ ሆኖም የእስር ቤቱ ሃላፊ ነበር፡፡ ታዲያ ስለሻዕቢያ ሀለዋ ሰውራ የሚያውቀውን ሚስጢር ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ለህዝብ የገለጸው ይኸው በበዓሉ ብዕር “ስዕላይ በራኺ” ተብሎ የተጠራው ሰው ነው፡፡ የዚህ ሰው ትክክለኛ ስም ተክላይ ገብረማሪያም ነው፡፡ በሻዕቢያ ውስጥ ይበልጥ የሚታወቀው ግን “ተክላይ አደን” በተሰኘው የበረሃ ስም ነው፡፡ ተክላይ የሻዕቢያ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበር፡፡ በ1981 (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1973) ከሻዕቢያ ከድቶ ለደርጎች እጁን ከሰጠ በኋላ ከኢትዮጵያ ሬድዮ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “ሀለዋ ሰውራ” ስለሚባለው የሻዕቢያ ሚስጢራዊ ተቋም የሚያውቀውን ሁሉ ዘርዝሯል፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ ስለ “ሀለዋ ሰውራ” የሚያውቁትን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የተዘረዘረው መረጃ የተገኘው ግን ከልዩ ልዩ የኤርትራ ድረ-ገጾች፣ ከመጽሔቶችና ከጋዜጦች ነው፡፡ በነገራችን ላይ ተክላይ በ“ኦሮማይ” ውስጥ የተጠቀሰውን የሻዕቢያ ስውር አርበኛነት ሚና አልተጫወተም፡፡ በዓሉ “ኦሮማይ” ብሎ የገለጸው አደገኛ ተልዕኮ ልብ ወለድ ነው፡፡ እውነተኛው ተክላይ አደን በደርግ መንግሥት ዘመን በልዩ ልዩ ቢሮዎች ሲሰራ ከሰነበተ በኋላ ደርግ ሲወድቅ ወደ ኔዘርላንድ ሸሽቷል፡፡ የዛሬ አስር ዓመት ገደማም በስደት ባለበት ሀገር ህይወቱ አልፏል፡፡ ***** የኤርትራ ሰዎች “ሀለዋ ሰውራ” የሚባለውን ተቋም Gestapo ከሚባለው የናዚ ጀርመኖች የስለላና የአፈና ድርጅት ጋር ያመሳስሉታል፡፡ ሆኖም “ሀለዋ ሰውራ”ን በዚያ ደረጃ ለመፈረጅ ያዳግታል፡፡ ቢያንስ ጉልበቱና አቅሙ ከዚያ ያንሳሉ፡፡ ይሁንና በሀለዋ ሰውራም በርካታ ሰዎች መሰቃየታቸውን ይናገራሉ፡፡ “ሀለዋ ሰውራ” በቀጥታ ሲተረጎም “አብዮት ጥበቃ” ማለት ነው፡፡ በዚህ ስም የሚጠራው የሻዕቢያ የስለላና የምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በስሩ ሶስት ክፍሎች አሉት፡፡

1. የመረጃ ክፍል፡- ማንኛውም የሻዕቢያ አባል አመራሩን የሚቃወም ንግግር ሲናገር እና ጽሑፍ ሲያሰራጭ ቢገኝ ሪፖርት የሚያደርገው ይህ ክፍል ነው፡፡ እንደሚባለው በትግሉ ዘመን ሻዕቢያ በሺህ የሚቆጠሩ ሰላዮችን በታጋዮቹ መካከል አሰማርቶ ነበር፡፡ እነዚያ ሰላዮች ከታጋዩ የቃረሙትን ወሬ ወደ ዋና ክፍሉ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ ታዲያ ሻዕቢያ የመንካዕ እና የብፅአይ ንቅናቄዎች ከመከሰታቸውም በፊት አባላቱን እርስ በራስ እንዲጠራጠሩ አድርጎ አቆላልፎአቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ አንድ ታጋይ ዕድሜው እንዲረዝም ከፈለገ አመራሩን ማሞገስ ወይንም ዝም ማለት ይገባዋል፡፡ 2. የምርመራ ክፍል፡- በሀለዋ ሰውራ ሰላዮች ተጠቁሞ የተያዘ ሰው ወደዚህ ክፍል ይተላለፋል፡፡ ይህ ክፍል ጥፋት ተገኝቶባቸዋል ተብለው የተያዙ ተጠርጣሪዎች ሚስጢር እንዲያወጡ በማለት በልዩ ልዩ የምርመራ ቴክኒኮች ይጠቀማል፡፡ ዋነኛው ስልት ግን ተጠርጣሪዎችን መግረፍና ማሰቃየት ነው፡፡ 3. የእስረኛ ክፍል፡ እስረኞች በምርመራ ላይ እያሉ የሚቆዩበት ክፍል ነው፡፡ በምርመራው ጥፋተኛ ተብለው ፍርድ የተላለፈባቸው ተጠርጣሪዎችም የሚታሰሩት በዚሁ ክፍል ነው፡፡ ታዲያ ታሳሪዎቹ በሰላም አይቆዩም፡፡ በየጊዜው ሰቆቃና ስቃይ ይፈጸምባቸዋል፡፡ ከሻዕቢያ እስር ቤት በህይወቱ የወጣ ሰው ዕድለኛ ነው-ታዛቢዎች እንደሚሉት፡፡ በትግሉ ዘመን ከ3000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በሀለዋ ሰውራ እስር ቤቶች ተሰቃይተው እንደሞቱ የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ቡድኖች በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡ ሻዕቢያ በትግል ዘመኑ አምስት ያህል እስር ቤቶች የነበሩት ሲሆን ሁሉም የሚገኙት በሳህል አውራጃ ነው፡፡ ከነዚህ እስር ቤቶች መካከል አራግ እና ሀክሺብ በተባለ ቦታ የሚገኙት ከፍተኛ የስቃይ ቦታዎች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ በሻዕቢያ እስር ቤቶች ስለሚፈጸመው ሰቆቃና ስቃይ ብዙ ተብሏል፡፡ ምግብና ውሃ መከልከል፣ እስረኞች ለተከታታይ ቀናት እንዳይተኙ መከልከል፣ እስረኞች ለረጅም ጊዜ ብርድ ላይ እንዲቆሙ ማድረግ፣ ለረጅም ጊዜ በአንድ ጎን ብቻ እንዲተኙ ማድረግ፣ ሽንት እንዳይሸኑ መከልከል፤ እስረኛው በአፉ አንድም ቃል እንዳይናገር መከልከል የመሳሰሉት የመጀመሪያ ደረጃ የማሰቃያ ስልቶች ሊባሉ ይችላሉ፡፡ እስር ቤቱ በቅማልና በትኋን የተወረረ ስለሆነ እስረኛው በነርሱ ሲሰቃይ ነው የሚከርመው፡፡ እስረኛው ለምርመራ የሚወሰደው ከእኩለ ሌሊት በኋላ ነው (ቀን ላይ ሌሎች ታጋዮች እንዳያዩት ተብሎ ነው እንዲህ የሚደረገው)፡፡ ይህ የምርመራ እጣ የወደቀበት እስረኛ መፈጠሩን እስኪጠላ ድረስ ይገረፋል፡፡ አለፍ ሲልም በሳንጃ የሚወጋ አለ፡፡ ቆሻሻ ውሃ በተጠራቀመበት በርሜል ውስጥ ፊቱን መክተት፣ ገላን በእሳትና በፈላ ዘይት ማቃጠል፣ የእስረኛውን ጸጉር ማቃጠልና ሌሎችም ስቃዮች ይወርዱበታል፡፡ በስቃዩ ተጸጽቶ ሚስጢር ያጋለጠ፣ ወይንም ጥፋተኛ ነኝ ብሎ ግለ-ሂስ ያወረደ ሰው ህይወቱ ሊተርፍ ይችላል፡፡ ምንም ሚስጢር ያልተናገረ ግን ሞት ነው የሚጠብቀው፡፡ ታዲያ በራሱ አባላት ላይ እንዲህ የሚጨክነው ሻዕቢያ የጦር ምርኮኞችን ብዙም አይወጥራቸውም፡፡ በምርኮኞች ላይ የሚካሄደው ግርፊያ እና ድብደባ በመጠኑ አነስ ይላል፡፡ በተለይ ምርኮኞቹ ማዕረግ ያላቸው ከሆነ በጣም ይንከባከባቸውና ሊጠቀምባቸው ይሞክራል፡፡ ስለደርግ መንግሥት የሚያውቁትን ወታደራዊ መረጃ እንዲሰጡት ስሜታቸውን ይኮረኩራል፡፡ ሆኖም ሁሉም ምርኮኛ እና እስረኛ በጉልበት ስራ እንዲሳተፍ ይገደዳል፡፡ በተለይ የናቅፋ ተራሮችን እያቆራረጡ ወደ ሰሜን

ኤርትራ በረሃ የሚወስዱ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የተሰሩት በእስረኞች ጉልበት መሆኑ ብዙ የተባለለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ የሻዕቢያው ሀለዋ ሰውራ መቼ እንደተመሰረተ ታውቃላችሁ? ሰልፊ ነጻነት የሚባለው ቡድን በዓላ በረሃ ላይ በተመሰረተበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ አለ (አሁን ስሙን ቀይሮ “ብሄራዊ የደህንነት ተቋም” ተብሏል)፡፡ ከሀለዋ ሰውራ ጋር ስማቸው በተደጋጋሚ የሚነሳው የሻዕቢያ ሰዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ 1. ሰለሞን ወልደማሪያም፡ ከሰልፊ ነጻነት ቡድን መስራቾች አንዱ ነው፡፡ ከኢሳያስ በፊት ከሻዕቢያ ከተገነጠሉት አስራ አንድ ወጣቶች መካከል ይመደባል፡፡ ይህ ሰው የሀለዋ ሰውራ መስራች እና ዋና ጸሓፊ ነው፡፡ ለብዙ ወጣቶች ህይወት መጥፋት ተጠያቂ እንደነበረ ይነገራል፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ሰለሞን በ1973-74 የተካሄደውን የመንካዕ ንቅናቄ ያዳፈነ ሰው ነው፡፡ ሆኖም በሻዕቢያ ውስጥ የነበረው ስልጣን መጨመሩ ያሰጋው የኢሳያስ ቡድን በዘዴ ካስወገደው በኋላ እራሱ በመሰረተው ድርጅት ተገድሏል፡፡ 2. ሀይሌ ወልደሚካኤል፡ የምርመራ ክፍሉ ሃላፊ ነበር፡፡ በመንካዕ ንቅናቄ የተሳተፉትን ከመረመረ በኋላ “ወንጀል አልተገኘባቸውም፤ የጦር ሜዳ ደንብ በመተላለፍ ግን ሊጠየቁ ይችላሉ” የሚል ሪፖርት አሳልፏል፡፡ ሆኖም አመራሩ የርሱን ሪፖርት ስላልተቀበለ በርሱ ቦታ ሌላ ሰው ተክቷል፡፡ እርሱን ወደ ከረን አካባቢ ከመደቡት በኋላ በውጊያ ላይ ከራሱ ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት እንደሞተ ይነገራል፡፡ 3. ሀይሌ ጀብሃ፡- በጭካኔው ብዙ የተነገረለት መርማሪ ነው፡፡ የመንካዕ ንቅናቄ መሪዎችንና ሌሎችንም በድብደባ፣ በግርፋትና በሌሎችም ዘዴዎች ብዙ አሰቃይቷል፡፡ ብዙ ሰዎችን በእጁ እንደረሸነም ይወሳል፡፡ በኋላ ግን ግንባሩ ራሱ “ያንተ ቶርች በዛ በማለት ረሽኖታል፡፡ 4. አሽኣል ወዲ ዘረ፡ የሀይሌ ጀብሃ ምክትል የነበረ መርማሪ ነው፡፡ እርሱም “ለእስረኛ የማይራራ ጨካኝ መርማሪ” ተብሎ በ1980 ተገድሏል፡፡ 5. ተክላይ አደን (ተክላይ ገብረማሪያም)፡ ኦሮማይ ውስጥ ያለው “ስዕላይ ባራኺ” በከፊል እርሱን ይወክላል (ግማሹ ታሪክ የተስፋሚካኤል ጆርጆ ነው)፡፡ ተክላይ የማዕከላዊ ኮሚቴ ሃላፊ እና በሀለዋ ሰውራ የእስረኞች ክፍል መሪ ነበር፡፡ ብዙ እስረኞችን ሲያሰቃይ ከቆየ በኋላ ህሊናው በጸጸት ስለተነካ አጋጣሚ ጠብቆ ለደርግ እጁን ሰጥቷል፡፡ 6. ዓሊ ሰዒድ አብደላ፡ ጀብሃ በዓለም ላይ የታወቀበትን የካራቺ ኦፕሬሽን የመራ ፈዳይን ነበር፡፡ ከዚያ በኀላ “ህዝባዊ ሀይሊ” የሚባለውን የሳላህ ሳቤ ቡድን ተቀላቅሎ ከጀብሃ ኮብልሏል፡፡ ህግዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) ከተመሰረተ በኋላ ከ1977 እስከ 1987 ድረስ የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሓፊ ሆኖ ሰርቷል፡፡ ኤርትራዊያን በዚህ ረጅም ዘመን ሻዕቢያ በእስረኞች ላይ ለፈጸመው ግድያና ሰቆቃ በዋናነት ተጠያቂ የሚያደርጉት እርሱን ነው፡፡ ይህ ሰው ከ1987 በኋላ በስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ውስጥ የኢኮኖሚ ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ ነበር፡፡ ከነጻነት በኋላ ደግሞ ለአስር ዓመታት ያህል የሀገር ውስጥ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ሆኖ ሰርቷል (ከ2001-2005 የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ነበር፡፡ አሁንም ሞቷል)፡፡ የሻዕቢያው “ሀለዋ ሰውራ” በጥቂቱ ይህንን ይመስላል፡፡ ሌሎቻችሁም የምታውቁትን ትጨምሩበት

ዘንድ ይጠበቃል፡፡ ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) የመጀመሪያ ጉባኤውን ካካሄደ በኋላ የአመራሩን ቁልፍ ቦታ እንዲይዙ የመረጣቸው አስራ ሶስት የፖሊት ቢሮ አባላት እነማን እንደነበሩ ታውቃላችሁ? ካላወቃችኋችሁ እኝሁላችሁ፡፡ 1. ረመዳን መሐመድ ኑር (ዋና ጸሓፊ) 2. ኢሳያስ አፈወርቂ (ምክትል ዋና ጸሓፊ) 3. ዓሊ ሰዒድ አብደላ 4. ዑቅበ አብረሃ 5. ስብሐት ኤፍሬም 6. ሀይሌ ወልደ ትንሳኤ 7. ጴጥሮስ ሰለሞን 8. ሙሐመድ ሰዒድ በርሄ 9. መስፍን ሐጎስ 10. ኢብራሂም አፋ 11. አል-አሚን መሀመድ 12. ብርሃነ ገብረ እግዚአብሄር 13. ማሕሙድ አሕመድ ሸሪፎ ናቸው፡፡ ከዝርዝሩ እንደምታዩት ለፖሊት ቢሮ አባልነት ሰባት ደገኛ ክርስቲያኖች እና ስድስት ቆለኛ ሙስሊሞች ተመርጠዋል፡፡ ከፖሊት ቢሮው በላይ ባለው የማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥም አስራ ዘጠኝ ደገኞች እና አስራ ስምንት ቆለኞች ነበሩ፡፡ የግንባሩ ፖሊት ቢሮ የኤርትራ ህዝብን ሀይማኖታዊ ተዋጽኦ በጠበቀ መልኩ የተዋቀረ ይመስላል (በኤርትራ የክርስትያኑና የሙስሊሙ ብዛት ተቀራራቢ ነው)፡፡ የግንባሩ አባላት ግን በአብዛኛው ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ ነገሩን ያጠኑ ምሁራን እንደሚሉት በፖሊት ቢሮው ውስጥ የክርስቲያን እና የሙስሊሙን ቁጥር ማመጣጠን ያስፈለገው በልዩ ልዩ ምክንያቶች ነው፡፡ ከነዚህም ምክንያቶች አንደኛው “ጀብሃ” ቆለኞችን ብቻ በአመራር ላይ በመሰየም ደገኞችን እያስከፋ ሲፈጽመው የነበረውን ታሪካዊ ስህተት ላለመድገም በሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እነ ዑስማን ሳልህ ሳቤ ከጀብሃ ተገንጥለው “ህዝባዊ ኃይልታትን” ለመመስረት የተጫወቱትን ሚና ላለመርሳት ሲባል ነው፡፡ ሶስተኛው ምክንያት የሻዕቢያ (ህዝባዊ ግንባር) ደጋፊ ከሆኑ የዐረብ ሀገራት (በተለይ ሱዳን) “በግንባሩ ውስጥ የሙስሊሙ ውክልና አንሷል” የሚል ጥያቄ እንዳይቀርብ ለመከላከል በሚል ነው፡፡ የተወሰኑ ጸሐፍት ግን በዚህ የፖሊት ቢሮ አወቃቀር ላይ የተለየ አመለካከት አላቸው፡፡ ለምሳሌ “የተገንጣዮችና እና የሲ.አይ.ኤ ግንኙነት” የሚለውን ታሪካዊ ጽሑፍ የጻፉት አቶ ተስፋሚካኤል ጆርጆ በጽሁፋቸው “ኢሳያስ ተንኮሉን አይተውምና በቡድኑ ውስጥ ደገኞች በብዛት እንዲመረጡ ያደረገው ድምጽ እንዲበዛለት ፈልጎ ነው” ይላሉ (የምጽዋ ስፖዚየም፣ ጥር 1974፣ ገጽ 60)፡፡ ሆኖም ይህ የአቶ ተስፋሚካኤል እይታ ትክክል አልመሰለኝም፡፡ “ህዝባዊ ግንባር” የሚባለው

ድርጅት በጉባኤ ከታወጀበት ከ1977 ጀምሮ ለኢሳያስ ከደገኞቹ ይልቅ ቆለኞች ናቸው የሚቀርቡት፡፡ እጅግ ጥብቅ የሆነ ታማኝነት በሚፈልጉ ቦታዎች ላይ የተቀመጡትም ቆለኞች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ዓሊ ሰዒድ አብደላ ለረጅም ዓመታት (ከ1977-1987) የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሐፊ ነበር፡፡ ኢብራሂም አፋ ደግሞ የወታደራዊ ኮሚቴ ሊቀመንበር ነው፡፡ ከነዚህ የሻዕቢያ መሪዎች መካከል ሁለቱ በህይወት የሉም፡፡ ሻዕቢያ “የጀግኖች ጀግና” እያለ የሚያሞካሸው ኢብራሂም አፋ በ1985 ከረን አቅራቢያ በተደረገ አንድ ውጊያ ላይ ሞቷል (ብዙዎች ኢሳያስ ራሱ ነው ያስገደለው እያሉ ቢጽፉም ከነጻ ምንጭ ለማረጋገጥ አልተቻለም)፡፡ ዓሊ ሰዒድ አብደላ ደግሞ ከ2001- እስከ 2005 ድረስ የኤርትራ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ ካገለገለ በኋላ ሞቷል፡፡ ማሕሙድ አሕመድ ሸሪፎ፣ ሀይሌ ወልደ ትንሳኤ፣ ብርሃነ ገብረ እግዚአብሄር፣ ጴጥሮስ ሰለሞን እና ዑቅበ አብርሃ ግን G-15 የሚባለው ቡድን ቀንደኛ መሪዎች ናቸው ተብለው ከታሰሩ 12 ዓመት ሆኖአቸዋል፡፡ መስፍን ሐጎስ እንዳጋጣሚ ውጪ ሀገር ስለነበር ከእስሩ አምልጧል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከኢሳያስ ጋር በስልጣን ላይ ያሉት ረመዳን ሙሐመድ ኑር፣ ሙሐመድ ሰዒድ በርሄ፣ ስብሐት ኤፍሬም እና አል-አሚን መሐመድ ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ ታላላቅ የሻዕቢያ ሰዎች ለእስር ሊዳረጉ የበቁት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራን ህገመንግሥት በአስቸኳይ በስራ ላይ እንዲያውሉ ፔቲሽን በመፈራረም በመጠየቃቸው ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሁለት ጊዜ ያህል “ተው.. እየተሳሳታችሁ ነው… እረፉ…” ከመለሰላቸው በኋላ በመስከረም ወር 2001 በቁጥጥር ስር እንዲዉሉ በማዘዝ ወደ እስር ቤት ወርውሮአቸዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያሉበት ሁኔታ በትክክል አይታወቅም፡፡ ሻዕቢያ የመጀመሪያ ጉባኤውን ያካሄደው በምስራቅና ሰሜን ኤርትራ የሚገኙትን ከረን፣ ደቀምሐረ፣ ጊንዳእ፣ ሰንአፌ፣ ሐሙሲት የመሳሰሉ ከተሞችን በተቆጣጠረ ማግስት ነው፡፡ ሆኖም ከሁለት ዓመታት በኋላ ከናቅፋ በስተቀር ሁሉንም ከተሞች መልቀቅ ግድ ሆኖበታል፡፡ ጀብሃም በወቅቱ በምዕራብ ኤርትራ የሚገኙትን መንደፈራ፣ አዲኳላ፣ ተሰነይ፣ አቆርዳትና ባርካን ተቆጣጥሯል፡፡ ሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ጠንካራ ማጥቃት ሲሰነዝርበት ግን ከተሞቹን በሙሉ ለቅቋል፡፡ ሻዕቢያ የደርግ ጦርን ጥንካሬ ከመዘነ በኋላ በርሱ አቅም የማይመለስ መሆኑን ሲያውቅ የተፈጥሮ መከላከያው ወደሆነው የሳህል በረሃ ገብቶ መደበቅን ነው የመረጠው፡፡ ጀብሃ ግን በጀብደኝነት ከደርግ ጦር ጋር ሲዋጋ ሀይሉን አስጨርሷል፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉም የኔ ደጀን ነው ብሎ የተማመነበት የባርካ ቆላማ አውራጃም በደርግ ተይዞበታል፡፡ ስለዚህ ለጊዜው ማምለጫ ከሆነኝ በሚል የሻዕቢያ አምባ በሆነው የሳሕል ተራራ ውስጥ መጠጊያ ለማግኘት ሞክሯል፡፡ ሁለቱ ግንባሮች የርስ በርስ መተላለቁን በ1974 በመጣባቸው የህዝብ ግፊት አቁመው ስለነበር ሻዕቢያ ከደርግ ሸሽቶ በመጣው የጀብሃ ሰራዊት ላይ ብረት አላነሳም፡፡ እየዋለ ሲያድር ግን የድሮው ቂም አገረሸባቸው፡፡ ሻዕቢያ “ባርካን አስረክበህ ሳሕልን ልትይዝ መጣህ እንዴ!” በሚል በጀብሃ ላይ ጠንካራ በትር ሰነዘረ፡፡ ጀብሃም በአልሞት ባይ ተገዳይነት ራሱን ለማትረፍ ሞከረ፡፡ ለሁለት አመታት ያህልም እየተከላከለ ቆየ፡፡ በመጨረሻ ላይ ግን ተፍረከረከ፡፡ ከደርግ ጥቃት የተረፈው መለስተኛ ጦሩ በሻዕቢያ ሲቀጠቀጥበት አንዲት መናኛ ምልክት እንኳ ሳይተው ወደ ሱዳን ተሰደደ፡፡ በ1961 በሀሚድ አዋቴ የተጀመረው የጀብሃ የትጥቅ ትግልም በዚሁ መንገድ አከተመ፡፡ ድርጅቱም ከ1982 ጀምሮ በስም ያለ፣ በተግባር ግን የሌለ የስደተኞች ማህበር ሆኖ ቀረ፡፡

በዚህ ዘመን መሰረታቸው “ጀብሃ” የሆነ ከሃያ ፓርቲዎች በላይ አሉ፡፡ ሁሉም የሚንቀሳቀሱት ከኤርትራ ውጪ ነው፡፡ ጥቂቶቹን ለማስታወስ ያህል እነሆ! 1. ELF-RC (ጀብሃ- ሰውራዊ ባይቶ) መሪው ከጀብሃ መስራቾች አንዱ የሆነው አብደላ ኢድሪስ ነው፡፡ 2. ELF-PLF (የኢራቅ እና የሶሪያው በዕሥ ፓርቲን የሚመስል ፍልስፍና ይከተላል፡፡ ለረጅም ዓመታት ቡድኑን የሚመራው አብዱልቃዲር ጄይላኒ ነበር) 3. EDM (በህሩይ ተድላ ባይሩ የሚመራ) 4. ELF-United Organization- በዑመር ቡራጅ የሚመራ 5. ሳግም-በነ ተወልደ ገብረሥላሴ የሚመራ ነው፡፡ 6. DFLE- በግብረ ብርሃን ዘረ-ሰናይ የሚመራ ነው፡፡ 7. ደምሕኤ (መሪው ማን እንደሆነ አላውቀውም)፡፡ ------

ለመግቢያ ያህል የዛሬው ጽሑፍ በ1970 በኤርትራ ምድር ስለተቀበረው አንድ አደገኛ ፈንጂ ይተርካል፡፡ ታዲያ ትረካው የኔ አይደለም፡፡ ሚስጢሩን ሁሉ የሚያጫውቱን በፈንጂ ቀበራው ውስጥ ከፍተኛ የሚና የነበራቸው ግለሰብ ናቸው፡፡ በዚያ አስደማሚ ቴአትር የተሳተፉት በርካታ ተዋንያን ናቸው፡፡ መሪ ተዋናዮቹ ግን የአሜሪካው ሲ.አይ.ኤ. እና የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ ነበሩ፡፡

ስለዚህ አስገራሚ ሚስጢር የሚያጨውቱን ሰሞኑን ስማቸውን በተደጋጋሚ አነሳ የነበረው አቶ ተስፋሚካኤል ጆርጆ ናቸው፡፡ አቶ ተስፋሚካኤል በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥት በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት፣ በአከለ ጉዛይ አውራጃ የደቀምሐረ ወረዳ ገዥ ነበሩ፡፡ “ኦሮማይ” በተሰኘው የበዓሉ ግርማ መጽሐፍ ውስጥ “ስዕላይ ባራኺ” በሚል ስም የሚታወቀው ገጸ-ባህሪ ከርሳቸው ታሪክ ጋር በከፊሉ ይመሳሰላል፡፡ የኦሮማዩ ስዕላይ ወደ ሳሕል በረሃ ከመውጣቱ በፊት በነበረው ህይወቱ አቶ ተስፋሚካኤል ጆርጆን ይወክላል፡፡ ከሳህል በረሃ በኋላ ያለው ህይወቱ ደግሞ የሻዕቢያውን ተክላይ አደንን (ተክላይ ገብረማሪያምን) ይወክላል፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት አቶ ተስፋሚከኤል ይህንን ታሪክ በጽሑፍ ያቀረቡት በቀይ ኮከብ ዘመቻ ወቅት በተካሄደው የምጽዋ ሲፖዚየም ላይ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን በ1976 በጀብሃ ተማርከው በነበሩበት ጊዜ በሱዳን ውስጥ በኦዲዮ ካሴት አስቀርጸውታል፡፡ ጀብሃ በሻዕቢያ ሲመታ ግንባሩን ለቀው ለደርግ መንግሥት እጃቸውን ሰጥተዋል፡፡ ለደርግ ሰዎች ታሪኩን ሲነግሯቸው ሻዕቢያን ለማሳጣት ሀይለኛ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ይሆናል ተብሎ ስለታመነ በጽሑፍ በምጽዋው ሲምፖዝየም እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ የደርጎች ግምት ትክክል ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በምጽዋው ከቀረቡት ጽሑፎች ሁሉ ከፍተኛ አትኩሮት የሳበው የአቶ ተስፋ ሚካኤል ጆርጆ ጽሑፍ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሚስጢሩ ይፋ በመደረጉ የሻዕቢያ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ በአቶ ተስፋሚካኤል ላይ ምህረት-የለሽ ቂም እንዲቋጥር ምክንያት ሆኗል፡፡ አቶ ተስፋሚካኤል በደርግ ዘመን በመንግሥት ስራ ተሰጥቷቸው በአዲስ አበባ ይኖሩ ነበር፡፡ በቫቲካን ኤምባሲ አካባቢም ቤት ሰርተዋል፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ ግን ብዙም መኖር አልቻሉም፡፡ የሻዕቢያ አዳኝ ኮማንዶዎች በእግር በፈረስ ሲፈልጓቸው ከቆዩ በኋላ ሚያዚያ 5/1984 ምሽት በቤታቸው በራፍ ላይ ገድለዋቸዋል፡፡ ከአቶ ተስፋ ሚካኤል ጽሑፍ እዚህ የለጠፍኩት በጣም መሰረታዊ ያልኩትን ብቻ ነው፡፡ ሌላው ፍሬ ነገር እኔ ካወጋኋችሁ ጋር ስለሚመሳሰል መደጋገም ይሆንብኛል ብዬ አስቀርቸዋለሁ፡፡ የአቶ ተስፋሚካኤልን ኦሪጂናል ጽሑፍ ዳውንሎድ ለማድረግ ካሻችሁ ይህንን ሊንክ ተከተሉ፡፡ http://www.ehrea.org/TesfaMikegiorgioAmarina.pdf አሁን ጽሑፉን ማንበብ ትችላላችሁ፡፡

የተገንጣዮችና የሲ.አይ.ኤ ግንኙነት ጸሓፊ፡ ተስፋሚካኤል ጆርጆ ምጽዋ-ጥር/1974 በኤርትራ ክፍለ ሀገር ከዚህ ቀደም የነበረውንና አሁንም በመታየት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ፣ ብዙ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ አገር ደራሲያን፣ የፖለቲካ ተመራማሪዎችና እንዲሁም ሌሎች በማያዳግም ሆኔታ በፖለቲካ፣ በኤኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች በሰፊው ተንትነውታል፡፡ በመሠረቱ የሁሉም ጸረ-አንድነት ቡድኖች አጀማመር፣ ከገዥ መደቦች ዓላማና ፍላጎት ጋር የተቆራኘ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ጸረ-አንድነት ቡድኖች ምንም እንኳ በተለያዩ ስያሜዎች ቢጠሩም፣ በዓላማ ግን አንድ ናቸው፡፡ ራሱን ጀብሃ ብሎ የሚጠራው ተገንጣይ ቡድን በ1954 ዓ.ም. እነ እድሪስ መሐመድ አደምን በመሳሰሉ መሳፍንት ከተመሰረተ አንስቶ፣ መሥራቶቹ ለእስልምና ሃይማኖት የምንታገል ዓረቦች ነን በማለት ፕሮፓጋንዳቸውን ሲያሰራጩ ቆይተዋል፡፡ ይህን መፈክር አንግበውም፣ በጀብሃ ውስጥ ነበሩትን የደጋውን ሕዝብ ቆሐይን፣ ጽንዓደገል፣ ጋሽና ሠቲት ሀዲዳም በተባሉ ቦታዎች ከህግ ውጭ

በሆነ መንገድ ጨፍጭፈዋል፡፡ ንብረቱን ዘርፈዋል፡፡ ይህም በወንበዴው ድርጅት ውስጥ ትልቅ ቅራኔን ፈጠረ፡፡ ይህን በደገኞቹና በቆለኞቹ መካከል የተፈጠረውን ችግር ለማስወገድ፣ ባጋጣሚውም የጀብሃን አጠቃላይ መዋቅርና ፖሊሲ ለመተለም፣ በ1960 ዓ.ም. አደብሃ (ሳህል አውራጃ) ላይ ስብሰባ ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በስብሰባው ላይ የተላለፉት አስታራቂ ውሳኔዎች፣ በተግባር ሳይተረጎሙ በመቅረታቸው፣ ኢሳያስ አፈወርቂና ተከታዮቹ መገንጠል ጀመሩ፡፡ ነገር ግን እነሱ በሙሉ ክርስትያን በመሆናቸው፣ የጀብሃ ደጋፊ የሆኑት የአረብ አገሮች እርዳታ ተነፈጋቸው፡፡ ይህም ሁኔታ፣ ከመሪዎቹ የንኡስ ከበርቴ ባህሪ ጋር ተዳምሮ ወደ ኢምፕሪያሊስት ጎራ ጭልጥ አድርጎ ወሰዳቸው፡፡ ነገር ግን ይህ እነ ኢሳያስ አፈወርቂ ከሃይለስላሴ ፊውዶ ቡርዥዋ መንግሥት ጋር በመመሳጠር፣ የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ ሲጨቁን ከቆየው ከአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ጋር የነበራቸው ቀጥተኛ ግኑኝነትና የጋራ ደባ እስካሁን ለህዝቡ ጆሮ በተብራራ መልክ አልቀረበም፡፡ ስለዚህ ማን ያውራ የነበረ እንዲሉ በዚያ ወቅት በኢሳያስና በቃኘው የአሜሪካ የጦር ባለስልጣኖች መካከል ይውጠነጠን የነበረውን ሴራ በቅርብ የማውቀውን ያህል በዚህ ጽሑፍ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ እንደሚታወቀው ከ1946 ዓ.ም. ጀምሮ አሜሪካኖች መረጃዎችን ለመሰብሰብና የሕዝቡን አጠቃላይ ሳይኮሎጂካል ይዘት ለፍላጎታቸው አመቺ እንዲሆን ለማድረግ በአሥመራ የቃኘው ጣቢያን አቋቋሙ፡፡ እንደዚሁም ከአሥመራ 45 ኪሎ ሜትር ያህል በሚርቀውና ጉራዕ በሚባለው ሥፍራ አንድ የራዳር ጣቢያ አቋቁመው ነበር፡፡ መረጃ ሊያመጡ የሚፈልጉ ሰዎችንም ለመደለል ይመቻቸው ዘንድ ለአሜሪካኖች ተብሎ ቀረጥ ሳይከፈልበት ይመጣ የነበረውን ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጥ በሚሸጡበት (PX) በተባለው ሱቃቸውና (Top Five Club) በተሰኘው ክበባቸው በተለይ ከፍተኛ ማእርግና ሥልጣን ያላቸውን እያስገቡ ማንኛውንም ዕቃ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በርካሽ እየሸጡ እንዲጠቀሙበትና እንዲነግዱበትም ያደርጉ ነበር፡፡ አነስተኛ ደረጃ ካላቸው ምሁራንና ወጣቶች ጋር ደግሞ ጎልፍ ክበብ በተባለው ማህበራቸውና በወጣቶች ወገኖች ክርስቲያናዊ ማህበር አማካይነት ሰፋ ያለ ግንኙነት ፈጥረው ነበር፡፡ የገጠሩን ገበሬ እንቅስቃሴ ለመከታተልም ለአደን የሚሔዱ በመምሰልና “በችግኝ ተከላ” ፕሮግራም አማካይነት በአስተዳደራዊ ጉዳዮችና መስኮች ጣልቃ በመግባት በኢትዮጵያ ባጠቃላይ፣ በተለይም በኤርትራ ክ/ሀገር ጉዳይ ውስጥ አጥፊ የሆነ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አሜሪካኖች በኤርትራ ክፍለ ሀገር የነበረውን ነባራዊ ሆኔታ ለራሳቸው እንደሚስማማቸው አድርገው በማቀነባበር ሲበዘብዙ የቆዩበት ዘዴ በጣም የረቀቀ ነበር፡፡ እንድያውም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት እያደገ የሚሄድ የሚሊተሪና የሲቢል ተቃውሞ ስለበዛበት የሚያስተማምን አለመሆኑን የተረዱት ቀደም ብለው ነበር፡፡ በምትኩም ለረጅም ጊዜ ደጋፊአቸው ሊሆን የሚችል የቡርዥዋ ሥርዓት ለማቋቋም በየአቅጣጫው ተስማሚ የሆኑ ግለሰቦችንና መሪዎችን በመፈለግ ላይ እንደነበሩ አያጠራጥርም፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ባላቸው የፖለቲካ ጥቅም ምክንያት በተለይ ጨለማው መስከረም (Black September) የተሰኘው የፍልስጥኤም ነጻ አውጭ ድርጅት (P.L.O.) ቡድን በየኤምባሲዎቻቸው የቦምብ ናዳ በማዝነብ ተቃውሞውን ይገልጽ ስለነበር አሥመራና ጉራዕ የሚገኙትን ጣቢያዎቻቸውን ያጠቃብናል የሚል ስጋት ነበረባቸው፡፡ ሆኔታዎች በዚህ ደረጃ ላይ በነበሩበት ወቅት ነበር፣ እነ ኢሳያስ አፈወርቂ ግኑኝነታቸውን ከአሜሪካኖች ጋር የጀመሩት፡፡ በአንጻሩ ደግሞ

በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራን ከ/ሀገር ችግር ለመፍታት የሚል ሙከራ በማድረግ ላይ ነበር፡፡ እንዲያውም ጥቅምት 7 ቀን 1962 ዓ.ም. በአሥመራ ውስጥ የኤርትራ ክ/ሀገር መኳንንት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች በተገኙበት የኤርትራ ከ/ሀገር የሰላም ጉባኤ በሚል ስያሜ አንድ ቋሚ ኮሚቴና ቋሚ ሊቀ መንበር ያለበት ቡድን ተቋቋመ፡፡ ዓላማውም የኤርትራ ክ/ሀገር ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ በመንግሥትና በተገንጣዮች መካከል የነበረውን የወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማቆም በአመቺ ቦታና ጊዜ ተገናኝቶ ለመነጋገር ነበር፡፡ ይህንንም ምክንያት በማድረግ የዚህ የተጠቀሰው ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ መንበር የነበሩት ደጃዝማች ገብረዮሃንስ ተስፋማርያም የፈረሙበት የሰላም ጥሪ ደብዳቤ በዑመር ሐንገለና በሌሎች አማካይነት ለተገንጣዮች እንዲደርስ ተደረገ፡፡ መልሱም ከተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ መ/ጠ/ሐ/ሠ ኤርትራ ከሜዳ በማለት በ24/11 69 እ.ኤ.አ. የተጻፈ ደብዳቤ “ከልጆቻችሁ ሓሳብ ለሓሳብ ለመለዋወጥ ባስቸኳይ በፈለጋችሁበት ቀን ክቡርነትዎ በወሰኑት ቦታ በአክብሮት እንጠባበቃለን” የሚል ደብዳቤ አብርሃም ተወልደና ሰሎሞን ወ/ማርያም በተባሉት ግለሰቦች ተፈርሞ መጣ፡፡ በዚህም መሠረት፣ ከተገንጣይ ቡድን መሪዎች ጋር ለመነጋገርና ለመደራደር፣ በደጃዝማች ገብረኪዳን ተሰማ (የከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ ዳኛ) ሰብሳቢነት፤ ሌተና ኮሎኔል ገብረእገዚአብሔር መሐረና፣ የኤርትራ ክፍለ ሀገር ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነርና እኔ ራሴ ተስፋሚካኤል ጆርጆ፣ በአባልነት ያለንበት ኮሚቴ ሕዳር 21 ቀን 1962 ዓ.ም. ተቋቋመ፡፡ እኔ በዚያን ወቅት የደቀመሐረ ወረዳ ገዢ ነበርኩ፡፡ ይህ ኮሚቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዳር 28 ቀን 1962 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ታሕሳስ 5 ቀን 1962 ዓ.ም. ተገንጣዮች ወደሚገኙበት ወደ ዓላ በረሃ ሄዶ ነበር፡፡ ነገር ግን የተገንጣይ ቡድን መሪዎቹ በኋላቀር አስተሳሰብና በሥልጣን ሽሚያ ምክንያት በመለያየታቸው በአንድነት ጉዳያቸውን ለማቅረብ አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ኮሚቴው መገናኘትና መነጋገር የቻለው ከክርስቲያኑ ተገንጣይ ቡድን ጋር ብቻ ነበር፡፡ ከኮሚቴው ጋር ቀርበው የተነጋገሩት የቡድኑ ቀንደኛ መሪዎችም፣ አብርሃም ተወልደ፣ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ሰለሞን ወ/ማርያም፣ ሀብተስላሴ ገ/መድህን፣ ወ/ሚካኤል ሃይለ፣ በራኺ ንጉሠና ሌሎችም ነበሩ፡፡ ያቀረቡትም ሐሳብ “እኛ ከእስላሞች ተለያይተናልና… እነሱን መውጋት እንድንችል ከመንግሥት ማተሪያላዊና ሞራላዊ እርዳታ ይሰጠን” የሚል ነበር፡፡ ኮሚቴውም መንግሥት በዜጎቹ መካከል የሃይማኖት ልዩነት እንደማይፈጥርና ጥያቄአቸውም ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ በበኩላቸው እጃቸውን ለመስጠት ዝግጁ ከሆኑ ግን መንግሥት እንደሚቀበላቸው ገለጸላቸው፡፡ ይህም በወንጀል መዝገብ ቁ. 557/62 መከላከያ ምስክር ሌ/ኮሎኔል ገብረእግዚአብሔር መሐረና በሚለው በገጽ 27 ላይ ሰፍረዋል፡፡ ተገንጣዮቹም፣ “ቁጥራችን ከፍተኛ ስለሆነ ተሰባስበንና ተመካክረን እጃችንን እስከምንሰጥ የቀሩት እንደኛ የመሰሉት ወንድሞቻችን አደጋ ላይ እንዳይወድቁ የተነጋገርንባቸው ጉዳዮች ይዘትና የመገናኘቱም ጉዳይ በከፍተኛ ምስጢር እንዲጠበቅልን” ስላሉና ይህም ሀሳባቸው ተቀባይነት ስላገኘ የሚሰበሰቡበት ቦታና ጊዜ ተወሰነ፡፡ ይሄም በወንጀል መዝገብ ቁ. 557/62 በደጃዝማች ተስፋዮሐንስ በርሄ ም/እንደራሴ የቀረበ የመካላከል ምስክር በሚለው ገጽ 63 ላይ ሰፍረዋል፡፡ ኮሚቴው ይህንን ሁሉ እንደተለመደው ለመንግሥት አቀረበ፡፡ ነገር ግን በምስጢር ይጠበቅልን ብለው ቃል ያስገቡን ጉዳይ ሊከበርላቸው አልቻለም፡፡ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ምሥጢራዊ መረጃዎችን በመለዋወጥ በኩል (Exchange of Confidential Information) የነበረው ስምምነት ጠንካራ በመሆኑ ኮሚቴው በምስጢር ያቀረበው ሪፖርት ሁሉ አሜሪካኖቹ እጅ ወደቀ፡፡

እነሱም (አሜሪካኖች) በበኩላቸው ከዚያ በኋላ “ሰልፊ ነጻነት” በሚል ስያሜ ተቋቋሞ የነበረውን የኢሳያስ ቡድን ለመገናኘት ለብቻቸው ሩጫ ጀመሩ፡፡በዚህ ዓይነት አሜሪካኖቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊገናኙና ሊነጋገሩ የቻሉት ሀብተሥላሴ ገ/መድህን ከተባለውና “ከሰልፊ ነጻነት” ተገንጣይ ቡድን መሪዎች መካከል አንደኛው ከነበረው ግለሰብ ጋር ነበር፤ ንግግሩም የተደረገው እኔ ራሴ በተገኘሁበት በቃኘው ጣቢያ ግቢ ውስጥ ሪቻርድ ኮፕላንድ ከሚባለው “የችግኝ ተከላ ፕሮጀክት” በሚል ሽፋን ከብዙ ሰዎች ጋር እየተገናኘ ስለላ በሰፊው ያካሄድ ከነበረው አሜሪካዊ ጋር ነበር፡፡ ሪቻርድ ኮፕላንድ ከሀብተሥላሴ ጋር ባደረገው የሀሳብ ልውውጥ ተገንጣይ ቡድኖቹ በአሜሪካኖች ላይ የቱን ያህል ከፍ ያለ ጥላቻና ቅያሜ እንደነበራቸው መረዳት ቻለ፡፡ አድሃሪውን የሃይለስላሴ መንግሥት አቅፈው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይ በኤርትራ ክፍለ ሀገር ሕዝብ ላይ ያደርሱ የነበረውን ጭቆና በመዘርዘር የቱን ያህል እንዳስቆጣቸው ሀብተስላሴ በግልጽ አስረዳው፡፡ ኮፕላንድ፣ ይህ ሁኔታ አሜሪካኖቹ ከመጀመሪያ ጀምሮ ይፈሩት የነበረውን ቅዋሜና፣ ወታደራዊ ጥቃት በቃኘውና በጉራዕ ጣቢያዎቻቸው ላይ፣ ወደፊትም በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ ባላቸው የረጅም ጊዜ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ክስረት ሊያደርሱ የሚችሉ መሆናቸውን ለመረዳት ቻለ፡፡ ስለሆነም ከተገንጣይ ቡድኖች ዋና ዋና መሪዎች ጋር እንዲያገናኘውና የጋራ ስምምነት ለመቀየስ እንዲቻል ያደርግ ዘንድ ሀብተሥላሴን ጠየቀ፡፡ ከዚህ ውይይት በኋላ ሀብተሥላሴ ከቃኘው ጣቢያ ጓደኞቹ ወደነበሩበት ወደ ዓላ በረሃ ተመልሶ ሄደ፡፡ ሃብተሥሳሌም “የሰልፊ ነጻነት” የበላይ መሪዎች ከነበሩት ከአብርሃ ተወልደና ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ስለ ጉዳዩ ከተወያየበት በኋላ ወደ ደቀምሐረ ከተማ ተመልሶ አሜሪካኖቹ ከዋና ዋናዎቹ የሠልፊ ነጻነት መሪዎች ጋር ሊነጋገሩ የሚችሉበትን አጀንዳ እንዲያዘጋጅ ታዘዘ፡፡ ከአሜሪካኖቹ ጋርም የግንኙነት ቀጠሮ አደረገ፡፡ በቀጠሮው መሠረትም ሪቻርድ ኮፕላንድ ደቀምሐረ ሲመጣ ጓደኛው የነበረውን ሪቻርድ ሲወልንና አንድ ትልቅ የጦር መሣሪያ ካታሎግ ይዞ መጣ፡፡ በወቅቱ በተደረገው ውይይት አሜሪካኖቹ በመጀመሪያ ደረጃ ለማወቅ የፈለጉት ተገንጣዮቹ የጦር መሣሪያ የሚያገኙበትን ምንጭና የንቅናቄአቸውን የውጭ ደጋፊ ሃይላት ነበር፡፡ ሀብተሥላሴንም በመጀመሪያ የጠየቁት ምን ዓይነት ጠመንጃና ሌላ መሣሪያ እንዳላቸው ነበር፡፡ እሱ ደቀምሐረ ይዞት መጥቶ የነበረውንም ክላሽን-ኮቭ አውቶማቲክ መሣሪያ ተውሰው፣ ቃኘው ጣቢያ ከወሰዱ በኋላ ፎቶግራፍ አንስተውና መርምረው መለሱለት፡፡ አሜሪካውያኑ በተጨማሪም የተገንጣይ ቡድኑ ዋና ዋና መሪዎች ስለቡድናቸው አጠቃላይ ፖሊሲ፣ ከጀብሃ ጋር ስላላቸው ቅራኔ፣ ለጀብሃ ሶሻሊስት አገሮች በፍልስጥኤም ነፃ አውጪ ድርጅት በኩል በእጅ አዙር እርዳታ እንደሚሰጡና “ሰልፊ ነጻነት” ከአሜሪካ ጋር ለማድረግ የሚፈልገውን ግንኙነት የሚገልጽ ኦፊሴላዊ ደብዳቤ በጊዜው የቃኘው ጣቢያ አዛዥ ለነበረው፣ ኮሎኔል ማሙዘር እንዲጽፉ ያደርግ ዘንድ ሀብተሥላሴን ጠየቁት፡፡ በዚህ መሠረት ደብዳቤው በመሪዎቹ ተረቅቆና ተዘጋጅቶ በፖስታ ቤት እንዲላክ ተደረገ፡፡ በደብዳቤው ውስጥ የሰፈሩት ዋና ዋና ነጥቦችም፤ 1ኛ/ በዓላ በረሃ የሚገኙት ታጋዮች፣ ክርስቲያን በመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካና የመሣሪያ ርዳታ ከዓረብ መንግሥትና፣ ከሶሻሊስት አገሮች በእጅ አዙር በሚያገኘው የጀብሐ ቡድን በየቀኑ የሚገደሉና የሚታረዱ መሆናቸውን፤ 2ኛ/ ጀብሃ የያዘችው ፖለቲካ ጭልጥ ያለ የሃይማኖት ይዘት ያለውና የእስራኤልና የአሜሪካ ዓይነተኛ ጠላት ከሆኑት የአረብ ሀገሮች ጋር ፖሊሲው የተዛመደ መሆኑን፤ የሰልፊ ነጻነት ቡድን ዋና ዓላማ ግን “ተራማጅና ዲሞክራቲክ እንቅስቃሴ” ለማካሄድ መሆኑን የሚገልጽና አሜሪካም የሚያስፈልገውን እርዳታ እንድትሰጣቸው የሚማፀን ነበር፡፡ (ይህ ደብዳቤ በ21/9/62 ቁ.

1039/18/31 ማህደር ቁ. ሀ/1/19ሠ2 በእንግሊዝኛ ጽሑፍ ሰፍሮ ይገኛል፡፡) በዚሁ ወቅት ይኸው ተገንጣይ ቡድን ተመሳሳይ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ቆንስልም [በአስመራ የአሜሪካ ቆንስላ ጽ/ቤት መሆኑ ነው] ጽፎ ነበር፡፡ የደብዳቤውም ዋና ይዘት ባጭሩ፣ “ኮሚኒስቶች እስላሞችን ስለሚረዱ እናንተ ምዕራባዊያን ደግሞ እኛን ልትረዱ ይገባል” የሚል ነበር፡፡ ይህ ደብዳቤ የተጻፈው እንደ አውሮጳ አቆጣጠር በ5/4/1970 ሲሆን፣ ቆንስላው ደብዳቤውን የኤርትራ ከ/ሀገር ምክትል እንደራሴ ለነበሩት ለደጀ/ተስፋዮሐንስ በርሄ ሚያዝያ 1/62 ዓ/ም. አስረክበዋል፡፡ ይህም በመዝገብ ቁ/ሀ/1/1042 ደብዳቤ ቁጥር 1091/18/31 ሰኔ 4 ቀን 1962 ዓ/ም. ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም መንግሥቱ ባይሩ ዑቅቢት በተባለው ግለሰብ አማካይነት፣ ከሌላ ካልታወቀ የውጭ አገር ሃይል ተመሳሳይ ዕርዳታ ለነ አብርሃ ተወልደና ለነ ኢሳያስ አፈወርቂ የሚገኝበት መንገድ ተቀይሶ እንደነበረና ከተባሉትም የውጭ ሀገር ሰዎች ጋር አገናኝቷቸው እንደ ነበረ ሃብተሥላሴ ገብረመድህን ተማርኮ በነበረበት ጊዜ በሰጠው ቃል አረጋግጡዋል፡፡ ይኸም በመዝገብ ቁ. ሀ/1/1042 ደብዳቤ ቁ. 091/18/31 አሥመራ ሰኔ 4/62 ዓ.ም ተጠቅሶአል፡፡ አሜሪካኖቹም፣ በበኩላቸው የመጣላቸውን ደብዳቤ በደስታ ተቀበሉት፡፡ ከዚያም በኋላ የቡድኑ መሪ የሆነው ኢሳያስ አፈወርቂ ራሱ መጥቶ ከአሜሪካኖቹ ጋር እንዲነጋገር ቀጠሮ ተደረገ፡፡ በተባለውም ቀን እኔ ራሴ በማሽከረክረው የመንግሥት ላንድሮቨር መኪና ከደቀምሐረ ዓላ በረሃ ድረስ ሔጄ፣ ኢሳያስን ወደ አሥመራ ይዠው መጣሁ፡፡ በአሥመራ ከተማ ውስጥም፣ ለሁለት ሰዓት ያህል በመኪናው ሳንሸራሽረው ቆይቼ በቀጠሮው ሰዓት ቃኘው ጣቢያ ወሰድሁት፡፡ አሜሪካኖቹም የሴኩሪቲ ችግር እንዳይፈጠር ብለው ውይይቱ ሚስተር ቦውሊንግ በተባለው የቃኘው ጣቢያ ሴንትራል ኢንተሊጀንስ ዲፓርትመንት ባልደረባ መኖሪያ ቤት፣ ማለትም ቅዱስ ፍራንሲስኮ ካቴድራል አጠገብ ተካሄደ፡፡ በአሜሪካኖቹ በኩል ከሪቻርድ ኮፕሊንግ ጋር ሌሎች ሶስት የሚሆኑ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ነበሩ፡፡ በንግግሩ ወቅት ኢሳያስ ካነሳቸው ነጥቦች መካከል፤ 1/ የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመመሳጠር የኤርትራን ዕድል በመወሰን ጉዳይ የሰፊውን የኤርትራ ሕዝብ ፍላጎት የማያሟላ የፌደሬሽን አቋም በመፍቀድዋ፤ 2/ ፌደራላዊ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ ደግሞ የኤርትራን ሕዝብ ለማጥፋትና እንቅስቃሴውን ለመደምሰስ ስፍር ቁጥር የሌለው መሣሪያና አማካሪዎች ለኢትዮጵያ መንግሥት ማቅረቡዋ በነሱ ዘንድ የተወገዘ ድርጊት መሆኑን፤ 3/ የዓረብ አገሮች ጀብሃን በመርዳት ቀይ ባህርን የዓረብ ግዛት ለማድረግ መወሰናቸውንና “ተራማጅ ድርጅትና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት” ለመመስረት በሚደረገው ትግል ያለፈውን ድርጊታቸውን በማረምና በማስተካከል የሱን ቡድን እንዲተባበሩ ሙሉ እርዳታን የሚጠይቁ ይገኙባቸዋል፡፡ አሜሪካዊያኑም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በዓላ በረሃ ይደረግ የነበረውን ድርድርና የጀብሃንም አኳኋን በሚገባ ስለሚያውቁ “ጀግኖቹ እንደተሰቃያችሁና እንደተገደላችሁ በይፋ የምናውቀው ነገር ነው፡፡ ከነሱ መገንጠላችሁም የሚደገፍ ነው” ካሉ በኋላ የፍልስጥኤም ቡድን አካል የሆነው “ጨለማው መስከረም” (Black September) ኤምባሲዎቻችንን በመደብደብ በየቦታው በገንዘብ በተገዙ የአገር ሰዎች ስለሚጠቀም፣ የዚህ ድርጅት መሣሪያ እንዳትሆኑ፤ በበኩላችሁ በንብረታችንና በአባሎቻችን ላይ ጉዳት እንዳታደርሱና፣ ለመከላከልም ቃል ከገባችሁልን አንዳንድ

የማቴሪያል እርዳታ እናቀርባለን በማለት ነው የጠራናችሁ” ብለው አስረዱ፡፡ ኢሳያስም የእርዳታው ጉዳይ በዓላው ቡድን በኩል ተቀባይነት እንዳለው ገልጾ ጨለማው መስከረም (Black September) የተባለው ቡድን ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት መከላከል ግን ከቡድኑ (ተገንጣይ) አቅም በላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡ አሜሪካዊያኑም ንግግራቸውን በመቀጠል “በታሪክ፣ ኤርትራ በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በደማዊ መተሳሰር ከኢትዮጵያ ሳትነጠል ቆይታለች፡፡ በኤርትራ ውስጥ የውስጥና የውጭ ቅራኔ ሳቢያ በጉዳዩ ጣልቃ ገብተን ሆኔታውን ለማረጋጋት በኤርትራ የፌዴሬሽን አቋም ወሰድን፡፡ አሁን ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ስርዓት በመዳከም ላይ ስለሚገኝና፣ የሚተካውም የተደራጀ ፓርቲ ባለመኖሩ፣ እንደሌሎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ ወታደራዊ አስተዳደር ይመጣል ብለን እንፈራለን፤ እምነትም የለንም” በማለት፤ ሀ/ የቃኘው ጣቢያ ህልውና እንዲጠበቅና ሌላ ተመሳሳይ ጣቢያም በቀይ ባሕር አካባቢ እንዲቋቋም ከሚተባበር ፤ ለ/ ፀረ ሶሻሊስት የሆነ አቋም ከሚይዝና የሶሻሊዝምን መስፋፋት ከሚቃወም፤ ሐ/ ለአንድ ዴሞክራሲያዊት የኤርትራ መንግሥት የሚታገል ቡድን ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነን” በማለት አስረዱት፡፡ በጊዜው የኤርትራ ክ/ሀገር እንደራሴ የነበረው ራስ አሥራተ ካሣ “ለሰልፊ ነፃነት” ሶስት አማራጭ ሰጥቷቸው ነበር፦ እነሱም፤ 1ኛ/ ሁሉም በምህረት ገብተው በየፊናቸው ትምህርትም ሆነ ሥራ እንዲቀጥሉ፤ 2ኛ/ ከጀብሃ ጋር መለያየታቸውን በይፋ ለማሳወቅ ጀብሃን በጦር ሃይል ወግተው መጣላታቸውን በግልጽ እንዲያረጋግጡ፤ ይህን ካደረጉ የመሣሪያ እርዳታም ሊሰጣቸው እንደሚችል፤ 3ኛ/ ሁሉም በምህረት ገብተው ወታደራዊ ትምህርት በመቀበል በጀብሃ ላይ ያላቸውን ቂም በቀል ከጦሩ ጋር በመተባበር እንዲወጡ፤ የሚሉ ነበሩ፡፡ አሜሪካኖቹም እነዚህን አማራጮች መነሻ በማድረግ ለኢሳያስ ምክራቸውን ለገሱት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ጀብሃንና የኢትዮጵያን መንግሥት ጦር ባንድነት ለመቋቋም አቅም እንደሌለው ገለጡለት፡፡ ስለሆነም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የመጀመሪያውን ድርድር፣ በከፊልም ቢሆን፣ እንዲቀጥልበት መከሩት፡፡ ለዚህ የሚሻለው ዘዴ ከቡድኑ መሪዎች መካከል ጥቂቶቹ በምህረት ገብተው የቀሩት በኢሳያስ መሪነት በበረሃ ጸረ ጀብሃ ትግሉን እንዲቀጥሉ ማድረግ፤ መሆኑን በዝርዝር አስረዱት፡፡ ይህን ማድረግ ከቻለ አሜሪካኖቹ ከአሥራተ ካሣ ጋር በመስማማት የኤርትራ ክ/ሀገር ተወላጆች ብቻ የሚገኙበት ጠንካራ የኮማንዶ ሃይል አሰልጥነው እንደሚልኩለትና ጀብሃን በተጨማሪ ሃይል እንደሚመልሱለት ቃል ገቡለት፡፡ ሁኔታውን ለማቀላጠፍ፣ የጀብሃንም አቅም በተሎ ለማዳከምና የምታገኘውም እርዳታ እንዲቋረጥባት በአረቦችና በእስራኤል መካከል ያለውን የመካከለኛውን ምስራቅ ጦርነት በማቀጣጠልና ጊዚያዊ ጦርነት በመክፈት የአረብ አገሮች በአካባቢያቸው ብቻ እንዲወሰኑ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገለጡለት፡፡ በዚህም ጊዜ በኢትዮጵያ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶ የፖለቲካ ሥልጣኑን የሚጨብጠው አካል ኤርትራን በፌደራላዊ መንግሥት የሚያውቅ ይሆናል፡፡ አሜሪካም ከዚሁ ክርስቲያናዊ መንግሥት ጋር ይተቃቀፋል፡፡ ምክንያቱም የቀይ ባህር ጌትነት ያመለጣቸው የዓረብ አገሮች የተዳከመውን ጀብሃ መርዳት ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ ሃይልም ለመግባት ሳይሞክሩ ስለማይቀሩና “ሰልፊ ነፃነት” ብቻውን ሊቋቋማቸው ስለማይችል ነው በማለት

አስረዱት፡፡ ኢሳያስ ግን “የኤርትራ ነፃነት ምንም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ስለሆነ፣ ፌዴሬሽን የሚባል ነገር አልቀበልም” አለ፡፡ አሜሪካዊያኑም በበኩላቸው “የኤርትራ ጥያቄ የውጭ ጥያቄ እንጂ የውስጥ ጥያቄ አለመሆኑን የሚያረጋግጡ አንዳንድ ነጥቦች ስለሚኖሩ የጠቀስንላችሁን ሦስት ዓላማዎች ለማሟላት ከተስማማችሁ ሙሉውን ነፃነታችሁን የምንደግፍ መሆናችንን እንገልጻለን” በማለት “በናንተውና በምንልከው የኮማንዶ ኃይል ብርታት የጀብሃ ድክመት ከታየ በኋላ በኢትዮጵያ የሚቋቋመው አዲሱ መንግሥት ኤርትራን በፌደራላዊ ስርዓት በሚያውቅበት ጊዜ እናንተ አትቀበሉ፡፡ በዚሁ ጊዜ እነኛ አስቀድመው ምህረት ጠይቀው የገቡት ጓደኞቻችሁ እኛ በምናቀርብላቸው የመሣሪያና የወታደራዊ ስልት እውቀት ደልበው ስለሚጠብቁ በብዛት ወደ እናንተው ይጎርፋሉ፡፡ ከደጋው ክፍል ወደ ቆላው በመውረድ ደግሞ የባህር ጠረፎችን በቁጥጥራችሁ ሥር ስለምታደርጉ በቪየትናሙ ጦርነት ከቪየት ኮንግ የማረክነውን የሩሲያ መሣሪያ በሙሉ በመርከብ እናቀርብላችኋለን፡፡” “አሜሪካ ሠራሽ መሣሪያዎችና ቁሳቁሶች ግን በሶስተኛው ዓለም የተያያዝነውን ፕሮፓጋንዳ ሊያቀዘቅዝብን ስለሚችል አናቀርብላችሁም፡፡ ጉዳዩ እንዲፋጠንም በኢትዮጵያ የሚመሠረተው አዲስ መንግሥት የምታውጁትን መንግሥት በይፋ እስከሚያውቀውና እስከሚቀበለው ድረስ የምንሰጠውን ማተሪያላዊና ሌላም እርዳታ በመጠኑ በማቋረጥ ተጽእኖ እናደርግበታለን” አሉ፡፡ ኢሳያስም ይህን ፕላን በቲዮሪ ደረጃ ከሰማ በኋላ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ምን ዋስትና አለው? በማለት ጠየቀ፡፡ አሜሪካኖቹም “ፖለቲካ የቁማር ጨዋታ ስለሆነ ቁማር ተጫወት” እናንተ የምትፈልጉት ነጻነት ነው፡፡ እኛ ደግሞ የምንሻው የቀይ ባህር ይዞታችን እንዲጠናከር ስለሆነ፣ ይኸው ዋስትናችን ነው” ብለው መለሱለት፡፡ ይህን አጠቃላይ ውይይት ካደረጉ በኋላ አሜሪካኖቹ ስለ ኤርትራና ስለ ኢትዮጵያ የወደፊት ህልውና ቀደም አርገው የዚህ ዓይነት የተራቀቀ ፖሊሲ ማውጣታቸው ያስደነቀው መሆኑን ኢሳያስ ገለጠላቸው፡፡ ስለተለዋወጥዋቸው ሀሳቦች ግን በሰፊው ከበረሃ ጓደኞቹ ጋር ተወያይቶ የመጨረሻውን መልስ በተከታታይ እንደሚልክላቸው አስታውቆ ስብሰባው አበቃ፡፡ እኛም ለአዳርና ለግብዣ ተመልሰን በቃኘው ጣቢያ በተለይ ተዘጋጅቶልን ወደነበረው የሚስተር ኮፕላንድ መኖሪያ ቤት ሔድን፡፡ በማግሥቱ ኢሳያስን ወደ በረሃ ለመመለስ አሜሪካኖቹ ብዙ ዝግጅት ማድረግ አስፈለጋቸው፡፡ ምክንያቱም በዚያን ወቅት በአሥመራ መውጫና መግቢያ በሮች ሁሉ የተሰማሩት ፀጥታ አስከባሪዎች ከባድ ፍተሻ ያካሔዱ ስለነበር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነበር፡፡ ስለሆነም ኮፕላንድ ራሱ ሾፌር ሆኖ የአሜሪካን ባንዴራ የሚውለበለብበትና፣ የዲፕሎማቲክ ታርጋ ያለውን እንዲሁም የሗላው መስተዋት በመጋረጃ የተሸፈነ ካዲላክ መኪና በማዘጋጀት እኔንና ኢሳያስን ይዞ በምፅዋ መንገድ በኩል የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪ ወታደሮችን ሰላምታ እየተቀበልን ወደ ነፋሲት አመራን፡፡ ከነፋሲት ወደ ደቀምሐረ በሚወስደው መንገድ እስከማይሐባር አካባቢ ድረስ ኢሳያስን ይዘነው ሔድንና እዚያ ይጠብቁት ለነበሩት ጓደኞቹ አስረክበነው፣ እኛ ደግሞ በደቀምሐረ በኩል ዞረን ወደ አሥመራ ተመለስን፡፡ አሜሪካኖቹ ወዲያውኑ ይህን ስምምነት ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ዝግጅት ተያያዙት፡፡ ጨለማው መስከረም የተባለው የፍልስጥኤም ነጻ አውጭ ድርጅት ጥቃት ያደርስብናል በሚል ሽፋን ራስ አሥራተ ካሣን በማግባባት ከሀገራቸውና፣ በፀጥታ አስከባሪዎች ከየቦታው ተቀብረው የተገኙትን፣

እንደዚሁም በጦርነት የተማረኩትን አያሌ መሣሪያዎች በኤንትረ ከባድ መኪናዎች አስጭነውና ሸፋፍነው በማሰራጨት ከኤርትራ እስከ መሀል አገር ያሉት የአሜሪካ ደጋፊዎች በየቦታው እንዲጠናከሩ አደረጉ፡፡ ወዲያውኑ በምስራቃዊና በምዕራባዊ የኤርትራ ቆላዎች ከበድ ያለ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማካሄድ ከመሃል አገር ቁጥሩ በርከት ያለ ሠራዊት እንዲመጣ ተደረገ፡፡ ምክንያቱም በኤርትራ ክ/ሀገር ውስጥ ጦርነት ማቀጣጠል አንድ ስንኩል መንግሥት በማሃል ኢትዮጵያ ለመፍጠር ለታቀደው መፈንቅለ መንግሥት የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ እንዲሆን ታቅዶ ነበር፡፡ ይህ በእዚህ እንዳለ እነዚያ በቃኘው ጣቢያ ከሃብተስላሴ ገብረመድህንና ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የተካሄዱት ስብሰባዎች በድብቅ በቴፕና በፎቶግራፎች ተቀርጸው ስለነበር የካቲት 17 ቀን 1962 ዓ.ም. ፍሬ ነገሩ በጽሑፍ ሰፍሮ ከነፎቶግራፎቹ በአሥመራ የአሥራተ ካሣ ሰላይ በነበረው በሚስተር ግለንቦየት በተባለ አሜሪካዊ ተደርሶበት ለአሥራተ ካሣ ቀረበ፡፡ ለዚሁም ወንጀል መዝገብ ቁጥር 557/62 ቀኛ/ ካሳሁን መከላከያ ምስክር ገጽ 28 የሚለውን መመልከት ይቻላል፡፡ በዚህ ምክንያት እኔም ከደቀምሐረ ባስቸኳይ ተጠርቸ ተጠየቅሁ፡፡ ራስ አሥራተ ካሣም ኢሳያስ አፈወርቅና ጓደኞቹ ከአሜሪካኖቹ ጋር ለመገናኘታቸው እኔን በሃላፊነት ለመጠየቅ ሞከረ፡፡ እኔ ግን በበኩሌ አሜሪካኖቹ እንደልባቸው በየገጠሩ ሁሉ እንዲዘዋወሩ በመንግሥት ስለተፈቀደላቸው ሰፊ ግንኙነት ማቋቋማቸውን ገልጨ፣ ጉዳዩ የኔ ሃላፊነት አለመሆኑን አስረዳሁ፡፡ እንደዚሁም እኔ የወረዳው ገዢ በመሆኔ ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥት የሰላም ጉባኤ በማለት ያቋቋመው ኮሚቴ ተወካይም ስለሆንኩ፣ በዓላ በረሃ የሚካሄደውን እንቅስቃሴ በቀጥታ ለመከታተል ኃላፊነት እንደነበረብኝ በተጨማሪ አስረዳሁ፡፡ ይህንን ከገለጽኩ በኋላ ሆኔታውን ወደፊት በምስጢር እየተከታተልኩ ዕለት በዕለት ሪፖርት እንዳቀርብ በአሥራተ ካሣ ትእዛዝ ተሰጠኝ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን የአሥራተ ካሣ የወደፊት ሴራ በየአቅጣጫው መወራት በመጀመሩ የተፈጠረውን ውዥንብር ለማርገብ እኔ እንድታሰርና በወንጀል እንድከሰስ ተደረገ፡፡ ራስ አሥራተ ካሣም ስሙን ለመጠበቅ ሲል በምስጢር ይደራደራቸው የነበሩት የዓላ በረሃ ተገንጣይ ቡድን አባሎች በጦር ኃይል እንዲመለሱ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡

እስከ አሁን ድረስ የሁለቱ የኤርትራ ግንባሮች ውስጣዊ እይታ ምን ይመስል እንደነበር በጥቂቱ ዳስሰናል፡፡ አሁን ደግሞ በደርግ ዘመን የነበረውን የግንባሮቹን ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንቃኛለን፡፡

ከቀይ ኮከብ ዘመቻ በፊት ከ1972-1974 በነበረው ዘመን የኤርትራ ግንባሮች እርስ በርስ ሲገዳደሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች ጋር መዋጋቱን በአብዛኛው ረስተውት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ በዚህም የተነሳ በወቅቱ በኤርትራ ምድር የነበረው ከ25፣000 የሚበልጥ ጦር ከጦር ሰፈሩ ወጥቶ አንቅስቃሴ አላደረገም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮት ከፈነዳ በኋላ ግን ግንባሮቹ ከህዝቡ በመጣባቸው ከፍተኛ ግፊት ምክንያት በጥቅምት 1974 የተኩስ አቁም አድርገዋል፡፡ የተኩስ አቁሙ እርስ በርስ ባለመዋጋት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ጠላትን በጋራ መመከት፣ አንደኛው የሌላኛውን ይዞታ ማክበር፣ ለውጊያም ሆነ ለሌላ እንቅስቃሴ የሚሰማራን ሀይል (የሻዕቢያና ጀብሃ) በመንገድ ላይ አለማገት ወዘተ… የመሳሰሉ ተጨማሪ ግዴታዎችም ነበሩት፡፡ የተኩስ አቁሙ ግንባሮቹ በኤርትራ ምድር መጠነ ሰፊ ማጥቃት እንዲሰነዝሩ አስችሎአቸዋል፡፡ በውጤቱም የጀብሃ ሰራዊት ተሰነይ፣ አቆርዳት፣ አሊጊደር፣ ኡምሀጀር፣ መንደፈራ እና አዲኳላ፣ ከመሳሰሉ ከተሞች በተጨማሪ የባርካ አውራጃን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ፡፡ ሻዕቢያ ደግሞ ከሳህል እና ሰንሒት አውራጃዎች በተጨማሪ ከረን፣ ደቀምሐረ፣ ጊንዳዕ፣ ሰገነይቲ፣ ነፋሲት፣ የመሳሰሉትን ከተሞች በእጁ አስገባ፡፡ በግንባሮቹ እጅ ያልገቡት አስመራ፣ ምጽዋ እና ባሬንቱ ብቻ ነበሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግንባሮቹ አስመራን በ10 ኪሎሜትር ቀለበት ከበዋት ከዛሬ ነገ እንገባለን በሚል ተስፋ ይጠባበቁ ነበር፡፡ በጥር ወር 1975 ሻዕቢያ አስመራን ለመያዝ ያደረገው አደገኛ ሙከራ አልተሳካለትም፡፡ በወቅቱ ለአራት ተከታታይ ቀናት በተካሄደ ውጊያ ከሁለቱም ወገን ከፍተኛ እልቂት አስከትሏል (በአንዳንድ ጋዜጠኞች ግምት ከሁለቱም ወገን 3000 ተዋጊዎች ሞተዋል)፡፡ በነዚህ ቀናት ሲቪሉ የአስመራ ነዋሪም የእልቂቱ ሰለባ ሆኗል፡፡ ጦርነቱን ተከትሎ በተካሄደው የማጽዳት ዘመቻ ከሺህ የማያንሱ ሲቪሎች እንደሞቱ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ይፋ አድርገዋል፡፡ በተለይም የደርግ መንግሥት ለአንድ ዓመት ያህል የኤርትራ አስተዳዳሪ እና የሁለተኛ ክፍለጦር አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ጌታቸው ናደው ግንባሮቹ ለሚፈጽሙት ጥቃት ሲቪሎችን ተጠያቂ በማድረግ ጭፍጨፋ ያካሂዱ እንደነበር የተለያዩ ጸሓፊዎች ዘግበዋል፡፡ ለምሳሌ ሚያዚያ 1975 ሻዕቢያ ጸሎት በተሰኘችው አነስተኛ መንደር ባካሄደው የደፈጣ ጥቃት በርካታ የመንግሥት ወታደሮችን ሲገድል ጄኔራል ጌታቸው ወደ አየር ሀይል መደብ ደውለው “አሁኑኑ ተነስተህ ወደ ጸሎት ብረር፡፡ ጸሎት ላይ የሚንቀሳቀስ ዛፍ እንደላይ፤ ከአስራ አምስት ደቂቃ በኋላ ስለ አፈጻጸሙ ሪፖርት እፈልጋለሁ” የሚል የጀብደኝነትና የጭካኔ ትዕዛዝ ሲሰጡ መስማታቸውን “ነበር” የተሰኘውን መጽሐፍ የጻፉት ዘነበ ፈለቀ (ገስሥ ተጫኔ) ይመሰክራሉ፡፡ በ1976 በብዙ ጸሓፊዎችና ምሁራን የተተቸውና በአሳዛኝ ፍጻሜ የተደመደመው የራዛ ዘመቻ ተካሄደ፡፡ ይህ ዘመቻ ለደርግ በማን እንደተወጠነ አይታወቅም፡፡ አንዳንዶች (ለምሳሌ ባቢሌ ቶላ) “የመኢሶን ውጥን ነው” እያሉ ቢጽፉም መኢሶን ከጥንስሱ ጀምሮ የዘመቻው ተቃዋሚ እንደነበር የደርግ ሰዎች ራሳቸው መስክረዋል፡፡ በርካታ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችም “ዘመቻው ይገታ!” በማለት ጮኸዋል፡፡ የራዛ ዘመቻ ዓላማ የጀብሃና የሻዕቢያን ሀይል ከጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ እና ትግራይ በተውጣጡ ገበሬዎች መምታት ነበር፡፡ እነኛ ገበሬዎች በቂ ስልጠናና የዝግጅት ጊዜ ሳይወስዱ ነበር የዘመቱት፡፡ ገበሬዎቹ የታጠቋቸው መሳሪያዎችም አልቤን፣ መውዜር፣ ቺኮዝ፣ ምንሽር፣ ዲሞትፈር የመሳሰሉት

ኋላቀር ጠመንጃዎች ነበሩ፡፡ በቂ ጥይትም ሆነ የስንቅ አቅርቦት አልነበራቸውም፡፡ ከሁሉም የሚያሳዝነው ደግሞ እነኝህ የውትድርና ልምድ ጨርሶ የሌላቸውን ገበሬዎች በደፈጣ ጥቃት በተካነው የጀብሃና ሻዕቢያ ሰራዊት ላይ ማዝመቱ ነበር፡፡ እነዚህ ገበሬዎች ለዘመቻቸው እንዲነሳሱ “ጀብሃ እና ሻዕቢያን አባርረው የማረኩት ንብረት በጠቅላላ የናንተ ይሆናል፤ ወንበዴዎቹ የለቀቁት መሬትም የናንተ የግል ንብረት ስለሚሆን እንደሻችሁ ትገለገሉበታላችሁ” የሚል ቃል ተሰጥቶአቸው ነበር፡፡ ዘማቾቹ በሶስት ግንባር ነው ወደ ኤርትራ የነጎዱት፡፡ አንደኛው ቡድን ተነስቶ ተከዜን ተሻግሮ ከኡምሀጀር ጀምሮ ጀብሃን እየመታ ተሰነይ እንዲገባ ነበር የታሰበው፡፡ ሁለተኛው ቡድን ከኢንቲጮ ተነስቶ መረብን በመሻገር ሻዕቢያን እየመታ እስከ ሰንአፌ እንዲደርስ ነበር የተፈለገው፡፡ ሶስተኛው ቡድን ከሽሬ (እንዳሥላሤ) በመነሳት በጾረና በኩል ወደ መንደፈራ እንዲዘምት ታስቦ ነበር፡፡ ሁለቱ ሽምቅ ተዋጊዎች ወደነርሱ የሚጎርፈውን የገበሬ ማዕበል ለመመለስ ምሽግ መቆፈር አላስፈለጋቸውም፡፡ ቦታ ቦታ ጠብቆ በአር.ፒ. ጂ ሮኬትና በመትረየስ መምታት ብቻ በቂአቸው ነበር፡፡ በዚህም አኳኋን ከሁመራ የተነሳው ዘማች ሀይል ገና ተከዜን እንደተሻገረ፣ በኢንቲጮ በኩል የዘመተው ከትግራይ ድንበር ሳያልፍ በሮኬትና በመትረየስ ተደበደበ፡፡ ይህ ቀረሽ የማይባል የኢትዮጵያዊያን እልቂት ተከሰተ፡፡ ብዙዎች ተማረኩ፡፡ ከእልቂትና ምርኮ የተፈረው መንገድ ጠፍቶት ሲዳክር በውሃ ጥም አለቀ፡፡ ጥቂቶች በጥንካሬ ወደ ትግራይ ከተሞች ለመድረስ ቢችሉም ከደረሰው ውድቀት አንጻር ቁጥራቸው ይህ ነው አይባልም፡፡ በሁለቱ ቡድኖች ላይ የደረሰውን እልቂት ያስተዋለው ወታደራዊ ደርግ ሶስተኛው ቡድን ከሽሬ ሳይንቀሳቀስ ወደመጣበት እንዲመለስ ሸኘው (በዘመቻው ተሳትፈው በሰላም ለተመለሱ ገበሬዎች የያዙት ጠመንጃ በነጻ ተሰጥቶአቸዋል)፡፡ በ1977 እዚህ ግባ የሚባል ወታደራዊ እንቅስቃሴ በኤርትራ ምድር አልተካሄደም፡፡ የዚህም ምክንያት በሶሻሊስት ሀገራት አሳሳቢነት በግንባሮቹና በደርግ መንግሥት መካከል ሰላማዊ ድርድሮች መካሄድ መጀመራቸው ነው፡፡ በዚህም መሰረት የቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን በህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) እና በደርግ መንግሥት መካከል የሚካሄደውን የሰላም ድርድር አመቻችታለች፡፡ በውይይቱ ላይ የሻዕቢያው መሪ አሳያስ አፈወርቂ ተሳፏል፡፡ በተጋድሎ ሓርነት ኤርትራና በደርግ መንግሥት መካከል የተካሄደውን ድርድር የሸመገለችው ደግሞ ሶቪየት ህብረት ነበረች (አብደላ ኢድሪስ ጀብሃን በመወከል ሞስኮ ተገኝቷል)፡፡ ይሁንና ሁለቱም ውይይቶች ፍሬ አላፈሩም፡፡ በሌላ በኩል በዚያ ዓመት (1977) የተጀመረው የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ደርግ ሙሉ ትኩረቱን በኦጋዴን ላይ ብቻ እንዲያደርግ ስላደረገው በኤርትራ ምድር የነበረውን ወታደራዊ ዘመቻ እንዲያቀዘቅዝ ምክንያት ሆኗል፡፡ የሶማሊያው ጦርነት በ1978 አጋማሽ ላይ በድል ሲጠናቀቅ የደርግ መንግሥት ከድል አድራጊው ጦር ግማሽ ያህሉን “ሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት” በማለት አደራጀ፡፡ ይህ 150 ሺህ ያህል የሰው ሀይል ያቀፈው ትኩስ ሀይል “የምስራቁ ድል በሰሜንም ይደገማል” የሚል መፈክር በመጨበጥ ወደ ኤርትራ ምድር ተመመ፡፡ ጦር ሰራዊቱ በአምስት ግብረ-ሀይሎች ተከፋፍሎ ነበር ወደ ኤርትራ የዘመተው፡፡ የግብረ-ሀይሎቹ መነሻና ግብ እንደሚከተለው ነበር፡፡ ሀ/. 501ኛ ግብረ ሀይል፡- ከሁመራ ተነስቶ በኡምሐጀር በማድረግ ተሰነይ ይገባል፡፡ ለ/. 502ኛ ግብረ ሀይል፡- ከሽሬ ተነስቶ፣ በሸምበቆ አድርጎ ባሬንቱን ከጀብሃ ያስለቅቃል፡፡ ከዚያም ከ501ኘ ግብረ-ኃይል ጋር ይጋጠምና ወደ አቆርዳት ይገባል፡፡

ሐ/.503ኛ ግብረ ሀይል-ሀ፡- ከመረብ ድልድይ ተነስቶ አዲኳላን በማስለቀቅ አረዛ ከተማ ይገባል፡፡ መ/. 503ኛ ግብረ-ኃይል-ለ፡- ከገርሁ ሰናይ ተነስቶ በጾረና በኩል በማድረግ ከዘላአምበሳ-አስመራ የሚያደርሰውን ጎዳና ማጽዳት ሠ/. 504ኛ ግብረ ኃይል፡- ከአስመራ ተነስቶ ኃይሉን በሶስት አቅጣጫ በማነቃነቅ በዙሪያው ያለውን የጠላት ኃይል ወደ ውጪ በመግፋት አረዛ ላይ ከ503ኛ/ሀ፣ ደቀምሐረ ላይ ከ503/ለ፣ ከረን ላይ ከ502ኛ ግብረ-ኃይሎች ጋር መገናኘት ነበር፡፡ ረ/. 505ኛ ግብረ-ሀይል ምጽዋን ሙሉ በሙሉ ከጠላት ከበባ ካላቀቀ በኋላ ኃይሉን ለሁለት ከፍሎ አንዱ ወገን ዶጋሊን ተቆጣጥሮ ከምጽዋ አስመራ መንገድን ነጻ ማድረግ ሌላው ወገን ደግሞ በመርከብ ወደ መርሳ ጉልቡብ ተጉዞ አልጌናን መያዝና ከናቅፋ ጀርባ መግባት ነው፡፡ በሁሉም ግንባሮች የዘመቱት ግብረ-ሀይሎች የተሰጣቸውን ግዳጅ በከፍተኛ መስዋእትነት ፈጸሙ፡፡ ሻዕቢያና ጀብሃም በጦር አውሮፕላኖች የተጠናከረውን የሁለተኛ አብዮታዊ ሰራዊት ጥቃት ለመመከት በብርቱ ሞከሩ፡፡ በተለይ ኤላበረድ በምትባለው አነስተኛ ከተማ አቅራቢያ የሻዕቢያ ሀይሎች ከአብዮታዊ ጦር ሰራዊት ጋር ለሶስት ተከታታይ ቀናት የዘለቀ ከባድ ውጊያ አካሄዱ፡፡ ሆኖም የጦር ሰራዊቱ ጥቃት ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ “ከረን” የተሰኘችውን ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ከተማ ለመልቀቅ ተገደዱ፡፡ አብዮታዊ ሰራዊት ግብ-ሀይሎችም በአማጺያኑ የተያዙትን የኤርትራ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩ፡፡ ሆኖም የተሰጣቸውን የመጨረሻ ግብ ማሳካት አልቻሉም፡፡ ሻዕቢያና ጀብሃን ከናቅፋ ማባረር እንዲህ በቀላሉ የሚደረስበት ሆኖ አልተገኘም፡፡ ስለዚህ ሰራዊቱ በተጨማሪ ስልጠናና ትጥቅ እስኪደራጅ ድረስ ይዞታውን እያጠናከረ እንዲቆይ ተደረገ፡፡ በ1978 መጨረሻ ገደማ ሁለት አነስተኛ ዘመቻዎች ተደርገዋል፡፡ በ1979 አጋማሽ ላይ አብዮታዊ ሰራዊት ናቅፋ ከሻዕቢያ ለማስለቀቅ ከባድ ዘመቻ ከፈተ፡፡ ሆኖም ሻዕቢያ በሰላዮቹ አማካኝነት ያገኘውን መረጃ በመጠቀም ተዋጊዎቹን በደፈጣ ስልት በማሰለፉ ከተቃጣበት ጥቃት ተረፈ፡፡ ይባስ አብዮታዊ ሰራዊቱ ተዘናግቶ በሰፈሩ ሲከትም ሻዕቢያ የተበታተነውን ሀይሉን በማሰባሰብ ድንገተኛ ጥቃት ከፈተበት፡፡ በአብዮታዊ ሰራዊት ላይ ብርቱ ጉዳት ደረሰበት፡፡ የሰፈረበት የናቅፋ መሬት ለጥቃት እንዳጋለጠው በመታመኑ ወደ አፋበት እንዲያፈገፍግ ተደረገ፡፡ ሻዕቢያም የሚያፈገፍገውን ጦር እየተከላከለ ወጋው፡፡ ከሶማሊያ ወረራ ወዲህ ታላቅ የተባለውን የመጀመሪያ ድሉን ተጎናጸፈ፡፡ በምዕራብ ኤርትራ የነበረው ሁኔታ ደግሞ ከዚህ ይለያል፡፡ በክፍል ሰባት እንደገለጽኩት ጀብሃ በርሱ ላይ የዘመተውን ብዙ ሺህ ሰራዊት ከመሸሽ ይልቅ በመጋፈጡ ሀይሉን አስጨርሷል፡፡ ለክፉ ቀን ይሆነኛል ብሎ የያዘው የባርካ ቆላ ሜዳማ በመሆኑ ከሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ጥቃት ሊያድነው አልቻለም፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ ልክ እንደ ሻዕቢያ ወደ ሳህል መሸሽ ነበር፡፡ ከ1979-1983 ድረስ በነበሩት ዓመታት የተደረጉት ጦርነቶች እዚህ ግባ የሚባሉ አልነበሩም፡፡ ሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ሻዕቢያ ከናቅፋ ተራሮች እንዳይወርድ በማድረግ ብቻ ተወስኖ ነበር፡፡ በሌላ በኩል በነኝህ ዓመታት ሻዕቢያና ጀብሃ በመካከላቸው የነበረውን ስምምነት አፍርሰው መተላለቅ በመጀመራቸው ሻዕቢያ ጀብሃን ከኤርትራ ምድር በማባረር ወደ ሱዳን እንዲገባ አድርጎታል፡፡ ጀብሃን በመምታቱ ረገድ ህወሐትም ከሻዕቢያ ጋር በትብብር ሰርቷል፡፡

የኤርትራ አማጺያንን ለማጥፋት ከተደረጉ ዘመቻዎች መካከል ብዙ የተባለለት ነው- የቀይ ኮከብ ዘመቻ፡፡ ታዋቂ የጦር ጠበብት እየደጋገሙ አውስተውታል፡፡ በጋዜጣና በሬድዮ ብዙ ተለፍፎለታል፡፡ አጀማመሩም ሆነ አፈጻጸሙ ትንግርተኛ መሆኑ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ ዘመቻው የተካሄደበት ለየት ያለ ድባብና በርሱ ሳቢያ የተፈጠረው ሀገር አቀፍ ንቅናቄ “ኦሮማይ” የተሰኘው ተወዳጅ ድርሰት እንዲጻፍ ምክንያት ሆኗል፡፡ ያ ዘመቻ በኦፊሴል “የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ” ተብሎ ነበር የተሰየመው፡፡ የዘመቻው ዓላማዎችም ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ሻዕቢያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ ነው፡፡ ሁለተኛው በጦርነቱ የፈራረሱ መሰረተ-ልማቶችን መገንባት ነው፡፡ ለዘመቻው “ቀይ ኮከብ” የሚል ስም የተሰጠው ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ-ማሪያም የአሜሪካ ባህር ሀይል “ብሩህ ኮከብ” (Bright Star) በሚል ስም በቀይ ባህር ላይ ላደረገው ወታደራዊ ልምምድ ምላሽ መሆን አለበት በማለት ባደረጉት ውሳኔ መሰረት እንደሆነ በወቅቱ የኤርትራ ክፍለ-ሀገር ኢሠፓአኮ ተጠሪ የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “ቀይ እምባ” (Red Tears) በተሰኘው መጽሐፋቸው ገልጸዋል፡፡ የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ ይፋ የተደረገው በሀገር አቀፍ ደረጃ በታወጀ ልዩ አዋጅ ነው፡፡ ዘመቻውን በበላይነት የሚያስፈጽም ከፍተኛ ስልጣን የተሰጠው ሀገር አቀፍ ምክር ቤት ተቋቁሞለታል፡፡ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ሲሆኑ ዋና ጸሓፊው ኤርትራዊው አቶ አማኑኤል አምደሚካኤል ነበሩ፡፡ የሀገሪቱ ምርጥ ምሁራን የተሳተፉበትና ድርጅታዊ ሀይሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሟላለት የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤትም አስመራ ላይ ተሰይሞም ነበር፡፡ ለዘመቻው ማስፈጸሚያ ከሁለት ቢሊዮን ብር የሚበልጥ (በዛሬው የምንዛሬ ተመን ወደ ሀያ ቢሊዮን ብር ያህል የሚሆን) በጀት ተመድቦለታል፡፡ ዘመቻውን ለማስፈጸም በሚልም ከሊቀመንበር መንግሥቱ ጀምሮ ሀገሪቷ ያሏት ከፍተኛ ወታደራዊና የሲቪል ባለስልጣናት አስመራ ላይ ከትመዋል፡፡ የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ በይፋ የተከፈተው ጥር 17/1974 ነበር፡፡ የዘመቻውን መከፈት በሚያበስረው ጉባኤ ላይ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር የተወከሉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሙያተኞች፣ መለዮ ለባሾች፣ የገበሬ ተወካዮች ወዘተ.. ተሳትፈዋል፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ጉባኤውን የከፈቱበት ንግግር በሬዲዮ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ ተላልፏል፡፡ የአስራ አራቱ ክፍለ ሀገር ተወካዮችም በጉባኤው ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡ ጉባኤው ጥር 23/1974 ሲጠናቀቅ ሰባት ነጥቦች ያሉት “የአስመራ ማኒፌስቶ” በአቋም መግለጫ መልክ ይፋ ተደርጓል፡፡ የቀይ ኮከብ ዘመቻ ጉባኤ በተከፈተበት ማግስት በቀይ ባህር ዳርቻ በምትገኘው “ጉርጉሱም” የተባለች ሰርጥ ላይ የተዘጋጀው የምጽዋ ኤክስፖ በሊቀመንበር መንግሥቱ ተመርቋል፡፡ ዶጋሊ ላይ ሊገነባ ለታቀደው የራስ አሉላ መታሰቢያ ሀውልት የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡትም ሊቀመንበር መንግሥቱ ነበሩ፡፡ በምጽዋ ከተማ በሚገኘው “አጼ ካሌብ አዳራሽ” ታሪካዊው የምጽዋ ሲምፖዚየም ተካሂዷል፡፡ በአስመራና በምጽዋ ከተሞች የሚገኙ በርካታ ፋብሪካዎችም ተጠግነው የማምረት ተግባራቸውን እንዲጀምሩ ተደርገዋል፡፡ ከምጽዋ-አቆርዳት የተዘረጋው የባቡር መስመርም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ይህ ሁሉ ከተገባደደ በኋላ ነው ወታደራዊው ዘመቻ የተካሄደው፡፡ የቀይ ኮከብ ወታደራዊ ዘመቻ በአራት ግንባሮች ነበር የተከናወነው፡፡

1. በብርጋዴር ጄኔራል አበራ አበበ የሚታዘዘው ውቃው እዝ በአልጌና በኩል (በሰሜናዊ ቀይ ባሕር ጠረፍ፣ ከናቅፋ ጀርባ እንዲያጠቃ) 2. በብርጋዴር ጄኔራል ውበቱ ጸጋዬ የሚታዘዘው ናደው እዝ ከከረን ጀርባ ወደ ናቅፋ በር በከርከበት ግንባር (ከናቅፋ ደቡባዊ ምሥራቅ በኩል) እንዲያጠቃ 3. በብርጋዴር ጄኔራል ቁምላቸው ደጀኔ የሚታዘዘው መብረቅ እዝ በቃሮራ ግንባር (ከናቅፋ ሰሜን ምዕራብ) እንዲያጠቃና የሻዕቢያን መውጫ እንዲዘጋ 4. በብርጋዴር ጄኔራል ከበደ ጋሼ የሚታዘዘው መክት እዝ የአስመራን ዙሪያ እንዲያጥር የሚል ትዕዛዝ ተቀብለው ለውጊያ ዝግጁ ሆኑ፡፡ የካቲት 8/1974 ጎህ ከመቅደዱ በፊት በሁሉም ግንባሮች ወደ ናቅፋ የመጠጋት እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ የናቅፋ ተራሮች በቢ.ኤም. እና በሞርታር ተደበደቡ፡፡ ከሰማይ በሚወርዱ የአውሮፕላን ቦንቦች ታረሱ፡፡ ሮኬቶችና ካሊበሮች ተወናጨፉ፡፡ ናቅፋ እሳተ ጎመራ የፈነዳባት መሰለች፡፡ ሻዕቢያ መጥፊያው የተቃረበ መሆኑን ገምቶ ከናቅፋ ምሽጉ ሊወጣ ሲሰናዳ በሁሉም አቅጣጫዎች ዝግ ሆነበት፡፡ ስለዚህ ተራሮቹን የሙጥኝ ብሎ መከላከሉን ቀጠለ፡፡ የእግረኛና ሜካናይዝድ ውጊያ እንዲጀምር የታዘዘው በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ የተሰለፈው መብረቅ እዝ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እዙ በታቀደለት ሰዓት ባለመንቀሳቀሱ ሻዕቢያ በርቀት ያሉ ሀይሎቹን እንዲያሰባስብ ጊዜ ሰጠው፡፡ በሌላ በኩል ለዚሁ የመብረቅ እዝ ግንባር ቀደም ሆኖ የማጥቃት ግዳጅ የተሰጠው 21ኛ ተራራ ክፍለጦር በብቃቱ እንደተጠበቀው ሆኖ አልተገኘም፡፡ ክፍለ-ጦሩ በተያዘለት እቅድ መሰረት ወደ ናቅፋ ተራሮች ምዕራባዊ ክፍል ተጠግቶ ሻዕቢያን ማባረር አቃተው፡፡ ይባስ ብሎም ጠላት በሰራለት ቀለበት ውስጥ ገብቶ ተከበበ፡፡ ሻዕቢያም ባለ በሌለ ኃይሉ ተረባረበበት፡፡ የተራራ ክፍለ ጦርም ተፍረከረከ፡፡ ሺዎች በሜዳ ላይ እንደ ቅጠል ረገፉ፡፡ የውቃው እና የናደው እዞች የተሻለ ጀግንነት አሳይተው ከናቅፋ ስምንት ኪሎሜትር ርቀት ላይ ደረሱ፡፡ ይሁንና ባልታወቀ ምክንያት በተሰጠ ትዕዛዝ እንቅስቃሴአቸው ተገታ፡፡ ከዚያ በኋላ እንንቀሳቀስ ቢሉ የማይቻል ነገር ሆነ፡፡ ሻዕቢያ ተዋጊዎቹን ከያሉበት አሰባስቦ ወደ ኋላ ይገፋቸው ጀመር፡፡ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ባደረገው መልሶ ማጥቃት በአፋቤት (ከርከበት) ግንባር በዘመተው ናደው እዝ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ፡፡ ሺዎች ሙትና ቁስለኛ ሆኑ፡፡ በትልቅ ሞራልና የድል ጉጉት የተጀመረው የቀይ ኮከብ ዘመቻም በከፍተኛ ሽንፈት ተፈጸመ፡፡ የውቃውና የናደው እዞች ከናቅፋ አጠገብ ደርሰው እንዲቆሙ የተደረገበት ምክንያት እስከዛሬ ድረስ በግልጽ አይታወቅም፡፡ ሻለቃ ጌታቸው የሮም በጻፉት መፅሐፍ “አንድ ከፍተኛ የኢሠፓ ባለስልጣን ሻዕቢያ እያዘናጋችሁ ሊፈጃችሁ ስለተዘጋጀ መቆም አለባችሁ’ የሚል ትዕዛዝ ስለሰጠ ነው” ይላሉ፡፡ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው “የጦር ሀይሎቹ መዋጋት ያቆሙት ናቅፋን የመያዙ ተግባር ሊቀመንበር መንግሥቱ ረጅም ዕድሜአቸውን ባሳለፉበት አንበሳው ሶስተኛ ክፍለ ጦር እንዲፈጸም ስለተፈለገ ነው” በማለት ጽፈዋል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ግን ይህንን አባባል በከፍተኛ ቁጣ

አስተባብለዋል፡፡ “ከሁሉም ጦሮች ቀድሞ ናቅፋ የደረሰውና ያለቀው ሶስተኛ ክፍለጦር ነው” በማለትም ተከራክረዋል፡፡ ለዘመቻው አጠቃላይ ውድቀት መንስኤ የሆነው ምክንያትም በታሪክ ጸሐፊዎችና በወታደራዊ ጠበብቶች ስምምነት አልተደረገበትም፡፡ ይሁንና አቶ ገስጥ ተጫኔ (ዘነበ ፈለቀ) በጻፉት “ነበር” የተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ የሰነዘሯቸው ነጥቦች ብዙዎችን የሚያስማሙ ይመስላሉ፡፡ እነርሱም 1. የመብረቅ እዝ በተሰጠው ሰዓት መሰረት ግዳጁን አለመፈጸሙ 2. ለኤርትራ መሬት እንግዳና ባዳ የሆነውና በቅርብ ጊዜ ከማሰልጠኛ የወጡ ሀይሎች የተሰባሰቡበት 21ኛው ተራራ ክፍለጦር ግንባር ቀደም መቺ ሀይል ሆኖ ወደ ናቅፋ እንዲዘምት መደረጉ 3. ሊቀመንበር መንግሥቱ ለድል በመቸኮላቸው የውጊያው እቅድ ሲከለስ ከወታደራዊ አዛዦች የተሰጡትን የእርማትና የማሻሻያ ሐሳቦች ጨርሶ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸው (ለምሳሌ ጄኔራል አበራ አበበ 21ኛው ተራራ ክፍለጦር አስተማማኝ ባለመሆኑ ግዳጁ ለሌላ ጠንካራ ክፍለ ጦር እንዲሰጥ ያቀረቡትን ሐሳብ ጨርሶ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው)፡፡ 4. የእዞቹ አዛዦች በእቅዱ ሳያምኑበት ወደ ውጊያ የገቡ መሆናቸውና ሌሎችም ምክንያቶች ናቸው፡፡ የቀይ ኮከብ ዘመቻ በውድቀት ከጨነገፈ በኋላ የውድቀቱ መንስኤ ተጠንቶ ለውሳኔ እንዲቀርብ ታዘዘ፡፡ በዘመቻው የውጊያ ኢኒስፔክሽን መምሪያ ሃላፊ የሚመራ ቡድን የመብረቅ እዝ ወደ ሚገኝበት ቃሮራ ግንባር ተላከ፡፡ ቡድኑ ማጣራቱን ካከናወነ በኋላ የ21ኛው ተራራ ክፍለ ጦር አዛዥ የነበሩት ኮሎኔል ውብሸት ማሞ እና የክፍለጦሩ 47ኛው ብርጌድ አዛዥ የሆኑት ሌ/ኮ/ል ስለሺ አስፋው የውድቀቱ ተጠያቂዎች ናቸው ተባሉ፡፡ ሁለቱ መኮንኖች በልዩ ትዕዛዝ ከተቋቋመ የጦር ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው በተላለፈባቸው ፍርድ መሰረት ኮ/ል ውብሸት ማሞ ተረሸኑ፡፡ ሌ/ኮ/ል ስለሺ አስፋው ደግሞ ማዕረጋቸውን ተገፍፈው ወህኒ ወረዱ፡፡ የመብረቅ እዝ ዋና አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ቁምላቸው ደጀኔ ወደ አስመራ ተጠርተው በቁም እስረኛነት ለረጅም ጊዜ ተቀመጡ፡፡ አንድ ዓመት ሙሉ ዝግጅት የተደረገበት የቀይ ኮከብ ዘመቻ በዚሁ መልክ ነበር የተደመደመው፡፡ ሁለት ቢሊዮን ብር በሁለት ወር ተንኖ ውስጥ ተንኖ ቀርቷል፡፡ ታዲያ ሊቀመንበር መንግሥቱ የባሰ እልህ ይዞአቸው “ቀይ ኮከብ ሁለት” እና “ቀይ ኮከብ ሶስት” የተሰኙ ዘመቻዎችን ሞክረው ነበር፡፡ ውጤቱ ግን ሊሰምርላቸው አልቻለም፡፡ በርካታ ታዛቢዎች እንደሚሉት ኮ/ል መንግሥቱ ዘመቻው እንዳበቃ የናደውና የውቃው እዞች የናቅፋን ዙሪያ አጥረው እንዲቆዩ ቢደረግና ለኤርትራ ችግር ሰላማዊ መፍትሔ ወደ ማፈላለጉ ቢሄዱ ኖሮ ጥሩ ውጤት በተገኘ ነበር፡፡ ምክንያቱም ዘመቻው ሻዕቢያንም ክፉኛ ያደከመ በመሆኑ ምናልባት አማጺው ሀይል ሰላማዊውን አማራጭ ይቀበል ነበር ተብሎ ይታሰብ ነበርና፡፡ የቀይ ኮከብ ዘመቻ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ነው ያለፈው፡፡ አብዮታዊ ሰራዊት በዘመቻው ማብቂያ ላይ ባጋጠመው ውድቀት ክፉኛ ተናግቷል፡፡ የወታደሮቹ ስነ-ልቦናም በጣም

ተቃውሷል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማንኛውም የጦር ሀይል ወደ ናቅፋ መጠጋት ይፈራ ነበር፡፡ ዘማቾች “ናቅፋ” ከተባለ “ሞት” ብቻ ነበር የሚታያቸው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የቀይ ኮከብ ዘመቻ ለሻዕቢያ ሀይሎች ከፍተኛ የሞራል ስንቅ ሆኖአቸዋል፡፡ “17,000 ሆነን ከ150,000 የሚልቅ፣ እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀና በአውሮፕላንና በቢ.ኤም የተጠናከረ ግዙፍ ሰራዊት ድል አድርገናል” በማለት እንዲኩራሩ አድርጎአቸዋል፡፡ ናቅፋንም “ምልክት ጽናትና” (የጽናታችን ምልክት) በማለት እንዲጠሯት መንስኤ የሆናቸው ይኸው ነው፡፡

ድህረ-ቀይ ኮከብ የቀይ ኮከብ ዘመቻ በሽንፈት ከተቋጨ በኋላ የዘመቻውን መጀመር በከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ ያበሰሩት የመንግሥት ሚዲያና ፕሬሶች በዝምታ ተዋጡ፡፡ በኤርትራ ምድር ስለሚካሄድ ወታደራዊም ሆነ ሰብዓዊ እንቅስቃሴ ደፍሮ የሚናገር ጠፋ፡፡ የቀይ ኮከብ ዘመቻም ይፋዊ ባልሆነ መንገድ በሰኔ 20/1984 ተሰረዘ (የዘመን አቆጣጠሩ እንደ አውሮጳ ቀመር መሆኑን አትርሱ)፡፡ አንዳንድ ጸሐፍት ዘመቻው እንደታቀደው በድል ቢደመደም ኖሮ ሻዕቢያ ከኤርትራ ምድር ይነቀልና ኤርትራም በማያሻማ ሁኔታ የኢትዮጵያ አካል መሆኗ ይረጋገጥ ነበር ይላሉ፡፡ ሌሎች ግን ይህንን አባባል ይቃወማሉ፡፡ “የኤርትራ ችግር በሰላማዊ መንገድ እስካልተፈታ ድረስ የሻዕቢያ መጥፋት ብቻውን የኤርትራን ኢትዮጵያዊነት አያረጋግጥም” በማለትም ያክላሉ፡፡ ታዲያ ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሔ ለማስገኘት የተደረገው ጥረት በጣም አነስተኛ ነበር፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማሪያም ከወታደራዊ እርምጃ በስተቀር የሰላሙን መንገድ መከተልን እንደ አማራጭ አልወሰዱትም፡፡ አንዳንድ ከፍተኛ የደርግ ባለስልጣናት ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሔ ለማስገኘት በራስ ተነሳሽነት ያደረጉት ጥረት ከግብ ሳይደርስ የቀረው ሊቀመንበር መንግሥቱ ችግሩን በወታደራዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት በመወሰናቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ለምሳሌ የቀድሞው የሀገርና ህዝብ ደህንነት ሚኒስትር ኮ/ል ተስፋዬ ወልደሥላሤ በግላቸው ያደረጉት የሰላም ጥረት በሊቀመንበሩ ግትርነት እንደተሰናከለባቸው በምሬት ተናግረዋል፡፡ በመጋቢት ወር 1975 አንዳንዶች “ጸጥተኛው ዘመቻ” በማለት የሚጠሩት ወታደራዊ ኦፕሬሽን ተጀምሮ ነበር፡፡ ዘመቻው “ጸጥተኛ” ተብሎ የተጠራው በህዝብ ሚዲያ ምንም ዓይነት ቅስቀሳ ስላልተደረገለት ነው፡፡ በዚህ ዘመቻ የተካፈለው የወታደር ብዛት በቀይ ኮከብ ጊዜ ከነበረው እጅግ በጣም ያንሳል፡፡ የዘመቻው ትኩረትም ከከረን ከተማ በስተሰሜን ያለችው “ሐልሐል” የተሰኘች ስትራቲጂካዊ መንደር ነበረች (“ሐልሐል” በ1969 የጀብሃ እውቅ ኮማንደር የነበረው ዑመር እዛዝ የሞተባት መንደር ናት)፡፡ በዘመቻው የአብዮታዊ ሰራዊት ሀይሎች የሻዕቢያ ተዋጊዎችን አሸንፈው ለማባረር ችለዋል፡፡ ሆኖም በሻዕቢያ ላይ የደረሰው ሽንፈት የአማጺውን ቅስም ለመስበር የሚችል አልነበረም፡፡ በ1984 የኢትዮጵያ መንግሥት ሰራዊት በታሪኩ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ ቁጥር ጨምሮ ነበር፡፡ የዚህም ምክንያት የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት መታወጁ ነው፡፡ በዚህ መሰረት የመጀመሪያው ዙር ዘማቾች በጥር ወር 1984 ወደ ማሰልጠኛ ጣቢያ ገብተዋል፡፡ ታዲያ ሻዕቢያም አልሰነፈም፡፡ መከላከልንና ማጥቃትን እያፈራረቀ የመንግሥት ሰራዊትን አስጨንቆ ይዞአል፡፡ ይባስ ብሎም የአብዮታዊ ሰራዊት አዛዦች ባልጠበቁት መንገድ የውጊያ ቀጣናውን ፊት ወደማይታወቅበት

የምዕራብ ኤርትራ ቆላማ መሬት አስፋፍቷል (በቀድሞ ጊዜ በዚህ ግንባር ጀብሃ እንጂ ሻዕቢያ ተዋግቶ አያውቅም)፡፡ በተለይም በሱዳንና ኤርትራ ድንበር ላይ የምትገኘውን የተሰነይ ከተማን በመቆጣጠር የመንግሥት ሀይሎችን ስጋት ላይ ጥሏል፡፡ አብዮታዊ ሰራዊት ከተማዋን በአውሮፕላን ደጋግሞ ቢደበድባትም ከሻዕቢያ ሊያስለቅቃት አልቻለም፡፡ እንዲያውም በአንደኛው ድብደባ ላይ ከፍተኛ የአብራሪነት ልምድ ያካበቱትና በሰሜን አሜሪካ (አሪዞና ስቴት) የሰለጠኑት እውቁ አብራሪ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ በሻዕቢያ አየር መቃወሚያ ተመትተው ለመማረክ በቅተዋል (እኝህ ኮሎኔል በሻዕቢያ እጅ ለስድስት ዓመታት ከቆዩ በኋላ የደርግ መንግሥት ከስልጣን ሲወገድ በምህረት ተለቀዋል፤ በ1998 የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲቀሰቀስ እንደገና ዘምተው በአየር ላይ በመመታታቸው በሻዕቢያ ተማርከዋል)፡፡ በሌላ በኩል በሀምሌ ወር 1984 ሻዕቢያ የጋሽና ሰቲት አውራጃ ዋና ከተማ የነበረችውን ባሬንቱን በመቆጣጠሩ ምዕራባዊው የኤርትራ ክፍል በአብዛኛው ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሆኖ ነበር፡፡ ሻዕቢያ ምዕራብ ኤርትራን በመቆጣጠሩ በሱዳን ካሉት ደጋፊዎቹና ኤርትራዊያን ስደተኞች ጋር እንደ ልብ የሚገናኝበት ሁኔታ ተፈጥሮለታል፡፡ በተለይ የኤርትራ እርዳታ ማህበር (Eritrean Relief Association-ERA) የተሰኘው ድርጅት ሻዕቢያ በሚቆጣጠራቸው ክልሎች ለሚኖሩትና በ1977ቱ ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች እንዳሻው እርዳታ ማቅረብ የቻለው በተሰነይ በኩል ወደ ሱዳን የሚዘልቀው ጎዳና በሻዕቢያ ቁጥጥር ስር ስለዋለ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ERA ለእርዳታ አቅርቦቱ የሚጠቀመው ከፖርት ሱዳን ወደ ሰሜናዊ ኤርትራ የሚያመራውን ረጅም ጎዳና ነው (እንደሚባለው ከሆነ የደርግ ሀይሎች ለኤርትራዊያን ዜጎች እርዳታ እንዳይደርስ አግደው ቆይተዋል፤እርዳታው በERA በኩል እንዲደርስ የተፈለገው ለዚህ ነው)፡፡

ዘመቻ ባህረ-ነጋሽ አብዮታዊው ሰራዊት ሻዕቢያን ከምዕራብ ኤርትራ ለማባረር በቂ ዝግጅት ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በሐምሌ ወር 1984 ለመልሶ ማጥቃት ተዘጋጀ፡፡ በአንደኛው ዙር የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት የተመለመሉ 60 ሺህ ዘማቾችን ጨምሮ ከመቶ ሀምሳ ሺህ የማያንስ የጦር ሰራዊት ለውጊያው ተሰለፈ፡፡ የዘመቻው ፕላን በሶቭየት ህብረት (USSR) ወታደራዊ ኤክስፐርቶች ተዘጋጀ፡፡ ከሶስት መቶ የማያንሱ ታንኮችና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ዝግጁ ሆኑ፡፡ ዘመቻውም “ባህረ ነጋሽ” ተብሎ ተሰየመ፡፡ “ዘመቻ ባህረ ነጋሽ” ሻዕቢያን ከምዕራብ ኤርትራ አባርሮ ወደ ሳሕል በረሃ የመመለስ እቅድ ነበረው፡፡ የዘመቻው እቅድ በመገናኛ ብዙሃን በይፋ ባይታወጅም እንኳ ለዘመቻ በተሰለፈው የሰው ሀይልና በተመደበለት የጦር መሳሪያ ዓይነትና ብዛት ከቀይ ኮከብ ሁለገብ ዘመቻ ጋር ይስተካከላል፡፡ ሀገሪቷ የነበሯት ምርጥ የጦር መኮንኖችም በአዛዥነት ተሰልፈዋል፡፡ የዘመቻው የበላይ አዛዥ እውቁ የጦር ሰው ሜጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ ሲሆኑ በርሳቸው ስር ሜ/ጄ/ ደምሴ ቡልቶ፣ ሜ/ጄ/ አበራ አበበና ሜ/ጄ/ ረጋሳ ጅማ ተሰልፈው ነበር፡፡ የአየር ሀይሉ ሜጀር ጄኔራል ፋንታ በላይም ከምርጥ አብራሪዎች ጋር ተሰልፈዋል፡፡

ዘመቻው በታቀደለት ፕሮግራም መሰረት በሰኔ ወር 1985 ተጀመረ፡፡ ሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት በከፍተኛ ወኔ ሻዕቢያን ከምዕራብ ኤርትራ እያባረረ በድል ገሰገሰ፡፡ ሻዕቢያ በታሪኩ አይቶት የማያውቅ ሀያል ሰራዊት ገጠመው፡፡ ከ2000 እስከ 4000 የሚሆን ተዋጊ አለቀበት፡፡ በዚህም የተነሳ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ባሬንቱና ተሰነይን ለመልቀቅ ተገደደ፡፡ ለአስራ ስምንት ወራት የገነባው መከላከያ ስላልሰራለት በስልታዊ ማፈግፈግ ስም ወደ ሳህል በረሃ መሸሽ ግድ ሆነበት፡፡ አብዮታዊ ሰራዊትም ማንንም ባስደነቀ ፍጥነት እየተጓዘ ከናቅፋ በር ላይ በድጋሚ ደረሰ፡፡ ሆኖም በዚህኛውም ጊዜ በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት ውጊያውን እንዲያቆም ታዘዘ፡፡ የዘመቻ ባህረ ነጋሽ አፈጻጸም ሲገመገም ውጤቱ ጥሩ ሆኖ በመገኘቱ ሊቀመንበር መንግሥቱ ቀጣይ ዘመቻዎችንም በተመሳሳይ ስልት ለማካሄድ ከውሳኔ ላይ እንዲደርሱ አድርጎአቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዘመቻው ከፍተኛ የሰው ሀይል መስዋእት ሆኖአል፡፡ በተለይ ከአስር ሺህ የማያንሱ የአንደኛው ዙር ብሄራዊ ውትድርና ዘማቾች አልቀውበታል፡፡ በዚህም የተነሳ በኢትዮጵያዊያን የጦር አዛዦች ልብ ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ ጄኔራል ፋንታ በላይ እንደተናገሩት ሊቀመንበር መንግሥቱን ከአመራር ለማስወገድ የመፈንቅለ መንግሥት ሴራ ማውጠንጠን የጀመሩት በዘመቻ ባህረ ነጋሽ ወቅት የተከሰተውን የወገን ጦር እልቂት ካዩ በኋላ ነው፡፡ ጄኔራል ፋንታ ሁኔታውን ሲገልጹት እንዲህ ብለው ነበር፡፡ “ሊቀመንበር መንግሥቱ እኛ ያዘጋጀነውን የውጊያ እቅድ ትተው የኛን ወታደሮች እንደ ጭራሮ በሚቆጥሩት የሶቪየት አዛዦች የተዘጋጀውን የውጊያ እቅድ በመቀበል ከፍተኛ መስዋእትነት እንድንከፍል አስደረጉን፤ መስዋዕትነት መክፈላችን ካልቀረም ውጊያውን በጀመርንበት ፍጥነት መቀጠል ሲገባን አለምንም ምክንያት እንድናቆም አዘዙን” (ዘነበ ፈለቀ፣ ነበር ቁጥር ሁለት፣ 2001፣ ገጽ 221) ከዘመቻ ባህረ ነጋሽ ፍጻሜ በኋላ በነበሩት ሁለት ዓመታት በኤርትራ ምድር የሚደረገው ውጊያ ጋብ ብሏል፡፡ በነዚያ ዓመታት ሁለቱም ተዋጊ ወገኖች አጣዳፊ ለሚሏቸው ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መሰረት የደርግ መንግሥት የመንደር ምስረታ እና ህገ-መንግሥት ማርቀቅን ለመሳሰሉ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ በነርሱ ላይ አተኩሯል፡፡ ሻዕቢያ ደግሞ ሁለተኛውን ድርጅታዊ ጉባኤ በማዘጋጀቱ ላይ ነበር ያተኮረው፡፡ ደርግ ያረቀቀው ህገ-መንግሥት በነሐሴ ወር 1979 ጸደቀ፡፡ ኢህዲሪ (የኢትዮጵያ ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) ተመሰረተ፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ በብሄራዊ ሸንጎ ምርጫ “ፕሬዚዳንት” ሆኑ፡፡ አዲሱ ህገ-መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ለኤርትራ ችግር ዘለቄታዊ መፍትሔ እንደሚሰጠውም ተገለጸ፡፡ ሆኖም ቃል የተገባው ሁሉ የጉባኤ ላይ ልፈፋ ሆኖ ቀረ፡፡ የጦርነት አማራጭ የመንግሥቱ ብቸኛ ምርጫ መሆኑ ሳይውል ሳያድር ታወቀ፡፡ ሆኖም የደርግ አካሄድ የሚያዛልቅ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ከደርግ ይልቅ መንገዱ ቀና ሆኖ የተገኘው በሚያዚያ 1987 ባካሄደው ጉባኤ ኢሳያስ አፈወርቂን በዋና ጸሓፊነት ለሰየመው ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) ነው፡፡ ለሳላሳ ዓመታት በዓላና ናቅፋ በረሃዎች ሲፋለሙ የቆዩት የኤርትራ አማጺያን ለመጨረሻው ግብ የሚያበቃቸውን ወታደራዊ ስልት በተግባር ላይ የሚያውሉበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር፡፡ ቀጣዮቹ ሶስት ዓመታትም የኢትዮጵያና ኤርትራን የታሪክ አቅጣጫ ከመሰረቱ የቀየሩ ታላላቅ ፍልሚያዎች የተካሄዱባቸው ነበሩ፡፡ እነዚያ ታላላቅ ፍልሚያዎች ምን ይመስላሉ? በሚቀጥለው ክፍል እናያቸዋለን፡፡

ጄኔራል ታሪኩ አይኔ ሞት በሳህል በረሃ ደቡባዊ ጠርዝ ላይ አፋቤት የምትባል አነስተኛ ከተማ ትገኛለች፡፡ በዚህች ከተማ እጅግ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን የታጠቀውና በሎጂስቲክስ አቅራቦት የተደራጀው የናደው እዝ ጠቅላይ መምሪያ ይገኝ ነበር፡፡ የናደው እዝ ከተማዋን ለመቀመጫነት የያዘው በበርካታ መንገዶች መጋጠሚያ ላይ ስለነበረች ነው ተብሎ ይወሳል፡፡ በተጨማሪም ከተራሮች ወርዶ ወደ መሬት ውስጥ እየገባ የተጠራቀመ ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃ ስለነበራት (በርካታ የውሃ ጉድጓዶች እየተቆፈሩ የሰራዊቱን የውሃ ፍላጎት ለማሟላት በሚያስችል ሁኔታ ስለነበረች) ለሰራዊቱ መቀመጫነት እንደተመረጠች ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም በትዝታቸው ውስጥ ገልጸውታል፡፡ ናደው እዝ በአፋቤት ላይ የተቋቋመው እ.ኤ.አ. በ1979 ግድም ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከከተማዋ እየተወናጨፈ ወደ ናቅፋ በመገስገስ ሻዕቢያን ለማጥፋት የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ በቀይ ኮከብ ዘመቻ ወቅት ከናቅፋ እስከ ሰባት ኪሎሜትር ድረስ (በሻለቃ ዳዊት ወልደ-ጊዮርጊስ አገላለጽ ሁለት ኪሎ ሜትር ድረስ) ተጠግቶ የነበረ ቢሆንም ሻዕቢያን ለመደምሰስ አልተቻለውም፡፡ በፕሬዚዳንት መንግሥቱና በኢሠፓ ዋና ዋና አለቆች ጣልቃ ገብነት ውጊያውን እንዲያቆም እየታዘዘ ለሽንፈት ተዳርጓል፡፡ ቢሆንም ሻዕቢያ ከናቅፋ ወርዶ ወደ ደጋማው የኤርትራ ክፍል እንዳይተላለፍ ገትሮ ይዞታል (በነገራችን ላይ ሻዕቢያ በ1985 ተሰነይን የተቆጣጠረው በአፋቤት ግንባር በኩል አይደለም፡፡ የባርካን ቆላማ አውራጃ አቋርጦ ነው ከሰሜን ወደ ደቡብ የዘመተው)፡፡ በናደው እዝ ስር ይገኝ የነበረው ሰራዊት ከአምስት ክፍለ ጦር በላይ ይሆናል (ወደ ሃምሳ ሺ የሚሆን የሰው ሀይል ነበረው)፡፡ ምርጥ ምርጥ የጦር መሳሪያዎችን ታጥቋል፡፡ የነዳጅና የመለዋወጫዎች ክምችቱ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በምግብና በሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችም ይህ ቀረሽ የማይባል እንክብካቤ ይደረግለታል፡፡ የእዙ አዛዦች ተለዋውጠዋል፡፡ በቀይ ኮከብ ዘመን አዛዥ ሆነው የተሾሙት ጄኔራል ውበቱ ጸጋዬ ነበሩ፡፡ በ1979 ደግሞ ጄነራል ታሪኩ አይኔ ተሹመውለታል፡፡ በክፍል አስራ አንድ ጽሑፌ እንደገለጽኩት ለሁለት ዓመታት ያህል በኤርትራ ምድር ጠንከር ያለ ውጊያ አልተደረገም፡፡ በታሕሳስ 6/1987 (እንደኛ አቆጣጠር ህዳር 27/1980) ግን ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) ሳይጠበቅ ከባድ የማጥቃት እርምጃ ሰነዘረ፡፡ የ15ኛው ክፍለ ጦር እና የ22ኛው ተራራ ክፍለ ጦር ተዋከቡ፡፡ ለሶስት ቀናት በተደረገ ውጊያ በርካቶች ሙትና ቁስለኛ ሆኑ፡፡ የየክፍለጦሮቹ የመገናኛና የመረጃ መኮንኖችም ተማረኩ፡፡ ሻዕቢያ ይህንን ድንገተኛ ጥቃት ያደረሰው የናደው እዝ አዛዥ ጄኔራል ታሪኩ አይኔ ዝውውር እንዲፈቀድላቸው ለመጠየቅ አስመራ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ ጥቃት መድረሱ እንደተሰማ ኮሎኔል መንግሥቱ እብድ ሆኑ፡፡ በናደው እዝ የደረሰውን ውድቀት መንስኤ ለማጣራት በሚልም ወደ አስመራ በርረው የሀገሪቱን ዋና ዋና የጦር አዛዦችን ሰበሰቡ፡፡ በዚያ ስብሰባ ላይ የተገኙት አዛዦች

1. ሌ/ጄ/ ተስፋዬ ገብረ-ኪዳን (የኤርትራ ክፍለ ሀገር የአስቸኳይ ጊዜ የበላይ አስተዳዳሪ) 2. ሜጀር ጄኔራል ኃይለ ጊዮርጊስ ሀብተማሪያም (የሀገር መከላከያ ሚ/ር) 3. ሜጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ (የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም) 4. ሜጀር ጄኔራል ረጋሣ ጅማ (የሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ዋና አዛዥ) ነበሩ፡፡ በአስረጅነትም 1. ጄኔራል ታሪኩ አይኔ (የናደው እዝ ዋና አዛዥ) 2. ጄኔራል ከበደ ጋሼ (የመክት እዝ ዋና አዛዥ) ተገኝተው ነበር፡፡ ስብሰባው በዋናነት የናደው እዝ ጥቃትን የሚመረምር ሆኖ ሳለ በመክት እዝ ላይም ሻዕቢያ ከመስከረም እስከ ጥር ወር ድረስ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ያደረሰ መሆኑ ስለተነገረ ነው የእዙ አዛዥ ጄኔራል ከበደ ጋሼ በስብሰባው ላይ እንዲገኙ የተደረገው፡፡ ስብሰባው ከሞላ ጎደል በመግባባት መንፈስ እየተካሄደ ሳለ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ጥፋቶችን በጄኔራል ታሪኩ አይኔ ላይ ማላከክ ጀመሩ፡፡ ጄኔራሉም “ለጥፋቱ እኔ ተጠያቂ አይደለሁም፣ እኔ እየተበደልኩ ነው እዚህ ያለሁት፤ ህመም እየተሰማኝ በረሃ ላይ ጥላችሁኝ ተጎድቻለሁ፤ እስከዛሬ ዝውውር ስጠይቅ መቼ ፈቀዳችሁልኝ?” በማለት በሀይለ ቃል ተናገሩ፡፡ ከዚያ በኋላ በስብሰባው ላይ መግባባት ጠፋ፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለቱ አስረጂ ጄኔራሎች ውጪ እንዲቆዩ ታዘዙ፡፡ የተቀሩት አዛዦች ከፕሬዚዳንቱ ጋር በስብሰባው ቀጠሉ፡፡ በማጠቃለያው ላይ ሁለቱ ጄኔራሎች በቁም እስር አስመራ ውስጥ እንዲቆዩ ተወሰነ፡፡ በነርሱ ምትክም ጊዜያዊ አዛዦች ለሁለቱ እዞች ተሾሙ፡፡ የጄኔራል ታሪኩን ጉዳይ ለማጣራት በሚል ምክንያት በወቅቱ የኤርትራ ክፍለ ሀገር ኢሰፓ አንደኛ ጸሓፊ በሻለቃ ካሳዬ አራጋው የሚመራ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡ ኮሚቴው በአፋቤትና በልዩ ልዩ ቦታዎች የተበታተኑ የእዙ ክፍሎችን ካነጋገረ በኋላ የጄኔራል ታሪኩ ጥፋቶችን እንደሚከተለው አስቀመጠ፡፡ 1. ተደጋጋሚ ስህተቶችን እየሰሩ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ተነግሯቸው እምቢተኛ ሆነው መገኘታቸው 2. ለስነ-ስርዓት የማይገዙና አለቆቻቸውን የሚንቁ መሆናቸው 3. በእዛቸው ስር የሚገኙት 15ኛና 22ኛ ክፍለ ጦሮች በጠላት አስገዳጅነት የመከላከያ ስፍራቸውን ሲለቁ በቦታው ተገኝተው ሁኔታው የሚለወጥበትን መንገድ ባለመሻታቸው 4. ሰራዊቱ ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ላይ እያለ እሳቸው በራስ ወዳድነት ስሜት ዝውውር መጠየቃቸው እላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ሌሎች ጥፋቶችም በጄኔራል ታሪኩ ላይ ተላክከው ነበር፡፡ ከነዚህ ውስጥ ብዙዎች የሚጠቅሱት ለሰራዊቱ የመዝናኛ ክበብ ማሰራታቸውን ነው፡፡ ጄኔራል ታሪኩ

ክበቡን ያሰሩት ከሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በተመደበ በጀት አይደለም፡፡ በኤርትራ ቆላማ መሬት የተወረሱ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በመሸጥ በተገኘ ገቢ ነው፡፡ ይህም እርምጃ በሰራዊቱ ተደንቆላቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ግን ሆን ብለው ለጥፋት ያደረጉት እንደሆነ አስመስለው ነው የተረኩት፡፡ “ሰላሳ ሳንቲም የሚሸጠውን ለስላሳ መጠጥ በአንድ ብር እየቸበቸበ ኪሱን አደለበ” በማለትም ከሰዋቸዋል፡፡ የጀኔራል ታሪኩን ጥፋቶች ለማግነንም “ድሮም እንዲህ ሲሰራ ነበር” እያሉ ልዩ ልዩ ታሪኮችን ዘርዝረዋል፡፡ ለምሳሌ “ታሪኩ በትግራይ ወታደራዊ አዛዥ በነበረበት ጊዜ ወያኔ የመቀሌን እስር ቤት ሲወር የወህኒ ቤቱ አዛዥ ለእርዳታ ለመነው፤ ታሪኩ ግን “እኔ የወህኒ ቤት ዘበኛ አይደለሁም” በማለት የመለሰ ሰው ነው” በማለት ሐጢአቱን ለርሱ አሸክመውታል (ህወሐት የመቀሌን እስር ቤት ወርሮ አንድ ሺ ያህል እስረኞችን ያስለቀቀበት ዘመቻ “አግአዚ ኦፕሬሽን” ይባላል፡፡ ኦፕሬሽኑን ያቀናበረውና በተግባር ላይ ያዋለው ሟቹ ጄኔራል ሀየሎም አርአያ ነው)፡፡ የጄኔራል ታሪኩን ጥፋት የመረመረው ኮሚቴ “ጄኔራል ታሪኩ የጡረታ መብቱ ተጠብቆለት ከሰራዊቱ በጡረቱ እንዲገለል” የሚል የውሳኔ ሃሳብ ነበር ያቀረበው፡፡ ሆኖም ውሳኔው በፕሬዚዳንቱ ተገለበጠ፡፡ በሰራዊቱ ደንብ መሰረት የጦር ፍርድ ቤት ሳይቋቋም፣ ማስረጃ ሳይመረመር፣ ምስክር ሳይቆጠርና የግራ ቀኝ ክርክር ሳይካሄድ በሞት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው፡፡ ጥር 26/1980 በአስመራ አቅራቢያ በምትገኘው አዲጓእዳድ በተባለች መንደር ጄኔራል ታሪኩ አይኔና ጄኔራል ከበደ ጋሼ ከወታደሮች ፊት ቀረቡ፡፡ የሁለቱም ጥፋት ከተነበበ በኋላ ጄኔራል ታሪኩ ተረሸኑ፡፡ ጄኔራል ከበደ ጋሼ ማዕረጋቸው ተገፍፎ ከሰራዊቱ ተባረሩ፡፡ ጄኔራል ታሪኩ ለምን ተረሸኑ? ከላይ የተዘረዘረው ጥፋት ለሞት የሚያበቃ ነበር? ይህ ጥያቄ እስከ አሁን ድረስ አከራካሪ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ጄኔራል ታሪኩ የተረሸኑት በነዚያ ጥፋቶች ነው የሚል አቋም ነው ያላቸው፡፡ በርካቶች ግን በመንግሥቱ እደበት የተነገረውን ያስተባብላሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ጄኔራል ታሪኩ የናደው አዛዥ ነበሩበት ጊዜ በእዙ ላይ የደረሰው ጥቃት ከዚያ በፊት ከደረሱትና ከዚያ በኋላ ከታዩትም በእጅጉ ያነሰ እንደሆነ በማመዛዘን ጄኔራሉ በህዳር ወር ማብቂያ ላይ በተከሰተው ጥቃት ሳቢያ ሞቱ የሚለውን አባባል እንደማይቀበሉ ይናገራሉ፡፡ በነዚህ ወገኖች አስተያየት ጄኔራል ታሪኩ የተገደሉት ለኤርትራ ችግር ሰላማዊ መፍትሔ እንዲበጅበለት በመጠየቃቸውና በኤርትራ ክፍለ ሀገር ለደረሰው ሽንፈት ሁሉ ተጠያቂው የፕሬዚዳንቱ የተሳሳተ አመራር እንደሆነ በመናገራቸው ነው፡፡ በርግጥም ጄኔራል ታሪኩን ለአንድ ዙር ጥቃት ብቻ ተጠያቂ አድርጎ መረሸን ሚዛናዊ ፍርድ አልነበረም፡፡ የሳቸው መገደል ሻዕቢያን የገታበት ሁኔታም አልታየም፡፡ ይልቁንም የሀገሪቱ ከፍተኛ መኮንኖች ለመፈንቅለ መንግሥት ዱለታ እንዲነሳሱ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ሆኖ ነው ያለፈው፡፡ ጄኔራል ታሪኩ የተገደሉት ለኤርትራ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት በመጠየቃቸውና የፕሬዚዳንቱን አመራር በመኮነናቸው እንደሆነ ነው የሚታመነው፡፡ እጅግ አሳዛኙ ነገር እኝህ እውቅ ጄኔራል ከተገደሉ ከአንድ ወር በኋላ ሻዕቢያ የናደው እዝን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ መቻሉ ነው፡፡ ይህ ሻዕቢያ የተቀዳጀው ድል የአብዮታዊ ሰራዊትን ውድቀት ካፋጠኑ ምክንያቶች አንዱ ሊሆን በቅቷል፡፡ የአፋቤቱ ውድቀት ምን ይመስል ነበር? በቀጣዩ ክፍል እንዳስሰዋለን፡፡ መጋቢት 17/1988 (መጋቢት 9/ 1980)-እኩለ ሌሊት፡፡ በዚያች ደረቅ ሌሊት ሻዕቢያ ሳይጠበቅ የናደውን እዝ ወረረ፡፡ አብዮታዊ ሰራዊትም ይዞታውን ለማስጠበቅ ተከላከለ፡፡ ይሁንና በለስ ሊቀናው አልቻለም፡፡ ሻዕቢያ ቀደም ብሎ ያገኘውን መረጃ በሚገባ ሊጠቀምበት ስለቻለ

የአብዮታዊ ሰራዊትን ማዘዣና የግንኙት መስመሮችን በጣጠሰ፡፡ ተዋጊ ብርጌዶችን ከእዙ መሀል አስገብቶ በሰራዊቱ ላይ ወደ ውጪ ተኮሰ፡፡ ከውጪ በኩል ደግሞ ዙሪያውን ከቦ በመትረየስና በከባድ መሳሪያ አዋገደው፡፡ በዚህም የተነሳ ከእዙ ጠቅላይ መምሪያ ራቅ ብለው የሰፈሩ ክፍለ ጦሮች ወደ መሐል ተመልሰው እገዛ ማድረግ አቃታቸው፡፡ ሁሉም ክፍለ ጦር በያለበት በራሱ ውጊያ ተጠመደ፡፡ አብዮታዊ ሰራዊት በዚያ ትንፋሽ በሚያሳጥር ውጊያ ለሶስት ቀናት ከተዋከበ በኋላ ሁሉም ነገር ተበላሸበት፡፡ መጋቢት 20/1988 መንፈቀ ሌሊት ላይ የናደው እዝ ሙሉ በሙሉ ተናደ፡፡ የእዙ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ግርማ ጌታነህ ከሶስት የሶቪየት ህብረት የጦር አማካሪዎች ጋር ተማረኩ፡፡ ዋናው አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ውበቱ ጸጋዬና ዘጠኝ የሶቪየት የጦር አማካሪዎች ከውጊያው አምልጠው ሲሸሹ የወገን ሄሊኮፕተር ደርሶ አነሳቸው፡፡ ሌሎች ክፍለ ጦሮች ከዋናው ማዘዣ የሬድዮ ግንኙነት እንደተቋረጠባቸው ሲረዱ የውጊያ ቀጣናቸውን እየለቀቁ ወደ ከረን አፈገፈጉ፡፡ ሻዕቢያም የአፋቤትን ከተማ በእጁ አስገባ፡፡ የናደው እዝንም ከሙሉ ግምጃ ቤቱ ጋር ተቆጣጠረ፡፡ ይህ የናደው ሽንፈት ብዙ ተብሎለታል፡፡ ብዙም ተጽፎበታል፡፡ በታወቁ የዓለም ዜና ማሰራጫዎች ግንባር ቀደም ወሬ ሆኖ ተዘግቧል፡፡ በርካታ የአውሮጳና የአሜሪካ ጋዜጠኞች ጦርነቱ የተካሄደባትን የአፋቤት ከተማ በመጎብኘት ዶክመንታሪ ፊልሞችን ሰርተውበታል፡፡ የታወቁ የጦር ኤክስፐርቶች ሻዕቢያ በአፋቤት ያገኘውን ድል የቪየት-ኮንግ ሽምቅ ተዋጊዎች በፈረንሳይ ቅኝ ገዥዎች ላይ ከተጎናጸፉት የ“ዲየን ቢየን ፉ” ድል ጋር አወዳድረውታል፡፡ በአጠቃላይ የናደው ሽንፈት ስለሻዕቢያ የሚያውቁትንም ሆነ የማያውቁትን የውጪ ዜጎች “አደገኛ የጎሪላ ተዋጊ ሀይል ነው” እያሉ በአድናቆት እንዲመለከቱት የጋበዘ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ በሌላ በኩል የናደው ሽንፈት በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የፖሊሲ ለውጥ አስከትሏል፡፡ በናደው ሽንፈት ማግስት የኢህዲሪ መንግሥት በይፋ ያልታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ ሀገሪቱ በስራ ላይ አውሏል፡፡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም መጋቢት 31/1988 ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው በኤርትራ ስለሚካሄደው ጦርነት ተናገሩ፡፡ ሰፊው ህዝብ ኤርትራን ከመገንጠል እንዲያድናት ጥሪ አቀረቡ፡፡ መንግሥት በሚመድበው በጀት ብቻ ጦርነቱን ማካሄድ ስላልተቻለ ህዝቡም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት በማለት ማሳሰቢያ ሰጡ፡፡ የ“አዲስ ዘመን” እና “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች” በፊት ገጾቻቸው ጥግ ላይ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” የሚል መፈክር በቋሚነት ማስነበብ ጀመሩ፡፡ የኢትዮጵያ ሬድዮም በምሽት ስርጭቱ ከሚያስተላልፈው ዜና ቀጥሎ “አንድነት ሀይል ነው”፣ “ሁሉም ለእናት ሀገሩ ዘብ ይቁም”፣ “የአባቶቻችንን አደራ አናስደፍርም” እና “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” የሚሉ አራት መፈክሮችን በመደበኛነት ማሰማት ጀመረ፡፡ ኤርትራ በአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር ስር ወደቀች፡፡ በኤርትራ መሬት የሚደረገው ቁጥጥር እንዲጠብቅ ትእዛዝ ተላለፈ፡፡ ክፍለ ሀገሩን ከሱዳንና ከቀይ ባህር ጋር የሚያገናኙ መሬቶች ለሲቪል እንቅስቃሴ ተከለከሉ፡፡ በናደው እዝ ላይ የደረሰው ሽንፈት በአብዮታዊ ሰራዊት ውስጥ ትልቅ ቀውስ መፍጠሩ እርግጥ ነው፡፡ በዘመኑ የነበሩ የታወቁ ወታደራዊ አዛዦችም “የፍጻሜው መጀመሪያ” በማለት ገልጸውታል፡፡ በጦርነቱ የተሰለፈው አብዮታዊ ሰራዊት ሃምሳ ሺህ ተዋጊዎችን ይዞ ከአስር ሺህ ያልበለጠ ሀይል በነበረው የሻዕቢያ ሰራዊት መሸነፉ በጣም አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ሻዕቢያ የጦርነቱን ውሎ አለም አቀፍ ዝና ለማግኘትና የአብዮታዊ ሰራዊት ሞራልን ለመስበር በሰፊው ተጠቅሞበታል፡፡ የሬድዮና የህትመት አውታሮቹ የሻዕቢያን ሀያልነት የሚያሳይ ፕሮፓጋንዳ እየደጋገሙ ሰርተውበታል፡፡ ለመሆኑ አስራ አምስት ሺህ ያህል የኢትዮጵያ ወታደሮች ሙት፣ ቁስለኛና ምርኮኛ

የሆኑበት የአፋቤት ሽንፈት እንዴት ተከሰተ? በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ ከነዚህ ሁሉ ሚዛናዊ መስለው የታዩኝ አቶ ገስጥ ተጫኔ (ዘነበ ፈለቀ) “ነበር” የሚል ርዕስ በሰጡት መጽሐፋቸው ያሰፈሯቸው ነጥቦች ናቸው፡፡ በገስጥ ተጫኔ አመለካከት የአፋቤት ሽንፈት ምክንያቶች 1. የእዙ አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ታሪኩ አይኔ መገደላቸውና በርሳቸው ምትክ የተመደቡት ጄኔራል ውበቱ ጸጋዬ የየክፍለጦሮቹን የውጊያ ቀጣና በደንብ ሳያጠኑና ተለዋጭ የውጊያ ስልት ሳይነድፉ ሻዕቢያ ፈጥኖ በማጥቃቱ 2. ሻዕቢያ በታሕሳስ ወር መጀመሪያ (በሐበሻ አቆጣጠር ህዳር ወር 1980 መጨረሻ ላይ) ባደረሰው ጥቃት ከማረካቸው መኮንኖችና የሬድዮ ሰራተኞች ስለናደው እዝ የጠራ መረጃ በማግኘቱ ወደ ውስጥ ዘልቆ በማጥቃት የማዘዣ ጣቢያውን መበተኑ 3. ውጊያው ጠላትና ወገን የተደባላለቀበት ስለነበር ለድጋፍ ሰጪ ከባድ መሳሪያዎች (ታንክ እና መድፍ) እና ለአውሮፕላኖች ድብደባ አለማመቸቱ 4. የእዙ ጠቅላይ መምሪያ ሻዕቢያ በታህሳስ ወር ያደረገውን ማጥቃት ተከትሎ ወደ አፋቤት እንደሚያመራ በመገመት ለጠንካራ መከላከል ዝግጅት አለማድረጉ 5. ሻዕቢያና ህወሐት የማዘዣ ጣቢያዎችን ቀድሞ መምታታቸው የተለመደ ስልት ሆኖ ሳለ የእዙ ዋና አዛዥ ምናልባት ማዘዣዬ ቢመታብኝ በማለት በሚስጢር የተሰናዳ ተለዋጭ የማዘዣ ጣቢያ አለማዘጋጀታቸው፤ ብሎም ሻዕቢያ ማዘዣቸውን እንዲለቁ ሲያስገድዳቸው “እዚህ ነኝ” ሳይሉ ግንኙነታቸውን አቋርጠው ወደ ከረን መሸሻቸው የመሳሰሉት ናቸው፡፡ የአፋቤት ውድቀት ከደረሰ በኋላ የሻዕቢያ አስመራ መግባት የጊዜ ጉዳይ እንደሆነ ሁለቱም ወገኖች ተረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ ተነጣጥለው ሁለት ሀገር እንደሚሆኑ መተንበይ የተጀመረውም ከዚያ በኋላ ነበር፡፡ የደርግ ከፍተኛ የጦር አዛዦች በአፋቤት የደረሰው ውድቀት የወገን ጦር በመዘናጋቱና የሻዕቢያን አቅም አሳንሶ በማየቱ የተከሰተ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በሽንፈቱ ማግስት የሻዕቢያ ሲሳይ የሆነው ግዙፍ የጦር መሳሪያና የቁሳቁስ ክምችት ለአፋቤት ወታደራዊ ጠቀሜታ በተሰጠው የተጋነነ ግምት ሳቢያ የተከሰተ እንደሆነ ያወሳሉ (ሻዕቢያ 50 ታንክና 60 ከባድ መድፎች ለመማረክ ችሎ ነበር)፡፡ ከተማዋና ዙሪያዋ በተራሮች የተከበቡ ሆነው ሳሉ አካባቢው ከሚችለው በላይ አምስት ክፍለ ጦር የሚሆን ሰራዊት ተፋፍጎ እንዲቀመጥበት ስለተደረገ ለሻዕቢያ የከባድ መሳሪያ ድብደባ መጋለጡንም ጨምረው ይናገራሉ፡፡ የጄኔራል ታሪኩ አይኔ መገደልም የወታደሮቹን ሞራል እንደሰበረ ያክላሉ፡፡ ሻዕቢያዎች ግን ይህንን አይቀበሉም፡፡ የአፋቤት ድል በነርሱ ጀግንነትና የጦር መላ አዋቂነት የተገኘ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ ጄኔራል ታሪኩ ባይረሸን እንኳ አፋቤትን ከመያዝ የሚገድባቸው ሀይል እንዳልነበረ ይከራከራሉ፡፡ ወጣም ወረደ ግን ሁሉም በአንድ ነገር ይስማማሉ፡፡ የአፋቤት ሽንፈት

የጦርነቱን አቅጣጫ ከመሰረቱ የቀየረ መሆኑን ያለ ምንም ማመንታት ይቀበሉታል፡፡ ከዚያ በኋላ የነበረው የአብዮታዊ ሰራዊት ጉዞ በኋላ ማርሽ የመጓዝ ዓይነት ነበር ይላሉ፡፡ በዚህ ረገድ የተለየ አስተያየት የሰጡት ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ብቻ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የአፋቤትን ሸንፈት ያጋነኑት የዓለም ሚዲያዎች ናቸው እንጂ በወቅቱ የሰራዊቱ አቅም አልተነካም (ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ለብሄራዊ ሸንጎ ባደረጉት የመጨረሻ ንግግራቸው በናደው እዝ ላይ የደረሰውን ውድቀት ትተው ስለአፋቤት ከተማ ከንቱነት ነበር የተናገሩት፤ “በኢትዮጵያ ስታንዳርድ ቀበሌ አይደለም፤ አልማዝ አይቆፈርበት፣ ቤንዚን አይወጣበት፣ ሀገር አይደለ፣ nothing” እያሉ ተሳልቀውባታል)፡፡ በፕሬዚዳንት መንግሥቱ አባባል በኤርትራ ምድር እጅግ ወሳኝ የሆነ ውድቀት የሚባለው በምጽዋ የደረሰው ነው እንጂ በአፋቤት የታየው አይደለም፡፡ የምጽዋው ውድቀትስ ምን ይመስል ነበር? ወደፊት እናየዋለን፡፡

የምጽዋ ውድቀት ሻዕቢያ በአፋቤት ወሳኝ ድል ከተቀዳጀ በኋላ አብዮታዊ ሰራዊት ከሳህል አውራጃ ለቆ ወጥቷል፡፡ ከዚያ በኋላ የሚያደርገው ስምሪት በደቡብ ኤርትራ የነበሩትን ከተሞች በመከላከል ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ይሁንና ሻዕቢያ ለሁለት ዓመታት ያህል በደፈጣ ጥቃት የሰራዊቱን ይዞታ መትቶ ከመሸሽ ውጪ ጠንካራ ዘመቻ ለመክፈት አልሞከረም፡፡ በየካቲት 1990 ግን ስትራቲጂካዊቷን የወደብ ከተማ ምጽዋን ለመያዝ ታላቅ ዘመቻ ከፈተ፡፡ ከአስር ቀናት ከባድ ውጊያ በኋላ በለስ ቀንቶት ውጥኑን አሳካ፡፡ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ጄኔራል መኮንኖችን በውጊያ ለመማረክ ቻለ፡፡ የምጽዋው ጦርነት ብዙ ተብሎለታል፡፡ ሀምሳ አለቃ ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ “አይ ምጽዋ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ሰፋ አድርገው ተርከውታል፡፡ ሌሎች ጸሐፍትም በመጽሐፍና በመጽሔት ዐምድ መጣጥፎችን ጽፈውበታል፡፡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ባደረጓቸው ቃለ-ምልልሶች በቁጭት አውስተውታል፡፡ ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) የኤርትራን ነጻነት ካረጋገጠ በኋላ በምጽዋው ጦርነት ድሉን ያጣጣመበትን ዕለት በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት ያከብረዋል፡፡ ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) ለ18 ወራት ያህል ከከባድ ጦርነት ታቅቦ ነበር-ከላይ እንደተገለጸው፡፡

በዚህ ሰፊ ጊዜ ውስጥ አብዮታዊ ሰራዊት ሻዕቢያን መልሶ ለማጥቃት የሚያስችል ስትራቴጂ ሳይነድፍ የቆየበት ምክንያት በግልጽ አይታወቅም፡፡ በተለይ በ1981 የተካሄደው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እና ህወሐት በየካቲት 1981 በሽሬ ከተማ የተቀዳጀው ድል የሰራዊቱን ሞራል ሊያንኮታኩተው እንደሚችል እየታወቀ ለአጸፋ የሚሆን በቂ የዝግጅት ስራ አለመሰራቱ እስከ አሁን ድረስ እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሚስተር ጂሚ ካርተር ሁለቱን ወገኖች ለማሸማገል የጀመሩት ጥረት የኢህዲሪን መንግሥት አዘናግቶት ሊሆን ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ሰራዊቱ የማጥቃትን ስትራቴጂ እርግፍ አድርጎ ትቶ በሰፈሩ ተገድቦ እንዲቆይ መደረጉ ለታላቁ ለሽንፈት አሳልፎ እንደሰጠው ይታመናል፡፡ የኢህዲሪ መንግሥት በኤርትራ ምድር በሚደረገው ጦርነት ምጽዋን የመከላከሉን ተግባር በአንደኛ ደረጃ እንዳስቀመጠው በዘመኑ የነበሩት ወታደራዊ አዛዦች ይናገራሉ፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያምም ይህንኑ ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ በዚህም መሰረት ምጽዋ ከዋና ከተማዋ ከአስመራም ሆነ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አላቸው ከሚባሉት የከረንና የተሰነይ ከተሞች በበለጠ ሁኔታ ትታይ ነበር ማለት ነው፡፡ ሰራዊቱ የመጨረሻውን መከላከል የሚያደርገው በምጽዋ ነው ተብሎ ተወስኗል፡፡ ምጽዋን ለዚህ ደረጃ ያበቃት የወደብ ከተማ መሆኗ ነው፡፡ ለሰራዊቱ የሚያስፈልገው ቀለብ፣ ጦር መሳሪያ፣ መጓጓዣ፣ የግንኙነት መሳሪያዎች፣ የመለዋወጫ ቁሳቁሶች ወዘተ… ወደ ኤርትራ የሚገቡት በምጽዋ በኩል ነው፡፡ ይሁንና የሰራዊቱ የመጨረሻ የመከላከያ ወረዳ ትሆናለች ተብላ የታሰበችው ምጽዋ ከሌሎቹ ከተሞች አስቀድማ በሻዕቢያ እጅ ወደቀች፡፡ በዚህም በሰራዊቱም ሆነ በመንግሥቱ ውስጥ ታላቅ ምስቅልቅል ተፈጠረ፡፡ ለመሆኑ የምጽዋው ጦርነት ምን ይመስል ነበር? የአብዮታዊ ሰራዊት ሽንፈትስ እንዴት ተከሰተ? ከልዩ ልዩ ምንጮች በተገኘው መረጃ ላይ በመመርኮዝ ታሪኩን እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡ በቀይ ኮከብ ዘመን የአስመራን ዙሪያ ይጠብቅ የነበረው የመክት እዝ የስምሪት ጠገጉ ሰፍቶ ከአስመራ በስተምስራቅ ያሉትንም አውራጃዎች እንዲያካልል ተደርጓል፡፡ የመጠሪያ ስሙም “606ኛ ኮር” በሚል ተቀይሯል፡፡ በዚህ ኮር ስር አራት ክፍለ ጦሮችና ሶስተኛው ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ይገኙ ነበር፡፡ የኮሩ ዋና መምሪያ የሚቀመጠው በአስመራ ከተማ ነው፡፡ ሆኖም ዋነኛ ትኩረቱ የምጽዋን ከተማ ከጥቃት መከላከል ነው፡፡ ታዲያ አብዮታዊው ሰራዊት ምጽዋን የሚጠብቃት በከተማው ብቻ በመመሸግ አልነበረም፡፡ በከተማው ዙሪያ ከ50-80 ኪ.ሜ. ራዲየስ ላይ የሚገኘውን መሬት በድርብርብ ተዋጊ ክፍለ ጦሮች በማጠር ነው ከተማዋን ከሻዕቢያ ለማትረፍ የተሰናዳው፡፡ በዚህ መሰረት ከምጽዋ በስተደቡብ ባለችው “ዙላ” የተሰኘች ጥንታዊት ወደብ አቅራቢያ ሁለት ተዋጊ ብርጌዶች ነበሩ፡፡ ከምጽዋ ወደ አስመራ በሚወስደው መንገድ ላይ ባለችው “ጋህተላይ” የተሰኘች መንደር ላይም ሶስት እግረኛ ብርጌዶችና አንድ ሜካናይዝድ ብርጌድ ነበር፡፡ ከምጽዋ በስተሰሜን ባሉት ሸዒብ እና “ሰለሙና” የተሰኙ ኩታገጠም መንደሮችም ላይ አራት ብርጌዶችና የ6ኛው ነበልባል ክፍለጦር ቀዳሚ መምሪያ ሰፍሯል፡፡ በምጽዋ ከተማ ውስጥ ከአራት ብርጌድ የማያንስ ተዋጊ ጦር ነበር፡፡ በዚህ ግንባር ባጠቃላይ ከ90 የማያንሱ ታንኮች ተሰልፈው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ባህር ሀይልም በብዙ ባህር ወለድ ተዋጊዎችና የጦር ጀልባዎች ተጠናክሮ በምጽዋ ዙሪያ ከትሟል፡፡ የ606ኛው ኮር ዋና አዛዥ የነበሩት ብ/ጄኔራል እንግዳ ወልደአምላክ በግንቦት 8/1981 በተሞከረው መፈንቅለ መንግስት ውስጥ እጃቸውን አስገብተዋል ተብለው በመከሰሳቸው ከቦታው ተነስተው ነበር፡፡ በርሳቸው ምትክ ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ ተሹመዋል፡፡ የ3ኛው ሜካናይዝድ ክፍለ

ጦር አዛዥ በነበሩት ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ ምትክም ብ/ጄኔራል ዓሊ ሐጂ አብዱላሂ ተተክተው ነበር፡፡ ይህ ኮ/ር በአዲስ ሁኔታ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ጠንከር ያለ ውጊያ አላጋጠመውም፡፡ ሻዕቢያ በባህር ወለድ ኮማንዶዎቹ ምጽዋን እየመታ ጦሩን ለማስደንገጥ ያደረጋቸው ሙከራዎችም በባህር ሃይሉ እየከሸፉ ተመልሰዋል፡፡ የካቲት 8/1990 (ጥር 30/1982)፡፡ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሆኖ ነበር፡፡ ምጽዋ ሰላማዊ እንቅልፏን መለጠጥ ጀምራለች፡፡ በከተማው የሚገኙ የአብዮታዊ ሰራዊት አባላትም ሀገር አማን ብለው ሌሊቱን በጸጥታ እያሳለፉ ነው፡፡ የስድስተኛው ክፍለጦር ዋና አዛዥ የነበሩት ብ/ጄኔራል ተሾመ ተሰማ ግን ሁኔታው ከብዶአቸዋል፡፡ ከምጽዋ በስተሰሜን ባለው የሸኢብ ግንባር ሻዕቢያ አዘናግቶ ጥቃት ይከፍት ይሆናል እያሉ ዘወትር ይሰጉ ነበር፡፡ ታዲያ በዚያች ደረቅ ሌሊት የፈሩት ነገር ደረሰ፡፡ ሻዕቢያ እጅግ ጠንካራ የሆኑ ተዋጊዎችን አሰልፎ በሸዒብ ከተማ የነበረውን የ6ኛ ክፍለ ጦር ቀዳሚ መምሪያ እንደወረረ በሬድዮ መልዕክት መጣላቸው፡፡ ወዲያውኑ ወደ ማዘዣ ጣቢያቸው ሄደው ከግንባሩ አዛዥ ጋር ግንኙነት ፈጠሩ፡፡ ያለውን ሁኔታ ከተረዱ በኋላ ረዳት ሀይል እስከሚላክላቸው ድረስ ጠንክረው እንዲዋጉ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ከዚያ በመለጠቅም አስመራ ለሚገኙት የ606ኛው ኮር አዛዥ ለብ/ጄ/ጥላሁን ክፍሌ ስልክ ደወሉ፡፡ ሆኖም ጄኔራሉን ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡ በርሳቸው ፈንታም ለሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት አዛዥ ለነበሩት ለሜ/ጄ/ ሑሴን አሕመድ በመደወል ሁኔታውን አስታወቁ፡፡ ጄኔራል ሑሴንም ረዳት ጦር እስከሚላክላቸው ድረስ ባለው ሀይል ሁኔታውን ለመቆጣጠር እንዲሞክሩ ትዕዛዝ ሰጧቸው፡፡ ጀኔራል ተሾመ በዚያች ቅጽበት በምጽዋ ዙሪያ የነበሩት የብርጌድ አዛዦች ጦራቸውን ለጠዋት እንዲያዘጋጁ ነገራቸው፡፡ ንጋት ላይም ከረዳቶቻቸው ጋር ወደ ውጊያው ቦታ ተንቀሳቀሱ፡፡ ሆኖም ያዩት ነገር ከጠበቁት ውጪ ሆነባቸው፡፡ ሻዕቢያ የሰለሞናን ግንባር ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር በአካባቢው በነበሩት ተዋጊ ብርጌዶች ላይ ከባድ ጉዳት እንዳደረሰ ተረዱ፡፡ የሰራዊቱ ብርጌዶችም ከሰለሞና በማፈግፈግ በምጽዋ-አስመራ መንገድ ላይ ወደምትገኘው ጋህተላይ እያፈገፈገ እንደሆነ ለማወቅ ቻሉ፡፡ ጄኔራል ተሾመ ባደረጉት ወታደራዊ ቅኝት የሻዕቢያ ግብ የምጽዋ-አስመራን መንገድ መቁረጥ ሊሆን እንደሚችል ገመቱ፡፡ ስለዚህ ሻዕቢያን በዚህ መስመር ገትረው ለመያዝ ወሰኑ፡፡ በአካባቢውም ከአራት ብርጌድ ያላነሰ እግረኛ ሰራዊት አስቀመጡ፡፡ ሆኖም የሻዕቢያን የግስጋሴ ፍጥነት ለመቆጣጠር ሳይቻል ቀረ፡፡ ከእኩለ ቀን ጀምሮ እስከ ቀኑ 10፡00 ድረስ ከባድ ውጊያ ከተደረገ በኋላ ሻዕቢያ “ጋህተላይ”ን ተቆጣጠረ፡፡ የአስመራ-ምጽዋ መንገድም በእጁ ወደቀ፡፡ አብዮታዊ ሰራዊትም ለሁለት ተቆረጠ፡፡ የሰራዊቱ አዛዦች ሻዕቢያ በያዘው ይዞታ ብቻ ተብቃቅቶ የሚገታ መስሎአቸው ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ረዳት ጦር እስከሚደርስላቸው ድረስ “ዶጋሊ” የተሰኘችውን ታሪካዊ አምባ በመያዝ መከላከልን መረጡ፡፡ ሆኖም ሻዕቢያ ግስጋሴውን አልገታም፡፡ ዋናውን ጎዳና ተከትሎ ሰራዊቱን ከኋላው እየተከታተለ ወጋው፡፡ ሰራዊቱ በዶጋሊ ላይ እልህ አስጨራሽ ትንንቅ አደረገ፡፡ ሻዕቢያም በዚያች ቀን ምጽዋን ከመያዝ ተገታ፡፡ ከጋህተላይ ወደ ምዕራብ የተንቀሳቀሰው የሻዕቢያ ሰራዊት ግን ምሽቱ ከመድረሱ በፊት ደንጎሎ የተሰኘችውን አነስተኛ መንደር ተቆጣጠረ፡፡ ከዚያም አልፎ ወደ አስመራ የቀረበችውን የጊንዳዕ ከተማ ለመያዝ ከፍተኛ ውጊያ ከፈተ፡፡

የኮሩ ወታደራዊ አዛዦችና የፖለቲካ ሰዎች ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ምጽዋ ባለው የ6ኛው ክፍለ ጦር መሰብሰቢያ አዳራሽ በጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ ሰብሳቢነት ተሰበሰቡ፡፡ የሻዕቢያን ግብና ዓላማ ምን ሊሆን እንደሚችል ተነበዩ፡፡ አንዳንዶቹ “ሻዕቢያ ውጊያውን የከፈተው ለጊዜው ሽብር ለመልቀቅ ነው” የሚል ግምት ሰነዘሩ፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ “ሻዕቢያ ምጽዋን ለመቆጣጠር ያለመ ይመስላል” በማለት ግምታቸውን አስቀመጡ፡፡ በዚህ ዙሪያ ክርክር ተደረገ፡፡ የኋላ ኋላም “ሻዕቢያ ምጽዋን ለመቆጣጠር ያልማል” በሚለው ሃሳብ ተስማሙ፡፡ ይሁንና በአዛዦቹ መካከል በነበረው አለመጣጣም ሳቢያ የሚረባ የውጊያ እቅድ ሳይነድፉ ተበታተኑ፡፡ ከስብሰባው የሚረባ ነገር ያጡት የ6ኛው ክፍለጦር አዛዥ ብ/ጄ/ ተሾመ ተሰማ ምጽዋን ለማዳን የራሳቸውን እርምጃ መውሰድ ጀመሩ፡፡ ከምጽዋ በስተደቡብ ራቅ ምሽግ ይጠብቁ የነበሩ ብርጌዶች ወደ ምጽዋ ተመልሰው ከተማዋን እንዲጠብቁ ለማድረግ ወሰኑ፡፡ በዕለቱ ከተያዘ አንድ የሻዕቢያ ምርኮኛ ከወሰዱት መረጃም ሻዕቢያ ምጽዋን ለመያዝ እጅግ ተጠናክሮ እንደዘመተ ለማወቅ ቻሉ፡፡ በቀጥታ ወደ ጄኔራል ሁሴን አሕመድ በመደወል ሁኔታውን ካስረዱ በኋላ ሁለት ክፍለ ጦር የሚሆን ረዳት ጦር እንዲላክላቸው ጠየቁ፡፡ ረዳት ጦር በአስቸኳይ ካልተላከ ግን የሻዕቢያ ድል አይቀሬ መሆኑን አስረግጠው ተናገሩ፡፡ ጄኔራል ሁሴንም የተባለው ጦር እንደሚላክ በመግለጽ እስከዚያው ባለው ሀይል እንዲከላከሉ አዘዙ፡፡ በዕለቱ የተማረከው መሐሪ ዮሐንስ የሚባል የሻዕቢያ ተዋጊ ነው፡፡ ይህ ልጅ በሰጠው ቃል በጦሩ ውስጥ የሀይሊ አዛዥ እንደነበረ ተናግሯል፡፡ ከርሱ በተገኘው መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው ዘመቻው በከፍተኛ ደረጃ የታቀደ ሲሆን አፈጻጸሙን በበላይነት የሚከታተሉትም ኢሳያስ አፈወርቂ እና ስብሐት ኤፍሬም ነበሩ፡፡ መሐሪ እንዳለው ሻዕቢያ ለውጊያ ያሰለፈው ሀይል

1. አምስት እግረኛ ብርጌድ 2. 2 ሜካናይዝድ ብርጌድ 3. አንድ ኮማንዶ ብርጌድ ነበሩ፡፡ በከባድ መሳሪያ በኩል 1. ሰባ ያህል T-55 ታንኮች

2. ሶስት መድፈኛ ሻለቃ 3. አራት የአየር መቃወሚያ ሻለቆች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ዘመቻው “ፈንቅል” የሚል ስያሜ ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን ዓላማውም የምጽዋን ወደብ መቆጣጠር እና የአስመራ-ምጽዋን መንገድ ከነአካቴው መቁረጥ ነው፡፡ የሻዕቢያ ሀይል የተሰማራው ከአፋቤት ከተማ ነው፡፡ ስምሪቱ ሲጀመርም (ጥር 30/1982 ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ) ኢሳያስ አፈወርቂና ስብሐት ኤፍሬም ንግግር አድርገውለታል፡፡ ከዚያም ለግዳጁ በሶስት አቅጣጫ (በሰለሞና፣ ሸዒብ እና ውቅሮ ግንባሮች) ተንቀሳቀሱ፡፡ እኩለ ሌሊት ላይ ሰለሞና አቅራቢያ ደርሰው ከላይ የተገለጸውን ድንገተኛ ጥቃት ከፈቱ፡፡ ጦሩን አሸንፈው ካባረሩ በኋላ ዱካውን እየተከተሉ ጋህተላይን ያዙ፡፡ ዋናው መንገድም ተቆረጠ፡፡

የአፋቤት ሽንፈት መጋቢት 17/1988 (መጋቢት 9/ 1980)-እኩለ ሌሊት፡፡ በዚያች ደረቅ ሌሊት ሻዕቢያ ሳይጠበቅ የናደውን እዝ ወረረ፡፡ አብዮታዊ ሰራዊትም ይዞታውን ለማስጠበቅ ተከላከለ፡፡ ይሁንና በለስ ሊቀናው አልቻለም፡፡ ሻዕቢያ ቀደም ብሎ ያገኘውን መረጃ በሚገባ ሊጠቀምበት ስለቻለ የአብዮታዊ ሰራዊትን ማዘዣና የግንኙት መስመሮችን በጣጠሰ፡፡ ተዋጊ ብርጌዶችን ከእዙ መሀል አስገብቶ በሰራዊቱ ላይ ወደ ውጪ ተኮሰ፡፡ ከውጪ በኩል ደግሞ ዙሪያውን ከቦ በመትረየስና በከባድ መሳሪያ አዋገደው፡፡ በዚህም የተነሳ ከእዙ ጠቅላይ መምሪያ ራቅ ብለው የሰፈሩ ክፍለ ጦሮች ወደ መሐል ተመልሰው እገዛ ማድረግ አቃታቸው፡፡ ሁሉም ክፍለ ጦር በያለበት በራሱ ውጊያ ተጠመደ፡፡ አብዮታዊ ሰራዊት በዚያ ትንፋሽ በሚያሳጥር ውጊያ ለሶስት ቀናት ከተዋከበ በኋላ ሁሉም ነገር ተበላሸበት፡፡ መጋቢት 20/1988 መንፈቀ ሌሊት ላይ የናደው እዝ ሙሉ በሙሉ ተናደ፡፡ የእዙ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ግርማ ጌታነህ ከሶስት የሶቪየት ህብረት የጦር አማካሪዎች ጋር ተማረኩ፡፡ ዋናው አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ውበቱ ጸጋዬና ዘጠኝ የሶቪየት የጦር አማካሪዎች ከውጊያው አምልጠው ሲሸሹ የወገን ሄሊኮፕተር ደርሶ አነሳቸው፡፡ ሌሎች ክፍለ ጦሮች ከዋናው ማዘዣ የሬድዮ ግንኙነት እንደተቋረጠባቸው ሲረዱ የውጊያ ቀጣናቸውን እየለቀቁ ወደ ከረን አፈገፈጉ፡፡ ሻዕቢያም የአፋቤትን ከተማ በእጁ አስገባ፡፡ የናደው እዝንም ከሙሉ ግምጃ ቤቱ ጋር ተቆጣጠረ፡፡

ይህ የናደው ሽንፈት ብዙ ተብሎለታል፡፡ ብዙም ተጽፎበታል፡፡ በታወቁ የዓለም ዜና ማሰራጫዎች ግንባር ቀደም ወሬ ሆኖ ተዘግቧል፡፡ በርካታ የአውሮጳና የአሜሪካ ጋዜጠኞች ጦርነቱ የተካሄደባትን የአፋቤት ከተማ በመጎብኘት ዶክመንታሪ ፊልሞችን ሰርተውበታል፡፡ የታወቁ የጦር ኤክስፐርቶች ሻዕቢያ በአፋቤት ያገኘውን ድል የቪየት-ኮንግ ሽምቅ ተዋጊዎች በፈረንሳይ ቅኝ ገዥዎች ላይ ከተጎናጸፉት የ“ዲየን ቢየን ፉ” ድል ጋር አወዳድረውታል፡፡ በአጠቃላይ የናደው ሽንፈት ስለሻዕቢያ የሚያውቁትንም ሆነ የማያውቁትን የውጪ ዜጎች “አደገኛ የጎሪላ ተዋጊ ሀይል ነው” እያሉ በአድናቆት እንዲመለከቱት የጋበዘ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ በሌላ በኩል የናደው ሽንፈት በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የፖሊሲ ለውጥ አስከትሏል፡፡ በናደው ሽንፈት ማግስት የኢህዲሪ መንግሥት በይፋ ያልታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ ሀገሪቱ በስራ ላይ አውሏል፡፡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም መጋቢት 31/1988 ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው በኤርትራ ስለሚካሄደው ጦርነት ተናገሩ፡፡ ሰፊው ህዝብ ኤርትራን ከመገንጠል እንዲያድናት ጥሪ አቀረቡ፡፡ መንግሥት በሚመድበው በጀት ብቻ ጦርነቱን ማካሄድ ስላልተቻለ ህዝቡም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት በማለት ማሳሰቢያ ሰጡ፡፡ የ“አዲስ ዘመን” እና “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች” በፊት ገጾቻቸው ጥግ ላይ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” የሚል መፈክር በቋሚነት ማስነበብ ጀመሩ፡፡ የኢትዮጵያ ሬድዮም በምሽት ስርጭቱ ከሚያስተላልፈው ዜና ቀጥሎ “አንድነት ሀይል ነው”፣ “ሁሉም ለእናት ሀገሩ ዘብ ይቁም”፣ “የአባቶቻችንን አደራ አናስደፍርም” እና “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” የሚሉ አራት መፈክሮችን በመደበኛነት ማሰማት ጀመረ፡፡ ኤርትራ በአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር ስር ወደቀች፡፡ በኤርትራ መሬት የሚደረገው ቁጥጥር እንዲጠብቅ ትእዛዝ ተላለፈ፡፡ ክፍለ ሀገሩን ከሱዳንና ከቀይ ባህር ጋር የሚያገናኙ መሬቶች ለሲቪል እንቅስቃሴ ተከለከሉ፡፡ በናደው እዝ ላይ የደረሰው ሽንፈት በአብዮታዊ ሰራዊት ውስጥ ትልቅ ቀውስ መፍጠሩ እርግጥ ነው፡፡ በዘመኑ የነበሩ የታወቁ ወታደራዊ አዛዦችም “የፍጻሜው መጀመሪያ” በማለት ገልጸውታል፡፡ በጦርነቱ የተሰለፈው አብዮታዊ ሰራዊት ሃምሳ ሺህ ተዋጊዎችን ይዞ ከአስር ሺህ ያልበለጠ ሀይል በነበረው የሻዕቢያ ሰራዊት መሸነፉ በጣም አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ሻዕቢያ የጦርነቱን ውሎ አለም አቀፍ ዝና ለማግኘትና የአብዮታዊ ሰራዊት ሞራልን ለመስበር በሰፊው ተጠቅሞበታል፡፡ የሬድዮና የህትመት አውታሮቹ የሻዕቢያን ሀያልነት የሚያሳይ ፕሮፓጋንዳ እየደጋገሙ ሰርተውበታል፡፡ ለመሆኑ አስራ አምስት ሺህ ያህል የኢትዮጵያ ወታደሮች ሙት፣ ቁስለኛና ምርኮኛ የሆኑበት የአፋቤት ሽንፈት እንዴት ተከሰተ? በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ ከነዚህ ሁሉ ሚዛናዊ መስለው የታዩኝ አቶ ገስጥ ተጫኔ (ዘነበ ፈለቀ) “ነበር” የሚል ርዕስ በሰጡት መጽሐፋቸው ያሰፈሯቸው ነጥቦች ናቸው፡፡ በገስጥ ተጫኔ አመለካከት የአፋቤት ሽንፈት ምክንያቶች 1. የእዙ አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ታሪኩ አይኔ መገደላቸውና በርሳቸው ምትክ የተመደቡት ጄኔራል ውበቱ ጸጋዬ የየክፍለጦሮቹን የውጊያ ቀጣና በደንብ ሳያጠኑና ተለዋጭ የውጊያ ስልት ሳይነድፉ ሻዕቢያ ፈጥኖ በማጥቃቱ 2. ሻዕቢያ በታሕሳስ ወር መጀመሪያ (በሐበሻ አቆጣጠር ህዳር ወር 1980 መጨረሻ ላይ)

ባደረሰው ጥቃት ከማረካቸው መኮንኖችና የሬድዮ ሰራተኞች ስለናደው እዝ የጠራ መረጃ በማግኘቱ ወደ ውስጥ ዘልቆ በማጥቃት የማዘዣ ጣቢያውን መበተኑ 3. ውጊያው ጠላትና ወገን የተደባላለቀበት ስለነበር ለድጋፍ ሰጪ ከባድ መሳሪያዎች (ታንክ እና መድፍ) እና ለአውሮፕላኖች ድብደባ አለማመቸቱ 4. የእዙ ጠቅላይ መምሪያ ሻዕቢያ በታህሳስ ወር ያደረገውን ማጥቃት ተከትሎ ወደ አፋቤት እንደሚያመራ በመገመት ለጠንካራ መከላከል ዝግጅት አለማድረጉ 5. ሻዕቢያና ህወሐት የማዘዣ ጣቢያዎችን ቀድሞ መምታታቸው የተለመደ ስልት ሆኖ ሳለ የእዙ ዋና አዛዥ ምናልባት ማዘዣዬ ቢመታብኝ በማለት በሚስጢር የተሰናዳ ተለዋጭ የማዘዣ ጣቢያ አለማዘጋጀታቸው፤ ብሎም ሻዕቢያ ማዘዣቸውን እንዲለቁ ሲያስገድዳቸው “እዚህ ነኝ” ሳይሉ ግንኙነታቸውን አቋርጠው ወደ ከረን መሸሻቸው የመሳሰሉት ናቸው፡፡ የአፋቤት ውድቀት ከደረሰ በኋላ የሻዕቢያ አስመራ መግባት የጊዜ ጉዳይ እንደሆነ ሁለቱም ወገኖች ተረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ ተነጣጥለው ሁለት ሀገር እንደሚሆኑ መተንበይ የተጀመረውም ከዚያ በኋላ ነበር፡፡ የደርግ ከፍተኛ የጦር አዛዦች በአፋቤት የደረሰው ውድቀት የወገን ጦር በመዘናጋቱና የሻዕቢያን አቅም አሳንሶ በማየቱ የተከሰተ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በሽንፈቱ ማግስት የሻዕቢያ ሲሳይ የሆነው ግዙፍ የጦር መሳሪያና የቁሳቁስ ክምችት ለአፋቤት ወታደራዊ ጠቀሜታ በተሰጠው የተጋነነ ግምት ሳቢያ የተከሰተ እንደሆነ ያወሳሉ (ሻዕቢያ 50 ታንክና 60 ከባድ መድፎች ለመማረክ ችሎ ነበር)፡፡ ከተማዋና ዙሪያዋ በተራሮች የተከበቡ ሆነው ሳሉ አካባቢው ከሚችለው በላይ አምስት ክፍለ ጦር የሚሆን ሰራዊት ተፋፍጎ እንዲቀመጥበት ስለተደረገ ለሻዕቢያ የከባድ መሳሪያ ድብደባ መጋለጡንም ጨምረው ይናገራሉ፡፡ የጄኔራል ታሪኩ አይኔ መገደልም የወታደሮቹን ሞራል እንደሰበረ ያክላሉ፡፡ ሻዕቢያዎች ግን ይህንን አይቀበሉም፡፡ የአፋቤት ድል በነርሱ ጀግንነትና የጦር መላ አዋቂነት የተገኘ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ ጄኔራል ታሪኩ ባይረሸን እንኳ አፋቤትን ከመያዝ የሚገድባቸው ሀይል እንዳልነበረ ይከራከራሉ፡፡ ወጣም ወረደ ግን ሁሉም በአንድ ነገር ይስማማሉ፡፡ የአፋቤት ሽንፈት የጦርነቱን አቅጣጫ ከመሰረቱ የቀየረ መሆኑን ያለ ምንም ማመንታት ይቀበሉታል፡፡ ከዚያ በኋላ የነበረው የአብዮታዊ ሰራዊት ጉዞ በኋላ ማርሽ የመጓዝ ዓይነት ነበር ይላሉ፡፡ በዚህ ረገድ የተለየ አስተያየት የሰጡት ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ብቻ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የአፋቤትን ሸንፈት ያጋነኑት የዓለም ሚዲያዎች ናቸው እንጂ በወቅቱ የሰራዊቱ አቅም አልተነካም (ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ለብሄራዊ ሸንጎ ባደረጉት የመጨረሻ ንግግራቸው በናደው እዝ ላይ የደረሰውን ውድቀት ትተው ስለአፋቤት ከተማ ከንቱነት ነበር የተናገሩት፤ “በኢትዮጵያ ስታንዳርድ ቀበሌ አይደለም፤ አልማዝ አይቆፈርበት፣ ቤንዚን አይወጣበት፣ ሀገር አይደለ፣ nothing” እያሉ ተሳልቀውባታል)፡፡ በፕሬዚዳንት መንግሥቱ አባባል በኤርትራ ምድር እጅግ ወሳኝ የሆነ ውድቀት የሚባለው በምጽዋ የደረሰው ነው እንጂ በአፋቤት የታየው አይደለም፡፡ የምጽዋው ውድቀትስ ምን ይመስል ነበር? ወደፊት እናየዋለን፡፡

ምንጮች 1. Dawit Wolde-Giorgis, “Red Tears”: Famine and War in Ethiopia, Red Sea Press, New York 1989 2. David Lamb, “Evil Days: Thirty Years of War and Famine in Ethiopia (1961-1991), Human Rights Watch Group, New York, 1992

3. Paul B. Henze, “Eritrea’s War”, Shama Books, Addis Ababa, 2002 4. ዘውዴ ረታ፡ “የኤርትራ ጉዳይ፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት፣ አዲስ አበባ፣ 1992 5. ጌታቸው ሀይሉ፡ “ቀያይ ተራሮች”፣ አዲስ አበባ፣ 1993 6. ልዩ ልዩ መጽሔቶች፣ ጋዜጦች እና ከዌብሳይት የተገኙ ጽሑፎች

View more...

Comments

Copyright ©2017 KUPDF Inc.
SUPPORT KUPDF